ዘመኑ ተናኘ
አምና ነሐሴ 1 ቀን 2008 ዓ.ም. በባህር ዳር ከተማ በነበረው ሁከት የሞቱ ሰዎችን ለማሰብ በተደረገው የመደብሮች መዝጋትና የትራንስፖርት አገልግሎት ማቋረጥ ምክንያት፣ በርካታ ሰዎች እየታሰሩ መሆኑ ተጠቆመ፡፡
ባህርዳር ከተማ
የሪፖርተር ምንጮች ሰሞኑን እንደገለጹት፣ በሁለት ቀናት ውስጥ ብቻ ከ200 በላይ የሚሆኑ ነጋዴዎችና ወጣቶች ታስረዋል፡፡ ከታሰሩት መካከል በከተማዋ ውስጥ ከፍተኛ ካፒታል ያላቸው፣ በሆቴልና በሌሎች ትልልቅ የንግድ ዘርፎች የተሰማሩ ግለሰቦች እንደሚገኙበት ለማወቅ ተችሏል፡፡
የአማራ ክልል መንግሥት እየታሰሩ ያሉ አካላት እንዳሉ ገልጾ እነማንና ቁጥራቸው ምን ያህል እንደሆነ ከመናገር ተቆጥቧል፡፡ የክልሉ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ምክትል ዳይሬክተር አቶ ፀጋዬ በቀለ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በዚህ ተቃውሞ እጃቸው እንዳለበት የተጠረጠሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር እየዋሉ ነው፡፡
‹‹አላስፈላጊ እንቅስቃሴ የሚያደርጉና የተለየ ዓላማ ያላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች በቁጥጥር ሥር እየዋሉ ትክክለኛ ትምህርት እንዲወስዱ እያደረግን ነው፤›› ብለዋል፡፡ ስማቸውን ከመግለጽ ግን ተቆጥበዋል፡፡
ሰኞ ነሐሴ 1 ቀን 2009 ዓ.ም. በባህር ዳር ከተማ ተነስቶ የነበረው መደብሮችን የመዝጋትና የትራንስፖርት አገልግሎት ተቃውሞ፣ ለሦስት ቀናት የዘለቀ እንደነበር ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
በሌላ በኩል ከቀን ገቢ ግምት ጋር በተያያዘ በአማራ ክልል ተቃውሞው እንደገና መነሳቱን የክልሉ መንግሥት አስታውቋል፡፡
አቶ ፀጋዬ እንደተናገሩት በክልሉ ውስጥ ባሉ አዋሳኝ ዞኖችና ወረዳዎች ከቀን ገቢ ግምት ጋር በተያያዘ ተቃውሞ ተነስቷል፡፡ በምሥራቅ ጎጃም ዞን ውስጥ ካሉ ወረዳዎች መካከል ስናን፣ ቢቡኝና ማቻከል ወረዳዎች ውስጥ ነጋዴዎች ለተከታታይ ሁለት ቀናት መደብሮችን በመዝጋት ተቃውሞ ማሰማታቸውን አቶ ፀጋዬ ገልጸዋል፡፡
ተቃውሞው ደብረ ታቦር፣ ወልዲያና ኮምቦልቻ አካባቢዎችም እንደነበር አቶ ፀጋዬ ጠቁመው፣ ተቃውሞውም ከአንድ እስከ ሁለት ቀናት የዘለቀ እንደነበር አስረድተዋል፡፡
በእነዚህ አካባቢዎች የተከሰተው ተቃውሞ ባህር ዳር ካለው ተቃውሞ ጋር እንደማይገናኝ አቶ ፀጋዬ ማስረዳታቸውን የሪፖርተር ዘገባ አመልክቷል፡፡