ስጋት ያንዣበበት የኢትዮጵያ ፖለቲካ ትኩሳት

ብስራት ወልደሚካኤል

ኢትዮጵያ ውስጥ ከወትሮ በባሰ መልኩ ውጥረት አንዣብቦበታል። በአገዛዙ ህወሓት/ኢህአዴግ አገዛዝ ህዝቡ ላይ የደረሰውና ዛሬም ያላባራው በደል ተደጋጋፊ በርካታ የመብት ጥያቄዎችን ወልዷል። ይሁን እንጂ ከአገዛዙ እየተሰጠ ያለው ምላሽ የመብት ተማጋችና ጥያቄው ላይ ተሳትፎ ያልነበራቸው ላይ ሳይቀር እየተወሰደ ያለው ርምጃ ወታደራዊ የፀጥታ ኃይል በማሰማራት ማስፈራራት፥ መግደል፥ ማሰር፥ ማሰቃየት ብሎም ከሀገር ማሰደድ ላለፉት 26 ዓመታት የተለመደ አካሄድ ነበር።

ከህዳር 22 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ በተለይ “የአዲስ አበባ የተቀናጀ ማስተር ፕላን” የሚለው የመንግሥት መሪ ዕቅድ ይፋ መደረጉን ተከትሎ በምዕራብ ኢትዮጵያ በተለይም በጊንጪ የአደባባይ ህዝባዊ ተቃውሞ ተጀመረ። በሂደትም ይህ ተቃውሞ መላው ኦሮሚያ ክልልን አዳርሶ የክልሉን አመራሮች ሹም ሽር ድረስ የዘለቀ የፀረ አገዛዝ ህዝባዊ ተቃውሞ ተዛመተ። ገዥው መንግሥትም ለህዝቡ ጥያቄና የፀረ አገዛዝ ተቃውሞ የሰጠው ምላሽ ወታደራዊ ኃይል በመሆኑ ለበርካታ ዜጎች ሞት፥ የአካል መጉደልና ንብረት መውደም ዋነኛ ምክንያት ሆኖ ቀጥሏል።

በተለይ ህዝባዊ ተቃውሞ ተጠናክሮ በቀጠለበት ወቅት የአገዛዙ አስኳል የሆነው የህወሓት እጅ አለበት እየተባለ የሚታመንበትና በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ “በብሔር” ማንነት ላይ ባነጣጠረ ጥቃት ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ የኦሮሚያ ማኅበረሰብ አባላት ከምሥራቅ ኢትዮጵያ ተፈናቅለዋል። ይሄም ተጨማሪ ቅራኔ ፈጥሮ የአገዛዙ አጋር አባላትንም አስቆጥቶ ህዝባዊ ተቃውሞ እንዲአቀጥል ሌላ ተጨማሪ የተቃውሞ ማቀጣጠያ ሆኗል ማለት ይቻላል።

በኦሮሚያ ክልል ያለው ህዝባዊ ተቃውሞ ተጠናክሮ በቀጠለበት ሁኔታ ሐምሌ 5 ቀን 2009 ዓ ም ሌላ ተጨማሪ ህዝባዊ ተቃውሞና ቁጣ በአማራ ክልልም ተጀመረ። በአማራ ክልል ህዝባዊ ተቃውሞ መነሻ የወልቃይት የአማራ ማንነት ጥያቄ ያነገቡ የህዝቡ ወኪል ተደርገው የተመረጡ ኮሚቴ አባላትን ከሚኖሩበት ጎንደርና አካባቢ ባሉ ከተሞች በሌሊት አፈኖ ለመያዝ የተደረገው ሙከራ በአብዛኞቹ ላይ ቢሳካም በተለይም ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ በወሰዱት የአፀፋ መልስና የህወሓት/ኢህአዴግ የኃይል ርምጃ የታፈነውን የህዝቡን ቁጣ ለተቃውሞ እንደ መነሻ ርሾ ሆኖታል። በኋላም ልክ እንደ ኦሮሚያ ክልልም በአማራ ክልልም ህዝባዊ ተቃውሞ ተዛምቶ ክልሉን ከተሞችና ወረዳዎች አዳርሶ ዛሬም እልባት አላገኘም።

በተመሳሳይም በደቡብ ክልል ኮንሶ ወረዳ፤ በቅርቡ ደግሞ በጉራጌ ዞን ተመሳሳይ የፀረ አገዛዝ ህዝባዊ ተቃውሞዎች ተደርገዋል። ይሁን እንጂ መንግሥት ተመሳሳይ ወታደራዊ የኃይል ርምጃ ከመውሰድ ያገደው አልነበረም። በዚህም ከ5 በላይ ዜጎች ሲገደሉ በርካታ ሰላማዊ ዜጎችም የቆሰሉ ሲሆን፤ የንብረት ውድመትንም አስከትሏል። ይህ በእንዲህ እንዳለ መንግሥት ከህዝባዊ ጥያቄዎች መካከል አንዱ የሆነውን የህሊና እና የፖለቲካ እስረኞች ይፈቱ የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ በሚል፤ የተወሰኑ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችን፥ የመብት ተሟጋቾችንና ጋዜጠኞችን ከእስር ለቋል። በርካቶች ግን ዛሬም እስር ቤት እንዳሉና ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ሊለቀቁ እንደሚገባም በቅርቡ ከእስር የተፈቱት፥ የታሳሪ ቤተሰቦችና የመብት ተሟጋቾች ጥያቄ ማቅረባቸው አልቀረም። በመጨረሻም ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በሀገሪቱ የፖለቲካ ቀውስ መኖሩን በማመንና እርሳቸውም የመፍትሄው አካል ለመሆን ሥልጣናቸውን በገዛ ፍቃዳቸው ለመልቀቅ የሥራ መልቀቂያ ማቅረባቸውን ይፋ አደረጉ። በርካታ የህዝቡ ጥያቄዎች ግን ዛሬም መልስ አላገኙም።

በቅርቡ የተወሰኑ የህሊና እና የፖለቲካ እስረኞችን መለቀቅ እና የጠቅላይ ሚኒስትሩን ከሥልጣን ለመልቀቅ መወሰናቸውን ተከትሎ ህዝቡ የፖለቲካ ማሻሻያዎች ይደረጋሉ ብሎ ሲጠብቅ፤ ሚኒስትሮች ምክር ቤትን ጠቅሶ ለቀጣይ 6 ወራት የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጆ፤ ከየካቲት 9 ቀን 2010 ዓ. ም. ጀምሮ ተግባራዊ ተደርጓል። አዋጁም በቅርቡ በህዝብ ተወካዮች እንደሚፀድቅ በመንግሥት ቢነገርም፤ አዋጁ በርካታ የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ከመጣስ በተጨማሪ ህገ መንግሥቱን የሚፃረሩ ድንጋጊዎችን ያዘለ በመሆኑ ለሌላ ጠንካራ ህዝባዊ ተቃውሞና አለመረጋጋት ያመራል በሚል ስጋት ከወዲሁ በሀገር ውስጥና በዓለም ዓቀፍ ተቋማትና ማኀበረሰብ ተቃውሞ ቀርቦበታል።

በሌላ በኩል ተተኪ ዕጩ ጠቅላይ ሚኒስትር ለማቅረብና ለመሾም በገዥው ግንባር ፓርትዎች ሽርጉዱ ቀጥሏል። በዚህም በእቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ይመራ ከነበረው ደኢህዴን/ኢህአዴግ በስተቀር ሶስቱ የግንባሩ አባል ድርጅቶች፤ ህወሓት፥ ኦህዴድ እና ብአዴን ጣጣቸውን የጨረሱ ይምስላሉ።

ህወሓት ዶ/ር ደብረጺዮን ገብረሚካኤልን ሊቀመንበር፥ ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገብረእግዚአብሔር (ሞንጆሪኖ)ምክትል ሊቀመንበር አድርገው መርጧል። እስካሁን ባለው መረጃም የትክግራይ ክልል ምክር ቤት አባል ያልሆኑት ዶ/ር ደብረጺዮን በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የትግራይ ክልል ፕሬዘዳንት ሆነው ቢሾሙም፤ ቀደም ሲል የነበራቸውን የፌደራሉን የኢንፎርሜሽን ኮሚኒኬሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትርነት ሥልጣናቸውን እላስረከቡም።

ኦህዴድ በበኩሉ ቀደም ሲል የድርጅቱ ሊቀመንበር የነበሩትን አቶ ለማ መገርሳን በፓርቲው ዋና ጸሐፊ በነበሩት ዶ/ር አብይ አህመድ ተተክተው፤ የድርጅቱ ምክትል ሊቀመንበርና የኦሮሚያ ክልል ፕሬዘዳንት ሆነው ተሹመዋል። በተለይ ኦህዴድ ቀጣይ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሆኑ በማሰብ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑትን ዶ/ር አብይ አህመድን በዕጩን ለማቅረብ የወሰነ ይመስላል።

ብዙ የተለየ ነገር ይዤ ቀርባለሁ ሲል የነበረውና ሌላኛው የህዝባዊ ተቃውሞ አካባቢ አስተዳደርን የሚመራው ብአዴን ከመሰብሰቡ በስተቀር የአመራር ሹም ሽር ወይም ማሻሻያ ሳያደርግ በነበረበት መቀጠሉን ይፋ አድርጓል። በዚህም መሰረት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን የድርጅቱ ሊቀመንበር፥ የአማራ ክልል ፔሬዘዳንት የሆኑትን አቶ ገዱ አንዳርጋቸውን ምክትል ሊቀመንበር እሆነው በነበሩበት እንዲቀጥሉ መወሰኑን ይፋ አድርጓል።

ሌላኛው የግንባሩ አባል የሆነው ደኢህዴን ይህ እስከተጠናቀረበት ድረስ ስብሰባውን ያልጨረሰ ሲሆን፤ ቀጥዩ የድርጅቱ ሊቀመንበርና ምክትሉ እንዲሁም የደቡብክ ክልል ፕሬዘዳንት ምን ማሻሻያ ወይም ለውጥ ሊኖረው እንደሚችል ለመገመት አስቸጋሪ አድርጎታል።

ሀገሪቱ በበርካታ ህዝባዊ ጥያቄና የፀረ አገዛዝ ተቃውሞ ባየለባትና መደበኛው የሀገሪቱ የህዝብ አስተዳደር በአስቸኳይ አዋጅ ሥር ወደ ወታደራዊ አገዛዝ በተቀየረበት ሁኔታ በዚህ በመጪው ሳምንት ኢህአዴግ አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር ይሾማል ተብሎ ይጠበቃል። በበርካታዎች ግምት ቀጣዩ ጠቅላይ ሚኒስትር ከኦህዴድ ዕጩ ሊሾም እንደሚችል ተጠብቋል። በተለይ የኦህዴድ/ኢህአዴግ ዕጩ የሆኑት ዶ/ር አብይ አህመድ ዓሊ ቀጣዩ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሊሆኑ እንደሚችሉ በርካቶች ግምታቸውን እየሰጡ ይገኛሉ።

ነገር ግን የሀገሪቱ ፖለቲካ በበላይነት የሚዘውረው ህወሓት በአዲሶቹ የኦህዴድ አአመራሮች በሐሳብና በተግባር እየተገዳደሩት፤ ይልቁንም ህዝባዊ ቅቡልነት ማግኘታቸው የበላይነቱን እንደተነጠቀ ስለሚሰማው በተፎካካሪነት ከራሱ ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገብረእግዚአብሔር ነጋን አሊያም ለህወሓት የምንጊዜም ታዛዥ እንደሆኑ የሚነገርላቸውን የብአዴን ሊቀመንበሩን አቶ ደመቀ መኮንን ሐሰንን ዕጩ ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ በማቅረብ የፖለቲካ ጨወታውን ሊቀይረው እንደሚችልም መጠርጠር አይከፋም። ደኢህዴን የህወሓትን የበላይነት ለማስጠበቅ በአጋርነት ለመቆም ዕጩ ተፎካካሪ ካላቀረበ በስተቀር፤ አዲስ ለሚጠበቀው ጠቅላይ ሚኒስትር ዕጩ ያቀርባል ተብሎ አይጠበቅም።

ምንም ሆነ ምን በቀጣይ ከሚጠበቀው አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር በነበረው የሟቹ አቶ መለስ ዜናዊ አሊያም የተሰናባቹን የአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ዓይነት አገዛዝ ማስቀጠል እጅግ አስችጋሪ ነው። ስለሆነም ብዙ ግምት የሚሰጠው ስጋት ያንዣበበትን የሀገሪቱን የፖለቲካ ትኩሳት ለማርገብ አዲሱ ተሿሚ ምን ዓይነት ማሻሻዮችን ያደርጉ ይሆን የሚለው ነው። ምክንያቱም ያለውን ትኩሳት ለማብረድና ሀገሪቱን እና ህዝቡን ከተጋረጠው አደጋ ለመታደግ ከአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ብዙ ይጠበቃልና። ሁሉን አቀፍና አሳታፊ የሆነ የሽግግር መንግሥት ምሥረታን ጨምሮ በርካታ የፖለቲካ ማሻሻዮች የማይደረጉ ከሆነ፤ ባለፉት 3 ዓመታት በሁለትና ሶስት ክልሎች የነበረው የፀረ አገዛዝ ህዝባዊ ተቃውሞ በሌሎችም የሀገሪቱ አካባቢዎች በመዛመት አገዛዙን በህዝባዊ አመፅ ከመገርሰስ በተጨማሪ የሀገሪቱ ደህንነት ላይ አደጋ ሊጋርጥ ይችል ይሆናል። ይህም በቀጣይ አገዛዙ በሚወስዳቸው ርምጃዎች የየተመሰረተ ይሆናል።

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: