ችሎት ማስከበር ወይስ ፍርሃት መፍጠር?

በቃሉ ፈረደ

ጉዳይ ኑሮት ወይም ለመታደም ችሎት ከሚገኘዉ ሰዉ ዉስጥ አብዛኛዉ ችሎት ሲቀርብ የመፍራትና የመራድ ስሜት ይሰማዋል፡፡ እንግዲህ ችሎት ፊት በፍርሐት መቆም አንድም ችሎቱን ከማክበር በሌላ ጎኑ ደግሞ ችሎቱን አስፈሪና ጭራቅ አድረጎ ከማየት ይመነጫል፡፡ አብዛኛዉ የሕብረተሰብ ክፍልም ስለ ሕግ ያለ ንቃትና ግንዛቤ አናሳ በመሆኑ ችሎት ሲገባ አንዱን ስቼ ብቀጣ የሚለዉ ዋና ስጋቱ ነዉ፡፡ በአናቱ ወንበሩ ላይ ቁጭ ያሉ ዳኞች ማን አለብኝነት የሚያጠቃቸዉ
እና ከስልጣናቸዉ በላይ በማለፍ ታዳሚዉን ስጋት ዉስጥ የሚከቱ ከሆነ ችሎቱ ከማስከበር አልፎ ሽብርና ፍርሐት መፍጠር ይሆናል፡፡ ዳኞች በችሎት ያላቸዉን ስልጣን ልክ አለመጠበቅ ችሎቱ ላይ ከሚፈጠረዉ የፍርሐት ድባብ ጋር ግንኙነት ስላለዉ የልደታዉን ጉዳይ አንስተን እንመልከተዉ፡፡
– – –
#አቤት አቤት የልደታዉ ችሎት!
– –
ሰሞኑን የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ችሎት በችሎት ታድመዉየነበሩ ግለሰቦችን እያስነሳ ማስጠንቀቂያ ሲሰጥ እንደነበር ተዘግቧል፡፡ በዚህ ችሎት የሚታዩ ጉዳዮች የፖለቲካ ጉዳይ በመሆናቸዉ ቀደም ሲል ጀምረዉ እንዳነጋገሩ ዛሬ ድረስ ዘልቀዋል፡፡ ህዝቡ በፍትሕ ስርዓቱ ላይ ያለዉን የእምነት ደረጃም አቅጣጫ ካስያዙት ዉሳኔዎች አብዛኞቹ ከዚህ ችሎት የተወሰኑት ናቸዉ። ችሎቱንም አስፈሪ እና ጭራቅ የሚያስመስሉ ዳኞች ቀደም ሲል ጀምረዉ ይመደቡበትም እንደነበር ይነገር የነበረ ሲሆን አሁንም ከዚህ ትችት እንዳላመለጠ እያየን ነዉ፡፡ ዳኞች በችሎት ያላቸዉ ስልጣን ገደብም አነጋጋሪ ሆኖ እየተነሳ በመሆኑ የሚባለዉ ነገር የሕግ ድጋፍ ይኖረዉ ይሆን እንድንል አድርጎናል፡፡
– –
# በቅድሚያ ከዚህ ችሎት ምን ተፈጠረ?
– – –
ህዳር 19-2010 ዓ.ም በነበረዉ የችሎት ዉሎ ችሎት ሊታደሙ የተገኙ ግለሰቦች በማህበራዊ ሚዲያ ፌስቡክ ላይ የችሎቱን ክብር ነክታችዋል ተብለው በየተራ እየተነሱ ተግሳፅና ማስጠንቀቂያ ሲሰጣቸዉ እንደዋለ ተዘግቧል፡፡
ተግሳጹ የችሎቱን ክብር ለማስጠበቅም እንደሆነ ሲገለፅም ነበር፡፡ በዕለቱም ፡-
1ኛ. ማህሌት ፋንታሁን የተባለችን ግለሰብ በፌስቡክ አክላቸዉ ወንደስን የተባለ ግለሰብ የዳኛ ስም ጠቅሶ የፃፈዉን ፅሁፍ በማጋራት(share) በማድረግ የፍርድ
ቤቱን ክብር ነክተሻል በሚል ፤
2ኛ. አሚር የተባለ ግለሰብ በፌስቡክ በተፃፈ ፅሁፍ ስር አስተያየት እንደሚሰጥና በችሎት በማስነሳት የምትጽፈዉን እናያለን ተብሏል፤
3ኛ. አንገቱ ላይ ሻርፕ ያደርጋል የተባለና በዕለቱ ችሎት ያልነበረ ናትናኤል የተባለ ግለሰብም እንዲሁ የፍርድ ቤቱን ክብር በሚነካ ፁሁፍ እንደተሳተፈ፤
4ኛ. ጋዜጠኛ ጌታቸዉ ሽፈራዉ የፍርድ ቤትን ዉሎ በሚፈልገዉ መንገድ ቆራርጦ የሚዘገብ ለመሆኑ እና የምትፅፈዉን እናያለን በማለት ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶታል፤ችሎቱ ይህንን ማስጠንቀቂያ የሰጠዉ የፍርድ ቤቱን ክብር ለማስጠበቅ እንደሆነና ዳኞች ፌስቡክ ላይ የሚፃፈዉን ፁሁፍም እንደሚያነቡ እና ወደ ፊት እንዲጠነቀቁ በማሳሰብ ነዉ፡፡ የችሎቱ ስራ ከህጉ አንፃር ሲታይ
ተገቢነት ይኖረዉ እንደሆነ እንመልከት፡፡
– –
# የዳኞች ስልጣን በችሎት፡-
– –
ዳኞች ህጉ በሚያዘዉ መሰረት ክርክሮችን መምራትና ሕግና ማስረጃን መሰረት በማድረግ የመወሰን ግዴታ አለባቸዉ፡፡ በስራቸዉም የፍርድ ቤት ነፃነትን እና ክብር የማስከበር ግዴታም ተጥሎባቸዋል፡፡ ይህንን ግዴታቸዉንም ሲወጡ ሕጉ
በሚፈቅድላቸዉ ልክ ከችሎት ጀምሮ ተገቢ የሚለዉን እርምጃ ሊወስዱ እንደሚችሉ የሕግ ድጋፍ አላቸዉ፡፡ አብዛኛዉን ጊዜ የችሎቱን ክብር የሚነኩ ድርጊቶች በችሎት ጊዜ ሆነ በችሎት ወጪ ሲፈፀሙ ተጠያቂ የሚያደርግ የህግ አግባብ ስላለ እሱን ተፈፃሚ የማድረግ ስልጣን አላቸዉ፡፡
ሆኖም በዳኞች የስነ-ምግባር ደንብ በግልጽ እንደተቀመጠዉ አንድ ዳኛ የባለጉዳዮቹን ስብዕና እና መብት የማክበር ግዴታ እንዳለበት እንዲሁም በአሰራሩ የፍርድ ቤቱን ክብር መጠበቅ ግዴታዉ ነዉ፡፡ የመዳኘት ስልጣን ብቻ ሳይሆን ለሕግ ተገዥነትም በተነፃፃሪ ግዴታ አለበት፡፡ በሕግ ከተሰጠዉ ስልጣን ዉጪም መዉጣት አይገባዉም፡፡ በግሉ የሚያዉቀዉን ነገር ሁሉ የችሎቱ አካል እያደረገ በማይገባ አሰራር የፍርድ ቤትን ታማኝነት ሊንድ አይፈቀድለትም፡፡
የሚቀርቡለትን ጉዳዮችም ሊወስን የሚችለዉ በሁለት መንገድ ሲቀርቡለት ነዉ፡፡
– – –
አንደኛዉ መንገድ ድርጊቱን ፈፀመ የተባለ ሰዉ መደበኛ የወንጀል ምርመራን ካለፈ በኋላ ክስ ተመስርቶበት ማስረጃ ተሰምቶ የሚወሰንበት ሥርዓት ነዉ፡፡ ይህ ሥርዓት አብዛኞቹ ክሶች የሚቀርብበት ሲሆን ለክሱ አስረጅ የሚሆኑ ማስረጃዎች በመርማሪዉና በከሳሹ አካል ተሰብስበዉ እና ተደራጅተዉ የሚቀርቡበት ነዉ፡፡ በክርክሩም ከሳሽና ተከሳሽ የተባለ በሁለት ጫፍ የቆመ ተከራካሪ ወገን አለ፡፡
– –
ሁለተኛዉ ሥርዓት ደግሞ ከሳሽ የሌለበት ፍርድ ቤቱ ክርክር በጀመረበት መዝገብ በሕግ የተገለፀ ሁኔታ ሲፈጠር በቂ ማስረጃ ሲኖር ወዲያዉ የሚወሰንበት ነዉ፡፡ ክስም የለም፤ የተፈፀመዉ ድርጊት ክስም ማስረጃም ሆኖ ከዚያዉ ጥፋተኝነትን የሚያቋቁም ነዉ፡፡ በዚህኛዉ ሥርዓት ሁሉን ስልጣን የሰጠዉ ለፍርድ ቤቱ ነዉ፡፡ ፍርድ ቤቱ ሌላ ማጣራት እና የምርመራ ሂደት ዉስጥ ሳይገባ የተጣሰዉን ሕግ ጠቅሶ ወዲያዉ የሚወስንበት ነዉ፡፡ ፍርድ ቤቱም ወዲያዉ ሊወሰን የሚችለዉም በሕግ በግልፅ ተቀምጦ በተለዬ ነገር ነዉ፡፡
በወንጀል ጉዳይ ፍርድ ቤቱ ሌላ ሂደት ሳያስፈልግ ሊወስን የሚችልባቸዉም በወንጀል ሕግ አንቀፅ 448 እና 449 የተገለፁት ድርጊቶች ሲፈፀሙ ነዉ፡፡ በወንጀል ህግ አንቀፅ 448 ለፍትሕ ሥራ እርዳታ ለመስጠት እንቢተኛ የሆነ ወገን የሚጠየቅበት ነዉ፡፡ በወንጀል ህግ አንቀፅ 449 ደግሞ ፍርድ ቤትን የመድፈር ድርጊት ሲፈጸም ነዉ፤ ድርጊቱም የፍርድ ቤቱን ወይም የዳኝነት ሥራ በማከናወን ያለን ዳኛ በማናቸዉም መንገድ ማወክ፣መስደብ፣ማፌዝና መዛት ሲሆን ዳኛዉ ስራዉን እያከናወነ ከሆነም ከችሎት ዉጪ የሚደረግ ሁከት በችሎት መድፈር ያስጠይቃል፡፡ በእነዚህ ሁለት ጉዳዮች ለፍርድ ቤቱ ሙሉ ስልጣን የሰጠዉ ከፍርድ ቤት በላይ ለጉዳዩ እማኝ የሚሆን ስለሌለ የፍርድ ቤቱን ክብር ለማስከበር በቀጥታ ሊወስን እንደሚችል የተቀመጠ ነዉ፡፡
– –
# ከችሎት ዉጪ የሚፈጠሩ ስጋቶች በምን ይፈቱ፡-
– –
በክርክር ሂደት ፍርድ ቤቱ በቀጥታ ሊወስንባቸዉ የማይችል ግን ለፍርድ ቤቱ ክብር ሆነ ለክርክር ሂደት ስጋት የሚሆኑ ጉዳዮች ከችሎት ዉጪ የሚፈጠሩበት አጋጣሚ አለ፡፡ አብዛኛዉን ጊዜ እንደ ስጋት የሚታዬዉ የፍርድ ሂደትን በተመለከተ ያልሆነ ወይም የተዛባ መረጃ መግለፅ ጋር በተገናኘ ነዉ፡፡ በወንጀል ህግ አንቀጽ 451 የፍርድ ሂደትን በተመለከተ ትክክለኛ ያልሆነ ወይም የተዛባ ነገር መግለጽ እንደሚያስጠይቅ ይናገራል፡፡ ሆኖም ተላለፈ የተባለዉ መረጃ ትክክል ያልሆነ ወይም የተዛባ ለመሆኑ ራሱን ችሎ ሊጣራ እና ትክክል ነዉ አይደለም የሚለዉ ሊያከራክር የሚችል በመሆኑ ችሎቱ በቀጥታ በጉዳዩ ላይ መወሰን አይችልም፡፡ ችሎቱም የተዛባ ወይም ትክክል ያልሆነ ነገር ተላልፏል ብሎ ካመነ ስልጣን ያለዉ መርማሪ አካል ጉዳዩን እንዲያጣራ ጥቆማ ከመስጠት የዘለለ ትክክለኛነቱ ባልተረጋገጠ ጉዳይ ላይ እርምጃ ተግሳፅ ወይም ማስጠንቀቂያ ጨምሮ ሊሰጥ አይችልም፡፡
– – –
# የፍርድ ሂደትን ማስተላለፍ እና የግልፅ ችሎት አስፈላጊነት
– – –
የፍርድ ቤቶችን ስራ በግልፅ ችሎት ማከናወን በመርህ ደረጃ የተቀመጠዉ የተቋሙን አሰራርና የፍርዱን ሂደት በግልፅ ለማሳየት ነዉ፡፡ ግልፅ የሆነ አሰራር ሲኖር የሂደቱ ትክክለኛነት በተመልካቹ ዕይታ ስር መዋሉ አይቀርም፡፡ በዚያዉም አሰራሩ ይተቻል፤ይገመገማል፡፡ ያኔም ተቋሙ በሕግ የተሰጠዉን ስልጣን በአግባቡ እየተወጣ መሆን አለመሆኑም በባለቤቱ በሕዝቡ ይታወቃል፡፡ በሕግ በግልጽ የተገደቡ እስካልሆነ እና በተለዬ ሁኔታ ክልከላ እስካልተደረገ ድረስ የፍርድ ሂደቶች እንደማንኛዉም ሁኔታዎች ዘገባቸዉ ይቀርባል፡፡ የሚቀርበዉ ዘገባ ትክክል ያልሆነ እና የፍርድ ሂደቱን በሚያዛባ መልኩ እስካልሆነ ድረስ በችሎት የነበረዉን የፍርድ ሂደት ማቅረብ የሚከለክል ሕግ የለም፡፡ሕጉ በግልጽ የከለከለዉ ትክክለኛ ያልሆነ እና የተዛባ ነገር መግለጽ እንጅ የተፈጠረዉን በሌላ ሁኔታ ክልከላ ከሌለበት በስተቀር እንደወረደ ማስተላለፍን አይከለክልም፡፡
– –
እንግዲህ ሕጉ ግልጽ ነዉ፤ አከራካሪም ነገር የለዉም፡፡ የፌደራል ከፈተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎትን ጉዳይ ብንለመከት ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸዉ ሰዎች አደረጉት ከተባለዉ ነገር ጀምሮ ዳኞቹ እስካስተላለፉት ማስጠንቀቂያ ድረስ አነጋጋሪ ነዉ፡፡-
– –
# አነጋጋሪ ጉዳይ አንድ፡- ግለሰቦቹ አደረጉት የተባለዉ ድርጊት ክርክር ላይ ባለ መዝገብ ችሎት ሊነሳ የሚገባ ይሆን?

ፍርድ ቤቶች ሕግ ተጥሷል ብለዉ ሲያምኑ በጉዳዩ ላዩ ትዕዛዝ ሊሰጡ የሚችሉት የተፈጠረዉ ነገር ሊታይ ሕግ በፈቀደበት መዝገብ ነዉ፡፡ ሕጉ እርምጃ እንዲወስዱ በማይፈቅድላቸዉ መዝገብ ላይ ጥፋተኛ ማለት ሆነ መቅጣትና ማስጠንቀቅ አይችሉም፡፡ 4ኛ የወንጀል ችሎቱ በፌስቡክ የፍርድ ቤት ክብር ነክተዋል፤የተዛባ መረጃ አስታልፈዋል ያላቸዉን ግለሰብ ማስጠንቀቂያ ከመስጠቱ በፊት የግለሰቦቹ ጉዳይ የሚሰተናገድበት ሕግ አግባብ ምንድነዉ በማለት ማየት ይጠበቅበት ነበር፡፡ የፍርድ ቤቱን ክብር ነክታችኋል የተባሉትም ሆነ መረጃ አዛብተህ ትዘግባለህ የተባለዉ ሰዉ ጉዳይ ራሱን የቻለ ክርክር የሚያስፈልገዉ እና ድርጊታቸዉም የተፈፀመበት አግባብ ምርመራ ተደርጎበት ራሱን ችሎ የሚታይ እንጅ ክርክር ላይ ባለዉ መዝገብ ሊታይ የሚገባዉ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ድርጊቱ የተፈፀመዉ ከችሎት ዉጪ በመሆኑ ክርክር በተጀመረዉ መዝገብ በቀጥታ ሊወሰን ሆነ ሊነሳ አይችልም፡፡ ከችሎት ዉጪ የፍርድ ቤት መድፈር ተግባር ሊፈጸም እንደሚችል የወንጀል ህግ አንቀፅ 449(2) ቢያስቀምጥም ከችሎት ዉጪ ፍርድ ቤት ተደፍሯል የሚባለዉ ዳኛዉ
ከችሎት ዉጪ ስራዉን በሚሰራበት ወቅት ድርጊቱ ተፈጽሞ ከሆነ ነዉ፡፡
– –
የ4ኛ ወንጀል ችሎት ዳኞች የፍርድ ቤቱ ክብር ተነክቷል ከማለት ዉጪ ከችሎት ዉጪ የዳኝነት ስራቸዉን እየሰሩ ድርጊቱ ተፈፅሟል አላሉም፡፡ ፌስቡክ ላይ ተፃፈ ያሉትን ፁሁፍ ያነበቡት መዝገቡን ቤታቸዉ ወስደዉ ፌስቡክ እየተጠቀሙ ሲመረምሩ ከሆነ ነገሩ ሌላ ነዉ፡፡ ከችሎት ዉጪ የተፈፀመን ድርጊት በያዙት መዝገብ አስታኮ ለማስጠንቀቅ የሚያስችላቸዉ እድል ስራቸዉን ከችሎት ዉጪ ማከናወንን የሚጠይቅ ስለሆነ ግለሰቦቹን ክርክር ባለበት መዝገብ ምንም የማለት ስልጣን የላቸዉም፡፡ በምሰራዉ ስራ ከችሎት ዉጪ እንደ ግል ተሰደቢያለዉ፣ክብሬ ተነክቷል፣የምሰራበት ተቋም ስሙ ጠፍቷል የሚል አካል ደግሞ እንደማንኛዉም ግለሰብ ለፖሊስ ሪፖርት ከማድረግ እና ምስክር ከመሆን
ዉጪ ጉዳዩን ችሎት ድረስ ጎትቶ ሊዳኘዉ ሆነ ትዕዛዝ ሊሰጥበት አይችልም፡፡
– –
የፍርድ ሂደቱም ተዛብቶ ተዘግቦ ቢሆን እንኳ ትክክለኛ ያልሆነ ወይም የተዛባ መረጃ አሰራጨ የተባለዉ ሰዉ በዘገበዉ መዝገብ ሊቀጣ አይችልም፡፡ ድርጊቱ ራሱን የቻለ የወንጀል ምርመራ ተደርጎበት የፍርድ ሂደቱ በትክክል መዘገብ አለመዘገቡ የመረጃዉ መዛባት አለመዛባት ምርመራ ተደርጎበት ራሱን ችሎ የሚወሰን እንጅ ችሎቱ መረጃዉ ተዛብቷል በማለት በቀጥታ እንዲወስን ስልጣን የለዉም፡፡ ችሎቱ እየሰራዉ ስላለዉ መዝገብ የተዛባ መረጃ ተሰራጭቶ ከሆነ እዉነት ስለመሆኑ እንዲጣራ እና ምርመራ እንዲያደርግ ለሚመለከተዉ አካል ከማሳወቅና ከማስተላለፍ ዉጪ በያዘዉ መዝገብ ለመቅጣት አልተፈቀደለትም፡፡
ፍርድ ቤቶች በቀጥታ በሚያከራክሩት መዝገብ ያለምንም ሂደት እንዲወስኑ የተፈቀደላቸዉ ድርጊቱ ከዚያዉ ከችሎት ከዳኝነት ስራዉ ጋር በተገናኘ ሲፈጠር ራሳቸዉ በተጨባጭ ስለሚያረጋግጡ ተብሎ ነዉ፡፡ ሆኖም ከችሎት ዉጪ ስለሚፈጠሩ ሁኔታዎች እዉነታነት እና ተጨባጭነት ሊታወቅ የሚችለዉ ራሱን የቻለ ሳይንሳዊ ምርመራ ተደርጎ በመሆኑ ችሎቶች የያዝነዉ መዝገብ ተነስቷል በማለት ብቻ በማናለብኝነት በዚያ መዝገብ መወሰን አይችሉም፡፡
– –
#አነጋጋሪ ጉዳይ ሁለት፡- ተፈፀመ የተባለዉስ ድርጊት እዉነተኛነት ሳይታወቅና ሳይረጋገጥ ማስጠንቀቂያ መስጠት ይቻል ይሆን?
– –
አንድ ሰዉ ጥፋተኛ ስለመሆኑ በማስረጃ እስካልተረጋገጠ ድረስ ነፃ ሆኖ የመገመት ሕገ-መንግስታዊ መብት አለዉ፡፡ ጥፋተኛም የሚባለዉ ሥነ-ሥርዓቱን የጠበቀ ክስ ቀርቦበት፣ያምን እና ይክድ መሆኑ በግልጽ ችሎት ተጠይቆ፣ማስረጃ ተሰምቶ እና የመደመጥ መብቱም እኩል ተከብሮለት እንጅ እንዲሁ ጥፋተኛ አይባልም፡፡ በወንጀል ህግ አንቀፅ 448 እና 449 ጋር የተገናኙ ጉዳዮች ለፍትሕ እርዳታ እምቢተኛ መሆን እና ፍርድ ቤት መድፈር ጋር በተገናኘ በቀጥታ ችሎቱ በያዘዉ መዝገብ ከሚወስናቸዉ ጉዳዮች ዉጪ አንድ ሰዉ ፍርድ ቤት በተጀመረ ክርክር ዝም ተብሎ እንዲህ አድርገሃል ተብሎ አይፈረጅም፡፡ የልደታ 4ኛ የወንጀል
ችሎቱ ማስጠንቀቂያ የሰጣቸዉ ግለሰቦች ድርጊታቸዉ ተፈፀመ የተባለዉ ከችሎት ስራ እና ከችሎት ዉጪ እስከሆነ ድረስ ክርክር ላይ ባለ መዝገብ ይህን አጥፍታችኋል ሊባሉ አይችልም፡፡ ችሎቱም ዳኞቹ ፌስቡክ ላይ አይተናል አንብበናል በማለት የፌስቡኩን መረጃቸዉን ከችሎት ስራቸዉ ጋር ሊቀላቅሉ እና በምርመራ ተጣርቶ በማስረጃ የሚረጋገጥን ጉዳይ ቀድመዉ ጥፋተኛ ናችሁ ለማለት አይችሉም፡፡
– –
ግለሰቦቹ ፈፀሙት የተባለዉ ተግባር ከችሎት ዉጪ በመደረጉ ሕግ መተላለፋቸዉ ተጣርቶ በማስረጃ ሳይረጋገጥ እና እነሱም የመከላከል መብታቸዉ ሳይጠበቅ ጥፋተኛ ናችሁ፤ ፍርድ ቤቱን ክብሩን እና ትክክለኛ የፍርድ ሂደቱን ተጋፍታችኋል በማለት ቀድሞ መወሰን የዳኝነት ስነ-ምግባሩም አይፈቅድም፡፡ ዳኞቹ ራሳቸዉ የስልጣናቸዉን ልክ በማለፍ የፍርድ ቤቱ ክብር እንዲወድቅና ሚዛናዊነቱ ፈተና ዉስጥ እንዲገባ የሚያደርገዉ ነዉ፡፡
– –
#አነጋጋሪ ጉዳይ ሶስት፡- ድርጊቱ የታወቀበትና የተገለጸበት መንገድ
– –
አንድ ዳኛ በግሉ የሚያዉቀዉንና ያወቀዉን ነገር ከፍርድ ስራዉ ጋር ሊቀላቅለዉ እንደማይገባ በሕግ በግልጽ የተቀመጠ ነገር ነዉ፡፡ ከችሎት ስራ ወጪ የተፈጸመን ነገር በግሉ ያወቀ ዳኛ እንዲህ ተፈጥሯል በማለት ራሱ አንስቶ፣ራሱ ምስክር ሆኖ ራሱ እንዲወስን የሙያዉ ስነ-ምግባር አይፈቅድለትም፡፡ የልደታዉ 4ኛ ችሎት ዳኞችም ከችሎት ዉጪ የዳኝነት ስራቸዉን በማይሰሩበት ሁኔታ ማህበራዊ ሚዲያ ላይ የተፃፈዉን አይተናል አንበናል በማለት ራሳቸዉ ጉዳዩን አንሽ፣ራሳቸዉ መስካሪ፣ራሳቸዉ ወሳኝ ሆነዉ መቅረባቸዉ ተገቢነት የሌለዉ ነዉ፡፡ ድርጊቱ የተፈፀመዉ ከችሎት ዉጪ እንደመሆኑ ችሎቱ ስለሁኔታዉ ያወቀዉ የችሎት ዳኞች በግላቸዉ ማህበራዊ ሚዲያ ሲከታተሉ እንደሆነ መረዳት ይቻላል፡፡ ከዳኝነት ስራቸዉ ዉጪ ከችሎት ዉጪ በግላቸዉ ያወቁትን ነገር ችሎት በሚሰሩበት መዝገብ ለማቅረብ ምንም የሕግ ድጋፍም የላቸዉም፡፡ ማህሌትን ፌስቡክ ላይ ስላያት የማህሌትን ስም ችሎት ጠርቶ ማስነሳት፣አንድ ሻርፕ የሚያደርግ ልጅ(የፌስቡክ ፎቶ ላይ መሆኑ ነዉ) እንዲህ ብለዉ ፅፈዋል እያሉ ችሎት ላይ እያስነሱ ማስጠንቀቅስ ትክክለኛ የስነ-ስርዓቱን ሂደት የጠበቀ ነዉ ለማለት ይቻል ይሆን? ፌስቡክ ላይ ተጻፈ የተባለዉን እና ግለሰቦቹ ፃፉት የተባለዉንስ ሶስቱም ዳኞች አይተዉት ይሆን?
– –
# እንደ መዉጫ!

የዳኝነት ስራ ክቡር ሲሆን ሙያዉም ከስሜት መፋታትን እና ለሕግና ለሕሊና ተገዥ መሆንን ይጠይቃል፡፡ የስራዉ ግብም ፍትሕን ማስፈን እና ሕግ እንዲከበር ማድረግ እስከሆነ ድረስ በቅድሚያ የሙያዉ ባለቤት ራሱ ዳኛዉ ለሕግ ተገዥ ሊሆን ይገባል፡፡ፍርድ ቤቶች ከፍርድ ሂደቱ ጋር በተገናኘ በግልፅ በሕግ በቀጥታ በችሎት እንዲወሰኑ ከተገለፁ ጉዳዮች ዉጪ ያሉትንና የራሳቸዉን የምርመራና የክርክር ሂደት የሚያስፈልጋቸዉን ጉዳዮች ከስነ-ስርዓት ዉጪ እያነሱ መወሰን አይችሉም፡፡ በሌላ መዝገብ ፋይል ተከፍቶና ሙሉ ክርክር የሚጠይቁ ጉዳዮችን ክርክር ላይ ባለ መዝገብ ቀድሞ በመደምደምም የሚሰጠዉ ትዕዛዝ ወይም ማስጠንቀቂያም ዜጎች ያላቸዉን እንደጥፋተኛ ያለመቆጠር መብት የሚጥስ ነዉ፡፡ በተጨማሪም ዳኞች ከችሎት ዉጪ በግላቸዉ ያወቁትን በሌላ የሕግ ሂደት የሚፈታን ጉዳይ ወደ ያዙት መዝገብ በማምጣት የሚወስኑ ከሆነ ችሎቶቹ የግል ፍላጎትን ማስፈፀሚያ ከመሆን የዘለለ ዉጤት አይኖራቸዉም፡፡
እንዲህ ዓይነት የስልጣንን ወሰን መጣስና ማን አለብኝነት ካልተወገዱ ችሎቶች ፍትሕ የሚገኝባቸዉ መድረክ ከመሆን ይልቅ ግለሰቦች ያሻቸዉን የሚፈጽሙበት እና ለተገልጋዩ ማሕበረሰብ ደግሞ የፍርሐትና የጥፋት መድረክ ከመሆን አይመለሱም!

(የአማራ ክልል ዳኞች እና ዓቃቢያነ ህጎች ድምፅ ከተሰኘ ገፅ ላይ የተወሰደ)

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: