ጠቅላይ ሚኒስትር እቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የሥራ መልቀቂያ ማስገባታቸውን ዛሬ የካቲት 8 ቀን 2010 ዓ. ም. በፅህፈት ቤታቸው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አረጋግጠዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሥራ መልቀቂያቸውን በቅድሚያ በስልጣን ላይ ያለው የገዥው ፓርቲ አባል ለሆነውና ተወክለው ለመጡበት ለደኢህዴን እና ኢህአዴግ ከሊቅመንበርነት ለመልቀቅ ያስገቡት ጥያቄ ተቀባይነቱን ማግኘቱን አስታውቀዋል። ይህንንም ተከትሎ ከጠቅላይ ሚኒስትርነት ኃላፊነት ለመነሳት ለገዥው ኢህአዴግ ምክር ቤት ጥያቄ ማስገባታቸውንና ውሳኔያቸው ተቀባይነት አግኝቶ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲፀድቅላቸው እንደሚንሱ ይጠበቃል።
አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ
ለረጅም ጊዜ በሥላጥን ላይ ቆይተው በሞት የተለዩት አቶ መለስ ዜናዊን በመተካት ከነሐሴ 2004 ዓ. ም. ጀምሮ በሥልጣን ላይ ያሉት አቶ ኃይለማርያም፤ ዛሬ በፅህፈት ቤታቸው በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን በሰጡት ይፋዊ የሥራ መልቀቂያ መግለጫ እንዳስታወቁት ከሆነ በእርሳቸው ምትክ በፓርላማው ሌላ አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር እስኪሾም ድረስ ሥራቸውን እንደሚቀጥሉ አስታውቅዋል። የሥልጣን መልቀቃቸውም በሀገሪቱ ያለውን ችግር ለመፍታት የመፍትሄ አካል አድርገው እንዳሰቡትም አስታውቀዋል።