(ዳጉ ሚዲያ) መንግሥት የፖለቲካ እስረኞች የነበሩት ጋዜጠኞችን፥ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችን እና የሰብዓዊ መብት ተከራካሪዎችን መፈታት እና የጥቅላይ ሚኒስትሩ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የሥራ መልቀቂያ ማስገባታቸውን ተከትሎ፤ ከትናንት የካቲት 9 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ የተደረና በሚኒስትሮች ምክር ቤት እንደፀደቀ የተነገረለት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁን ገዥው መንግሥት አስታውቋል።
የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ሲራጅ ፈጌሳ
አዋጁም ለቀጣዮቹ 6 ወራት የጸና መሆኑን የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ሲራጅ ፈጌሳ ዛሬ የካቲት 10 ቀን 2010 ዓ.ም. በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል። አዋጁም እንደ አስፈላጊነቱ ታይቶ ለተጨማሪ 4 ወራት ሊራዘም እንደሚችልም ተገልጿል።
የአስቸኳይ አዋጁ የመሰብሰብ፥ የመደራጀት፥ መረጃዎችን የመለዋወጥ፥ የመፃፍ፥ የተለያዩ ምልክቶችን ማሳየት፥ ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ ብርበራ፥ ፍተሻ እና የመሳሰሉ መብቶችን የገደበ መሆኑን ሚኒስትሩ አስታውቀዋል። እንደ እዋጁ ከሆነ፤ የጊዜ ገደብን ጨምሮ መንግሥት የመገናኛ ብዙኃንን ከማገድ እስከመዝጋት የሚደርስ ርምጃን እንዲወስድ የሚፈቅድ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።
ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መውጣት በመንግሥት የተገለፀው፤ በሀገሪቱ የተፈጠረው አለመረጋጋት እንደሆነ ተጠቅሷል። አዋጁንም ከ15 ቀናት በኋላ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት እንደሚፀድቅ ሚኒስትሩ አቶ ሲራጅ ቢናገሩም፤ የምክር ቤቱ አባላት ካልተቀበሉት ውድቅ ሊደረግ እንደሚችል አሊያም ሌላ አማራጭ ስለመኖሩ ከመግለጽ ተቆጥበዋል።