የቀድሞው የአውራምባ ታይምስ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ የነበረው ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ በ2003ዓ.ም. ሰኔ ወር ላይ ከሌሎች 4 ሰዎች ጋር (ጋዜጠኛ ኤልያስ ክፍሌ፣ ጋዜጠኛ ርዕዮት ዓለሙ፣ አቶ ዘሪሁን ገ/እግዚአብሄር እና ወ/ሮ ሂሩት ክፍሌ) የፀረ ሽብርተኝነት ህጉን ተላልፈሃል ተብሎ ክስ ተመስርቶበት የነበረ ሲሆን፤በዚህም የ14 አመት የእስር ቅጣት እንደተወሰነበት የሚታወስ ነው።
ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ
ቅጣቱ ከተላለፈበት በኋላ ጥፋተኛ መባሉን በመቃወም ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ቢልም መዝገቡ በይቅርታ ጉዳይ እየታየ መሆኑ ተገልፆለት በወቅቱ ይግባኝ ማለት ሳይችል ቀርቷል። ከእርሱ ጋር የይቅርታ ጥያቄ ያቀረቡ የስዊድን ጋዜጠኞች እና በተመሳሳይ መዝገብ የምትገኘው ሂሩት ክፍሌ ከእስር የተለቀቁ ሲሆን፤ የጋዜጠኛ ውብሸት የይቅርታ ጉዳይ ግን እስካሁን ድረስ ተፈፃሚ አልሆነም።
በመሆኑም በቅርቡ በወንጀለኛ መቅጫ ስነስረዓት ህጉ አንቀፅ 191 ስር በተመለከተው መሰረት የይግባኝ ጊዜ ካለፈ በኋላ ይግባኝ ለማቅረብ ፈቃድ ለማግኘት የሚቀርብ ማመልከቻ በማስገባት ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኙን አቅርቦ ነበር። የወንጀለኛ መቅጫ ስነስርአት ህጉ አንቀፅ 196 (1) እና (2)፤ የተፈረደባቸው ብዙ ሰዎች ሆነው አንዱ ብቻ ይግባኝ ያቀረበ እና የተጠቀመ [ከእርሱ ጋር አብራ የተከሰሰችው ጋዜጠኛ ርዕዮት አለሙ ከጋዜጠኛ ውብሸት ጋር ተመሳሳይ የቀረበባት እነወዲሁም የስር ፍርድ ቤት 14 ዓመት ከፈረደባት በኋላ በይግባኝ ወደ 5 አመት እንደተቀነሰላት ይታወቃል።] እንደሆነ ሌሎቹም ይግባኝ እንዳሉ እንደሚቆጠር እንደሚደነግግ በመጥቀስ ነው ይግባኙን ያቀረበው። ይግባኙን የተመለከተው ይግባኝ ሰሚ ችሎት የይግባኙን አቤቱታ ሳይቀበለው ውድቅ አድርጎበታል። ጋዜጠኛ ውብሸትም ይግባኝ ሰሚ ችሎት መሰረታዊ የህግ ስህተት በመጣስ ይግባኙን እንዳልተቀበለው በመግለፅ ያቀረበው አቤቱታ ዛሬ ሰበር ሰሚ ችሎት ቀርቦ ነበር። ዳኞች ጉዳዩን መርምረው ብይኑን ሰኔ 12 ቀን 2009 ዓ ም ቀን እንደሚያደርሱ እና ውሳኔውን ከመዝገብ ቤት ከማግኘት እንደሚቻል ተናግረዋል።
ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ በ2007 ዓ. ም. “የነፃነት ድምፆች” እና “ሞጋች እውነቶች” የተሰኙ መፅሐፍት ለንባብ ያበቃ ሲሆን በመጪው ሰኞ ሰኔ 12/2009 ቀን ከታሰረ 6ዓመት ይሞላዋል።
EHRP