ጌታቸው ሺፈራው
የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት በጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እና የኦሮምያ ክልል ባለስልጣናት ምስክርነት ጉዳይ ላይ ዛሬ ብይን እሰጣለሁ ባለው መሰረት ብይን መስጠት አልቻለም።
ታህሳስ 17 ቀን 2010 ዓ.ም. አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በጊዜ ጥበት ምክንያት ፍርድ ቤት ቀርበው መመስከር እንደማይችሉ በጠቅላይ ሚንስትሩ ፅህፈት ቤት በኩል ለፍርድ ቤቱ በደብዳቤ ተገልፆአል። በዚሁ ቀን አቶ ለማ መገርሳን ጨምሮ በእነ ጉርሜሳ አያኖ የክስ መዝገብ ከ1ኛ እስከ 4ኛ ተከሳሾች መከላከያ ምስክርነት የተጠቀሱት የኦሮምያ ክልል ባለስልጣናት መቅረብ ባለመቻላቸው ፍርድ ቤቱ በቀጠሮው መጨረሻ፣ ዛሬ ታህሳስ 19 ቀን 2010 ዓ.ም. ብይን እሰጣለሁ ብሎ የነበር ቢሆንም ብይን ሳይሰጥ ቀርቷል። ታህሳስ 17 ቀን 2010 ዓ.ም. በዋለው ችሎት ተከሳሾች አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ታስረው ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ለችሎት ያመለከቱ ሲሆን ለኦሮምያ ክልል ባለስልጣናት ትዕዛዝ ስላልደረሳቸው በቀሪዎቹ ሁለት ቀናት ይቀርባሉ ተብሎ ተጠብቆ ነበር።
ትናንት ታህሳስ 18 ቀን 2010 ዓ.ም. በእነ ጉርሜሳ አያኖ የክስ መዝገብ ከ1ኛ እስከ 4ኛ ተከሳሾች ጠበቃ አብዱልጀባር ሁሴን በመከላከያ ምስክርነት የተጠቀሱትን የኦሮምያ ባለስልጣናት በአካል አግኝተው ባነጋገሯቸው መሰረት ባለስልጣናቱ ለዛሬ ታህሳስ 19 ቀን 2010 ዓ.ም. ፍርድ ቤት ቀርበው ሊመሰክሩ እንደሚችሉ ለፍርድ ቤቱ አስረድተው ነበር። ይሁንና ዛሬ ታህሳስ 19 ቀን 2010 ዓ.ም. የኦሮምያ ክልል ባለስልጣናት በስብሰባ ምክንያት ቀርበው መመስከር እንዳልቻሉና ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷቸው ፍርድ ቤት ቀርበው እንዲመሰክሩ ከኦህዴድ ማህከላዊ ኮሚቴ ፅህፈት ቤት በተፃፈ ደብዳቤ ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል።
ሆኖም ፍርድ ቤቱ በቀጠሮው የመጨረሻ ታህሳስ 19 ቀን 2010 ዓ.ም. አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ታስረው እንዲቀርቡ የተነሳው አቤቱታ ላይ ብይን ይሰጣል ተብሎ ሲጠበቅ በዚህ ጉዳይ ላይ ብይን ለመስጠት ለታህሳስ 27 ቀን 2010 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል። ከአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በተጨማሪ በስብሰባ ምክንያት ለዛሬ ቀርበው መመስከር ባለመቻላቸው ተለዋጭ ቀጠሮ እንዲሰጣቸው በደብዳቤ የጠየቁት የእነ ለማ መገርሳ አቀራረብ ጉዳይ ላይም ታህሳስ 27 ቀን 2010 ዓ.ም. ብይን እሰጣለሁ ብሏል።
የተከሳሾቹ ጠበቃ አቶ አምሃ መኮንን ባለስልጣናቱ ተለዋጭ ቀጠሮ በጠየቁበት ሁኔታ በእነሱ ጉዳይ ላይ ብይን ለመስጠት ቀጠሮ መያዙ ግልፅ እንዳልሆነ ተናግረዋል። ታህሳስ 27 ቀን 2010 ዓ.ም. በባለስልጣናቱ የመከላከያ ምስክርነት አቀራረብ ላይ ብይን ለመስጠት ብቻ የተያዘ ቀጠሮ ሲሆን ለተከሳሾቹ ከየካቲት 5 እስከ የካቲት 9 ተከታታይ ቀጠሮ ተይዟል።