ታምሩ ጽጌ
በ184 ሚሊዮን ብር ሙስና የተጠረጠሩ ብርጋዴር ጄኔራል ተካተዋል
የስኳር ኮርፖሬሽን የቀድሞ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ታሰሩ
በከፍተኛ የሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ የመንግሥት ኃላፊዎችን፣ ነጋዴዎችንና ባለሀብቶች በቁጥጥር ሥር ማዋል የጀመረው ፌዴራል ፖሊስ፣ ከሁለት የስኳር ፋብሪካዎችና ከአንድ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች ሦስት ተጠርጣሪዎችን አስሮ ፍርድ ቤት አቀረበ፡፡
የፌዴራል ፖሊስ መርማሪ ቡድን በቁጥጥር ሥር አውሎ ሐሙስ ሐምሌ 27 ቀን 2009 ዓ.ም. ፍርድ ቤት ካቀረባቸው ግለሰቦች መካከል አንዱ፣ በ184,008,000 ብር የተጠርጣሩት ብርጋዴር ጄኔራል ኤፍሬም ባንጌ ናቸው፡፡ ብርጋዴር ጄኔራሉ የተጠቀሰውን ገንዘብ ለግላቸው በመዋላቸው ኦሞ ኩራዝ አምስት ስኳር ፋብሪካ ፕሮጀክት በሁለት ዓመት እንዲዘገይ ማድረጋቸውንም አስረድቷል፡፡
ሌላው በቁጥጥር ሥር የዋሉት የቀድሞ የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዮሴፍ በጋሻው ናቸው፡፡ በመንግሥት የተጣለባቸውን አደራ ወደ ጎን በመተው ኦአይኤ ለተባለ ኮንትራክተር በትውስት አርማታና ሲሚንቶ መስጠታቸውን፣ ከሰጡ በኋላም ከተከፋይ ከ31 ሚሊዮን ብር በላይ ባለመቀነሱ፣ ጉዳት ማድረሳቸውን መርማሪ ቡድኑ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሁለተኛ ወንጀል ችሎት አስረድቷል፡፡
አቶ ዮሴፍ ሥራ አስኪያጅ በነበሩበት ወቅት ሌላም ጉዳት አድርሰዋል ያለው መርማሪ ቡድኑ፣ የአገዳ ምንጠራ ሥራ በአንድ ሔክታር 25,000 ብር ለባቱ ኮንስትራክሽን ኩባንያ ተሰጥቶ እያለ ሥራውን ከባቱ በመንጠቅና በአንድ ካሬ ሜትር 72,150 ብር ለየማነ ግርማይ ጠቅላላ ኮንስትራክሽን ኩባንያ በመስጠት፣ በሕዝብና መንግሥት ላይ ከ42 ሚሊዮን ብር በላይ ጉዳት ማድረሳቸውን መርማሪ ቡድኑ ገልጿል፡፡ ሥራ አስኪያጁ በተመሳሳይ የአገዳ ምንጣሮ ላይ፣ ሥራው ሳይከናወን አሥር ሚሊዮን ብርና 20 ሚሊዮን ብር ለተለያዩ ግለሰቦች በመክፈልም ጉዳት ማድረሳቸውን፣ መርማሪ ቡድኑ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡
የኢትዮጵያ መንገዶች ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን ቡድን መሪ የነበሩት አቶ ካሳዬ ካቻ ደግሞ 26,771,681 ብር ጉዳት በማድረስ ተጠርጥረው ታስረዋል፡፡
ተጠርጣሪው ሳትኮን ኮንስትራክሽን ለተባለ ኩባንያ ከመካኒሳ እስከ ዓለም ገና ለሚሠራ መንገድ፣ 400 በርሜል ወይም 23,456,481 ብር ግምት ያለው አስፋልት በውሰት መስጠታቸውን መርማሪ ቡድኑ ገልጿል፡፡ አቶ ካሳዬ በውሰት የሰጡትን አስፋልት በሦስት ወራት ውስጥ ማስመለስ ሲገባቸው ባለማስመለሳቸው፣ በመንግሥት ላይ የ26,771,681 ብር ጉዳት ማድረሳቸውን ቡድኑ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡
አቶ ካሳዬ በጠበቃቸው አማካይነት በሰጡት ምላሽ፣ ለሳትኮን በትውስት የተሰጠው አስፋልት በባለሥልጣን ተፈቅዶ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ድርጅቱም በወቅቱ ባለመመለሱ በፍትሐ ብሔር ክስ ተመሥርቶበት በሒደት ላይ መሆኑን በማስረዳት ሊጠየቁ እንደማይገባቸው ገልጸዋል፡፡ መጠየቅ አለባቸው ቢባል እንኳን በዋስ ሆነው በውጭ ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ ፍርድ ቤቱ እንዲፈቅድላቸው ጠይቀዋል፡፡ ሁሉም ተጠርጣሪዎች የዋስትና መብታቸው እንዲጠበቅ የጠየቁ ቢሆንም፣ መርማሪ ቡድኑ ተቃውሟል፡፡
ፍርድ ቤቱ ግራ ቀኙን ካዳመጠ በኋላ በሰጠው ብይን የዋስትና መብት ጥያቄውን በማለፍ፣ ብርጋዴር ጄኔራል ኤፍሬምና አቶ ዮሴፍ የተጠረጠሩበት ጉዳይ ቀደም ብሎ ከቀረቡ ተጠርጣሪዎች ጋር ተመሳሳይ መሆኑን በመጥቀስ፣ ለነሐሴ 3 ቀን 2009 ዓ.ም. እንዲቀርቡ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ አቶ ካሳዬ ላይ የተጠየቀውን 14 ቀናት በመፍቀድ፣ ለነሐሴ 8 ቀን 2009 ዓ.ም. እንዲቀርቡ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ ያለመከሰስ መብት ያላቸውን የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር ዴኤታን አቶ አለማየሁ ጉጆን ሐምሌ 28 ቀን 2009 ዓ.ም. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያለመከሰስ መብታቸውን በማንሳቱ በቁጥጥር ሥር አውሏቸዋል፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ የስኳር ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ኪሮስ ደስታ በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ዓርብ ሐምሌ 28 ቀን 2009 ዓ.ም. በቁጥጥር ሥር ውለዋል፡፡ አቶ ኪሮስ በኮርፖሬሽኑ የቤቶችና የመስኖ ዘርፍ ልማት ዋና ዳይሬክተር እንደነበሩ ለማወቅ ተችሏል፡፡ እንደሪፖርተር ዘገባ ከሆነ፤ በአጠቃላይ በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር የዋሉ ግለሰቦች ቁጥር እስከ ዓርብ ሐምሌ 28 ቀን 2009 ዓ.ም. ምሽት ድረስ 51 ደርሷል፡፡