የተከሳሾች እና ከሳሾች ወግ ትዝብት

በጌታቸው ሺፈራው

“ቶርች ሲያስደርጉን የነበሩት ጌታቸው አምባዬ ናቸው። እግርና እጃችን በካቴና አሳስረውናል።” 36ኛ ተከሳሽ ካሳ መሃመድ
~”አማራ፣ ጉራጌ፣ ኦሮሞ፣ ሙስሊም በመሆናችን ብቻ ተከሰናል። እኔ የተከሰስኩት ጉራጌ ስለሆንኩ ነው። የዶ/ር ብርሃኑ ነጋ፣ የዶ/ር ታደሰ ብሩ ዘመድ ነህ እየተባልኩ ነው የተመረመርኩት። “22ኛ ተከሳሽ ሚስባህ ከድር
~”እኔ ከዚህ ፍርድ ቤትም፣ ከአምባገነኑ መንግስትም ፍትህ አልጠብቅም። ለታሪክ ነው የምከራከረው። ” 1ኛ ተከሳሽ መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ
~”የሰውን ልጅ እንደሰው አለመቁጠር፣ ህሊና ቢስነት ነው።” 13ኛ ተከሳሽ ዶ/ር ፍቅሩ ማሩ
~”እኛ የተከሰስነው ለምን ከእሳትና ከጥይት ተረፋችሁ ተብለን ነው።” 31ኛ ተከሳሽ ጌታቸር እሸቴ
~”ማረሚያ ቤት አንድ ቀን ባደርኩ ቁጥር ለህይወቴ እሰጋለሁ” 5ኛ ተከሳሽ አግባው ሰጠኝ
~”በሌላ ሀገር ከእግዚያብሔር ቀጥሎ ፍትሕ የሚሰጥ ፍርድ ቤት ነው። በእኛ ሀገር ግን በደሕንነት ብጣሽ ውቀትና ስልክ ትዕዛዝ ነው የሚሰራው።” 3ኛ ተከሳሽ አሸናፊ አካሉ
~”እነዚህን ዐቃቤ ሕግ ብሎ መጥራት አይቻልም። ዐቃቤ ሕግ ማለት በጥላቻ ግለሰብን የሚያጠቃ፣ ህሊና ቢስ አይደለም።” 25ኛ ተከሳሽ ደረጀ መርጋ
~”ከአሁን በኋላ ወደ ፍርድ ቤት መመላለስ አልፈልግም። ፍርድ ቤት በሌለሁበት የሚወስነውን ውሳኔ በማረሚያ ቤት ሆኜ እቀበላለሁ” 18ኛ ተከሳሽ አንጋው ተገኘ
~”እኔ ለህሊናዬ የምኖር ሰው ነኝ። ስሜ መጥፋት የለበትም። እኔ እንደዛ ባደርግ እንኳ ተቋሙ ነው የሚከራከረው።” መኩሪያ አለሙ (ዐቃቤ ሕግ)
~”በሚዲያ የሚነገር ነገር አለ።ተፅዕኖ ያመጣል። ምስክሮችም ላይመጡ ይችላሉ። ከሳሽ የለሁበትም ሲል ወዲያውኑ ማንሳት አለበት። …” ፍርድ ቤቱ

ዐቃቤ ሕግ በቂሊንጦ ቃጠሎ ሰበብ በታሰሩት፣ በእነ መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ ክስ መዝገብ (38) ተከሳሾች ላይ 85 ምስክር አስቆጥሯል። ዐቃቤ ሕግ ተደጋጋሚ ቀጠሮዎች ተሰጥተውት ምስክሮችን አሰምቷል። ከነሃሴ 1 እስከ ነሃሴ 12/2009 በነበረው ተከታታይ ቀጠሮ የተወሰኑ ካሰማ በኋላ፣ የ5 ወር ቀጠሮ ከታህሳስ 23 እስከ ጥር 3/2010 ዓም በተሰጠው ቀጠሮ ጥቂት ምስክሮችን አሰምቷል። በዚህ ቀጠሮ ለተከታታይ 5ቀን ምስክር ሳያቀርብ ተከሳሾች ተመላልሰዋል። በ5ቱ ተከታታይ ቀናት ጉዳዩን የማያውቁ ዐቃቤ ሕጎች ተመላልሰዋል።ዛሬ ጉዳዩን የሚያውቁት ሶስት ዐቃቤ ሕጎች ተሰይመው ቀሪ 28 ምስክር ስላላቸው ተለዋጭ ቀጠሮ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል። አንድ ዐቃቤ ሕግ ቀጠሮው እስከ ጥር 7/2010 ስለመሰላቸው፣ በዚህ ጊዜ ለማቅረብ ሀሳብ እንደነበራቸው ገልፀዋል። ዐቃቤ ሕጎች ተለዋጭ ቀጠሮ እንዲሰጠው ጥያቄ ካቀረቡ በኋላ ጠበቆችና ተከሳሾች ተቃውሞ አቅርበዋል። በተለይ ተከሳሾች ምሬታቸውን ጭምር ገልፀዋል። ዐቃቤ ሕግ ተዘለፍኩ ብሏል። ፍርድ ቤቱ በመሃል ገብቷል። የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት የነበረው ክርክር ከሞላ ጎደል እንደሚከተለው ቀርቧል።

~3ኛ ተከሳሽ አሸናፊ አካሉ:_ “በዚህ ችሎት 5አመት ተመላልሻለሁ። ዐቃቤሕግ ይጀምራል። ዐቃቤ ሕግ ይጨርሳል። ዐቃቤ ሕጉ መኩሪያ አለሙ ቀጠሮው እስከ ጥር 7/2010ዓም ስለመሰለኝ ነው ብሏል። በጣም ያሳዝናል። አምስት አመት በሙሉ ምንም ፍትሕ ሳላገኝ ተጨማሪ ቀጠሮ ይሰጠኝ የሚለው ሌላ ስድስተኛ አመት እንድታሰር ነው። እንደአለመታል ሆኖ እንጅ በሌላ ሀገር ከእግዚያብሔር ቀጥሎ ፍትሕ የሚሰጥ ፍርድ ቤት ነው። በእኛ ሀገር ግን በደሕንነት ብጣሽ ውቀትና ስልክ ትዕዛዝ ነው የሚሰራው። እስኪ ስልጣናችሁን ተጠቀሙበት! በጣም ያሳዝናል።”

~18ኛ ተከሳሽ አንጋው ተገኘ:_”(ዐቃቤ ሕጎች) ባህሪያቸው እንደዚህ ነው። ነሃሴ ላይ በነበረው ቀጠሮው ምስክር ሳያቀርቡ ብዙ ቀን አሳልፈዋል። እኛ ትግስት ያደረግነው እውነቱ እንዲወጣ ነው። 5ወር ቀጠሮ ተሰጥቷቸው ምስክር ማቅረብ አልቻሉም። እነሱ በ5ውስጥ የወር ደሞዛቸውን ይወስዳሉ።……ምስክር የተባሉት ሰዎች አንመሰክርም ብለዋል። የመሰከሩትም “ቶርች”ተደርገው የመሰከሩ ናቸው። ከአሁን በኋላ ወደ ፍርድ ቤት መመላለስ አልፈልግም። ፍርድ ቤት በሌለሁበት የሚወስነውን ውሳኔ በማረሚያ ቤት ሆኜ እቀበላለሁ”
~13ኛ ተከሳሽ ዶ/ር ፍቅሩ ማሩ:_ “ሁሉ ነገር በፅሑፍ የለም። ዳኝነትም በህሊና ነው። ዐቃቤ ሕግ ቤተሰብ የምናስተዳድር፣ ህይወት የምንመራ ሰዎችን አስሮ በህይወታችን ላይ ቀልድ ነው የያዘው። በመጀምርያው 10 ቀን እንድታቀርብ ተብሎ በራሱ ቁጥጥር ስር ያሉትን ማቅረብ አልቻለም። ባለፈው ቀጠሮ ፖሊስ ምስክር ስላላመጣ ዐቃቤ ሕጉ ፖሊስ ያላቀረበው ቀጠሮው ለአንድ ቀን ብቻ ስለመሰለው ነው ብሎ ነበር። ላለፉት 5 ቀናት አላመጣም። በ5 ቀን ያላመጣውን በመላ ኢትዮጵያ ተፈላልገው ይምጡልኝ ማለት የሰውን ልጅ እንደሰው አለመቁጠር፣ ህሊና ቢስነት ነው።”

~1ኛ ተከሳሽ መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ:_ “ዐቃቤ ሕግን እንደተቋም ነው የምናየው። እነሱም ይላሉ። ከሆነ በየቀኑ የሚመጡት ዐቃቤ ሕጎች ተመሳሳይ ነገር መናገር ነበረባቸው። የሚሰጡት ማስተባበያ አሳፋሪ ነው። ለህግ እውቀት ላላቸው ደግሞ ይበልጥ ያሳፍራል። እኔ ከዚህ ፍርድ ቤትም፣ ከአምባገነኑ መንግስትም ፍትህ አልጠብቅም። ለታሪክ ነው የምከራከረው። የተገደሉት ወንድሞቻችን እንደኛ በማንነታቸው ተከሰው እስር ቤት የገቡ ናቸው። ከዐቃቤ ሕግ ለእኛ ይቀርባሉ። እኛም ሞት ተፈርዶብን ነበር። እንደ እድል ሆኖ በህይወት አለን።……… የተገረፍነውን ግርፋት ረስተን፣ ችለን ከዐቃቤ ሕግ ጋር እየተከራከርን ነው። እኛ ሞትን ተጋፍጠን ነው እየተከራከርን ያለነው። የታፈነው የነሃሴ 28/2010 (የቂሊንጦ ቃጠሎ) ታሪክ ትተነው የምናልፈው አይደለም። በዚህ ችሎት በተደጋጋሚ ቀርቤያለሁ። በዚህ ችሎት ምንም አይነት እምነት የለኝም። እናንተ ለእኛ መልካም ስትሆኑ በሙስና ትከሰሳላችሁ፣ለእኛ ክፉ ስትሆኑ ደግሞ ሹመት ይሰጣችኋል። ከዚህ አምባገነን መንግስት ጋር ተከራክሬ ፍትህ አገኛለሁ ብየ አልጠብቅም።

ውሃ እንኳን በህግ አምላክ ሲባል ይቆማል የሚል ማህበረሰብ ነው ያሳደገኝ።……እኔ በሙያዬ ስለ አየር ኃይል ልከራከር እችላለሁ። ስለ ፍትህ መከራከር ያለባችሁ እናንተ ናችሁ።”
~5ኛ ተከሳሽ አግባው ሰጠኝ:_” እኛ ያለነው በማረሚያ ቤት ነው። አንድ ቀን ባደርኩ ቁጥር ለህይወቴ እሰጋለሁ። እናንተ እስረኞችን በአደራ በማረሚያ ቤት አስቀምጣችኋቸው ሲሞቱ ለምን ሞቱ ብላችሁ አልጠየቃችሁም። እኔም በማረሚያ ቤት አንድ ቀንም እንድቆይ የሚያደርግ ቀጠሮ እንዲቀጠርብኝ አልፈልግም።”

~31ኛ ተከሳሽ ጌታቸር እሸቴ:_”እኛ የተከሰስነው ለምን ከእሳትና ከጥይት ተረፋችሁ ተብለን ነው። ክራውን ፍርድ ቤት ስንቀርብ መኩሪያ (ዐቃቤ ሕግ) አዎ ቀርጬሃለሁ ብሎኛል። የቀረፀኝ ለእኔም ለፍርድ ቤቱም ስለሚጠቅም እንዲያቀርብልኝ እፈልጋለሁ።30ኛ የዐቃቤ ሕግ ምስክር ከመቀሌ ይመጣሉ ተብሏል። በእርግጥ ከመቀሌ ካልሆነ ከየትም ሊመጡ አይችሉም።……በድሉ በላይ የተባለ ምስክር በነፍስ የገባ፣ ሲገባ እኔ የተቀበልኩት ሰው ነው። ነፍስ አጥፍቶ የታሰረ ሰው መስክሮ ተፈትቷል። ምስክሮች ወንጀላቸው እየተነሳላቸው ከእስር በተፈቱበት ሁኔታ አላገኘናቸውም ማለት በእኛ ላይ ቁማር መጫወት ነው። ”
~38ኛ ተከሳሽ ከድር ታደለ:_ “……ከዐቃቤ ሕግ ጋር ተነጋግራችሁ ነው የምትሰሩት? መስክሩ የሚባሉት ተገደው ነው። የተፈቱት መመስከር ስለማይፈልጉ ይጠፋሉ። ማረሚያ ቤት ውስጥ ያሉት መስክሩና ትፈታላችሁ ስለሚባሉ ይመሰክራሉ። መስክሩ ከእስር ትለቀቃላችሁ እየተባሉ ነው። ዛሬ ዐቃቤ ሕጎች እንደሰርግ አጃቢ ተሰብስበው የመጡት ቀጠሮ ለማስቀጠር ነው። እስከዛሬ ጉዳዩን የማያውቅ ዐቃቤ ሕግ ነበር የሚልኩት ። ፍርድ ቤቱ በዐቃቤ ሕግ ጥያቄ መሰረት ቀጠሮ የሚፈቅድ ከሆነ ከዐቃቤ ሕግ ጋር ተነጋግሮ እንደሚሰራ 100 % ማረጋገጫ ይሆናል።

25ኛ ተከሳሽ ደረጀ መርጋ:_ ምስክሮች ተለይተው አንድ ቦታ ነበር የተቀመጡት። እየመከሯቸው ይሆናል።…ዐቃቤ ሕግ ምስክሮችን በጥንቃቄ መያዝ ነበረበት።…ከጫፍ እስከጫፍ መብቱን የጠየቀውን ስንት ሰው የሚያስር መንግስት ምስክሮችን ማምጣት አይከብደውም ነበር።……እነዚህን ዐቃቤ ሕግ ብሎ መጥራት አይቻልም። ዐቃቤ ሕግ በጥላቻ ግለሰብን የሚያጠቃ፣ ህሊና ቢስ አይደለም። መኩሪያ ሸዋሮቢት እስር ቤት መጥቶ “የመንግስት ስም ከሚጠፋ እናንተ ብትጠፉ ይሻላል” ብሎናል።……
~አንተነህ አያሌው (ዐቃቤ ሕግ):_ እኛ እዚህ የምንቀርበው ህጋዊ ክርክር ለማድረግ እንጅ ማንም እንዲሰድበን አይደለም። እስካሁን ባደረግነው ክርክር የማንንም ተከሳሽ፣ ወይም ጠበቃ ስም አንስተን አልዘለፍንም። ማንም እየተነሳ ህሊና ቢስ እያለ እያደበን ፍርድ ቤቱ ዝም እያለ ቆመን ቆመን መከራከር አንችልም። ተከራካሪ ወገኖችን ለማሸማቀቅ እየተሰራ ነው። እኛ፣ ፍርድቤቱ እና ህብረተሰቡ እየተዘለፈ ነው።
~መኩሪያ አለሙ(ዐቃቤ ሕግ):_ የህግ ባለሙያ ነኝ ተቋሙ በላከኝ ቦታ ሄጄ እሰራለሁ።ሸዋሮቢት የተከሳሾችን አያያዝ አጣራ ተብሎ ሄጃለሁ። እንደ ባለሙያ ሁለት ተከሳሾችን አነጋግሬያለሁ። እዛ ቦታ ላይ የተነገረውን ብናወራው ተከሳሾችን ይጎዳል። እኔ ለህሊናዬ የምኖር ሰው ነኝ። ስሜ መጥፋት የለበትም። እኔ እንደዛ ባደርግ እንኳ ተቋሙ ነው የሚከራከረው። የተማርኩትም ያሳደገኝ ማህበረሰብም እንዲህ ነገር አላስተማረኝም።

~ካሳሁን አውራሪስ (ዐቃቤ ሕግ):_ በዚህ አይነት ክርክር የግለሰብ ስም በመጥራት መከራከር ጉዳዩን አቅጣጫ የሚያስቀይር ነው። ችሎት ተደፈረ የሚባለው ችሎቱ ሲዘለፍ ብቻ አይደለም። ህሊና ቢስ እየተባልን እየተዘለፍን ነው።……
~ፍርድ ቤቱ (መሃል ዳኛው):_ ሰው መብቱን ለመጠቀም ተብሎ የሚናገረውን ቃል ከወጣ በኋላ መመለስ አይቻልም። ነገር ግን የችሎቱን ክብር በሚጠብቅ መልኩ ማነገር ይገባል። … ዐቃቤ ሕግ ያቀረቡትም ይህን ነው። የዳኛ ስራ ከትምህርት ቤት የተለየ ነው። የተከሰሰ፣ ከሳሽ፣ የተጎዳውም ሀሳቡን የሚያቀርበው ፍርድ ቤት ነው። ሀሳቡን ሲገልፅ ግን ለዳኞች ፈተና ነው። እንደትምህርት ቤት አይደለም። ጎጅውም ተጎጅውም በአካል ነው የሚመጡት።ዳኞች ፈተና ውስጥ ይገባሉ። ፈተናውን ለመቋቋም የችሎቱ ሂደት ሰላማዊ መሆን አለበት።…… ትርፍ ነገር ይነገራል። ይህን ስንገድብ ሌላ ይቀራል በሚል እንታገሳለን። መታገሱ ለህግ የበላይነት ይጠቅማል። ኮሽ ባለ ቁጥር አይተኮስም እንደተባለው ነው። በተናገራችሁ ቁጥር 1 አመት ብንቀጣ 25 አመት ይደርሳል። መሳደብ አይጠቅምም። አፍ መያዝ ግን አንችልም።…… በሚዲያ የሚነገር ነገር አለ።ተፅዕኖ ያመጣል። ምስክሮችም ላይመጡ ይችላሉ። ከሳሽ የለሁበትም ሲል ወዲያውኑ ማንሳት አለበት። ……የፍርድ ቤት ክብር የእኔ አይደለም። በክብር የተቀመጠው ሰው ጭምር ነው።…”
~25ኛ ተከሳሽ ደረጀ መርጋ:_ የፍትህ አካሉንም እውነቱ እንዲወጣ እንከራከራለን። የተገደሉት ወንድሞቻችን ናቸው። ሲገደሉ በአይናችን አይተናል። ያም ሆኖ ገድላችኋቸዋል ተብለን ተከሰናል። ይህ ሁሉ ስሜታዊ ያደርገናል።…… ዐቃቤ ሕግ የሚያቀርባቸው ምክንያቶች ምክንያታዊ የሚያደርጉ አይደሉም። ፍርድ ቤቱ ይህን አይቶ ውሳኔ እንዲሰጥ ነው።

~22ኛ ተከሳህ ሚፍታህ ከደር:_ በዚህ ሀገር የዐቃቤ ሕግ ስልጣን ገደብ ሊኖረው ይገባል። ከታሰርኩ አራት አመት ሊሞላኝ ነው። ባልተጣራ ክስ ከሶኝ ነፃ ተብያለሁ። አሁን ደግሞ ሌላ ክስ አቅርቦብኛል። የተከሰስኩት በማንነቴ ነው። በፈለገው ወንጀል እየከሰሰ የፈለገውን ያህል ያስራል። ይህን በማድረጉ አይጠየቅም። እኛ ደግሞ አንካስም። የተወሰኑ ሰዎች እንዳይከሰሱ ሲባል ዐቃቤ ሕግ ሸዋሮቢት ሄጀ አነጋግሬያቸዋለሁ ብሏል። ስለተፈፀመብን ነገር ግን አልገለፀም። ሰብአዊ መብት ግን ጥፍራችን መነቀሉን፣ ጣታችን መሰበሩን…መገረፋችን ገልፆአል። የትኛው ነው እውነቱ? ገዳይ ነው እየመሰከረብን ያለው። ኦፊሰር ገ/ማርያመው ሲገድል እያየን ነው መጥቶ የመሰከረብን። ክሱ ላይ ያልተጠቀሰ 24ኛ ሰው መሞቱን መስክሮ ሄዷል። ቴዎድሮስ የሚባለው ሟች በክሱ አልተጠቀሰም።…… በማናውቀው ጉዳይ ነው የተከሰስነው። ከፍተኛ በደልና ስቃይ እየደረሰብን ነው። አንድ ፍራሽ ላይ ለሁለት ነው የምንተኛው።

~34ኛ ተከሳሽ ፍፁም ጌታቸው:_ ለሞቱት ነው የምንከራከረው ብለዋል። የሞተውኮ ከ150 ሰው በላይ ነው። ዞን 5 አርማዬ ዋቄ ተደብስቦ ነው የተገደለው። እነዚህ ገዳዮች አይጠየቁም? ……ከዚህ ችሎት ከሚከታተለው መካከል የሟች ቤተሰብ አለ? በመኪና አደጋ የሞተ ሰው ቤተሰብ እንኳ ችሎት ይታደማልኮ!
~36ኛ ተከሳሽ ካሳ መሃመድ:_ፍርድ ቤቱ ማረሚያ ቤት ውስጥ ያለውን ችግር ይወቅልን። ዞን 5 ያለን እስረኞች ኦፊሰር ገብረማርያም መስክሮ ከሄደ በኋላ ማስፈራሪያ እየደረሰብን ነው። ኦፊሰር ጉኡሽ መለስ ምስክርነቱ ይለቅና እንተያያለን እያለ እየዛተብን ነው። በህይወት እንድንቆይ ካስፈለገ ማረሚያ ቤቱ ጉዳይ መስተካከል አለበት።አሁንም እኛን ገድለው ሌላ የአማራና የኦሮሞ ልጆችን እኛን ገደላችሁ ብለው ይከሷቸዋል። እዚህ ወንበር ላይ የመሰከረው ገብረማርያም በጥይት እደፋሃለሁ ብሎኛል። እነ ካሳ መሃመድ፣ ተመስገን ማርቆስ፣አሸናፊ መለስ፣ ሚስባህ ከድር፣ አጥናፉ አበራ ቀይ መስመር አልፈዋል ዋጋቸውን ያገኛሉ ተብለናል። እኔ የድንግል ማርያም ልጅ ነኝ፣ በእናቴ ፀሎት እወጣለሁ። የእኛ አልበቃ ብሎ ሀገራቸውን ለማገልገል የመጡ ምሁራን ከእኛ ጋር ተከሰው እየተሰቃዩ ነው። ……ከእነ አግባው ጋር ዝዋይ ተወስደን፣ ራቁታችን በፓንት ብቻ ሆነን ተደብድበናል።……ይህ የለበስኩት ልብስ የተገደለው ጓደኛዬ የአርማዬ ዋቄ ልብስ ነው። ጫማውም የእሱ ነው። ከዝዋይ ስንመለስ ገድለውታል። እነ ገብረማርያም የህወሓትን ተልዕኮ ለማስከበር ነው። እኛ ደግሞ መብታችን ለማስከበር ፍርድ ቤት እንናገራለን። ቶርች ሲያስደርጉን የነበሩት ጌታቸው አምባዬ ናቸው። እግርና እጃችን በካቴና አሳስረውናል።… በሀገራችን ተገልብጥን ተገርፈናል። ኩላሊት በሽተኛ ሆነን ነው ተገልብጠን የተገረፍነው። ኧረ ስለመድሃኒያለም! እነሱ የተጨመቀ ቡና ሲጠጡ እኛ እየተጨነቅን ነው። እነሱ ዝልዝልና ቁርጥ ሲበሉ እኛ እየተዘለዘልን ነው።

(ፍርድ ቤት ዐቃቤ ሕግ ቀሪ 28 ምስክሮችን ለማቅረብ ተለዋጭ ቀጠሮ እንዲሰጠው ያነሳውን ጥያቄ፣ የተከሳሽ ጠበቆችና ተከሳሾች የዐቃቤ ሕግን ጥያቄ በመቃወም ምስክርነቱ ታልፎ ብይን እንዲሰጥ ያቀረቡትን ተቃውሞ ለመበየን ለነገ ጥር 4/2010ዓም ቀጠሮ ይዟል። በሌላ በኩል የቂሊንጦ ጥበቃና ደህንነት ኃላፊ ምስክርነት ከሰጡ በኋላ ኃላፊውን በችሎት ተናግራችኋል በሚል በማረሚያ ቤት ዛቻ እየደረሰብን ነው ያለው ካሳ መሃመድ አቤቱታውን በፅሁፍ አቅርቦ እንዲጣራ ፍርድ ቤቱ ገልፆለታል። ጉዳዩ ከምስክር አሰማም ጋር የተገናኘና ዝም ተብሎ መታለፍ ስለሌለበት ይጣራል ብሏል።)

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: