(ዳጉ ሚዲያ) የአርበኞች ግንቦት 7 የነፃነት፥ የዴሞክራሲ እና የፍትህ ንቅናቄ ዋና ጸሐፊ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ከእስር ተፈቱ። አንዳርጋቸው ጽጌ ሰኔ 2006 ዓ.ም. የሚመሩትን ድርጅት ተልዕኮ ለመፈፀም እና ንቅናቄውን በመደበኛነት ወደ ሚመሩበት ኤርትራ በረሃ ለማቅናት ከዱባይ በየመን ሰነዓ ጉዞ ላይ እያሉ በየመን እና በህወሓት-ኢህአዴግ የደህንነት ኃይሎች ታፍነው ከቆዩበት የአራት ዓመታት እስር በኋላ ማክሰኞ ግንቦት 21 ቀን 2010 ዓ.ም. ከእስር ተለቀዋል።
የአቶ አንዳርጋቸውን ከእስር የመፈታት ዜና የሰሙ ወዳጅ ዘደምድ እና አድናቂዎች እንዲሁም በርካታ የአዲስ አበባ እና አካባቢዋ ነዋሪዎች በትውልድ ከተማቸውና ወላጆቻቸው በሚገኙበት መኖሪያ ቤት ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል። በተለይ የአዲስ አበባ ወጣቶች የ17 ግራም ወርቅ የአንገት ሐብል ሸልመዋቸዋል።
ባለትዳርና የሶስት ልጆች አባት የሆኑት አቶ አንዳርጋቸው የእርሳቸውን መፈታት አስመልክቶ አቀባብል ላደርጉላቸውና መልካም ምኞታቸውን ለገለጡላቸው እንዲሁም በሀገር ውስጥና በመላው ዓለም ላሉ ደጋፊዎቻቸውና አድናቂያዎቻቸው ምሥጋና አቅርበዋል። የትግላቸውና እስራቸው ዋነኛ ምክንያትም በሀገሪቱ ያለው የመብት ጥሰትና በሥልጣን ያለው አገዛዝ የሚወስዳቸው ጭካኔያዊ የተሞላባቸው ርምጃቸዎች እንደሆኑ ይታወሳል።
አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በብሔራዊ ቤተመንግሥት
አቶ አንዳርጋቸው ከተፈቱ በኋላ በተለይ ረቡዕ ግንቦት 22 ቀን 2010 ዓ.ም. በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በቤተመንግሥት በተደረገላቸው ግብዣ ተገኝተው በሀገራዊ ጉዳይ ላይ መወያየታቸው የተጠቆመ ሲሆን፤ ሐሙስ ግንቦት 23 ቀን 2010 ዓ.ም. ምሽት ደግሞ ቤተሰቦቻቸው ወደሚገኙበት እንግሊዝ ለንደን ማቅናታቸው ታውቋል። አቶ አንዳርጋቸው ቀደም ሲል የሚመሩት ድርጅት ግንቦት 7 በአዋጅ በአሸባሪነት የተፈረጀ ሲሆን፤ እርሳቸውም በሌሉበት ሁለት ጊዜ የሞት እና ዕድሜ ልክ እስራት ተፈርዶባቸው እንድነበር አይዘነጋም።