በጌታቸው ሺፈራው
የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት በእስር ላይ የምትገኘው ጫልቱ ታከለን በገንዘብ ቀጥቷል። በእነ ደቻሳ ሞሲሳ የክስ መዝገብ 4 ተከሳሽ ጫልቱ ታከለ “እናንተ ኢህአዴግ ናችሁ፣ ከኢህአዴግ ፍርድ ቤት ምንም አልጠብቅም” ብላ ተናግራለች በሚል በችሎት መድፈር የገንዘብ ቅጣት ተጥሎባታል።
ፎቶ፡- ጫልቱ ታከለ
ህዳር 28 ቀን 2010 ዓም እነ ደቻሳ ሞሲሳ ተከላከሉ የሚል ብይን በተሰጠባቸው ወቅት 3ኛ ተከሳሽ የሆነችው ጫልቱ በሰነድ ማስረጃነት የቀረበባት የደህንነት ሪፖርት ወደ ኤርትራ ስለመሄድ የጠቀሰው ነገር ሳይኖር ብይን ላይ ወደ ኤርትራ ልትሄድ እንደነበር ተጠቅሶ ተከላከይ መባሏ እንዳሳዘናት ገልፃለች።
ጫልቱ ታከለ በወቅቱ “ከኢህአዴግ ፍርድ ቤት ምንም አንጠብቅም። ወደፊትም ፍትህ እንደማናገኝ ነው የምናስበው።” ብላ በመናገሯ በችሎት መድፈር ጥፋተኛ ተብላ በአዳር ዛሬ ህዳር 29 ቀን 2010ዓ.ም. የ500 ብር የገንዘብ ቅጣት ተጥሎባታል።
ጫልቱ ታከለ ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ ክስ ተፈርዶባት ፍርዷን ጨርሳ እንደወጣች ተገልጿል።