እውነት የሆኑ ታላላቅ “ውሸቶች”

አፈንዲ ሙተቂ
—–
በዚህ መጣጥፍ የማወጋችሁ “ውሸት” ሲባሉ ቆይተው “እውነት” ሆነው የተገኙ ኩነቶችን ነው፡፡ እነዚህ ኩነቶች በጊዜያቸው በትክክል ተፈጽመዋል፡፡ ሆኖም እኔ ጸሓፊው እነርሱን የሚመለከት መረጃ ያገኘሁት ድርጊቶቹ ከመፈጸማቸው ከሶስትና አራት ወራት በፊት ነበር፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችም እንደኔው ድርጊቶቹ ከመፈጸማቸው በፊት መረጃውን አግኝተዋል፤ በዚህ ረገድ ከብዙዎች በፊት መረጃው ነበረኝ ብዬ የምመጻደቅበት ምክንያት የለም፡፡ ይሁንና ከክስተቶቹ መፈጸም በኋላ በድርጊቶቹ ተዋናይነት እጃቸውን ባስገቡ ግለሰቦችና ድርጅቶች ዘንድ የሚታየው እውነታን የመሸምጠጥ አባዜ ዘወትር ስለሚያስገርመኝ ያኔ የነበሩ ሰዎች ሐሳባቸውን ይስጡበት በማለት እንደገና ላስታውሳቸው ወደድኩኝ፡፡

====የኮሎኔል መንግሥቱ ወደ ዚምባብዌ መሰደድ===

ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማሪያም ወደ ዚምባብዌ የተሰደዱበትን ምክንያት በድንገት በተፈጠረ ግፊት ያመካኙታል፡፡ “ወደ ኬንያ የሄድኩት ከቻይና በ60 ሚሊዮን ዶላር የተገዛውን የጦር መሳሪያ በሞምባሳ ወደብ ለማስገባት ነበር፤ ኬንያ ስደርስ ግን ያልጠበቅኩት ነገር ተከሰተ፡፡ የኔ ባለስልጣኖች በቤተመንግሥት ተሰብስበው ከስልጣን ወርደሃል የሚል መልዕክት ላኩልኝ፤ የኔ ጓዶች ናቸው የከዱኝ እንጂ እኔ ሀገሬን አልከዳኋትም” በማለት ኦፊሴላዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ በሬድዮም፣ በጋዜጣም፣ በመጽሐፍም ተመሳሳይ ቃል አሰምተዋል፡፡

የመንጌ ተሿሚ የነበሩ ባለስልጣኖች ደግሞ ከዚህ ትንሽ ለወጥ ያለ ቃል ነው ያሰሙት፡፡ “ፕሬዚዳንቱ ስለ መሳሪያ የተናገረው ውሸት ነው፤ ነገር ግን ይሰደዳል ብለን ፈጽሞ አልጠበቅንም፤ በጦርነቱ ማብቂያ ገደማ አንዳንድ ምልክቶች ብናይም እኛን ከድቶ ይጠፋል የሚል ጥርጣሬ አልነበረንም” ይላሉ፡፡ ነገሩን በጥልቀት ያውቁታል የተባሉት የደህንነት ሚኒስትሩ ኮ/ል ተስፋዬ ወልደስላሴም ይህንኑ ነበር እየደጋገሙ ሲናገሩት የነበረው፡፡

የደርግ ባለስልጣን የነበሩት አቶ ገስጥ ተጫኔ (በብዕር ስማቸው “ዘነበ ፈለቀ”) “ነበር” የሚል ርዕስ በሰጡት መጽሓፋቸው “የውጪ መገናኛ ብዙኃን ጓድ መንግሥቱ የወደፊት ኑሮአቸውን በዚምባብዌ ለማሳለፍ እንዳቀዱ በሰፊው ያትቱ ነበር” ይላሉ፡፡ ከደርጎች ወገን እንዲህ ብለው ለመጻፍ የደፈሩት እሳቸው ብቻ ናቸው፡፡ እሳቸውም ቢሆኑ ግን “የምዕራብ ዜና አውታሮች እንዲህ ብለው ያወሩት ወደዚያ ብትሄድ እንደግፍሃለን ለማለትና የፕሮፓጋንዳ ሽብር ለመንዛት ሊሆን ይችላል” በማለት ነገሩን ይሸፋፍኑታል፡፡
ሐቁ ግን እንዲህ ሽፍንፍን አልነበረም፡፡ ጓድ መንግሥቱ ወደ ዚምባብዌ ሊኮበልሉ እንደተዘጋጁ መወራት የተጀመረው በጥር/የካቲት ወር 1983 ገደማ ነው፡፡ እኔ በግሌ ወሬውን ለመጀመሪያ ጊዜ የሰማሁት ከበረሃ በሚተላለፈው የኢህአዴግ ሬድዮ ጣቢያ ነው፡፡ ከትንሽ ጊዜ በኋላም ከልዩ ልዩ ክፍለ ሀገራት ወደኛ ከተማ የመጡ ዘመዶቻችን ወሬውን ሲያወሩት ነበር፡፡

ዛሬ በርካታ ሰዎች “የመንግሥቱ ስደት አስገርሞናል” ብለው ቢናገሩም ያኔ ተማሪ ነኝ የሚል ሰው (ቢያንስ ከስምንተኛ ክፍል በላይ የደረሰ) ወሬውን በየመንገዱ ያወራው ነበር፡፡ እንዲህ ብዙ የተወራለት ወሬ በትክክል ተፈጽሞ ሲገኝ በእቅድ አልተከናወነም ሊባል ነው? ነገሩ አስቀድሞ በተደረገ ዝግጅት እንደተፈጸመ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ደ’ሞ እቅድ ብቻ ሳይሆን ማንንም ሰው የሚያስማሙ ተግባራዊ እርምጃዎች ተወስደውበታል፡፡ ለምሳሌ ጓድ መንግሥቱ አጎታቸውን ወደ ዚምባብዌ ልከው ቤተሰባቸውን ሲያደራጁ እንደነበር ማስረጃው ኋላ ላይ ተገኝቷል፡፡ ደርጎች ግን እስከ ዛሬ ድረስ “ዐይኔን ግንባር ያድርገው” እያሉ ነው፡፡ በስተእርጅናም ከህዝብ ጋር አይታረቁም፡፡

የደርጎቹስ ይሁን እሺ! ኢህአዴጎች በረሃ እያሉ ሲያወሩት የነበረውን ያንን ብርቅ የፕሮፓጋንዳ ወሬ ከዚያ በኋላ አልደገሙትም፡፡ እነርሱም እንደ ደርግ ባለስልጣናት “መረጃው የለንም” ማለት ይዳዳቸዋል፡፡ ወሬውን ለመደበቅ የሚፈልጉበትን ምክንያት ባናውቅም የአሜሪካና የካናዳ መንግሥት መንጌን ወደ ዚምባብዌ በሰላም ለማስወጣት ከኢህአዴጎች ጋር በሚስጢር ተስማምተዋል የሚለው ነገር እንዳይነሳ የሚፈልጉ ይመስላሉ፡፡ ከዚህ ሁኔታ እንደምንገነዘበው ደርግ ያለቀለት ከግንቦት 20/1983 በፊት ነው፡፡ ቢያንስ ቢያንስ ከየካቲት እስከ ግንቦት ድረስ ሲካሄድ የነበረው የማስመሰል ጦርነት ሊሆን ይችላል ማለት ነው፡፡ ደርግም “ስልጣን ጥለህ ፈረጠጥክ” እንዳይባል፣ ኢህአዴግም “ያለመስዋእትነት ወንበሩን ተረከብክ” እንዳይባል!! በመሀል ግን የህዝቡ ልጆች አለቁ!! እሳቱ በአስር ሺህ የሚቆጠሩ ወገኖቻችንን በላብን፡፡
የታሪክና የህግ ምሁራን ይህንን ነገር የመመርመር ኃላፊነት አለባቸው፡፡ እውነታው ተጣርቶ ለህዝብ ይፋ መደረግ አለበት፡፡

====የኦነግ ጦር ወደ ካምፕ መግባት===

ይህኛውን ወሬ የሰማሁት በጥቅምት ወር 1984 ይመስለኛል፡፡ በዘመኑ በሀረርጌ ክፍለ ሀገር ሶስት አውራጃዎች በኦነግ ቁጥጥር ስር ነበሩ፡፡ ኢህአዴግና ኦነግ በሽግግር መንግሥቱ ውስጥ ስለነበሩ በመርህ ደረጃ አብረው ይሰሩ ነበር፤ ይከባበሩም ነበር (እንዲህም ሆኖ ከሐምሌ 1983 ጀምሮ ሲጋጩ ቆይተዋል)፡፡ በወቅቱ አሁን ኦህዴድ የሚባለውን ድርጅት የወከሉ አራት ካድሬዎች ቢሮአቸውን በኛ ከተማ ከፈቱ፡፡ እኔና ሶስት ጓደኞቼም ስለዓላማቸው እንዲያስረዱን በማለት ወደ ጽሕፈት ቤታቸው ሄድን፡፡ አንዱ ካድሬ (ስሙ “ዋቅቶሌ” ይመስለኛል) ብዙ ካወራ በኋላ “ወደፊት እኮ ድርጅቶች እንዲህ አይዘልቁም፤ የኦነግ ጦር ካምፕ ይገባና OPDO (ኦህዴድ) ኦሮሚያን ያስተዳድራል” አለን፡፡ እኛም በነገሩ በጣም እየተገረምን ሳቅንና “ይህ የማይመስል ነገር ነው” በማለት ከርሱ ተለየን፡፡

ከሰባት ወር በኋላ (ግንቦት 1984 መጀመሪያ ገደማ) ካድሬው የተናገረው ነገር እውነት ሆነ፡፡ ኦነግ ጦሩን ወደ ካምፕ አስገባ፡፡ ኢህአዴግ በውጊያ ሊይዛቸው ባልቻላቸው አካባቢዎች ሰራዊቱን በሰላም አስከባሪነት አሰማራ፡፡ ከአንድ ወር በኋላ ደግሞ አብዛኛው የኦነግ ጦር ከካምፑ ርቆ ሳይሄድ ተማረከ፡፡
ያንን ድራማ ካየሁ ከጥቂት ዓመታት በኋላ በቢሮው እንደዚያ ያለን የኦህዴድ ካድሬ ትዝ አለኝ፡፡ “ለምን እንደዚያ ብሎ ተናገረን? ኦነጎች ይህንን ኢንፎርሜሽን አያውቁትም ኖሯል? ደግሞ ለእንደኔ ዐይነቱ ታዳጊ እንዲያ ዓይነት ሚስጢር እንዴት ይነገራል?” እያልኩ ተመራመርኩ፡፡ ግን ምንም ሊገባኝ ያልቻለ ጉዳይ ሆኖ አለፈ (በዘመኑ እድሜዬ ከአስራ አራት አይበልጥም፤ ሆኖም እኔ ህጻኑ እድለኛ ነበርኩኝ ማለት እችላለሁ፤ ከኔ የሚበልጡ ብዙ ሰዎች ወሬውን በጭራሽ ሰምተውት አያውቁም ነበርና)፡፡

ያ ዘመን እንዲያ ካለፈ በኋላ ሐሳቤን ይበልጥ ያወሳሰበ መረጃ በቅርብ ጊዜ አግኝቻለሁ፡፡ መረጃው “ኦነግ ራሱ ነው ካምፕ እንግባ ብሎ ጥያቄ ያቀረበው” የሚል ነው፡፡ በጣም ያስገረመኝ ደግሞ ኢህአዴግ “እኔ ካምፕ አልገባም” የሚል ሆኖ ሳለ የኦነግ መሪዎች “የሁላችንም ጦር በፍጥነት ካምፕ መግባት አለበት” እያሉ ያስጨንቁት ነበር መባሉ ነው፡፡ ይህ እውነት ከሆነ እንግዲህ ኦነግ ኢህአዴግን መክሰስ የለበትም ማለት ነው፡፡ ራሱ በቆረጠው ልምጭ ነው ራሱን የገረፈውና! እውነቱ ሌላ ከሆነ ደግሞ የኦነግም ሆነ የኢህአዴግ ሰዎች ሐቁን ይንገሩን እንላቸዋለን፡፡

===የዶ/ር ነጋሶ ፕሬዚዳንት ሆኖ መመረጥና የአቶ መለስ ዜናዊ ጠ/ሚ/ መሆን====
ይህኛውን ብዙ ሰው አስቀድሞ ሰምቷል፡፡ በግል ጋዜጦችም ብዙ ተጽፎበታል፡፡ ዶ/ር ነጋሶ ግን ነገሩን ይሸፋፍኑታል፡፡ እኔ እንደማስታውሰው ወሬው የተወራው በሚያዚያ 29/1987 ምርጫው ከመካሄዱ ቀደም ብሎ ነው፡፡ ይሁንና ዶ/ር ነጋሶ ያልጠበቁትና በአጣዳፊ ሁኔታ የተወሰነ ውሳኔ አድርገው ነው “ዳንዲ” በተሰኘው መጽሐፍ የተረኩልን፡፡

ይገርማል! ከወዲህም ከወዲያም እውነት የለም ማለት ነው፡፡ ዶ/ር ነጋሶ ሐቁን ቢነግሩን ምን አለበት? በህገ-ወጥ ሁኔታ ወንበሩ ላይ ተቀመጡ እንዳንላቸው ነው? እንደዚያ ብንላቸውስ ምን እናመጣለን? ምንም አናመጣም!! እኛ ከመታዘብ ውጪ ምንም የምናመጣው ነገር የለም፡፡ ሽማግሌ ግን እውነቱን ቢያወራ ነው የሚያምርበት፡፡ ለዛሬ ባይሆን ለታሪክ ይጠቅመናልና፡፡

ዶ/ር ነጋሶ በመጽሐፉም ሆነ በልዩ ልዩ መጽሔቶች የሰጧቸው የምስክርነት ቃላት በአብዛኛው እውነት ሆነው ተገኝተዋል፡፡ እስከ አሁን ከኢህአዴግ አፈንግጠው ከወጡት ባለስልጣናት መካከል ለእውነት የቀረበ ነገር ሲናገሩ የተሰሙት እሳቸው ናቸው፡፡ የነ ዮናታን ዲቢሳ እና አልማዝ መኮን ነገር ለጊዜው እንርሳው (ሁለቱም አያስተማምኑም)፤ እነ ስዬ አብርሃ ግን ድፍንፍን ያለና ለሰው የማይገባ ውስጠ-ወይራ ነገር ነው የሚናገሩት፤ አንዳንዴ እንዲያውም በኮድ የሚያወሩ ይመስለኝና “ንግግራቸውን እየበታተነ የሚያስረዳን ውስጠ-አዋቂ እንፈልግ እንዴ?” ያሰኘኛል፡፡

ለዚህ ለዚህ ዶ/ር ነጋሶ በጣም ይሻላሉ፡፡ ሆኖም በርካታ ነገሮችን ያድበሰብሳሉ፡፡ በተለይ የፕሬዚዳንትነቱ ዘመን ሲነሳባቸው “ወገቤን” ይላሉ፡፡ እዚህ ላይ ማስተካከያ እንዲያደርጉልን እንፈልጋለን፡፡

===የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት==

ይህኛው እላይ ከጠቀስኳቸው በሚበልጥ ሁኔታ ብዙ የተባለለትና የተጻፈበት ነው፡፡ የነጻው ፕሬስ አባላት ከ1990 መግቢያ ጀምሮ በሰፊው ሲጽፉበት ቆይተዋል፡፡ ወሬው ከሀገርም አልፎ በውጪ የዜና አቀባዮች በስፋት በመናፈሱ የወቅቱ የሀገሪቱ መሪዎች የማስተባበያ መግለጫ ለመስጠት ላይ ታች ሲሉ ተስተውለዋል፡፡ በተለይም ጠቅላይ ሚ/ር መለስ ዜናዊ ከአንዴም ሁለቴ ወደ መንግሥት የመገናኛ ብዙሃን (ሬድዮና ኢቴቪ)፣ አዲስ ዘመን ጋዜጣና እፎይታ መጽሔት እየቀረቡ ሰፋ ያለ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ በሁለቱ ሀገሮች መካከል ወደ ግጭት ሊያመራ የሚችል ልዩነት ተፈጥሯል እያሉ የሚጽፉ የነጻ ፕሬስ አባላትን “ሟርተኞች” እና “ጦርነት ናፋቂዎች” በማለት ከሰዋቸዋል፡፡ በተለይም ከእፎይታ መጽሔት ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ “አንድም ግጭት የለም፤ ግጭት ያለው በትምክህተኞች ጭንቅላት ውስጥ ብቻ ነው” የሚል ሀይለ-ቃል ተናግረዋል፡፡ (እፎይታ፡ ጥር 1990)

የግንቦት ወር ሲደርስ ግን በነጻው ፕሬስ የተወራው ሁሉ እውነት ሆኖ ተገኘ፡፡ ኤርትራ ግዙፍ ሰራዊት አንቀሳቅሳ ባድመ እና ሽራሮን ያዘች፡፡ በማስከተልም ዘላ አንበሳ እና ባዳን ተቆጣጠረች፡፡ ይሄኔ የኢትዮጵያ መንግሥት የተወረርኩኝ ጥሪውን በያቅጣጫው ያሰማ ጀመር፡፡ “ህዝባዊ ግንባርና የኤርትራ መንግሥት ከያዙት መሬት ካልለቀቁ ህጋዊ እርምጃ እንወስዳለን” አለ፡፡

እንዲህ ከተባለ በኋላ ደግሞ አስገራሚው ድራማ ተከተለ፡፡ ባለስልጣናቱ “ኤርትራ ወረራ መፈጸሟ በፍጹም ያልጠበቅነው ነገር ነው” አሉ፡፡ ግጭቱንም በአንድ ጀምበር የተፈጠረ ለማስመሰል ተፍጨረጨሩ፡፡ ህዝቡ ግን በጣም ታዘባቸው፡፡ እውነታውንም በልዩ ልዩ መንገዶች አገኘው፡፡ (የሁለቱ ግጭት ድንገተኛ እንዳልሆነ በትክክል ለማረጋገጥ የተቻለው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ እ.ኤ.አ. ነሐሴ 12/1997 የጻፉት ደብዳቤ እና ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ከሳምንት በኋላ የሰጡት መልስ በኢንተርኔት መስኮት ከተለቀቀ በኋላ ነው፡፡ ደብዳቤዎቹን የለቀቀው ሻዕቢያ ራሱ እንደሆነ ይታመናል፡፡ ይህም “ግጭቱን በቅድሚያ የጀመርኩት እኔ ሳልሆን ወያኔ ነው” የሚለውን ጭብጥ ለማስረዳትና ራሱን ከወራሪነት ነጻ ለማድረግ ታቅዶ የተደረገ ይመስላል፡፡ በደብዳቤው አቶ ኢሳያስ አቶ መለስን “ሰዎችህ በባዳ አካባቢ ዜጎቻችንን ገድለውብናል” ይሏቸዋል)፡፡

ለመሆኑ የኢህአዴግ ባለስልጣናት ግጭቱን ድንገተኛ በማለት ለማድበስበስ የፈለጉት ለምንድነው? ምንም ሚስጢር የለውም፡፡ አንደኛ “ህዝቡ ለወረራው ቅድመ-ዝግጅት አላደረጋችሁም” ብሎ እንዳይከሳቸው ነው፡፡ ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ የነጻውን ፕሬስ ተአማኒነት ለማደብዘዝ ባላቸው ፍላጎት የተነሳ ነው፡፡ ህዝቡ “ነጻው ፕሬስ ውሸታም ነው!” ብሎ እንዲያሽቀነጥረው ነበር የሚፈልጉት፡፡ ሁለቱም አልተሳካም፡፡ የተጠያቂነቱ ጥያቄ ከህዝቡ በኩል ባይሆንም ከዚያው ከኢህአዴጎች ዘንድ ተነስቷል፡፡ ነጻው ፕሬስም ተአማኒነቱን አላጣም (እርግጥ ፕሬሱ በጣም ተዳክሟል)፡፡

===እንደ ምርቃት===

ከላይ የጠቀስኳቸው ድርጊቶች ሁሉ በትክክል ተፈጽመዋል፡፡ መረጃው ግን ከኩነቶቹ በፊት ተሰራጭቷል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ ወሬዎቻቸው በቅድሚያ እየተወራላቸው በእውነታው ዓለም የተከሰቱ ሌሎች ድርጊቶችም አሉ፡፡ አንዳንዶች ደግሞ በቀጥታ ባይወራላቸውም በፖለቲካ ቋንቋ እየተሸሞነሞኑ ሲነገርላቸው ህዝቡ አዳምጧል፡፡ እነዚህን መሰል ኩነቶችን እየለቀምን በስፋት መመርመር እንችላለን፡፡ ሆኖም ያንን ማድረግ ለአሁኑ ብዙም አያስፈልገንም፡፡ ሁለት የማስታውሳቸው ክስተቶች ጥለውብኝ ያለፉትን ትዝታ ልመርቅላችሁና ላብቃ፡፡

የህወሐት ማዕከላዊ ኮሚቴ ለሁለት መከፈል ለሁላችንም ያልተጠበቀ ዱብ እዳ ነው የሆነብን፡፡ አብዛኞቻችን ክስተቱን የሰማነው በዕለተ ረቡዕ መጋቢት 12/1993 ነው፡፡ በዕለቱ ከወጡት ጋዜጦች መካከል “ኢትኦጵ” የተሰኘችው ናት መረጃውን ይፋ ያደረገችው፡፡ ታዲያ ብዙዎችን ያስደነቀው እንዲህ ዓይነት ዜና ለሀገሪቱ የመረጃና ደህንነት መዋቅሮች ቅርብ ነው በሚባለው “ሪፖርተር” ጋዜጣ ላይ አስቀድሞ አለመውጣቱ ነው፡፡

ሆኖም ነገሩ በትክክል ሲጠና “ሪፖርተር” ወሬውን በጨረፍታ የነካካ መሆኑ ታውቆለታል፡፡ ሪፖርተር በየካቲት ወር ማብቂያ ገደማ በርዕሰ አንቀጹ “ኢህአዴግ ከጭነቱ ልክ በላይ የሆነ ችግር ገጥሞታል” ይልና በካርቱን ስዕል አቶ መለስ በጣም ከባድ የሆነ ጭነት ለመሸከም ሲሞክሩ ያሳየናል፡፡ ርዕሰ አንቀጹ ወደታች ሲነበብም “ኢህአዴግ ተቸግሯል፤ አስቸጋሪ ሁኔታ ገጥሞታል፤ ይህንን ችግር በሰከነ መንፈስ ለማሳለፍ መጣር አለበት” ወዘተ እያለ ይቀጥላል፡፡ ይሁንና ስለተፈጠረው ክፍፍል አንድም ነገር አይናገርም፡፡ የሪፖርተርን ርዕስ አንቀጽ በትኩረት የሚከታተሉ አንባቢያን (በተለይ ጋዜጠኞች) “ምን ችግር ተፈጠረ” በማለት ጉዳዩን ማነፍነፍ ጀመሩ፡፡ በአስር ቀናት ውስጥም ጮማ ወሬ ይዘው ብቅ አሉ፡፡ ከዚያ በኋላ ለሶስት ወራት ያህል አገር ምድሩ ጋዜጣ አንባቢ ሆነ፡፡ ለያኔው ወሬ ክሬዲቱ የሚሰጠው ለማን ነው? እኔ እንጃ! በዚህ አጋጣሚ ሪፖርተርን የምንጠይቀው ለወደፊቱም እንዲህ ዐይነት ወሬ ሲገኝ በቆረጣ ማውጋቱን እንዳይረሳ ነው፡፡

ሌላ እንደ ጭማሪ የማወራላችሁ የመቶ አለቃ ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ ፕሬዚዳንት ሆኖ መመረጥን የሚመለከት ነው፡፡ ትዕይንቱ እስከ አሁን ድረስ ያስቀኛል፡፡ የኢህአዴግ አባል ከሆኑ የፓርላማ ተመራጭ ጓደኞቼ በፊት ወሬውን የሰማሁት መሆኔ ነው የሚያስቀኝ፡፡ በጊዜው “ፖለቲካ” የምትባል ጋዜጣ መታተም ጀምራ ነበር (ጋዜጣዋ ባልተለመደ መልኩ ሰኞ ሰኞ ነበር የምትወጣው)፡፡ እናም “ፖለቲካ” ጋዜጣ ላይ “ውስጠ አዋቂዎች እንደተናገሩት የ75 ዓመቱ አዛውንት ፕሬዚዳንት ሊሆኑ ነው ይባላል” የሚል ዜና አየሁ፡፡ በወቅቱ የጋዜጣው አዘጋጆች ወሬውን እየተጠራጠሩት እንዳወጡት ተናግረዋል፡፡ እኛ አንባቢያንም ተጠራጥረናል፡፡ ቢሆንም ከጋዜጣው ያገኘሁትን ወሬ ለጓደኛዬ አደረስኩ፡፡ እርሱ ፓርላማ ግቢ ውስጥ ሆኖ በስልክ ያናግረኝ ነበር፡፡ “ይህማ ውሸት ነው፡፡ እንዴት ያንን ሽማግሌ ያስመርጡናል? ደግሞ እኮ መንግሥትን በጣም ይቃወማል” አለኝ፡፡ “ቢሆንም ወሬውን ለምናልባቱ ያዘው” አልኩትና ተለያየን፡፡

ከአንድ ሰዓት በኋላ ከፖለቲካ ጋዜጣ ያገኘሁት ወሬ ልክ ሆኖ ተገኘ፡፡ እውነትም መቶ አለቃ ግርማ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሆነው ተሰየሙ፡፡ ፓርላማ ውስጥ የነበረው ጓደኛዬ ያንን ሁኔታ ካየ በኋላ ወደ ቢሮዬ መጥቶ የተናገረኝን ነገር በፍጹም አልረሳውም፡፡ “ለስሙ እኔ ነኝ የፓርቲው አባል፡፡ መረጃውን በቅድሚያ የምታገኙት ግን አባል ያልሆናችሁት ናችሁ፤ በዚህ ዓይነት አራት ኪሎ ሄጄ ፓርላማ ከመግባቴ በፊት በቀጥታ ጆሊ ባርን ብጎበኘው ይሻለኛል ማለት ነው” አለኝ፡፡ በጣም ሳቅኩኝ፡፡ በወቅቱ ብዙዎቹ የኢህአዴግ አባላት ግምገማ አለ እያሉ ስለሚፈሩ የግል ጋዜጣ ከመግዛት ይቆጠቡ ነበር (እኔም የሳቅኩት ይህንን ስለማውቅ ነው)፡፡

ጆሊ ባር የሚገባ ሰው በርግጥም በርካታ ወሬዎችን በቀላሉ ያገኛል (የአራት ኪሎው ጆሊ ባር አሁን ትክክለኛ የፈረንጅ ጆሊ ባር ሆነ እንጂ)፡፡ ወይንም ጆሊ ባር አጠገብ ጋዜጣና መጽሔት እያነጠፉ የሚሸጡትን እነ “ቦቸራ”ን የተወዳጀ ሰው ሁለት ብር ከፍሎ ብዙ ወሬ አንብቦ ይመለሳል፡፡ ቢሆንም ሰፊው ህዝብ ወሬውን ለመስማት የግዴታ ወደ ጆሊ ባር መሄድ አይጠበቅበትም፡፡ የትም ቢሆን ወሬው ይደርሰዋል፡፡ በተለይ ባለስልጣናት የሚደብቋቸውና “ውሸት ነው” እያሉ የሚያስተባብሏቸው ግንባር ወሬዎች የኋላ ኋላ ህዝቡ ዘንድ መድረሳቸው አይቀርም፡፡ ባለስልጣናቱ “ውሸት” ያሉት ወሬ እውነት ሆኖ ከተገኘ ህዝቡ ለጊዜው በትዝብት ያልፈዋል፡፡ ለትክክለኛው ፍርድ ደግሞ ወደ ታሪክ ያስተላልፈዋል፡፡ ታሪክም ሳያዳላ እውነተኛውን ፍርድ ይበይናል፡፡
ከታሪክ ፍርድ ይሰውረን!!

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: