በርካቶችን ለሞት የዳረገው የኦሮሚያ – ሶማሌ ግጭት እስከ ትናንት አለመቆሙን መንግስት አስታውቋል

አለማየሁ አንበሴ
Abdi,kassa & Lemma
አቶ አብዲ መሐመድ፥ እቶ ካሳ ተክለብርሃን እና አቶ ለማ መገርሳ

በኦሮሚያ እና በሱማሌ ክልሎች መካከል የተፈጠረው ግጭት እንደቀድሞ የወሰን ጉዳይ እንዳልሆነ የተጠቆመ ሲሆን፣ ትክክለኛ መንስኤው እየተጣራ መሆኑን ያስታወቁት የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ፤ ግጭቱ እስከ ትናንት አርብ ድረስ በተለያዩ ቀበሌዎች መቀጠሉንና በርካቶች ተገድለው፣ ከ20 ሺህ በላይ ዜጎች መፈናቀላቸውን አስታውቀዋል፡፡

ለበርካታ ቀናት በቀጠለ ግጭት፤ የሠው ሕይወት ጠፍቷል፣ ንብረት ወድሟል፣ ዜጎች ተፈናቅለዋል ያሉት ሚኒስትሩ፤ ግጭቱ በቅርቡ እንዲገታ ይደረጋል፤ የሃይማኖት አባቶች፣ የሃገር ሽማግሌዎችም በመሃል ገብተው የማረጋጋት ስራ ይሠራሉ ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለ ማርያም ደሣለኝ፤ ከሁለቱ ክልል አመራሮች ጋር በግጭቱ ላይ በስልክ ውይይት ማድረጋቸውንና ግጭቱ እንዲቆም ማሣሠቢያ መስጠታቸውንም ሚኒስትሩ አስታውቀዋል፡፡
በአካባቢው ለግጭቱ መባባስና ለሠው ህይወት መጥፋት ምክንያት የሆኑ ለህግ እንዲቀርቡ ይደረጋል ያሉት ሚኒስትሩ፤ የመሳሪያ ትጥቅ የማስፈታት ስራም ይሰራል ብለዋል፡፡

የመከላከያ ሰራዊትና የፌደራል ፖሊስ በግጭቱ መሃል ገብቶ ለማረጋጋት ለምን ዘገየ ተብለው የተጠየቁት ሚኒስትሩ፤ ክልሎቹ ችግሮቹን በራሳቸው ይፈቱታል የሚል እምነት በመጣሉ ነው ብለዋል፡፡
በግጭቱ የሶማሊያ ሪፐብሊክ ኃይሎችና የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል መሳተፋቸው ተጣርቶ ህጋዊ እርምጃ ይወስዳል ብለዋል – ሚኒስትሩ፡፡ ግጭቱ በታጠቁ አካላት የታገዘ መሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትሩ፤ እነዚህ የታጠቁ አካላት እነማን ናቸው የሚለው ግን እስካሁን ምላሽ አለማግኘቱንና በማጣራት ሂደቱ እንደሚታወቅ ተናግረዋል፡፡ ግጭቱ የህዝብ ለህዝብ አለመሆኑን ግን አስረግጠው በመግለፅ፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ የሁለቱ ክልሎች የመንግስት ኮሚኒኬሽን ኃላፊዎች ጉዳዩን አስመልክቶ በየሚዲያው የሚያስተላልፏቸው መግለጫዎች፣ ግጭቱን ሊያባብሱ የሚችሉ በመሆኑ ከእንግዲህ በኋላ ግጭት አባባሽ መግለጫዎችን ከመስጠት እንዲቆጠቡ ዶ/ር ነገሪ አሳስበዋል፡፡

የኮሚኒኬሽን ኃላፊዎቹ ከዚህ ድርጊታቸው የማይቆጠቡ ከሆነ፣ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድም ሚኒስትሩ ጠቁመው፤ በሁለቱም የሚገለፁ አሃዛዊ መረጃዎችንም ገና ያልተጣሩ መሆናቸውንና መንግስት ሁኔታውን አጣርቶ እንደሚገልፅ አስታውቀዋል፡፡

የሶማሌ ክልል ግጭቱን አስመልክቶ ለቪኦኤ በሰጠው መግለጫ፤ በአወዳይ ከተማ 50 ሠዎች መገደላቸውን ሲገልፅ፣ የኦሮሚያ ክልል በበኩሉ፤ በአወዳይ ከተማ 18 ሰዎች መገደላቸውን፣ ከነዚህ ውስጥ 12ቱ የሶማሌ ተወላጆች፣ ቀሪዎቹ የኦሮሞ ጃርሶ ጎሣ አባላት መሆናቸውን አስታውቋል፡፡

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ቃል አቀባይ አቶ አዲሱ አረጋ ትናንት ምሽት ባሰራጩት መረጃ፤በሰሞኑ ግጭት ከተፈናቀሉት ከ22ሺ በላይ ዜጎች በተጨማሪ አጠቃላይ የድንበር ግጭቱ ከተከሰተበት ከ2009 ጀምሮ 416ሺ807 ዜጎች መፈናቀላቸውን አስታውቀዋል፡፡

በአወዳይ የደረሠውን ግጭት ተከትሎ፣ ከሶማሌ ክልል ከ21 ሺህ በላይ ዜጎች ተፈናቅለው በጭናቅሠን፣ ባቢሌና ሐረር ከተሞች ተጠልለው እንደሚገኙ የኦሮሚያ ክልል ቃል አቀባይ አቶ አዲሱ አረጋንና ምንጮቹን ጠቅሶ ቪኦኤ ዘግቧል፡፡

የሱማሌ ክልል የመንግስት ኮሚኒኬሽን ሃላፊ አቶ ኢንድሪስ አህመድ በበኩላቸው፤ “ሰዎች ከአካባቢው የተፈናቀሉት በግዴታ ሳይሆን በፍቃዳቸው ነው፤ ጥቃት አልተፈፀመባቸውም” ብለዋል፡፡ ምንጮች በበኩላቸው፤ የግዳጅ ማፈናቀል መፈፀሙንና በዜጎች ላይ ድብደባና እንግልት እንደደረሰባቸው ለመገናኛ ብዙኃን ተናግረዋል፡፡

የሱማሌ ክልል መንግስት ኮሚኒኬሽን ሃላፊ አቶ ኢንድሪስ አህመድ፤ በአወዳይ ከተማ የደረሰውን ግድያ ተከትሎ ባስተላለፉት መግለጫ፣ የኦሮሚያ ክልል መንግስትን “የአሸባሪነት አላማ አራማጅ” በሚል የፈረጀ ሲሆን የኦሮሚያ ክልል ቃል አቀባይ በበኩላቸው፤ ፍረጃውን አጣጥለው፣ ከአንድ ክልልን ከሚያስተዳድር አካል የማይጠበቅ ነው ብለዋል፡፡

የሶማሌ ክልል መንግስት ኮሚኒኬሽን ሃላፊ ለቪኦኤ በሰጡት መረጃ፤ በአስራ አንድ የሶማሌ ወረዳዎች፣ ማንነታቸው ባልታወቀ አካላት በተሠነዘሩ ጥቃቶች፣ ከሁለት መቶ አስራ ሶስት ሰዎች በላይ ህይወት ማለፉን አስታውቀዋል፡፡ ይሄን ተከትሎም የሶማሌ ክልላዊ መንግስት፣ ለ5 ቀናት የሚቆይ ብሄራዊ የሃዘን ቀናት በክልሉ ማወጁንም ለማወቅ ተችሏል፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ፣የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የግጭቱን መነሻና የደረሰውን ጉዳት የሚያጣራ ቡድን ከትላንት በስቲያ ሐሙስ ወደ አካባቢው መላኩንና ማጣራት መጀመሩን የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ደምሰው በንቲ ለአዲስ አድማስ አስታውቀዋል፡፡

ሰሞኑን የሁለቱ ክልሎች የመንግስት ኮሙኒኬሽን ኃላፊዎች በማህበራዊ ድረ-ገፆቻቸው የሚያሰፍሯቸው የእርስ በርስ ውንጀላዎች አስደንጋጭና ግጭቱን የሚያባብሱ መሆናቸውን አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ፡፡ ክልላዊ መንግስታቸውን ወክለው መልዕክት የሚለዋወጡ እንደማይመስሉና ኃላፊነት የጎደሏቸው እንደሆነም ተገልጿል፡፡
ምንጭ፡ አዲስ አድማስ

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: