በቅርቡ ከእስር ከተፈቱት መካከል ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ እና አቶ አንዱዓለም አራጌን ጨምሮ 11 ሰዎች በድጋሚ ታሰሩ

(ዳጉ ሚዲያ) እሁድ መጋቢት 16 ቀን 2010 ዓ.ም. የአዲስ አበባ ወጣቶች በቅርቡ ከእስር ለተፈቱት ጋዜጠኞች፥ የመብት ተሟጋቾች እና ፖለቲከኞችን “እናመሰግናለን” በሚል በጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ቤተሰብ መኖሪያ ቤት በተዘጋጀ መርሃ ግብር ላይ ተገኝተው ከነበሩት መካከል 11 ያህሉ በፖሊስ ታግተው መቆየታቸው ታውቋል። ፖሊስም ታጋቾቹን ከጋዜጠና ተመስገን ደሳለኝ ቤተሰብ መኖሪያ ቤት በበርካታ የፖሊስ ኃይል በማጀብ በአዲስ አበባ ንፋስ ስልክ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ስር በሚገኘው ጀሞ ፖሊስ ጣቢያ የወሰዷችው ሲሆን፤ ከምሽቱ 4፡30 ሰዓት ላይ ጎተራ ወደ ሚገኘው ፖሊስ መምሪያ ወስደው እንዳሰሯቸው ለማወቅ ተችሏል።

Andualem-Eskindir
አቶ አንዱዓለም አራጌ ኤና ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ

እንደምንጮች መረጃ ከሆነ፤ ለእገታው ምክንያት የሆነው በመርሃ ግብሩ ላይ የገዥው ስርዓት መለያ የሌለበት የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ተሰቅሎ በማየታቸው በተቆጡ የአገዛዙ ፖሊሶች በፈጠሩት አለመግባባት መሆኑ ተጠቁሟል። በተለይም በስፍራው የነበረው መርሃ ግብር ከተጠናቀቀ በኋላ በስፍራው ደርሰው የነበሩ ሁለት ፖሊሶች ሰንደቅ ዓላማውን ከተሰቀለበት በግድ ነጥቀው በመውሰድ ድርጊቱን ስብሰባ አድርጎ በመቁጠር ለምን አላስፈቀዳችሁም በሚል ለድርጊቱ ኃላፊነቱን የሚወስድ አካል ማናገር እንፈልጋለን በማለት ፖሊሶቹ ታዳሚውን ለማስፈራራት ሞክረዋል። ይህንንም ተከትሎ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝም የነበረው መርሃ ግብር የተለመደ የማኀበራዊ ወዳጅነት እንጂ ስብሰባ አይደለም፥ ለማኀበራዊ ወዳጅነት ፈቃድ እያስፈልግም ሲል ምላሽ በመስጠቱ በተለይ ሲያናግረው የነበረውን ፖሊስ እንዳስቆጣ ለማወቅ ተችላል።

በጋዜጠኛው ምላሽ ደስተኛ ያልነበረው ፖሊስ ጉዳዩን በማክረር ኃላፊነቱን የሚወስዱ 3 ሰዎችን ማናገር እንፈልጋለን ወደሚል እልህ ውስጥ መግባቱን ተከትሎ አቶ አንዱዓለም አራጌ ጉዳዩን ለማረጋጋት በሚል ፖሊሱን ለማግባባት ቢሞክርም፤ ፖሊሱ ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል። በመጨረሻም አቶ አንዱዓለም አራጌ ለፖሊሱ ” ችግር አለ ብላችሁ ምታምኑት ነገር ካለ እና ማናገር ከፈለጋችሁ ሁላችንንም ወስዳችሁ ማናገር ትችላላችሁ፤ ከዛ ውጭ በተናጥል ኃላፊነት የሚወስድም ሆነ የሚያናግር የለም” የሚል ምላሽ ይሰጣል።

በተሰጣቸው ምላሽ ደስተኛ እና ፈቃደኛ ያልሆነው ፖሊስ በመርሃ ግብሩ ላይ ከተሳተፉት መካከል በወቅቱ በስፍራው የነበሩትን እንዳይንቀሳቀሱ በማስገደድ፤ በያዘው የፖሊስ መገናኛ ሬዲዮ ወደበላይ አለቆቹ በመደወል በአካባቢው ከፍተኛ ችግር እንዳለ እና ለዚህም በርካታ የፖሊስ ኃይል እንዲታዘዝለት ጥሪ ያስተላልፋል። ከተወሰኑ ደቂቃዎች በኋላም በተሽከርካሪ መኪና ተጭነው የመጡ በርካታ ፖሊሶች የጦር መሳሪያዎቻቸውን በመደገን አካባቢውን በመቆጣጠር በስፍራው በቅርቡ ከእስር ከተፈቱት እና በወቅቱ የ “እናመሰግናለን” ሽልማት መርሃ ግብር ከተጠናቀቀ በኋላ በስፍራው የነበሩትና ከእስር ተለቀው የነበሩ 11 የፖለቲካ እና የህሊና እስረኞች አቶ አንዱዓለም አራጌ፥ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፥ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ፥ ጋዜጠኛ እና ጦማሪ በፈቃዱ ኃይሉ፥ ጦማሪ ማህሌት ፋንታሁን፥ ጦማሪ ዘለዓለም ወርቅአገኘሁ፥ የመብት ተሟጋች ወጣቶች አቶ ስንታየሁ ቸኮል፥ አቶ አዲሱ ጌታነህ፥ ወ/ት ወይንሸት ሞላ፥ አቶ ይድነቃቸው አዲስ እና አቶ ተፈራ ተስፋዬ በድጋሚ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለዋል።

ፖሊስ አግቶ ያሰራቸውን 11 ሰዎች ለምን እንደሆነ እስካሁን በይፋ የሰጠው ማብራሪያም ሆነ ምክንያት የለም። ይሁን እንጂ የታገቱት ጋዜጠኞችና የመብት ተሟጋቾች ታፍነው ተወስደውበት ከነበረው ጀሞ ፖሊስ ጣቢያ ማምሻውን ጎተራ ፊትለፊት ወደሚገኘው የንፋስ ስልክ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ እንደታሰሩ ለማወቅ ተችሏል። ጋዜጠኞቹ እና የመብት ተሟጋቾቹ በታሰሩብት ዕለት ቀደም ሲል በቅርቡ በሀገሪቱ ላለፉት 3 ዓመታት ጀምሮ ያልተቋረጠውን የፀረ ጭቆና አገዛ ህዝባዊ ተቃውሞን ተከትሎ በቅርቡ ከእስር ከተፈቱት በርካታ የፖለቲካና የህሊና እስረኞች ጋር የሰማያዊ ፓርቲ ባዘጋአጀው ተመሳሳይ መርሃ ግብር ላይ ተሳትፈው ካጠናቀቁ በኋላ ተጨማሪ በሌሎች በጎ ፈቃድ ወጣቶች ባዘጋጁት መርሃ ግብርን አጠናቀው ርስ በርስ በመጨዋወት ላይ እያሉ መታሰራቸውን ለማወቅ ተችሏል።

በአሁን ወቅት ሀገሪቱ ለ6 ወራት በሚቆይ የአስቸኳይ አወጅ ስር ሆና በወታደራዊ ዕዝ ቁጥጥር ስር መውደቋ ይታወቃል።

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: