ውብሸት ሙላት
(ክፍል አንድ)
ሰሞኑን ዓለምአቀፍ የመገናኛ ብዙኃንን ከተቆጣጠሩ አጀንዳዎች ውስጥ አንዱ የመገንጠል ጉዳይ ነው፡፡ የኩርድስታን እና የካታላን ሕዝበ ውሳኔዎች፣ እንግሊዝኛ ተናጋሪ የሆኑት ካሜሩኖች የመገንጠል እንቅስቃሴ ተጠቃሽ ናቸው፡፡
በኢራቅ፣በስፔንም ይሁን በካሜሩን ሕገ መንግሥቶች ላይ ከአገር መገንጠያ አንቀጽ የላቸውም፡፡ ለነገሩ በቀድሞዎቹ የሶቪየት ኅብረት (ሩሲያ) እና ዩጎዝላቪያ፣አሁን ደግሞ ሴንት ኪትስና ኔቪስ ከምትባል የካሪቢያን ደሴት እና ከአውሮፓ ኅብረት ቻርተር ውጭ የመገንጠያ አንቀጽ ያለው ሕገ መንግሥት የለም፤ከኢትዮጵያ በስተቀር፡፡ የኢትዮጵያው ወደ ሩሲያና ዩጎዝላቪያ የሚቀርብ ነው፡፡ ይሁን እንጂ፣ እነዚህ አገራት ጥቅም እንደሌለው ተረድተው ሲተውት፣ ኢትዮጵያ እንደ አዲስ ተቀብላዋለች፡፡ ሩሲያና ዩጎዝላቪያም ቢሆኑ ግን ሕገ መንግሥታቸው ላይ በተቀመጠው ሁኔታ አለመገንጠላቸውን ልብ ይሏል፡፡
ይህ ጽሑፍ የሚዳስሰው ሕገ መንግሥቱ ሲረቀቅም ሆነ ሲጸድቅ እንዲሁም ኋላ ላይ ፖለቲከኞችም ይሁኑ ምሁራን ብዙም ትኩረት ካልሰጠባቸው ጉዳዮች አንዱ የሆነውን የመገንጠል ሥነሥርዓትን ወይንም ሒደትን ነው፡፡
ሕገ መንግሥቱ ሲረቀቅም ይሁን ሲጸድቅ እጅግ ካጨቃጨቁት ጉዳዮች ዋነኛው አንቀጽ 39 ንዑስ ቁጥር 1 ላይ የተገለጸው የብሔሮች፣ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ያለምንም ገደብ መገንጠልን በሕገ መንግሥቱ የመካተቱ ነገር ነው፡፡በዚህ አንቀጽ ውስጥ የተዘረዘሩት ሌሎች አራት ንዑሳን አንቀጾች ግን ከጅምሩም ትኩረት አልሳቡም፣ወይንም አልተሰጣቸውም፡፡
የመገንጠል መብት ሕገ መንግሥታዊ ዋስትና እንዲኖረው በትጋት የተከራከሩት እና የሚከራከሩት ሰዎች ከሚያነሷቸው ምክንያቶች መካከል ቀዳሚው እና ዋነኛው ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች በኢትዮጵያዊነት ጥላ ሥር አብረው መኖር ካልቻሉ ያለ ጦርነት ወይንም በሰላም ለሚለያዩበት ሁኔታ ዋስትና ይሰጣል የሚል ነው፡፡
በመሆኑም፣ መገንጠልን የመረጡ ቡድኖች ደረጃ በደረጃ ሊከተሏቸው የሚገቡ አምስት ሥነሥርዓቶች በዚሁ አንቀጽ ንዑስ ቁጥር አራት ላይ ተቀምጠዋል፡፡ ‘የሰይጣን ጆሮ አይስማና’፣ አንድ ብሔር መገንጠል ቢፈልግ እና እነዚህን ሥነሥርዓቶች በመከተል ምንም ዓይነት ጦርነት ወይንም እልቂት ሳይኖር በሰላም የመገንጠልን መብት ሥራ ላይ ለማዋል ማስቻላቸው ግን ፍተሻ ያስፈልጋቸዋል፡፡
ይህ ጽሑፍ እነዚህን ሥነሥርዓቶች ያሉባቸውን እንከኖች በማሳየት የመገንጠል መብትን ሥራ ላይ ማዋል የሚፈልግ ብሔር ቢኖር በሰላም ለመለያየት የማያስችሉ መሆናቸውን ማሳየት ነው፡፡
መገንጠል በዘፈቀደ የሚፈጸም ድርጊት እንዳይሆን በማሰብ ሥነሥርዓቶቹ ቀድመው ተቀምጠዋል፡፡ የመገንጠልን ጉዞ ለሚመርጥ ተጓዥ፣ መንገዱ እንዲህ ነው፡፡
መገንጠልን የሚፈልገው ብሔር ወይንም ብሔረሰብ ወይንም ሕዝብ ምክር ቤት በ2/3ኛ መገንጠሉን ሲደግፍ፣ የፌደራሉ መንግሥት በሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ሕዝበ-ውሳኔ ሲያዘጋጅ፣ መገንጠሉን አብዝኃኛው ሕዝብ ሲደግፈው፣ የፌደራሉ መንግሥት ሥልጣን ሲያስረክብ፣ እና የንብረት ክፍፍል ሲካሔድ ነው፡፡
እነዚህ የመገንጠያ መንገዶች ናቸውና ተራ በተራ እንያቸው፡፡
የምክር ቤት ውሳኔ፤
=============
በመጀመሪያ፣ መገንጠል የሚፈልገው ብሔር የራሱ ምክር ቤት ሊኖረው ግድ ነው፡፡ ምክር ቤቱም በ2/3ኛ ድምፅ የመገንጠሉን ሐሳብ ካልደገፈ በስተቀር ቀጣዮቹ ሥርዓቶች ምንም ፋይዳ የላቸውም፡፡ በመሆኑም ጥያቄው በዚሁ ተኮላሸ ማለት ነው፡፡
በሴንት ኪትስ እና ኔቪስም (ከኢትዮጵያ 12 ዓመታት በመቅደም የመገንጠል መብትን በሕገ መንግሥቷ ያካተተች ባለ ሁለት ክልሎች አገር ናት፡፡) መጀመሪያ የኔቪስ ደሴት ሕግ አውጭ ምክር ቤት በ2/3ኛ የድጋፍ ድምፅ መስጠት አለበት፡፡ከዚያ በኋላ ይሄው ምክር ቤት በሕዝበ-ውሳኔ ወቅት ለኔቪስ ደሴት መራጮች የሚያቀርበውን አማራጮች ሕዝቡ ድምፅ ከመሰጠቱ ቢያንስ ከዘጠና ቀናት በፊት ማሳወቅ ይጠበቅበታል፡፡
አማራጮቹም፣ ከሴንት ኪትስ ተለይቶ ነጻ አገር መመሥረት፣ ከሌላ አገር ጋር መቀላቀል ወይንም አለመለየት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በካናዳም፣ ለሕዝበ ውሳኔ የሚቀርበው ጥያቄ ግልጽ መሆን እንዳለበትና ቀድሞ በአገሪቱ ፓርላማ መጽድቅ አለበት፡፡
በኢትዮጵያ፣ የብሔሩ ምክር ቤት ለመገንጠሉ አጀንዳ የ2/3ኛ የድጋፍ ድምፅ ከሰጠ ይሄንኑ ውሳኔ በጽሑፍ ለፌደሬሽን ምክር ቤት ያቀርባል፡፡ የፌደሬሽን ምክር ቤትም ጥያቄው ከደረሰው ጀምሮ በሚታሰብ በሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ሕዝበ-ውሳኔ ማዘጋጀት አለበት፡፡
በኔቪስ ደሴት ግን ሕዝበ-ውሳኔውን የሚያከናውነው የፌደራል መንግሥቱ ሳይሆን ራሷ ደሴቷ ናት፡፡ የምርጫ ኮሚሽኑም የሚዋቀረው የደሴቷ ገዥ የሚሾመው ሰብሳቢ፣ተቃዋሚ ፓርቲዎችን እና የአገሪቱን ጠቅላይ ሚኒስትርን አማክሮ ሁለት በድምሩ ሦስት አባላት ባሉት የምርጫ ኮሚሽን አማካይነት ይከናወናል፡፡ በኩርድስታንና በካታሎኒያም ቢሆን ኢራቅ ወይንም ስፔን አይደሉም ምርጫውን የሚያስፈጽሙት፡፡
በመሆኑም፣በኢትዮጵያ፣ከፌደሬሽኑ ለሚገነጠል ብሔር የፌደራሉ መንግሥት (የቀሪው አካል) የምርጫ ቦርድ አስፈጽሞት በምን መልኩ ሰላምን ሊያመጣ ይችላል? ቅሬታዎችም ወደ እዚሁ ቦርድ እና ወደ ፌደራል ፍርድ ቤቶች የሚመጡ ከመሆናቸው አንጻር እንደምን ተኣማኒነትና ተቀባይነት ይኖራቸዋል? የፌደራሉ መንግሥት ሊይዝ የሚችለው አቋም እንዳይገነጠሉ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡ ምናልባት እንደ ኤርትራ “ተገንጠሉልን፣ሂዱልን” ካልተባለ በስተቀር!
“የማሰላሰያ ጊዜ”፤
===========
ብሔሮች፣ ከኢትዮጵያ ከመፋታታቸው በፊት የማሰላሰያ ጊዜ ባይቀመጥም የፌደራሉ መንግሥት በሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ሕዝበ-ውሳኔ እንዲያዘጋጅ መደንገጉ ወይንም በጣም አጭር ጊዜ አለመሆኑ መገንጠል የሚፈልገው ብሔርም እንዲያስብበት፣ ቅስቀሳና የማሳመን ሥራ የማከናወኛ ጊዜ በመሆን ሊያገለግል ይችላል፡፡
በተቃራኒው ደግሞ አንድነትን ለሚሰብኩትና የሚደግፉት የማግባባትና የመቀስቀስ ተግባራቸውን በዚህ ወቅት ለማከናወን ዕድል ያገኛሉ፡፡ በመሆኑም፣ይህ እንደ ማሰላሰያ ጊዜ ሊወሰድ ይችላል፡፡
የመገንጠያ ሥነ-ሥርዓት በሕገ መንግሥቷ አብጅታ የነበረችው ሩሲያ ግን ከዚህ የተለየ የማሰላሰያ ጊዜ ነበራት፡፡ የሩሲያ ሪፐብሊኮች(ክልሎች) ለመገንጠል በትንሹ አምስት ዓመት ይፈጅባቸዋል፡፡ ምክንያቱም ሕዝበ-ውሳኔ ተደርጎ በ2/3ኛ ድምፅ ድጋፍ ካገኘ በኋላ በድጋሜ በአምስተኛ ዓመቱ መጨረሻ ላይ የማረጋገጫ ሕዝበ-ዉሳኔ በማከናወን ድምፅ መስጠት ከሚችለው ከሪፐብሊኩ ኗሪዎች ውስጥ 2/3ኛው መገንጠልን መደገፋቸው መረጋገጥ አለበት፡፡
በመሆኑም ሐሳባቸውን ሊቀይሩ ከቻሉም ዕድል ይሰጣል፡፡ ይህ አድራጎት ሽማግሌዎች ባልና የሚስት ለማስታረቅና ለማግባባት የሚጠቀሙበትን ስልት ያስታውሰናል፡፡ ባልና ሚስት ተጣልተው ጉዳያቸው በሽምግልና እንዲታይላቸው ለመረጧቸው ሽማግሌዎች ብሶታቸውንና በደላቸውን ማሰማት ሲጀምሩ ሽማግሌዎች የጠቡን ምንጭ ጊዜያዊነት ወይንም ጥንካሬ ለመረዳት ሁለቱንም ወገኖች “እስኪ ከማሸማገላችን በፊት ጉዳዩን ነት ይንካው” በማለት ይመልሷቸዋል፡፡
“ነት” ማለት፣ ብዙ በገጠር አካባቢ የሚኖር ሰው እንደአንሶላ የሚጠቀሙበት የለሰለሰ (የታረበ) የበሬና የላም ቆዳ ነው፡፡ “ነት ይንካው” ሲባል ባልና ሚስት ጥልና ብሶታቸውን ከማሰማታቸውና ውሳኔ ከማሳለፋቸው በፊት አብረው በአንድ ነት ላይ ተኝተው አድረው በድጋሜ እንዲያጤኑት ለማድረግ ነው፡፡ በንዴት የተፈጠረ፣ በድንገት የተከሰተ ከሆነ ነቱ ላይ ይቀራል፡፡ የመረረና የከረረ ከሆነ አንድ ነት ላይ መተኛት ስለማይችሉም የችግሩን መጠን ለመረዳት ይረዳል፡፡
የሩሲያዎች ሕገ-መንግሥት “ነት ይንካው” የሚለውን አካሔድ የተከተለ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ አምርረው በ2/3ኛ ድምፅ ከወሰኑም በኋላ አምስት ዓመት ነት ማሥነኪያ ወይንም ማሰላሰያ ጊዜ ሰጥተዋል፡፡ ከዚህ አንጻር የእኛን ሕገ-መንግሥት ስናየው አፍን ሞልቶ ለማሰላሰል፣” ሽልም ከሆነ መግፋቱን ቂጣም ከሆነ መጥፋቱን” ለማወቅ የሚያስችል ጊዜ እንዳልተሰጠው መረዳት ይቻላል፡፡
የፌደራሉ መንግሥት በሦስት ዓመት ጊዜ ሕዝበ-ውሳኔ እንዲያስፈጽም፣ እንዳያጓትት የጊዜ ጣሪያ ከማስቀመጥ በዘለለ በወሩም ይሁን በዓመቱ ማዘጋጀትን አይከለክልም፡፡
(ይቀጥላል)