የቅይጥ ትይዩ የምርጫ ሥርዓት ምንነት፤ዲሞክራሲን ላለማሻሻል ያሉበት ተግዳሮቶች

Wuobishet Mulat

ውብሸት ሙላት

ሕገ መንግሥቱ እንደ መገለጫ ወይም ባሕርይ በማድረግ ከወሰዳቸው አንዱ ዴሞክራሲያዊ መሆን ነው፡፡ ዴሞክራሲያዊ መሆኑ የሚታወቀው ደግሞ አገሪቱ ሉዓላዊ የሥልጣን ባለቤቶች የሆኑት ብሔሮች፣ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ራሳቸው በቀጥታ ወይንም በመረጧቸው ተወካዮች አማካይነት ሲሳተፉ፣ሲወስኑ እና ሲወከሉ ነው፡፡

በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የአገሪቱ ሕዝብ በጅምላ ወይም በብሔር፣ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ ደረጃ በተለያዩ አስተዳደራዊ እርከኖች ላይ ፍትሐዊ በመሆነ ስልት በመወከል፣ተሳታፊ ሆነው ውሳኔዎችን ማሳለፍን ይጠይቃል፡፡ ይህን ዓይነቱን አሠራር ለማስፈን ደግሞ የምርጫ ሥርዓት ሊኖር ግድ ነው፡፡
ከ1983 ዓ.ም. ጀምሮ ለተለያዩ ዓላማዎች፣ በበርካታ ምክር ቤቶች አባል፣የመራጩም እንደራሴ ይሆኑ ዘንድ ለመምረጫነት ተግባር ላይ የዋለው በጥቅል አጠራሩ “አብላጫ የምርጫ ሥርዓት” የሚባለውን ነው፡፡
አሁን ኢትዮጵያ የፌደራል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት እንዲመረጡበት እየተጠቀመችበት ያለው ከአብላጫ የምርጫ ሥርዓት ዘውጎች ውስጥ አንዱ የሆነው በአንድ የምርጫ ወረዳ ውስጥ ከተወዳደሩት መካከል አንደኛ የወጣው ተወዳዳሪ አላፊ የሚሆንበት (ከአሁን በኋላ የአንደኛ አላፊ ሥርዓት በማለት የሚጠራውና በእንግሊዝኛ First-Past-The-Post የሚባለው) የምርጫ ሥርዓት ነው፡፡

ይህ የምርጫ ሥርዓት በድምጽ አባካኝነቱ፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በአገር አቀፍ ደረጃም ይሁን በክልሎች ወይም ከዚያ በታች በሚገኙ ምክር ቤቶች ዘንድ ባገኙት ድምጽ መጠን እንዳይወከሉ እንቅፋት እንደሆነ ስለተቆጠራና በሌሎች በርካታ ምክንያቶችም እንደሚቀየር ከታወቀ ዓመት ሞላው፡፡ ይሁን እንጂ፣ወደምን ዓይነት የምርጫ ሥርዓት እንደሚቀየር በቁርጥ አልታወቀም፡፡

ገዥው ፓርቲ ከሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር እያደረገ ባለው ድርድር ላይ በተቃዋሚዎች (ቢያንስ በተወሰኑት) በጥቅሉ ተመጣጣኝ ውክልና በመባል የሚታወቀውን በአማራጭነት ማቅረባቸው ተሰምቷል፡፡ ገዥው ፓርቲ በበኩሉ ቅይጥ ትይዩ እንዲሆን ሐሳብ አቅርቧል፡፡

ይህ ጽሑፍ ገዥው ፓርቲ በአማራጭነት ያቀረበው አማራጭ ለአገሪቱ እንግዳ ስለሆነ፣የተወሰነ መግለጫ በመስጠት የምርጫ ሥርዓቱን ለማሻሻል ምክንያት የሆኑትን ችግሮች በመቅረፍ ዴሞክራሲን ለማስፈን ማስቻሉን ለመፈተሸ የሚረዱ ሐሳቦችን ማቅረብ ነው፡፡

ለምርጫ ሥርዓት ቅያሬ ምክንያቶቹ፤
===========================
የነበሩት ሕገ መንግሥታት ሊቀርፋቸው ካልቻሉት ችግሮቻችን አንዱ እጅግ የጠነከረ/ግትር መንግሥትን ወደ ውይይት ማምጣት አለመቻል፣ የሌሎችን ሐሳብ ወደ ማዳመጥና ልዩነቶችን ወደ ማስተናገድ ማረቅ የሚችል ተቋም መገንባት አለመቻል ነው፡፡

ሌላው፣ አሸናፊው ሁልጊዜም አንድ ፓርቲ በመሆኑ የአሸናፊው ፓርቲና የደጋፊዎቹ ሐሳብና ፍላጎት በቋሚነት እያሸነፈ እንዲኖር የቀሪዎቹ ደግሞ ሁልጊዜም ተሸናፊነታቸውን እየተቀበሉ እንዲኖሩ፣ ሐሳብና ፍላጎታቸው ደግሞ በተካታታይ በፓርላማው እንዳይሰማ፣ ልዩነታቸው እንኳን አለመንጸባረቁም ሌላው እንከናችን ነው፡፡ በእንዲህ ዓይነት ሥርዓት ቅያሜው እየበረታና እየገነነ እንደሚሄድ ግልጽ ነው፡፡

የምርጫ ሥርዓታችንና ውጤቱ እያሳየን ያለው በቋሚነት (በ1997ቱ ከነበረው ውጪ) ውክልና ያለው አንደኛውን ቡድን ብቻ ነው፡፡ በተቃራኒው ሌሎች ቡድኖች ቋሚ ተሸናፊ እንደሆኑ ቀጥለዋል፡፡ ከእኒህ ፓርቲዎች ጀርባ ወይንም ገዥው ፓርቲን ከማይመርጠው ውጭ ያለው ሕዝብም በተሸናፊነቱ እንደቀጠለ ነው፡፡ የምርጫ ሥርዓታችንም ይሁን ፖለቲካው እነዚህን ኃይሎች ለማካተት ሲሞክር አልታየም፡፡
ቢያንስ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በየቦታው የሚያገኙት ድምጽ ወደ ፓርላማ ወንበር ሊቀየርላቸው፣ በአስፈጻሚው ውስጥ ሊካተቱ ይገባል፡፡ ሊያሳስበንም የሚገባው ይኼው የተሸናፊዎች (Losers) ሁኔታ ነው፡፡ ለዚያውም ነጻና ፍትሐዊ መሆኑ አጠያያቂ በሆነበት፣ ከዚያም ከዚህም የሚሰበሰቡ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ድምጾችን ይዞ ነገር ግን ሁልጊዜ ሽንፈትን መቀበል አዳጋች ነው፡፡ ሁልጊዜ “አሜን” እያሉ ለመቀበል ትልቅ ጸጋና ጥበብን ይጠይቃል፡፡

ሕገ መንግሥታዊው የዴሞክራሲ ሥርዓት ተረጋግቶ እንዲቀጥል፣ሥር የሰደደ መሠረት እንዲኖረው የምርጫ ተሸናፊዎቹ ሥምምነት ጉልህ ድርሻ አለው፡፡ በጉዳዩ ዙሪያ ጥናት ያደረጉት ዊሊያም ራይከር የተባሉ ምሁር እንዲህ ብለዋል፡-“የፖለቲካው መዘውር (dynamics) ያለው በተሸናፊዎች እጅ ላይ ነው፤እነሱ ናቸው መቼ እና እንዴት እንዲሁም እንደሚፋለሙት ወይንም እንደማይፋለሙት ሊወስኑ የሚችሉት፡፡”
ሌላ ጸሐፊም የተወሰነ ደጋፊ ኖሮ፣ በቋሚነት ፈጽሞ የማይወከሉ ከሆነ ተስፋ ስለሚቆርጡ በምርጫ አለመሳተፍን ወይንም ምርጫ ሲደርስ ከምርጫው መውጣትን (boycott ማድረግን) ሊያስከትል ይችላል፡፡ ሲብስም አመጽና አብዮት ወይንም ጦርነት ሊያስነሳ እንደሚችል የተለያዩ ሀገራትን ልምድ ዋቢ በማድረግ አቅርበዋል፡፡

በየትም አገራት ቢሆን የምርጫ ሥርዓቱን ለመቀየር ሲፈለግ ቀድሞ የነበረው ሊቀርፋቸው ያልቻሉ ችግሮች የመኖሩ ጉዳይ አያጠያይቅም፡፡ በጥቅሉ ሊጤኑ ከሚገባቸው ጥያቄዎች ውስጥ የሚከተሉትን ማንሳት ይቻላል፡፡

በመራጩ ኅብረተሰብ ዘንድ ከተቀባይነት አንጻር ውጤታማነትን የሚጨምር፣ የተለየ ድምጽን አካታች ማድረግ መቻሉ፣ ለመራጮች ቀላል ግልጽና ተደራሽ የሆነ፣ ሕዝብ ዓመኔታ የሚጥልበት የሚቆጣጠረውም ሊሆን ይገባል፡፡

እስከ ዛሬ ጥቅም ላይ ውሎ የነበረው የአንደኛ አላፊ የምርጫ ሥርዓት ድክመቶቹ ምንድን ነበሩ? ከአንድ ዓይነት የምርጫ ሥርዓት ይልቅ ቅይጥ የሆነን ለመጠቀም የሚገፉ ምክንያቶች አሉን? አዲሱ የምርጫ ሥርዓት ልዩ ፍላጎት/ጥቅም ያላቸውን አነስተኛ ወገን ሳይሆን የብዙኃኑን ድምጽ የሚያንጸባርቅ ነው ወይ? ቅይጥ የምርጫ ሥርዓት በሚሆንበት ጊዜ ምን ዓይነት ቅርጽ ያላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲኖሩ ይጠበቃል/ይፈለጋል? በሚሻሻለው የምርጫ ሥርዓት አሸናፊ እና ተሸናፊ እንዲሆኑ የሚፈለጉት ምን ዓይነት ወይንም የትኞቹ ፓርቲዎች ናቸው? የሚመረጠው የምርጫ ሥርዓት ዝርዝሩ ምን መምሰል/መሆን አለበት?
አንድ የምርጫ ሥርዓት ሲመረጥ ወይንም ሲሻሻል ከግምት ማስገባት ያለበትን ዕሴቶችና መርሆች ማወቅ ጉዳዩን የበለጠ ለመረዳት ስለሚጠቅም አስቀድመን እነሱን እንይ፡፡

የምርጫ ሥርዓት መምረጫ መስፈርቶች፤
==========================
ዶናልድ ሆሮዊትዝ ለሚባሉት ምሁር፣ የድምጽና የምክር ቤት መቀመጫ ተመጣጣኝነት፣ ተመራጮች ለመራጮቻቸው ተጠያቂ እንዲሆኑ ማስቻሉ፣ የተረጋጋ መንግሥት ማስፈን መቻሉ፣ በሕዝብ እውቅናና ድጋፍ ያላቸውን ተወዳዳሪዎች ማስመረጡ፣ ብሔርነክና ሃይማኖታዊ ልዩነቶችን ለማስታረቅ የሚያግዝ መሆኑ እና አናሳ ቡድኖች ሥልጣን ማስያዙ መለኪያዎች ናቸው፡፡

ለዓለም አቀፉ የምርጫና የዲሞክራሲ ተቋም ደግሞ (International Institute for Democracy and Electoral Assistance/IDEA) መስፈርቶቹ ከመልክአ ምድር፣ ከርዕዮተ ዓለም፣ በብሔርና ሌሎች ምክንያት የተከፋፈሉ ማኅበረሰብን በተገቢው ሁኔታ እንዲወከሉ ማስቻሉ አንዱ ሲሆን ለሕዝቡ ተደራሽና ትርጉም ባለው መልኩ መራጮች እንዲወከሉ ማድረጉ፣ ስምምነትንና እርቅን ማበረታቱ፣ ቀልጣፋና የተረጋጋ መንግሥት እንዲኖር ማሳለጡ፣ በአንድ በኩል የመንግሥትን በሌላ በኩል ደግሞ የተመራጩን ተጠያቂነት ማስፈኑ፣ ጠንካራና ውጤታማ ፓርቲዎች እንዲኖሩ ማገዙ፣ በሕግ አወጣጥ ሂደት ወቅት ተቃዉሞና ቁጥጥር እንዲያድግ መርዳቱ ብሎም የምርጫ ቀጣይነትን የሚያመጣና ከዓለምአቀፍ መስፈርቶች ጋር የተጣጣሙ መሆን መቻላቸው በመስፈርትነት ይወስዳቸዋል፡፡

ኢትዮጵያ የምትጠቀምባቸው የምርጫ ሥርዓቶች፤
==============================
በሕገ-መንግሥታችን በአንቀጽ 54(2) መሠረት በአንድ የምርጫ ክልል ውስጥ ከቀረቡት ተወዳዳሪዎች መካከል አብላጫ ድምጽ ያገኘው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባልነት እንደሚመረጥ ስለሚደነግግ የአንደኛ አላፊ ሥርዓት መሆኑን እንረዳለን፡፡ ይህንን የአመራረጥ ሒደት በምሳሌ ለማስረዳት በዚህ ዓመት ከአዲስ አበባ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተከናወነውን ምርጫ እንይ፡፡

በአንድ የምርጫ ክልል ውስጥ 12 ፓርቲዎች እጩዎቻቸውን አቀረቡ፡፡ እንበልና 50,000 መራጮች ከ12 ተመራጮች አንዱን ለመምረጥ ድምጽ ሲሰጡ የኢሕአዴጉ እጩ 6000 ብቻ አግኝቶ ሌሎቹ ከዚህ በታች ቢያገኙ አንደኛ ሆኖ ያልፋል ማለት ነው፡፡ ከሌሎቹ መብለጥን እንጂ ከግማሽ በላይ ማግኘትን አይጠይቅም፡፡በመሆኑም ወደ 44000 የሚደርስ ድምጽ ይባክንና አናሳው ብዙሃኑን መግዛቱን ይቀጥላል፡፡ በዚህ ሥርዓት አንድ ፓርቲ በአንድ የምርጫ ክልል የሚያቀርበው ተወዳዳሪ አንድ ብቻ ነው፡፡

የክልል፣ የልዩ ዞን፣ ወረዳ እና ቀበሌ ምክር ቤት አባላት የሚመረጡበት ሥርዓት አሁንም የአብላጫ ድምጽ ይሁን እንጂ ከላይ ለፌደራሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትን ከሚመርጥበት ይለያል፡፡ ለእነዚህ ምክር ቤቶች በአንድ የምርጫ ክልል ውስጥ አንድ ፓርቲ ከአንድ በላይ ተወዳዳሪዎችን ስለሚያቀርብ መራጮችም እንዲሁ ከአንድ በላይ እጩዎችን መምረጥ ይችላሉ፡፡ ይኽ የምርጫ ዓይነት በእንግሊዝኛው Block Vote ይባላል፡፡

የአንደኛ አላፊ የምርጫ ሥርዓት ጥቅምና ጉዳቶች፤
=============================
አንደኛ አላፊ የምርጫ ሥርዓት በቀላልነቱ፣ የአንድ ፓርቲ አገዛዝ ስለሚፈጥር ቅልጥፍናን በማምጣቱ፣ ወጥነት ያለው አቋም የሚይዝ ፓርቲ እንዲኖር በማበረታታቱ፣ ሰፊ መሠረት ያለው ፓርቲ እንዲፈጠር በመርዳቱ፣ ጽንፈኛ ፓርቲዎችን ከምክር ቤት የማራቅ ፋይዳ ስላለው፣ በምርጫ ጣቢያና ተመራጭ መካከል ግንኙነት በመፍጠሩ ብሎም ተጠሪነት እንዲኖር በማስቻሉ፣ መራጮች ከፓርቲ በዘለለ ሰዎችንም ስለሚያስመርጥ እንዲሁም ግለሰብ ተወዳዳሪዎችን ለማሳተፍ ክፍት በመሆኑ በአሁኑ ወቅት 45 የሚሆኑ አገራት ይጠቀሙበታል፡፡

ይሁን እንጂ ይኽ የምርጫ ሥርዓት አናሳ ፓርቲዎችን ከፓርላማና ከአስፈጻሚው አካል ስለሚያስወግድ፣ አናሳ ብሔሮችንና ሴቶችን በአግባቡ ስለማያካትት፣ ብሔር ተኮር ፓርቲዎችን እንደአሸን እንዲፈለፈሉ እና ክልላዊነትን (አካባቢያዊነትንም ማለትም ይቻላል) በማበረታቱ፣ በድምጽ አባካኝነቱ እና ድምጽን በመሰነጣጠቁ እና ለሕዝብ አስተያየት ጆሮ ዳባ ልበስ ባይነቱ በርካታ እንከኖች ያለቡት በመሆኑ ከ150 አገራት በላይ ይሄን የምርጫ ሥርዓት አይጠቀሙበትም፡፡

የተመጣጣኝ ውክልና ሥርዓት ፋይዳዎች እና ፍዳዎች፤
=================================
እንደ አንደኛ አላፊ ሁሉ የተመጣጣኝ ውክልና የምርጫ ሥርዓትም በሥሩ የተወሰኑ ልዩነት ያላቸው ሌሎች ዘርፎች ያሉት ሲሆን የራሱ ጥቅምና ጉዳቶችም አሉት፡፡ ጠቀሜታዎቹ ድምጽን በታማኝነት ሳያባክን ወደመቀመጫ መቀየር ማስቻሉ፣ በአንድ ፓርቲ ውሥጥ ተመሳሳይ አቋም ያላቸውን ሰዎች ከምርጫ በኋላ በፓርላማ እንዲሳተፉ ማስቻሉ፣ ድምጽን አለማባከኑ፣ የአናሳ ቡድኖችን ውክልና ማስፋቱ፣ ፓርቲዎች በምርጫ ጣቢያ ሳይወሰኑ መቀስቀስ መቻላቸው፣ ክልላዊነትን (ጎጠኝነትን) መቀነሱ፣ የፖሊሲ ቀጣይነትና መረጋጋትን እንዲሰፍን ማገዙ እንዲሁም የሥልጣን መጋራትን በማለማመዱ በአሁኑ ወቅት ከ70 ሀገራት በላይ እየተጠቀሙበት ይገኛሉ፡፡ በርካታ አገራትም ከአንደኛ አላፊ ወደዚህ እንደተቀየሩ ይታወቃል፡፡

ነገር ግን እሱም ቢሆን በርካታ ሳንካዎች ያሉበት እንጂ በራሱ ብጽእና የለውም፡፡ ስለሆነም ለጥምር መንግሥት ምስረታ የተጋለጠ ስለሆነ፣ የፓርቲ ክፍፍልን ስለሚያበረታታ፣ ጽንፈኛ ፓርቲዎች የፓርላማ መቀመጫ እንዲያገኙ ስለሚያደርግ፣ የማይግባቡ ፓርቲዎችን ሊያጣምር ስለሚችል፣ አናሳ ፓርቲዎች ተመጣጣኝ ያልሆነ ሥልጣን እንዲኖራቸው ሊያደርግ ማስቻሉ እና ተመራጮች ለመራጮች ተጠሪነት እንዳይኖርባቸው ስለሚያደርግ ትችቶች ይቀርቡበታል፡፡

ቅይጥ የምርጫ ሥርዓት ምንነት፤
=====================
ጠቅለል ተደርጎ ሲታይ በ19ኛው ክፍለ ዘመን የምርጫ ሥርዓት በመሆን ያገለገለው ከአንድ የምርጫ ወረዳ ላይ ከሚወደዳደሩት ዕጩዎች መካከል የበለጠ ድምጽ ያገኘው የሚያልፍበት ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ምርጫ ድምጽን አባካኝ በመሆኑ ጥያቄ ውስጥ መግባት ሲጀምር የሃያኛው ክፍለ ዘመን የፖለቲካ ፓርቲዎች ባገኙት ድምጽ የምክር ቤት ወንበር የሚከፋፈሉበት የተመጣጣኝ ውክልና እየተስፋፋ መጣ፡፡

በተለይ በሃያኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃና የሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ጥያቄ የሆነው መራጩ ተመራጮችን የሚቆጣጠርበት እንዲሁም ድምጽ ሳይባክንም ፓርቲዎች የሚወከሉበት ሥርዓት በሕዝብ ዘንድ ተፈላጊ እየሆነ በመምጣቱ ቅይጥ የምርጫ ሥርዓት መተግበሩ እየሰፋ መጣ፡፡

ከላይ ከተገለጸው ምክንያት ባለፈም፣ ከቀዝቃዛው ጦርነት ማክተምን ተከትሎ ቀድሞ ሶሻሊስት የነበሩ አገራት ርእዮተ ዓለማቸውን ሲተው የተከተሉት የምርጫ ሥርዓት ቅይጥ የሆነውን ነው፡፡ መነሻቸውም፣ በአንድ በኩል በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች በመፈጠራቸው እነሱን ማካተት አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ እንደ አዲስ የሚደራጁ አገራት በመሆናቸው ጠንካራና ውጤታማ መንግሥት ይኖራቸው ዘንድ ግድ ነው፡፡

በመሆኑም አገራቱ እነዚህን አፍጥጠው የመጡ ተግዳሮቶች በአግባቡ መመለስ ስለነበረባቸው መንግሥታቸው ጠንካራ ይሆን ዘንድ የአብላጫ ድምጽን(ብዙዎቹ አንደኛ አላፊን)፣የፖለቲካ ፓርቲዎቹን ለማካተት ደግሞ የተመጣጣኝ ውክልናን በማጣመር መጠቀም ቀጠሉ፡፡ አስቀድመው አብላጫ ድምጽ ሥርዓትን ይከተሉ የነበሩ ሌሎች አገራትም አካታችነት እንደሚጎድለው የሚወተውቱ ድምጾች በመብዛታቸው ወደ ቅይጥ ሥርዓት ለመቀየር ተገድደዋል፡፡

የቅይጥ ምርጫ ሥርዓት ዓይነቶች፤
=====================
ቅይጥ የምርጫ ሥርዓት በዋናነት ሁለት ዓይነት ናቸው፡፡ አንዱ ‘ቅይጥ ተመራጭ ተመጣጣኝ ውክልና’ (mixed-member proportional representation) በመባል የሚታወቀው ነው፡፡ በዚህ የምርጫ ሥርዓት የአንድ ምክር ቤት አባላትን ለመምረጥ ሁለት የምርጫ ሥርዓቶችን በአንድነት ሥራ ላይ ማዋልን ይጠይቃል፡፡ ከአብላጫ ድምጽ እና ከተመጣጣኝ ውክልና ሥር ከሚገኙት ውስጥ ሁለቱን በመምረጥና በማጣመር ይጠቀማል፡፡ ጀርመን እ.አ.አ. ከ1953 ጀምራ እየተጠቀመችበት ትገኛለች፡፡

ሁለተኛው ደግሞ ቅይጥ-ትይዩ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም፣ የትይዩ ምርጫ (parallel voting)፣ የተመራጭ ማሟያ ሥርዓት (supplementary member system)፣ የአብላጫ ቅይጥ ተመራጭ (mixed member majoritarian) በሚሉ ስያሜዎችም ይታወቃል፡፡ የአጠራር ልዩነት ይኑረው እንጂ ሁሉም፣ የአንድ ምክር ቤት አባላትን ለመምረጥ ሁለት ምርጫዎች ሥርዓትን በአንድነት ሥራ ላይ የሚያውል የምርጫ ማከናወኛ ዘዴ ነው፡፡ በጥቅሉ፣ከፊል ተመጣጣኝ ውክልና ነው፡፡

ሁለቱንም የምርጫ ሥርዓቶች በተጓዳኝ በመጠቀም፣በአንዱ የምርጫ ዘዴ የሚሰጠው ድምጽ ሌላው ላይ ተጽእኖ እንዳይኖረው ወይንም እንዳይቆጠር ተደርጎ ለየብቻ ድምጽ እንዲሰጥ የሚጠይቅ የምርጫ ሥርዓት ነው፡፡

በመሆኑም፣ለአንድ ምክር ቤት የሚያስፈልጉትን እንደራሴዎች ለመምረጥ ሁለት የተለያዩ የምርጫ ሥርዓትን ይጠቀማል፡፡ ለምክር ቤቱ ከሚያስፈልጉት እንደራሴዎች የተወሰኑትን በአንድ የምርጫ ዘዴ፣ቀሪዎቹን ደግሞ በሌላ ዓይነት እንዲመረጡ ይደረጋል፡፡ መራጮችም በሁለቱም ሥርዓት ለመምረጥ ቢያንስ ሁለት ድምጽ ይሰጣሉ፡፡

ስለሆነም፣ሁለት የምርጫ ሥርዓቶችን የአንድ ምክር ቤት አባላትን ለመምረጥ ስለሚተገበሩ ቅይጥ ተሰኘ፡፡ አንድ መራጭ ሁለቱም የምርጫ ሥርዓቶች በመጠቀም በእያንዳንዱ ሥርዓት ድምጽ ስለሚሰጥ ትይዩ ይሆናል፡፡ አንድ መራጭ በአንዱ ሥርዓት የሰጠው ድምጽ ከሌላው ጋር ግንኙት አይኖረውም፡፡
ከበርካታ አገራት ልምድ በመነሳት ቅይጥ- ትይዩ የምርጫ ሥርዓት የሚቀይጣቸው የምርጫ ዓይነቶች የአንደኛ አላፊንና እጩዎቹ ቀደመው ይፋ የሆነበት የተመጣጣኝ ውክልናን (List proportional representation) ነው፡፡

በፖለቲካ ፓርቲዎች ድርድር ወቅት እንደተሰማው የኢሕአዴግ ፍላጎት አብዝኃኛውን የምክር ቤት መቀመጫ ለመያዝ የአንደኛ አላፊን፣የተወሰኑ መቀመጫዎችን ደግሞ ለተመጣጣኝ ውክልና በማስቀረት የሚተገበር ቅይጥ ትይዩ ሥርዓትን መጠቀም ነው፡፡ በምሳሌ ለማስረዳት፣ የፌደራሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 550 ተወካዮችን ስለሚያሳትፍ ከዚህ ውስጥ 300 በአንደኛ አላፊ ቀሪው በተመጣጣኝ ውክልና ይሆናል ማለት ነው፡፡ 550 የነበሩት የምርጫ ወረዳዎች ታጥፈው በምትኩ 300 ወረዳዎች ይዋቀራሉ ማለት ነው፡፡ ቀሪ 250 ወንበሮችን ለመያዝ ደግሞ ፓርቲዎቹ በአገር አቀፍ ደረጃ ባገኙት ድምጽ መሠረት በመቶኛ ይከፋፈሉታል፡፡ በምርጫ የተወዳደሩት ፓርቲዎች አስር ቢሆኑ በፓርቲዎቹ ስም ከተሰጠው ድምጽ በመቶኛ እየተሰላ ሁለት መቶ ሃምሳውን ይከፋፈሉታል፡፡

መጀመሪያ ላይ በተገለጸው ቅይጥ የምርጫ ሥርዓት ቢሆን መራጮች ፓርቲ ወክለው ለሚወዳደሩ እጩዎች የሰጡት ድምጽ ከምርጫ ወረዳው ባለፈ በአገር ወይም በክልል ደረጃ ተደምሮ ቀሪ ወንበሮች (ለምሳሌ ሁለት መቶ ሃምሳውን በመቶኛ ለመጋራት) ለመካፈል ጥቅም ላይ ይውላል፡፡ መራጮችም አንድ ጊዜ ብቻ ድምጽ በመስጠት ይገላገላሉ፡፡

የቅይጥ ሥርዓት ጥቅምና ጉዳት፤
====================
ለአነስተኛ ፓርቲዎች የተወሰነ ወንበር እንዲያገኙ ይረዳል፡፡ እንደ የአብላጫ ድምጽ የምርጫ ሥርዓት ፓርቲዎችን ወደ ሁለትና ሦስት ሊያመጣ ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ እንደ ተመጣጣኝ ውክልና በተሻለ ሁኔታ ድምጽን ከብክነት አይታደግም፡፡

ለመራጩም ውስብስብ በመሆኑ አወዛጋቢ ነው፡፡ የጀርመን ልምድ ለዚህ ዋቢ ስለመሆኑ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ ኒውዚላንድ የዛሬ ሃያ ዓመታት ገድማ ሥትቀበለው እንደ ችግርም ስጋትም የተነሳው ይሄው ነው፡፡ እነዚህ ሁለት አገራት የሚጠቀሙት ሥርዓት፣ ከቅይጥ ትይዩ በአንጻራዊነት ውስብስብነቱ ዝቅተኛ ነው፡፡ በተለይ በጀርመን ሥራ ላይ ከዋለ ከ60 ዓማታት በላይ ቢሆንም እስካሁን ድረስ ይኼው ትችት እና ችግር አለ፡፡
በኒውዚላንድም የፓርቲ ተወዳዳሪዎች ስም ለመራጭ ይፋ ሳይሆን ከምርጫ ጣቢያው አንድ ተወዳዳሪ እና በአገር አቀፍ ደግሞ አንድ ፓርቲ መምረጥ እንዳለባቸው ሰፊ ትምህርት አስፈልጎ እንደነበር ስለአገሪቱ ምርጫ ኮሜሽን የተጻፉ ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡ ጥሩ የምርጫ ልምድ ያላቸው ዜጎች ባሉበት አገራት በአንጻሩ ይቀላል፡፡ ይህ በእንዲህ ከመራጮች መወዛገብ የሚጠቀሙ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ መገመት አይከብድም፡፡

ሌላው፣ቅሬታም የሚፈጠረው በሁለት መንገድ ነው፡፡ ግለሰብ ተወዳዳሪዎችን መሠረት አድርጎ እንዲሁም በፓርቲው በኩል፡፡ ለአስተዳደር አስቸጋሪ እንደሆነ ይገመታል፡፡

ከላይ ከተገለጹትና ሌሎች ተግዳሮቶች አኳያ አብዝኃኛው ዜጋ ማንበብና መጻፍ በማይችልበት፣ከሰማኒያ በመቶ በላይ በግብርና በሚተዳደርበት እና ከመገናኛ ብዙኃን ሩቅ በሆነበት አገር ምን ያህል ውጤታማ ሊሆን እንደሚችል ውይይት ያስፈልገዋል፡፡

ለነገሩ አይደለም አብዝኃኛው መራጭ ይቅርና ስለ ኢትዮጵያ የምርጫ ሁኔታ የተጻፉትን ያገላበጠ ሰው የሚታዘበው ቁምነገር ቢኖር ስለምርጫ ሥርዓቱ ጥቅምና ጉዳት የተጻፉት በጣም ጥቂት መሆናቸውን ነው፡፡ በተቃውሞው ምድብ የሚገኙት አብዝኃኛዎቹ እና ጎምቱ የሚባሉት ፖለቲከኞች እንኳን ትችታቸው የምርጫ ሥርዓቱን አይመለከትም፡፡

ከዚህ በባሰ እና በከፋ መልኩ፣ በገዥው ፓርቲም ይሁን በሌሎቹ፣ የሚገኙ ፖለቲከኞች አሁን በሥራ ላይ ያለው የምርጫ ሥርዓት የአብላጫ ድምጽ አንዱ ዘርፍ ቢሆንም “50 ፐርሰንት ሲደመር አንድ” ዓይነት እንደሆነ ሲናገሩ መስማት የተለመደ ነው፡፡ ፖለቲካን ሥራቸው፣ በትምህርትም የተሻሉ የሚባሉት ሰዎች የምርጫውን ባሕርይ እና መገለጫ የሚስቱት ወይንም የማያውቁት ከሆነ መራጩ ሕዝብ እንደምን አድርጎ በቀላሉ ሊገነዘበው ነው? መራጩ መገንዘብ ብቻ ሳይሆን ከዚህ በላቀ ሁኔታ ብዙ ነገሮችን ከግምት ማስገባት ይጠበቅበታል፡፡

ገዥው ፓርቲም፣ ይህንን የምርጫ ሥርዓት በአማራጭነት ሲያቀርብ በድርድር ላይ ያሉት ተቃዋሚ ፓርቲዎች የዚህን የምርጫ ሥርዓት ጠባይ፣ጥቅምና ጉዳት ራሱ ኢሕአዴግ እንዲያስረዳቸው፣ብሎም ከዚያ በኋላ እንደሚወስኑ መጠየቃቸው በመገናኛ ብዙኃን ተላልፏል፡፡ ተደራዳሪ ፓርቲዎች ቀደመው አውቀው የሚደራደረው ወገን የሚያመጣውን አማራጭ (ቅይጥ ትይዩ) ያለውን ጉዳት ማስረዳት ሲጠበቅባቸው እራሱን ተደራዳውን እንዲያስረዳቸው መጠየቃቸውን ስንመለከት ከ80 በመቶ በላይ አርሶ አደር በሆነበት አገር ሊረዳው እንደሚችል መገመት አስቸጋሪ ነው፡፡

ከላይ ከተገለጹት ተግዳሮቶች ባለፈም፣ ድንበር በማጠማዘዝ ለሚመጣ አድልኦ የተጋለጠ ነው፡፡ ከቅይጥ ተመራጭ ተመጣጣኝ ውክልና አንጻር ይህ የምርጫ ሥርዓት የምርጫ ወረዳ ወሰኖችን በማጠማዘዝ (gerrymandering) ለሚመጣ አድልኦ የተጋለጠ ነው፡፡ በተለይም የምርጫ ወረዳዎች በአንድ ፓርቲ ቁጥጥር ሥር ያለው የፌደሬሽን ምክር ቤት ስለሚያካልላቸው ጥርጣሬዉን ሊያጎላው ይችላል፡፡

እነዚህ ተግዳሮቶች በምሳሌነት ብቻ የሚታዩ ናቸው፡፡ የቅይጥ ትይዩ የምርጫ ሥርዓት አሁን አገሪቱ ላጋጠማት ወይም ለማሻሻል መነሻ የሆኑትን ምክንያቶች ሊመልስ መቻሉ ብሎም በሕገ መንግሥቱ ላይ የተቀመጠውን የዲሞክራሲ ግቦችን፣ ሕገ መንግሥታዊ ዓላማዎችን መመለስ ስለመቻሉ በአግባቡ ማጤን ያስፈልጋል፡፡ የምርጫ ዓይነት ለመምረጥ ጥቅም ላይ ከሚውሉት መርሆች አንጻርም ፍተሻ ያስፈልገዋል፡፡
ለማጠቃለል ያህል ብዙ አገራት የምርጫውን ዓይነት በሕገ መንግሥታቸው አላካተቱም፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ እንደ ሁኔታው መቀየር እንዲቻል ነው፡፡ በኢትዮጵያ ግን በሕገ መንግሥቱ ስለተካተተ ሕገ መንግሥቱን ማሻሻል ይጠይቃል፡፡ ምናልባት ማሻሻያው ከሕገ መንግሥቱ እንዲወጣ የሚያደርግና በአዋጅ የሚወሰን ቢሆን ጥሩ ነው፡፡ እንደ ሁኔታው ለማሻሻል ያመች ዘንድ፡፡

ሌላው ትኩረት የሚያስፈልገው የምርጫ ሥርዓቱ የዜሮ ድምር (ሁሉን ታገኛለህ ወይ ሁሉን ታጣለህ) ፖለቲካዊ ጨዋታን የሚያስቀር ብሎም ሁሉንም አሸናፊ ለማድረግ የሚያበረታታ የመሆኑ ጉዳይ ነው፡፡ በየትኛውም ደረጃ የሚገኙት ምክር ቤቶች ሚና አምስቱንም ዓመታት ሙሉ የልዩነት ሐሳቦች ለውይይት እያቀረቡ ሕዝቡም እያወቃቸው ወደ ስምምነት (Consensus) መዳረሻ መድረኮች እንዲሆኑ የሚያስችሉ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ ስለሆነም፣የምርጫ ሥርዓቱ ይህንን ለማምጣት የሚያግዝ እንጂ ተሻሽሏል ለማለት ያህል ብቻ መሻሻል የለበትም፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: