ከመስከረም 3 ቀን 2004 ዓ ም ጀምሮ በእስር ላይ የነበሩት የቀድሞ የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ (አንድነት) ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር እና የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አንዱዓለም አራጌ ፥ የፓርቲያቸው አመራር አባላት የነበሩት አቶ ናትናኤል መኮንን፥ የቀድሞ የፓርላማ አባል አቶ አንዱዓለም አያሌው የካቲት 7 ቀን 2010 ዓ ም ከእስር ተለቅዋል።
አቶ አንዱዓለም አራጌ
በተመሳሳም የቀድሞ የጋምቤላ ፕሬዘዳንት የነበሩት አቶ ኦኬሎ አኳይ፥ የመብት ተሟጋቿ ወ/ሮ እማዋይሽ አለሙ፥ የኦፌኮ/መድረክ አመራር የነበሩት አቶ ኦልባና ሌሊሳ፥ የቀድሞ መኢአድ ፕሬዘዳንት አቶ ማሙሸት አማረ፥ የመኢዴፓ አመራር የነበሩት አቶ ክንፈሚካኤል ደበበ (አበበ ቀስቶ)፥ የኢብአፓ ፕሬዘዳንት የነበሩት አቶ ዘሪሁን ገብረእግዚአብሔር፥ የቀድሞ የሰማያዊ ፓርቲ አመራር የነበረው ወጣት ብርሃኑ ተክለያሬድ፥የመብት ተሟጋቿ ጫልቱ ታከለ እና ደርቤ ኢተና፤ የሙስሊሙ መፍትህ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላትና የመብት ተሟጋቾች አህመዲን ጀበልና አህመድ ሙስጠፋ እና አርቲስት ሴና ሰለሞን ከእስር ተለቅዋል።
በተለይ አቶ አንዱዓለም አራጌ እና ወ/ሮ እማዋይሽ አለሙ ተይዘው ከታሰሩ ጀምሮ በተለያየ ክስ መዝገብ ዕድሜ ልክ እስር ተፈርዶባቸው እንደነበር ይታወቃል።
ከላይ የተጠቀሱትን ጨምሮ በተመሳሳይ ቀን ከ746 ያላንሱ የፖለቲካ እስረኞች እንደሚፈቱ የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ለመግንግሥት መገናኛ ብዙኃን ማሳወቁ ይታወሳል። ይሁን እንጂ አሁንም በርካታ የፖለቲካ እስረኞች በተለያዩ የሀገሪቱ ወህኒ ቤቶች እንደሚገኙ መረጃዎች ይጠቁሟሉ።
የነ አቶ አንዱዓለም አራጌን መፈታት ተከትሎ በርካታ ህዝብ በአዲስ አበባ ቃሊቲ ወህኒ ቤት እና በየመሮሪያ ቤታቸው በመገኘት ደስታውን ሲገልፅና እና ድጋፉን ሲያደርግ ተስተውሏል። እነ አንዱዓለምም ለመላው ህዝብ ምሥጋናችውን አቅርበዋል።