~የኦፌኮ አመራሮችን ደግፈው ያጨበጨቡ የግንቦት 7 ተከሳሾች ተፈርዶባቸዋል
ጌታቸው ሺፈራው
ፎቶ፡ እነ በቀለ ገርባ (ከማኅበራዊ ገፅ የተወሰደ)
ከአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ጋር በተያያዘ በተቀሰቀሰው ህዝባዊ ንቅናቄ የተከሰሱት አራት የኦፌኮ አመራሮች ዛሬ ጥር 3/2010 በችሎት መድፈር ቅጣት ተወስኖባቸዋል። በእነ ጉርሜሳ አያኖ ክስ መዝገብ የተከሰሱት ጉርሜሳ አያኖ፣ ደጀኔ ጣፋ፣ አዲሱ ቡላላ እና በቀለ ገርባ በመከላከያ ምስክርነት የጠቀሷቸው እነ ለማ መገርሳ እንዲሁም በእስር ላይ የሚገኘው አንደየዓለም በምስክርነት እንዳይቀርቡ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት ብይን በሰጠበት ወቅት ተቃውሞ በማሰማታቸው ችሎት ደፍራችኋል በሚል እያንዳንዳቸው 6 ወር ተፈርዶባቸዋል።
ፍርድ ቤቱ ” በሚረባና በማይረባ ጉዳይ የመንግስት ባለስልጣናት ለምስክርነት መቅረብ የለባቸውም” በሚል ባለስልጣናቱ በምስክርነት እንዳይቀርቡ ውድቅ ያደረገ ሲሆን አቶ በቀለ ገርባ “በሚረባና በማይረባ እያላችሁ የምትጠቀሙት ቃል ከእናንተ የሚጠበቅ አይደለም” ማለታቸውን ችሎቱ የታዘቡ ገልፀዋል። አቶ ደጀኔ ጣፋ በበኩላቸው “አቃቤ ህግ አመራሮችን ጠርቶ አስመስክሮብናል። እኛ አመራሮችን በምስክርነት ስንጠራም መመስከር የለባቸውም ሊባል አይገባውም” ሲሉ በችሎቱ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።
ተከሳሾቹ “ደም ደም ትሸታላችሁ፣ 26 አመት ሙሉ የኦሮሞን ህዝበ ገድላችኋል፣ 26 አመት ሙሉ በኢትዮጵያ ህዝብ ደም ተጨማልቃችኋል፣ ሞት በእኛ ይብቃ ” ሲሉ እንደተናገሩና እንደዘመሩም ታውቋል። አመራሮቹ በፍርድ ቤቱ ውሳኔ ተቃውሞ በማሰማታቸው በችሎት መድፈር በተፈረደባቸው ወቅት ፍርድ ቤቱ ሲያነብ አንሰማም ብለዋል።
በእነ በለጠ ክስ መዝገብ በግንቦት 7 የተከሰሱት 3 ተከሳሾችም፣ እነ ጉርሜሳ ሲፈረድባቸው አጨብጭባችኋል በሚል በችሎት መድፈር 3 ወር ተፈርዶባቸዋል። 3 ተከሳሾች “ለምን አጨበጨባችሁ?” ተብለው በፍርድ ቤት ሲጠየቁ “ወንድሞቻችን ስለሆኑ ነው” ብለው መልስ መስጠታቸው ታውቋል። ከችሎት ወጥተው የእስረኞች ጊዜያዊ ማቆያ የነበሩ እስረኞችም በኦሮምኛ ሲዘምሩ ተደምጠዋል። በአማርኛም “ሞት በእኛ ይብቃ! ደም ደም ይሸታል ቤቱ፣ የፍርድ ቤቱ! ” እያሉ ሲዘምሩ ተሰምተዋል።
በተያያዘ ዜና መንግስት የፖለቲካ እስረኞችን እፈታለሁ ብሎ መግለጫ ከሰጠ በኋላም የፖለቲካ እስረኞች እየተፈረደባቸው ነው። ትናንት ጥር 1/2010 ዓ•ም የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት በግንቦት 7 ክስ የተመሰረተባቸው በእነ ትንሳኤ በሪሶ ክስ መዝገብ 3ኛ ተከሳሽ ግሩም አስቀናው ላይ የ4 አመት ፍርድ ውሳኔ አስተላልፏል።
ፍርድ ቤቱ የ”ወንጀሉን” ደረጃ በመከካለኛ በመያዝ መነሻ ቅጣቱን 7አመት አድርጎ፣ በአራት ማቅለያዎች 4 አመት ፅኑ እስራት ፈርዶበታል። አቶ ግሩም አስቀናው የሰው ምስክር እና ቃል ማስረጃ የሌለበት ሲሆን በሰነድነት የተያያዘበት የስልክ ማስረጃም ከእሱ ስልክ ያልገኘ እንደሆነ ሲከራከር ቆይቷል።
መንግስት በቅርቡ በሰጠው መግለጫ የፖለቲካ እስረኞችን እፈታለሁ ቢልም እስረኞች ይፈታሉ ተብሎ በሚጠበቅበት ወቅት እንደ ግሩም ቅጣት የተላለፈባቸው፣ እንዲከላከሉ የተበየነባቸውም የፖለቲካ እስረኞች ይገኙበታል።