የቂሊንጦ ቃጠሎና የሀሰት ክስ

ጌታቸው ሺፈራው

እስረኞች ውጩን ከሚናፍቁበት ጊዜያት አንዱ የበዓል ወቅት ነው። የውጩን ትዝታ ለመርሳት ከቤተሰብ የገባላቸውን ምግብና ገንዘብ ከሌሎች ጋር ተካፍለው በዓሉን በዓል ለማስመሰል ይሞክራሉ። ከቤተሰብ የሚገባላቸውን ገንዘብ አዋጥተው ዳቦ እና ፈንድሻ ያስገባሉ። የድምፅና የምግብ ውድድር ያዘጋጃሉ። ለበዓል ወጫቸው ይሸፍንላቸው ዘንድ ሌሎች ውድድሮችን ያዘጋጃሉ። ለምሳሌ አንዱ ተነስቶ ሽንት ቤቱን ” ከአሁን በሁዋላ በ1000 ብር አዘግቸዋለሁ። እንዲከፈት የሚፈልፍግ ካለ 1000 ብር ከፍሎ ያስከፍተው ” ብሎ ሽንት ቤቱን ይዘጋል። ጨረታ መሆኑ ነው። እስረኛው አዋጥቶ ወይንም አንዱ ሀብታም እከፍላለሁ ካላለ ሽንት ቤቱ ይዘጋል። ገቢው ግን ለእስረኛው ነው። አንዱ ተነስቶ በተለይ ሀብታሞቹን እንትና ጎላውን ከተሸከመ ይህን ያህል ብር እከፍላለሁ ይላል። ያ ሰው ወይ ጎላ መሸከም ይኖርበታል ወይንም ገንዘቡን ይከፍላል።የተጠራበት ሰውም ራስህ ተሸከም 2ሺህ ብር እከፍላለሁ ሊል ይችላል። ሌላው ተነስቶ ይህ ቲቪ ይዘጋና እኔ 600 ብር እከፍላለሁ ይላል። ተዋጥቶ ወይንም ሀብታም ተለምኖ ከፍሎ ያስከፍተዋል። ይህ ሁሉ ገቢ እስረኛው በአንድነት በዓልን ደመቅ አድርጎ እንዲውል ያግዛል። ከዚህ በተጨማሪ ቃል የሚገባ ይኖራል። ገንዘብ አሰባሳቢ ኮሚቴ ግዴታ የሚጥልባቸው እስረኞች አሉ። ቤተሰብ ይጠይቃቸዋል የሚባሉ።

ነሃሴ አጋማሽ ጀምሮ እስረኛው ለበዓል ገንዘብ ያሰባስባል፣ ያቅዳል። ነሃሴ 21 እነሰ 22 2008 ዓም ማታ ቂሊንጦ እስር ቤት ዞን 1 ያሉ ቤቶች አዳሩን ሲጨበጨብ እና ሲሳቅ ነበር ያደረው። በየቤቱ ያሉ ኮሚቴዎች ገንዘብ ማሰባሰቡን ተያይዘውታል። ቃል ለሚገባ ይጨበጨባል። እንትና ጎላ ይሸከም፣ ሽንት ቤት ዳር ይተኛ፣ በፓንት ክፍሉን እየዞረ ይሩጥ፣ አንድ ጀሪካን ውሃ ይሸከም፣ ይዝፈን………… ተብሎ ጨረታ ሲወጣበት ይሳቃል። አንዱ ጥጋበኛ ቲቪ ወይንም ሽንት ቤቱን አዘግቶ ሌላኛው ከፍሎ ሲያስከፍተው ይጨበጨባል! ቀን የተጫራቾች ጀብድ፣ የከፋዮች ልግስና አውልቀው ለሮጡት ፌዝ ሲወራ ይውላል። አንዱ ቤት ቅዳሜ ያደረገውን ሌላው እሁድ ይደግመውና ገንዘብ ይሰበስብበታል። የቂሊንጦ እስረኞች ነሃሴ መጨረሻ ያስቡ የነበረው ስለ በዓል ነው። ሌላ ነገር አልነበረም!

ነሃሴ መጨረሻ የቂሊንጦ ድባብ እንዲህ እየቀጠለ፣ በዓል እየቀረበ እስር ቤቱ አንድ ያልተጠበቀ ነገር ይዞ ብቅ አለ። አጣዳፊ ተቅማጥና ተውከት ተከስቷል በሚል ከነሃሴ 28/2008 ዓም ጀምሮ ከቤተሰብ ከደረቅ ምግቦች ውጭ እንደማይገባ የሚገልፅ ማስታወቂያ ተለጠፈ። ከዛ በፊትም ይህ ሀሳብ ቀርቦ እስረኛው እንደማይቀበል በግልፅ አስቀኝጦ ነበር። ነሃሴ 28 እና 29/2008 ተመሳሳይ የገንዘብ ማሰባሰብ ሊቀጥል አቅዶ የነበረው እስረኛ በምግብ መከልከሉ ምክንያት ትኩረቱ ተቀየረ። የእስረኛ ተወካዮች ለቂሊንጦ አስተዳዳሪዎች እስረኛው ደስተኛ እንዳልሆነ እና መነጋገር እንደሚያስፈልግ ቢገልፁም እነ ተክላይ ፈቃደኛ አልሆኑም። የእስረኛው ብቸኛ አማራጭ “ምግብ” ብሎ ለመጥራት የሚከብደውን እስር ቤቱ የሚያቀርበውን “ደያስ” አልበላም ማለት ነው። ምግብ መከልከል የሚጀምረው ቅዳሜ ነሃሴ 28 ነውና ቁርስ አንበላም አለ። በጆንያ የመጣው ዳቦና በጎላ የመጣው ሻይ ከቤት እንዳይገባ ተደረገ። ይህን ያዩት ፖሊሶች ከቆጠራ በሁዋላ ከፍተውት የሚሄዱትን የኮሪደር በር ዘግተው እስረኛው ወደ መስጊድና ቤተ ክርስቲያን፣ ካፌ፣ ፀጉር ቤት እንዳይሄድ ከለከሉ። እስረኛው በሩ እንዲከፈት ቢጠይቅም ፖሊሶቹ ፈቃደኛ አልሆኑም።

ቂሊንጦ ውስጥ እስረኛ ይደበደባል፣ ተገዶ የማረሚያ ቤት ልብስ ለብሷል፣ ፍርድ ቤት በተደጋጋሚ የወርና ለዛ በላይ ቀጠሮ ይሰጠዋል። እስረኛው በበርካታ ጉዳዮች ተማሯል። አሁን ደግሞ ምግብ ተከልክሏል። ይህ በሆነበት በር ዘግተውበት ወጥተዋል። ይህ ሁሉ የሚደርስበት እስረኛ በር ዘግተውበት የሄዱ ፖሊሶች ላይ ጩኸት ማሰማት ጀመረ። በተነሳውግርግር ከክላሽ አልፎ መትረየስ ወደ እስረኛው ተተኮሰ። በዚሁ ሰዓት ዞን 2 እና ዞን 3 እየነደደ ነው። በሁሉም ዞኖች አሮጌ ፍራሾች ስለተቃጠሉ እስር ቤቱ በጭስ ታፍኗል። ፖሊስ የሚተኩሰው አስለቃሽ ጭስ እስር ቤቱን የባሰ በጭስ እንዲታፈን አድርጎታል። በዚህ በታፈነ እስረኛ ላይ የእሩምታ ተኩስ ይተኮሳል። ዞን 2 እና ዞን 3 ቤቶቹ በመቃጠላቸው እስረኛ ሊያልቅ ሲሆን ፖሊስ የዘጋውን በር ከፈተ። እስከዛ ሰዓት ድረስ ግን ብዙ እስረኞች ሞተዋል። ቆስለዋል። የመተንፈሻ አካል በሽታ ያለበት ውሃ እየተደፋለት፣ ሻወር ቤት ውስጥ ገብቶ፣ አፍና አፍንጫውን አፍኖ ለመትረፍ ችሏል። ራሱን ስቶ የወደቀው ብዙ ነበር።

የሌሎች ዞኖች እስረኞች ከወጡ በሁዋላ ፌደራል ፖሊስና እስረኛውን በማግባባት የዞን 1 በር ተከፍቶ እስረኛው ወደ ውጭ እንዲወጣ ተደረገ። መትረየስ በየቦታው ተጠምዶ እስረኛው ሜዳ ላይ ተቀመጠ። ከቆይታ በሁዋላ እስረኛው በየ ተራ ወደ ውጭ እንዲወጣ ሲያዙ እስረኛውም የተሻለ ቦታ ይወስዱናል የሚል ተስፋ ነበረው። ሆኖም የያዘውን እቃ እያስጣሉ፣ ጫማውን እያስወለቁ፣ በካናቴራና በቁምጣ ( ልብስ ያለው እንኳ ልብስ እንዳይደርብ ከልክለው ) ወደ አንድ ሰፊ አዳራሽ አስገቡት። ቀሪው ዝናብ እየወረደበት ሜዳ ላይ ተቀመጠ። ማታ 12 ሰዓት አካባቢ አዳራሽ ውስጥ እና ሜዳ ላይ ከነበረው ወደ ዝዋይና ሸዋ ሮቢት መጫን ጀመሩ። እስረኛ በሚጫንበት ወቅት በ”ሽብር” ክስ ገብተው የማረሚያ ቤቱን አስተዳደር የሚጠይቁ እስረኞች እየተለዩ ለብቻ ተያዙ። አግባው ሰጠኝ የመጀመሪያ ስሙ የተጠራ እስረኛ ነበር። ብዙዎቹ እየተለዩ ተደብድበዋል።

ሸዋ ሮቢትና ዝዋይ ከተወሰዱት ውጭ የቀሩት ዶፍ ሲጥልበት ውሎ ከጨቀየው ሜዳ ላይ እንዲያድሩ ተደረገ። እስከ ነሃሴ 29 11 ሰዓት እዛው ጭቃ ላይ ታግተው ዋሉ። ፀሀይና ዝናብ እየተፈራረቀባቸው። ከነሃሴ 30/2008 ጀምሮ ደግሞ እየተገረፉ በባዶ እግራቸው ሶስቱንም ዞን በግዳጅ እንዲያፀዱ ተደረገ። ለ15 ቀን ያህል እየተደበደቡ የግዳጅ ስራ ከሰሩ በሁዋላ ወደ ዝዋይ እስር ቤት እንዲዛወሩ ተደረገ።
እስረኞች ወደ ዝዋይና ሸዋሮቢት ተወስደው በርካታ የትህነግ/ኢህአዴግ አባላት ግን ቂሊንጦ እንዲቆዩ ተደረገ። እነዚህ አባላቱ ቂሊንጦ የቆዩት እስር ቤቱ ውስጥ ትህነግን የሚቃወሙ እስረኞችን ቀድመው ስለሚያውቋቸው እንዲጠቁሙ ነው። ካድሬዎቹ በስም የማያውቋቸው ነገር ግን ገዥዎቹን ሲቃወሙ የሰሟቸውን ይለዩ ዘንድ ደግሞ ሸዋ ሮቢትና ዝዋይ የነበሩ እስረኞች ፎቶ ተነስተው ፎቷቸው ወደ ቂሊንጦ ተላከላቸው። ሸዋሮቢትና ዝዋይ አብረው የሄዱ ካድሬዎችን ትህነግ/ ኢህአዴግን ሲቃወም ያዩትን፣ የሰሙትንና እስር ቤት ውስጥ ከአስተዳደሮቹ ጋር የማይስማማው ስም አሳልፈው ሰጡ። አቃጥለዋል በሚል የሀሰት ክስ ለመበቀል!

በነሃሴ ወር 2007 ውጭ ተቃውሞ የበረታበት ስለነበር፣ እስር ቤቱ ይቃጠላል ተብሎ ባይገመትም በአሳሪዎቹም በኩል ስጋት፣ በእስረኛው በኩል ደግሞ ተስፋ ነበር። በተለይ የእስር ቤቱ አስተዳዳሪዎች ውጭ በሞቀ ቁጥር የሚጠሏቸውን እስረኞች ያስፈራሩ ነበር። ምግብ በመከልከሉ ምክንያት ነሃሴ 26/2008 ዞን 3 መጠነኛ ተቃውሞ ታይቶ ስለነበር ዞን 1 የነበረው አግባው ሰጠኝ ተጠርቶ ” አንድ ነገር ቢፈጠር እንገድልሃለን!” የሚል ማስፈራሪታ ደርሶታል። ከቀጠሎው በሁዋላ ገና ምርመራ ሳይጀመር የቂሊንጦ አዛዦች” ከኦነግ ተከሳሾች በቀለ ገርባን፣ ከግንቦት 7 ደግሞ አግባው ሰጠኝ ዋና ተከሳሾች ናቸው” ብለው ለራሳቸው ሰዎች ተናግረዋል። ቀድመው ማን መከሰስ እንዳለበት ወስነዋል።

ትህነግን ስለሚቃወሙ ብቻ በቃጠሎው እጃቸው አለበት ተብለው የተጠረጠሩት እስረኞች ወደ ሸዋ ሮቢት ተወስደው ሰቆቃና ስቃይ ደርሶባቸዋል። እንደሚታረድ በግ ተሰቅለው ተገርፈዋል። መስቀል አደባባይ ላይ እንዳይደገም ብለው ሀውልት የሰሩት ሰዎች ሸዋ ሮቢት ላይ የቀይ ሽብርን ግርፋት ደግመውታል። ጫካ ውስጥ ወስደው ” ብትፈልግ በአማርኛ፣ ብትፈልግ በኦሮምኛ፣ ብትፈልግ በእንግሊዘኛ ጩኽ! ማን እንደሚደርስልህ እናያለን” እያሉ የባዕድ ሀገር ዜጋ አድርገው ገርፈዋቸዋል። እነዚህ እስረኞች በእስር ቤቱ አስተዳደር ጥርስ ውስጥ እንደገቡ ስለሚያውቁ በቃጠሎው ወቅት ከቤት አልወጡም፣ ቤቱ መንደድ ሲጀምርም ወጥተው ከፖሊስ ጋር አልተጋተሩም። እነ ማስረሻ ሰጤ፣ አበበ ኡርጌሳን የመሰሉት ጨለማ ቤት ፣ ፍቅረ ማርያም አስማማው ዝዋይ፣ ዶ/ር ፍቅሩ ማሩ ደግሞ ቃሊቲ ነበሩ። ግን ለቂሊንጦ እስር ቤት ቃጠሎ ተጠያቂ ተደርገዋል። ድራማ የማይችሉት አሳሪዎች እስር ቤቱን ሰብሮ ለማምለጥ እስረኞች 20 ያህል ሆነው ቴኳንዶ ይሰለጥኑ ነበርም ብለዋል።

ለቂሊንጦ እስር ቤት ቃጠሎ ምንም ገንዘብ አስፈላጊ አልነበረም። ሆኖም የእስረኛውን ልብስና ንብረት ሲወርሱ ገንዘብም ይዘዋል። ወደ ዝዋይ ከተጫኑት እስረኞች ብቻ ከ170 ሺህ ብር በላይ ወርሰዋል። ልብሱን በጆንያ እየጫኑ ውጭ ላሉ ሰዎቻቸው አስረክበዋል። በተለይ ይህ ቃጠሎ ይመጣል ብሎ ያላሰበው እስረኛ ለበዓል በቅጣትና በሌሎች መንገዶች በየቤቱ ብር ሰብስቦ ነበር። ይህንና እስረኛው በግሉ ያስቀመጠውን ብር የቀሙት አሳሪዎቹ ገንዘቡ ለቃጠሎ ማስፈፀሚያ የገባ ነው አሉ። ይህም አንደኛ የእስረኛውን ገንዘብ ለመቀማት ሲሆን በሌላ በኩል የእስር ቤቱ ቃጠሎ ታስቦበት እና ሆን ብሎ የተደረገ ለማስመሰል ነበር። በዚህ አልበቃቸው ስላለ በምርመራ ወቅት እስረኞች ብር እንደገባላቸው እንዲያምኑ ተደረገ። ለዚህ የጦስ ዶሮ የሆኑት ደግሞ ዶ/ር ፍቅሩ ማሩ ናቸው። እስረኞቹ በሀሰት እንዲያምኑ በተደረገው መሰረት ዶ/ር ፍቅሩ ማሩ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ለቃጠሎው ማስፈፀሚያ እንዳስገቡ ተደርጎ ቀርቧል።

ግንቦት 7፣ ኦነግና አልሻባብ የት እንዳሉ የማያውቋቸው እስረኞች ከእነዚህ ድርጅቶች ጋር በመገናኘት እስር ቤቱን ሰብረው ወደ ድርጅቶቹ ሊቀላቀሉ ነበር ተብለው ተከሰሱ። እነዚህን እስረኞች ወደ ኤርትራ፣ ወደ ኬንያ እና ሶማሊያ ለማጓጓዝ 80 አውቶቡስ እስር ቤቱ አጠገብ ቆሞ እየጠበቀ ነበር ተብሎ የፈጠራ ክስ ቀርቦባቸዋል።

በቃጠሎወረ ወቅት በተተኮሰ ጥይት በርካቶች ቆስለዋል። ሞተዋል። ሆኖም በምርመራ ወቅት እስረኞች በእሳትና በጥይት የተገደሉትን ” እኔ ነኝ የገደልኩት” ብለው እንዲያምኑ ተደርገዋል። አንድ ሰው እስከ 5 ሰው ገድለሃል ተብሏል። ምርመራው አሰቃቂ ስለነበር ያልሞተ ሰው ሁሉ ገድያለሁ ያለ እስረኛ አለ። እስረኞች የሚድሩበት ቆርቆሮ ቤት ነው። ከጎኑ ደግሞ ሶስት መግረፊያዎች አሉ። አንድ እስረኛ ሲገረፍ ሌላው የሚሆነውን ይሰማል። ከ170 በላይ እስረኛ ተሰቅሎ ሲገረፍ ሌላው ይሰማል። በዚህ ሁሉ መከራ የስነ ልቦና ችግር ያጋጥማል። ይህን ሁሉ ሰቆቃ ሲሰማ የሰነበተ አንድ እስረኛ ሳይገረፍ ገና ወደ ምርመራ ክፍሉ ሲገባ ያልገደለውን ገደልኩ ብሏል። እስረኛው ማንን እንደገደለ ሲጠየቅ ” ጠሃን እኔ ነኝ የገደልኩት “ይላል።

መርማሪዎቹ አልተስማሙም። ጠሃን በተመሳሳይ ሁኔታ ለሌላ ሰው አድለውታል። በዚህ መከራ ወቅት እንትናን ገድየዋለሁ ብሎ ከመርማሪው ይሁንታ ማግኘት ቀላል አይደለም። ከሰቆቃ ያድናል። እስረኛው አሁንም ሞቷል የተባለ ሰው ስም ጠርቶ እኔ ነኝ የገደልኩት ይላል። ሲሰማ የሰነበተው መከራ እንዳይደርስበት ነው። አሁን የጠራው ሟችንም ቀድሞ የተመረመረ “እድለኛ” ወስዶታል። እስረኛው በዚህ ሁኔታ እስከ አምስት ሰው እየጠራ ” እድሉን ይሞክራል”። አልቀናውም። በሙሉ ተይዘዋል። መርማሪውም ” ተይዘዋል” እያለ ሌላ እድል ይሰጠዋል። አምስተኛ ላይ የሰጠኝ ሙሉን ስም ጠራ። “እስኪ ቆይ” ብሎ መርማሪው መዝገቡን አገላበጠና ” ያዘው አልተያዘም! አለው። ሰጠኝ ሙሉን ገድለኸዋል ተብሎ ተከሰሰበት። የቂሊንጦ ድራማ እንዲህ ነው። ሰው ባልሰራው የሚከሰስበት ድራማ!

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: