የአቶ ዮናታን ተስፋዬ ይግባኝ ክርክር ተሰማ

ጌታቸው ሺፈራው

በማነሳሳት የ”ሽብር” ክስ ተመስርቶበት 6 አመት ከ6 ወር የተፈረደበት አቶ ዮናታን ተስፋዬ የይግባኝ ክርክር ዛሬ ጥቅምት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተሰምቷል። አቶ ዮናታን ተስፋዬ የተፈረደበት ፌስ ቡክ ላይ በፃፈው ፅሁፍ ሲሆን ጠበቃው አቶ ሽብሩ በለጠ አቶ ዮናታን ተስፋዬ የተከሰሰውና የተፈረደበት ሀሳቡን በነፃነት በመግለፁ እንደሆነ ለፍርድ ቤቱ አብራርተዋል። ከዚህም ባሻገር አቶ ዮናታን የተከሰሰበትና የተፈረደበት አንቀፅ በህትመት ለወጣ ፅሁፍ የተደነገገ እንጅ በማህበራዊ ሚዲያ ለወጣ (ላልታተመ ፅሁፍ) እንዳልሆነ በመግለፅ አቶ ዮናታን በፀረ ሽብር አዋጁ አንቀፅ 6 ሊከሰስ እና ሊቀጣ አይገባም ነበር ብለው ተከራክረዋል።

ጠበቃው አቶ ዮናታን ህገ መንግስታዊ መብቱን ተጠቅሞ ሀሳቡን በነፃነት ገለፀ እንጅ ሽብርተኝነትን የማበረታት ተግባር አለመፈፀሙን፣ ሆኖም የስር ፍርድ ቤቱ የሰጠው ውሳኔ ህግና ማስረጃን መሰረት ያላደረገ፣ ስህተትና ያልተገባ ነው ብለዋል። በመሆኑም ጠቅላይ ፍርድ ቤት የስር ፍርድ ቤቱ የሰጠው የጥፋተኝነትና የቅጣት ውሳኔ በመሻር ይግባኝ ባይን እንዲያሰናብት ጠይቀዋል። ይህ ከታለፈ እንኳን እስካሁን የታሰረው ጊዜ በቂ ተብሎ ከእስር እንዲለቀቅ አመልክተዋል። ፍርድ ቤቱ አቶ ዮናታን በበቂ እንዲለቀቅ የቀረበውን ጥያቄ ካለፈውም ፣ ለስር ፍርድ ቤቱ 6 በመረጃ የተረጋገጡ ማቅለያዎች ቀርበው ፣ በእነዚህ ማቅለያዎች መሰረት ስድስት እርከን ዝቅ ብሎ መወሰን ሲገባ ሶስት እርከን ብቻ በመቀነስ ውሳኔ ስለተሰጠ ማቅለያዎቹ ተይዘው የቅጣት ውሳኔው ተሻሽሎ እንዲወሰን የይግባኝ ክርክር አቅርበዋል።

በሌላ በኩል አቃቤ ህግ አቶ መኩርያ አለሙ አቶ ዮናታን ተስፋዬ በፅሁፉ በኦነግ አላማ ሲያነሳሳ እንደነበር እና የተፈረደበትም በዝቅተኛ ደረጃ በመሆኑ ፍርዱን ሊቀንስለት አይገባም ብሎ ተከራክሯል። አቶ ዮናታን በበኩሉ አቃቤ ህግ ከኦነግ ጋር ግንኙነት አለው ብሎ ክስ ማቅረቡንና በዚህም እንደተፈረደበት በማስታወስ፣ ሆኖም በቀረበው ክስ ላይ ከኦነግ ጋር አለው ስለተባለው ግንኙነት ማስረጃ እንዳልቀረበ፣ ፍርዱም ትክክል እንዳልሆነ ተከራክሯል።

አቶ ዮናታን ተስፋዬ የተከሰሰውና የተፈረደበት ከ”ማስተር ፕላን” ጋር በተያያዘ ኦሮሚያ ክልል ተቀስቅሶ በነበረው የህዝብ ንቅናቄ ሰበብ ሲሆን አቶ ኃይለማይያም ደሳለኝ በመንግስት ሚዲያዎች ቀርበው ኦሮሚያ ውስጥ የተፈጠረው ችግር የመልካም አስተዳደር ችግር እንጅ የሽብር ባህሪ የለውም ብለው መግለጫ ሰጥተው እንደነበር ጠበቃ ሽብሩ በለጠ አስታውሰዋል። የግራ ቀኙን ክርክር መርምሮ ለመበየን ለህዳር 18 ቀን 2010 ዓ.ም. ተቀጥሯል።

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: