(ዳጉሚዲያ) በአባይ ወንዝ ላይ እየተሰራ የሚገኘው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ስመኘው በቀለ ዛሬ ሐምሌ 19 ቀን 2010 ዓ ም ከጠዋቱ 2፡20 ሰዓት አካባቢ አዲስ አበባ በሚገኘው መስቀል አደባባይ በግል የቤት መኪናቸው ውስጥ በጥይት ተገድለው መገኘታቸውን የፌደራል ፖሊስ ዋና ኮሚሽን ዳይሬክተር ጄነራል ዘይኑ ጀማል ይፋ አድርገዋል። ይሁን እንጂ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ድረስ ግድያው እንዴት እና በማን እንደተፈፀመ ያልታወቀ ሲሆን፤ የፌደራል እና የአዲስ አበባ ፖሊስ ምርመራ እያደረጉ መሆኑን ኮሚሽነሩ በመግለጫቸው አስታውቀዋል።
ፎቶ፡ ኢንጂነር ስመኘው በቀለ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ስራ ላይ
እንደፖሊስ መረጃ ከሆነ ኢንጂነሩ ጠዋት አዲስ አበባ በሚገኘው ቢሯቸው ገብተው እንደነበር የገለፅ ሲሆን፤ ከጠዋቱ 2፡20 ሰዓት ላይ ግን መስቀል አደባባይ ከመደበኛው የተሽከርካሪ መንገድ ገባ ብሎ ወጣቶች ስፖርት ወደሚያዘወትሩበት ቅርብ ርቀት በኮድ 3 አ.አ (AA)29722 ቶዮታ ብርማ ቀለም መኪና ውስጥ በአሽከርካሪው ወንበር ላይ እንድተቀመጡ በቀኝ ጆሯቸው በስተኋላ በጥይት ተገድለው መገኘታውን አረጋግጧል። ይህ በእንዲህ እንዳለ በጥይት የተመቱበት ጆሯቸው አካባቢ ደም ሲፈሳቸው እንደነበር፤ እንዲሁም በቀኝ እጃቸው በኩል ኮልት ሽጉጥ መገኘቱን ፖሊስ አስታውቅዋል። ፖሊስም ለምርመራ ይረዱኛል ያላቸውን መረጃዎች ከሰበሰበ በኋላ ለተጨማሪ ምርመራ ከረፋዱ 5፡30 ሰዓት ላይ አስከሬናቸው ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል መወሰዱንም ጨምረው ገልፀዋል። ከግድያው ጋር በተያያዘ መረጃ ይኖራቸዋል በሚል በርካታ ተጠርጣሪዎች እና የአይን እማኞች ወደ ፌደራል ፖሊስ ምርመራ መወሰዳቸውም ታውቋል። የምርመራው ውጤት እንደተጠናቀቀ ለህዝብ ይፋ እንደሚደረግም ኮሚሽነሩ ገልፀዋል።
ፎቶ፡ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሲጠናቀቅ የሚኖረው ገፅታ በከፊል
ኢንጂነሩ ትናንት ሐምሌ 18 ቀን 2010 ዓ ም ከቢቢሲ የአማርኛ ፕሮግራም አጭር ቃለመጠይቅ ሰጥተው እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፤ ህይወታቸው እስካለፈ ድረስ በተለይም ከታህሥሥ 2 ቀን 2003 ዓ ም የታላቁ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ዋና ስራ አስኪያጅ በመሆን እያገለገሉ እንደነበር ታውቋል።