ጌታቸው ሺፈራው
“እንደ አለመታደል ሆኖ የራሴን እውቀት በቀጥታ ለተተኪ ኢትዮጵያውያን ሐኪሞች ማስተላለፍ ባልችልም በርካታ ሃኪሞችን በራሴ ወጪ ሲውዲን ሃገር ልኬ በማስተማር የዘርፉን እውቀት ወደ ሃገራችን ሃኪሞች እንዲያሸጋግሩ አመርቂ ስራ እየሰራሁ እገኛለሁ፡፡ ” ዶ/ር ፍቅሩ ማሩ
ፎቶ፡ ዶ/ር ፍቅሩ ማሩ
ቀን፡ 22/02/2010
ለፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት
የልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት
አዲስ አበባ
ከሳሽ፡ የፌደራል ጠ/አ/ህግ
ተከሳሽ፡ ዶ/ር ፍቅሩ ማሩ ወርዶፋ (በነ ማስረሻ ሰጠ የክስ መዝገብ 13ኛ ተከሳሽ)
ጉዳዩ፡- ሃኪሞችን እና የሆስፒታል አመራሮች በምገኝበት ማ/ቤት በቢሮ በኩል እንዳገኛቸው ለማ/ቤት ትዕዛዝ እንዲሰጥልን ስለመጠየቅ
እኔ አመልካች በዚሁ ችሎት ቀርቤ እየተከታተልኩ በምገኝበት ክስ ምክንያት በማረሚያ ቤት የምገኝ ሲሆን ቀደም ሲል በሲውዲን ሃገር ሰርቼ ያገኘሁትን ገንዘብ እና 40 ዓመታት በልዩ የልብ ሕክምና ያዳበርኩትን እውቀት ይዤ ወደ ሃገሬ በመመለስ በሃገራችን ሁለት የልብ እና የልብ ነክ ሕክምና ሆሰፒታሎችን በማቋቋም ቀደም ሲል በህክምና እጦት ወደ ውጪ ሄደው መታከም ባለመቻላቸው ህይወታቸውን ያጡ የነበሩ የበርካታ ዜጎችን ህይወት መታደግ እንዲችሉ እና ባለፉት 11 ዓመታት ከ50 ሺ (ሃምሳ ሺ) ለሚበልጡ ዜጎች በአነስተኛ ዋጋ ህክምና እንዲያገኙ አድርጌአለሁ፡፡
እነዚህ ሆስፒታሎችን አሁን ድረስ በቦርድ ሊቀመንበርነት እየመራሁ እገኛለሁ፡፡
እንደ አለመታደል ሆኖ የራሴን እውቀት በቀጥታ ለተተኪ ኢትዮጵያውያን ሐኪሞች ማስተላለፍ ባልችልም በርካታ ሃኪሞችን በራሴ ወጪ ሲውዲን ሃገር ልኬ በማስተማር የዘርፉን እውቀት ወደ ሃገራችን ሃኪሞች እንዲያሸጋግሩ አመርቂ ስራ እየሰራሁ እገኛለሁ፡፡
ሆኖም ግን ተጠርጥሬ በእስር ላይ የምገኝ በመሆኑ ይኸው ምትክ የሌለው ህክምና ለዜጎች በተሻለ አኳኋን እንዲሰጥ በአካል በቦታው ላይ ሆኜ መምራት ባለመቻሌ በቋሚነት ህክምና የሚደረግላቸው እና አዳዲስ ህሙማንን በሚመለከት በሆስፒታሉ ያሉ ሃኪሞች አገልግሎት እንዴት መስጠት እንዳለባቸው ለሃኪሞች የተሻለ ሃሳብ /ምክር/ መስጠት እንድችል ፍ/ቤቱ የዜጎችን እጅግ ከፍተኛ ጥቅም ከግምት በማስገባት ቁጥራቸው እስከ አራት የሚሆኑ ባለሙያዎችን በቤተሰብ መጠየቂያ በኩል ቢመጡ የሚሰጠው የመነጋገሪያ ጊዜ እጅግ በጣም አጭር ደቂቃዎች ብቻ በመሆኑ ለማነጋገር አስቸጋሪ መሆኑን ከግምት በማስገባት ከእነዚህ ሃኪሞች እና የሆስፒታሉ አመራሮች ጋር በማረሚያ ቤቱ ቢሮ በኩል ተፈቅዶልኝ ከላይ ለተጠቀሰው በጣም አስፈላጊ ጉዳይ መገናኘት እንድችል እንዲፈቀድልኝ እና ለቂልንጦ ማረሚያ ቤት ትዕዛዝ እንዲሰጥልን በማክበር አመለክታለሁ፡፡
ከሠላምታ ጋር” ሲሉ ጥያቄያቸውን ማቅረባቸው ታውቃል።