በጌታቸው ሺፈራው
• ‹‹ደንበኞቻችን እየተንገላቱ ነው›› ጠበቆች
በእስር ላይ የሚገኙ የወልቃይት ኮሚቴ አባላት በከፊል
የፌደራል ፖሊስ በሽብር ተከሰው ጉዳያቸውን በፍርድ ቤት እየተከታተሉ የሚገኙት የወልቃይት ኮሚቴ አባላት ላይ በተደጋጋሚ ያልቀረበውን አንድ ምስክር አስሮ እንዲያቀርብ በፍርድ ቤት ታዞ የነበር ቢሆንም ምስክሩ የሚኖረው ትግራይ ክልል በመሆኑ እና በጀት ስላልተለቀቀልኝ ምስክሩን አስሮ የሚያመጣ አባል መላክ አልቻልኩም ሲል ዛሬ ሐምሌ 18 ቀን 2009 ዓ.ም ለከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አራተኛ ወንጀል ችሎት መልሱን በደብዳቤ ገልፆአል።
አቃቤ ህግም ፍርድ ቤቱ ፖሊስ አጋጠመኝ የሚለውን ችግር ከግምት ውስጥ በማስገባት ምስክሩን ይዞ እንዲያቀር ተለዋጭ ቀጠሮ እንዲሰጠው ጠይቆአል። በሌላ በኩል የተከሳሽ ጠበቆች ደንበኞቻቸው እስር ቤት ከመሆናቸውም ባሻገር ፖሊስ ያቀረበው ምክንያት ተቀባይነት የሌለው በመሆኑ ምስክሩ ታልፎ ለብይን እንዲቀጠርላቸው ጠይቀዋል። አቃቤ ህግ ለመመስከር የሚመጡትን ምስክሮች አልፈልጋቸውም ብሎ እያሰናበተ፣ የማይገኝና የሌለ ምስክር አመጣለሁ በማለት ደንበኞቻቸውን እያንገላታ መሆኑን ለፍርድ ቤቱ አስረድተውታል።
‹‹ትግራይ ኢትዮጵያ ውስጥ ነው። በአከባቢው የክልሉ ፖሊስ አለ። ፖሊስ ምስክሩን ማቅረብ ቢፈልገግ በቀላሉ ማቅረብ ይችላል ነበር።›› ሲሉ ፖሊስ ሆን ብሎ በደንበኞቻቸው ላይ በደል እየፈፀመ እንደሆነ ገልፀዋል። አቃቤ ህግና ፖሊስ ቀጠሮ በማራዘም ደንበኞቻቸው ላይ የሰብአዊ መብት ጥሰት እየፈፀሙ ነው ያሉት ጠበቆቹ ‹‹የታሰረው ሰው ነው። ሰውን እስር ቤት አስቀምጠው ምስክሩን ለማቅረብ በጀት የለንም ማለት የተከሳሾችን ሰብአዊ መብት መጣስ ነው። የቀረበው ምክንያትም አሳማኝ ባለመሆኑ ምስክሩ ይታለፍ›› የሚል አቤቱታ አቅርበዋል።
ይሁንና ፍርድ ቤቱ ፖሊስ የሰጠውን ምክንያት ታሳቢ አድርጌያለሁ በሚል የመጨረሻ ቀጠሮ ሰጥቶአል። እነ መብራቱ ለአራተኛ ጊዜ ለምስክር ተቀጥረው ምስክሩ ከመቅረቱም በተጨማሪ የዛሬው ቀጠሮ ለመጨረሻ እንዲሆን እና ፖሊስ ምስክሩን አስሮ ማምጣት ካልቻለ ምስክሩ ታልፎ መዝገቡ ተመርምሮ ብይን ለመስጠት ሊቀጠር ይገባ እንደነበር ገልፀዋል። ፖሊስ በበጀት ምክንያት ማቅረብ አልቻልኩም ያለውን ቀሪ አንድ ምስክር ለመስማት ለነሐሴ 11 ቀን 2009 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡