(ዳጉሚዲያ)በኢትዮጵያ ፖለቲካ እና ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ከሟቹ አቶ መለስ ዜናዊ ቀጥሎ ዋነኛ ሰው የነበሩት አቶ በረከት ስምዖን ከመሰረቱት እና ከሚዘውሩት ብአዴን_ኢህአዴግ አርብ ነሐሴ 18 ቀን 2010 ዓ.ም. ታግደዋል። አቶ በረከት ከፓርቲያቸው ማዕከላዊ ከሚቴ አመራር አባልነት የታገዱት አብሯቸው የብአዴን_ኢህአድግ መስራች ከነበረት እና የጥረት ኮርፖሬት ስራ አስፈፃሚ አቶ ታደሰ ካሳ (ታደሰ ጥንቅሹ) ጋር ነው። የአቶ በረከት መታገድ በኢትዮጵያ የለውጥ ምልክት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። ምክንይቱም በሀገሪቱ የፕሬስ ነፃነት አፈና፥ ሐሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ጥሰት እና የመደራጀት መብቶች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ይዘወሩ የነበሩት በአቶ በረከት ስምዖን ነበር። የአቶ በረከት ስንብት የሰሞኑ ዋነኛ መነጋገሪያ የፖለቲካ ጉዳዮች ቀዳሚ ያደረገው ሌላው ጉዳይ ላለፉት 27 ዓመታት ሀገሪቱን በአንባገነንነት እና በጭካኔ ሲመራ የነበረው የኢህአዴግ “አብዮታዊ ዴሞክራሲ” የፖለቲካ ” ርዕዮተ ዓለም” ዋነኛ አሰልጣኝ እና ተንታኝ ቁልፉ ሰው በመሆናቸውም ጭምር ነው። ይሄንንም ተከትሎ የሀገሪቱን ህዝብ ህይወት ኣ የሀገሪቱን ህልውና ያመሰቃቀለው ” አብዮታዊ ዴሞክራሲ” ርዕዮተ ዓለም ግብዓተ መሬት እየተፈፀመ እንደሆነ የገመቱ በርካቶች ናቸው።
በሀገሪቱ ለተፈፀሙ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ጥሰትም በዋነኝነት ከሚወቀሱ ቀዳሚ ሰው ናቸው። ለሀገሪቱ ነፃው ፕሬስ ጋዜጠኞች እስር፥ ስቃይ፥ ስደት እና ለፕሬስ መቀጨጭ እንዲሁም በመንግሥት ቁጥጥር ስር ያሉ የህዝብ መገናኛ ብዙኃን ትክክለኛ መረጃ እንዲትፈን በማድረግ የተሳሳተ መረጃ እንዲሰራጭ በማድረግ ዋነኛ ተጠያቂ ሰው ናቸው።
በአጠቃላይ አቶ በረከት ስምዖን በኢትዮጵያ ፖለቲካ እንደ ተክለቁመናቸው አንድ ሰው ሳይሆኑ እጀ ረጅም የጭቆና እና አፈና አድራጊና ፈጣሪ ከሆኑ ቀዳሚ ሰዎች ቁልፍ ሰው በመሆናቸው፤ እንዳሻቸው በሚዘውሩት ፓርቲያቸው ብአዴን “አሁን ባላቸው ወቅታዊ አቋም የአማራን ህዝብ ጥቅም እንደማያስጠብቁ በመረጋገጡና በጥረት ኮርፖሬት ላይ በሰሩት ጥፋት” በሚል መታገዳቸው ኢትዮጵያ ወደ ዴሞክራሲያዊ ለውጥ እያደረገች ላለው ትግል የራሱ በጎ ጎን እንደሚኖረው እሙን ነው።
በርግጥ አቶ በረከት የተደረገባቸውን እገዳ በመቃወም ላገዳቸው ብአዴን ይፋ ደብዳቤ ፅፈዋል። ለደብዳቤያቸውም ከብአዴን አመራር እና ከአማራ ክልላዊ መንግሥት ቃል አቀባይ ምላሽ ተሰጥቷቸዋል። ሁለቱም ደብዳቤዎች እንደሚከተለው ቀርበዋል።
የአቶ በረከት ስምዖን እና ታደሰ ካሳ ምላሽ:-
ከግራ ወደ ቀኝ አቶ በረከት ስምዖን እና አቶ ታደሰ ካሳ
ይህን ግልፅ ደብዳቤ ለብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ማዕከላዊ ኮሚቴ የምንፅፈው ላለፉት 37 ዓመታት ካታገለን ድርጅት ጋር እሰጥ አገባ ውስጥ ለመግባት ተነሳሽነት መውሰድ አለብን ብለን በማመን አይደለም። ይልቁንም ረዘም ላለ ጊዜ በእኛ ላይ በሚካሄደው ተደጋጋሚ ጥቃትም ሆነ የስም ማጥፋት ዘመቻ ተገፋፍተን በሚዲያ እሰጥ አገባ ውስጥ ላለመግባት ከፍተኛ ጥንቃቄ ስናደርግ ቆይተናል። ይህም ለመናገር የሚያስፈራ ነገር ስላለብን ሳይሆን፣ በመንግሥትና በድርጅት አመራር ደረጃ ያሉ ኃላፊዎች ሕግና ሥርዓት የማስከበር ግዴታቸውን በአግባቡ ይወጣሉ በሚል ተስፋ በትእግስት ማለፍን በመምረጣችን ነው። ነገር ግን ማዕከላዊ ኮሚቴው ሌላ ትልቅና አንገብጋቢ ክልላዊና አገራዊ አጀንዳና ተግባር የጠፋ ይመስል የግለሰቦችን ስም ለማጥፋትና የጥቂት ቂም በቀልተኞችን ድብቅ ፍላጎት ለማሟላት ተባባሪ መሆን መምረጡን በማስተዋላችን ይህን ግልፅ ደብዳቤ ለመፃፍ ተገድደናል፡፡ ምንም እንኳ በእያንዳንዳችን ነባር የብአዴን አመራሮች ላይ የሚካሄደው የስም ማጥፋትና የጥቃት ዘመቻ የተለያየ ቢሆንም፣ ከነሐሴ 18/ 2010 ዓ.ም ጀምሮ የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽ/ቤትን ዋቢ በማድረግ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃንና፣ ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ በመሠራጨት ላይ የሚገኘው “ዜና” ሁለታችንን ስለሚመለከት ግልፅ ደብዳቤውን በጋራ ማቅረብን መርጠናል፡፡ ሰፊው የአማራ ህዝብም ሆነ መላ የአገራችን ህዝቦች የብአዴን አመራር በእኛ ላይ የሚያካሂደውን መሰረተ ቢስ ዘመቻ በአግባቡ ይገነዘቡት ዘንድም በዚሀ ግልፅ ደብዳቤ እንጠይቃለን።
የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ማዕከላዊ ኮሚቴ ከነሐሴ 17 እስከ 18 ድረስ ያካሄደውን መደበኛ ስብሰባ መጠናቀቅን ምክንያት በማድረግ፣ ነሐሴ 18 ማታ በሁለት ሰዓት የዜና እወጃ ላይ በአማራ መገናኛ ብዙሃንና በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን “አቶ በረከት ስሞዖንና አቶ ታደሠ ካሣ በጥረት ውስጥ በፈጠሩት ችግር በመስከረም አጋማሽ ላይ እስከሚካሄደው ድርጅታዊ ጉባኤ ድረስ ከብአዴን ማእከላዊ ኮሚቴ እንዲታገዱ ተወስኗል” የሚል መግለጫ በሰበር ዜና ሰምተናል፡፡ ሁለታችንም በየቤታችን ከቤተሰቦቻችን ጋር ቁጭ ብለን “ሰበር ዜናውን አዳምጠናል፡፡ አንድ ፖለቲካዊ ድርጅት በውስጣዊ አሠራሩ መሠረት፣ በአባላቱ ላይ የሚያስተላልፈው የቅጣት ውሳኔ እንዴት ለመላ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ሰበር ዜና እንደሚሆን ግልፅ አይደለም፡፡ ምናልባት ማእከላዊ ኮሚቴ ዜናውን በማስጮህ ለማግኘት የከጀለው የትርፍ ስሌት ሊኖር ይችል ይሆናል እንጅ። እኛ ከማእከላዊ ኮሚቴው እንድንታገድ የተላለፈውና ነባር የማእከላዊ ኮሚቴ አባላትን በድምፅ አልባ ለማሳተፍ ወጥቶ የነበረውን መመሪያ የመሻር ውሳኔ በአንድ ላይ የመግለፁ አስፈላጊነትም የትርፍ ስሌቱ ማሳያ ሊሆን ይችላል፡፡
በድርጅታችን አሠራርና የቆየ ባህል መሠረት አንድ አባል በሌለበት ወይም ራሱን ለመከላከል በማይችልበት ሁኔታ አስተዳደራዊ እርምጃ አይወሰድበትም፡፡ በአባሉ ላይ የቀረበ ሂስ ወይም የተሰጠ አስተያየት ካለ ለሌላ አካል ወይም አባላት ከመገለፁ በፊት ራሱ ባለጉዳዩ እንዲያውቀውና መልስም እንዲሰጥበት ይደረጋል፡፡ የብአዴን ማእከላዊ ኮሚቴ ተጠይቀን መልስ ባልሰጠንበት ክስ መበየንና እንደ ማእከላዊ ኮሚቴ አባልነታችን ውሳኔ በቀጥታ እንዲደርሰን ማድረግ ሲገባው ይህን አለማድረጉም ግልፅ አይደለም። በስብሰባው መገኘት ነበረባቸው የሚል መከራከሪያ ሊቀርብ እንደሚችል እንገምታለን፡፡ ያልተገኘንበት ምክንያት ግን ለማእከለዊ ኮሚቴው ስውር አይደለም፡፡ ታደሰ ጥሪው ቢላክለትም አልደረሰውም። በረከት ከብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ፅ/ቤት ነሐሴ 9 ቀን 2010 በተላከ ኢሜይል የስብሰባው ጥሪ ደርሶታል። ጥሪው እንደደረሰው ለጊዜው የፅ/ቤት ሃላፊ ለሆኑት ለአቶ ጌታቸው ጀንበርና መልእክቱን ለላኩት ለአቶ ዘለቀ አንሉ በስብሰባው ቢሳተፍ ደስ እንደሚለው፣ ነገር ግን በክልሉ በሌለበት ጭምር እየተካሄደ ባለው ተደጋጋሚ የጥቃት ሙከራ ሰለባ መሆን እንደማይፈልግና አመራሩ የፀጥታ ዋስትና ከሰጠው መምጣት እንደሚችል አሳውቋል። የፅህፈት ቤቱ ሃላፊዎችም ችግሩ ተጨባጭ እንደሆነ እንደሚቀበሉና መፍትሄ እንደሌላቸው ገልፀውለታል። “የመጣው ቢመጣ መገኘት አለባችሁ፣ እኛ /እኔ ሃላፊነቱን እወስዳለሁ” የሚል ደፋር በሌለበት ሁኔታ፣ እንኳን እኛ ከወታደራዊ ሳይንስና ጥበብ ጋር ትውውቅ ያለን ሰዎች፣ ሌላውም ቢሆን አደጋን ከሩቁ ተመልክቶ ለማስወገድ ይሞክራል እንጂ፣ ራሱን በጀብደኝነት አሳልፎ የሚሰጥ አይመስለንም።
ማእከላዊ ኮሚቴዉ እኛን ለማገዱ የሰጣቸው ምክንያቶች ሁለት ናቸው፡፡ ዓርብ ማታ “ጥረት ውስጥ በፈጠሩት ችግር” በማለት መግለጫ ሰጥቷል። ቅዳሜ ደግሞ “አሁን ባላቸው ወቅታዊ አቋም የአማራን ሕዝብ ጥቅም እንደማያስጠብቁ በመረጋገጡ” የሚል ፍረጃ ወይም ውንጀላ ታክሎበታል፡፡ እድሜ ልካችንን ግንባራችንን ሳናጥፍ ለኢትዮጵያና ለአማራ ሕዝቦች ጥቅም መከበር ስንታገል መኖራችንን መላ የብአዴን አባላትና የአማራ ሕዝብ አሳምረው ስለሚያውቁት በ”ሰበር ዜና” ማስተባበል የሚቻል አይደለም፡፡ የእኛ ወቅታዊ አቋም የሚባለው ጉዳይ ከሆነ ደግሞ ሰሞነኛ ሆኖ እንደምንሰማው “የለውጡ ደጋፊና፣ የለውጡ አደናቃፊ” ዲስኩር ከሆነ፤ “ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ” ነው፡፡ ማን አሁን ለመጣው ለውጥ እንደታገለና፣ ማን ደግሞ ሲፃረር እንደነበረ፣ የብአዴን የማእከላዊ ኮሚቴ አባላት ብቻ ሳይሆን፣ መላ የብአዴን አባላት፣ እንዲሁም በካድሬ ስልጠና ያለፉ፣ በኢሕአዴግ ሥራ አስፈፃሚ፣ በኢሕአዴግ ምክር ቤትና በኢሕአዴግ ጉባኤዎች የተሳተፉ የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች በሙሉ በይፋ ያውቁታል፡፡
እጅግ ዘግይቶም ቢሆን “የድርጅታችንና የስርአቱ ችግሮች እንደተባባሱና ተሃድሶ እንደሚያስፈልግ ከ2002 ዓ.ም ክረምት ጀምሮ ሲነሳ የነበረውን ሃሳብ በወቅቱ ብንቀበል ኖሮ፣ የአሁኑን ቀውስ ማስቀረት ይቻል ነበር” በሚል በሙሉ ድምፅ አቋም የያዘ ማእከላዊ ኮሚቴ፣ ዛሬ በረከትና ታደሰ የለውጡ አደናቃፊዎች ናቸው የሚል አቋም መያዙ “ይብላኝ!” ከማለት በቀር ሌላ ምን ሊባል ይችላል፡፡ ህዝቡን ያስመረሩት የመልካም አስተዳደርና የሙስና ችግሮች ካልተፈቱ፣ የወጣቱን የሥራ ጥያቄ ተረባርበን ካልፈታን፣ ዐመፅ አይቀርልንም፣ 2008 ዓ.ምን በሰላም ማለፍ አይቻልም፤ ለሕዝቡ ቃል እየገባን በተግባር ግን መመለስ አልቻልንም፣ ሰነፍ ተማሪ ከአንዴ፣ ቢበዛ ከሁለት ጊዜ በላይ እንዲደግም እድል እንደማይሰጠው ሁሉ፣ ኢሕአዴግ ሁለት ጊዜ እድል ተሰጥቶታል። ፈጥነን ካላረምነው ግን ሌላ እድል አይሰጠንም….. የሚሉ ሃሳቦችን ስናነሳ፣ “ሟርተኞች፣ ሕዝቡ ከጎናችን ነው፣ የሌለ ነገር እየተናገራችሁ ድርጅታችንን አታጥላሉ፣ ለተቃዋሚዎች መናገሪያ አጀንዳ አትስጡብን” እያሉ ለውጥ ፈላጊዎችን በማሸማቀቅ ሻምፒዮን የነበሩ ግለሰቦች፣ አሁን ደርሰው ራሳቸውን ምርጥ የለውጥ ኃይል እያስመሰሉ እኛን የለውጥ አደናቃፊ ለማለት ከቶም የሞራል ብቃት አላቸው ብለን አናምንም። ወቅታዊ አቋማችን ግልፅ ነው፡፡ ኢሕአዴግ ሪፎርም መካሄድ አለበት ብሎ በሙሉ ድምፅ ወስኗል። እኛ የዚህ ሪፎርም አካል ብቻ ሳንሆን ግንባር ቀደም አራማጆች እንደነበርን ጠንቅቃችሁ ታውቃላችሁ።
በድርጅቱ ሊቀመንበር ለመጀመሪያ ጊዜ “የአማራን ህዝብ ጥቅም አያስከብሩም” የሚል ስሞታ በነባሮች ላይ የቀረበው ሚያዝያ 2010 ዓ.ም ላይ በተካሄደው የብአዴን ኮንፈረንስ ላይ ነው። ሊቀ መንበሩ “አሁን ያለው የብአዴን አመራር የሙት ልጅ (Orphan) ነው፣ ነባሮቹ አያግዙትም። ከመለስ ህልፈት በኋላ ምክትል የነበረው እንደተካው ሁሉ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ከኢሕአዴግ ሊቀመንበርነት ሲለቅ መተካት የነበረብኝ እኔ ነበርኩ፡፡ ነገር ግን ነባሩ እኔን መደገፍ ሲገባው እድሉ ለኦሮሞ ሊሰጥ ይገባዋል የሚል አቋም በማራመዱ ጠቅላይ ሚኒስትር የመሆን እድሌ እንዲዘጋ አድርጓል። ይህ ብቻ ሳይሆን ቀደም ብሎም አቶ አዲሱ በመተካካት ሲለቅ እኔ ሲኒየሩ እያለሁ አቶ ኃይለማርያም ምክትል እንዲሆን ተደረገ፡፡ ይህ ሁሉ እኔን በግል ባይፈልጉኝ እንኳ ለአማራ ባለማሰባቸውና አማራ ወደ ስልጣን እንዲመጣ ስለማይፈልጉ የሆነ ነው…” ማለቱን በምስልም በድምፅም የተቀረፀ ማስረጃ በድርጅቱ ጽ/ቤት ይገኛል። በእኛ እምነት በአንዲት የፌዴራል የስልጣን ወንበር የሚቀመጥ ማንኛውም ሰው የመላው የአገራችን ህዝቦች ወኪልና አገልጋይ እንጅ የአንድ ብሄር ብቻ ባለመሆኑ እጩነት በብቃት እንጅ በብሄር መለካት የለበትም ብለን አቋማችንን ገልፀናል። በበኩላችን አሁንም ቢሆን የአማራ ህዝብ ተጠቃሚነት ክልሉን ለመለወጥ በሚደረግ ርብርብ እንጅ አንድን ወንበር የሚይዝ ሰው በመምረጥና ባለመምረጥ ሊለካ አይገባውም ብለን እናምናለን።
እጅግ በጣም የገረመን ሌላው ነገር “ጥረት ውስጥ በፈጠሩት ችግር” በሚል አማርኛ ያቀረባችሁት ምክንያት ነው። “አያ ጅቦ ሳታመኻኝ ብላኝ” እንዳለችው ፍጥረት፣ በበኩላችን በዚሁ ቅኝት ያለጥፋታችን ተጠያቂነትን ልንቀበል አንችልም። ከሁሉ በፊት “በፈጠሩት ችግር” ምን ማለት ነው? ይህ አጠቃላይ ድምዳሜ ነው? ማስረጃ ነው? ማስፈራሪያ ነው? እስኪ በቅጡ አብራሩትና አገር ይስማው። ችግር ፈጠራችሁ ከተባልን በምንድነው? በስንፍና ወይስ በስርቆት ችግር ፈጠርን? በስንፍና እንዳትሉን የስራ ባህላችንን ታውቁታላችሁ፡፡ ድርጅት፣ መንግሥትና ሕዝብ የሰጠንን ኃላፊነት ሌት ተቀን በመሥራት ከውጤት ላይ ውጤት ስናመጣ እንጂ በታካችነት አንታወቅም። እኛ የራሳችንና የቤተሰባችን ጥቅም ስናሳድድ አልኖርንም፡፡ በየጊዜው በንባብ፣ ልምዶቻችንን በመቀመርና ለአራት አሥርት አመታት ሌት ተቀን በመልፋት የአመራር ብቃታችንን ለማሳደግ ስንጥር እንጂ፣ በሥራቸውም ሆነ በራሳቸው ላይ አንድም ለውጥ ሳያመጡ፣ ግልፅ ባልሆነ መስፈርት ከአንድ ኃላፊነት ወደ ሌላ ኃላፊነት ሲንጠላጠሉ እንደኖሩት ደካሞች እንዳልሆንን የማእከላዊ ኮሚቴውም ሆነ መላ የብአዴን አባላት አሳምረው ያውቁታል፡፡
ሁሌም “በሥራ አናማችሁም” ስትሉን ኖራችኋል። ችግር የምትሉት ስርቆት ከሆነም “ የብአዴን ነባሮች እጃችሁ ንፁህ በመሆኑ እንኮራባችኋለን” ስትሉን ኖራችኋልና ይህን ቃላችሁን ካጠፋችሁ ቀድማችሁ የምታፍሩት እናንተው ራሳችሁ መሆናችሁ አያጠያያቅም፡፡ በተጠናወታችሁ የማላከክና የውንጀላ አባዜ በድፍረት የምትገፉበት ከሆነም፣ አስራ ምናምን ሚሊዮን ዶላር ሰርቆ፣ በፍርድ ቤት ተረጋገጦበት፣ የእድሜውን አንድ ስድስተኛ በእስር ቤት የጨረሰን ወንጀለኛ፣ እንዲሸለም፣ ካባ ለብሶ እንዲሽሞነሞን አመራር ሰጭዎች ያሉበት ማእከላዊ ኮሚቴ ሌብነትን ይጠየፋል ብለን ለማሰብ እንደምንቸገር ልታውቁልን ይገባል። የጥረትን ገንዘብ ዘርፋችኋል፣ ሀብት አባክናችኋል እያላችሁ ከሆነም ማጣራቱ ቀላል ነው፡፡ የጥረት ሀብት በግልፅ የሚታይና በየአመቱም በውጭ ኦዲተር እየተመረመረ በሰነድ የሚገኝ በመሆኑ አስቸጋሪ አይደለም፡፡ የተሰጠንን ኃላፊነት በታማኝነት ከመፈፀምና አቅማችንን ሳንሰስት ከመረባረብ በቀር ሌላ ነገር አናውቅምና አለን የምትሉትን ይዛችሁ በህግ ፊት እንሟገት።
ሁለታችንም የጥረት መሥራች አባላት ነን፡፡ በረከት ከምሥረታው ወቅት ጀምሮ እስከ ሚያዝያ 2009 ዓ.ም ድረስ በቦርድ ሊቀመንበርነት ጥረትን መርቷል፡፡ ታደሰ ደግሞ ከህዳር 2ዐዐ1 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ሚያዝያ 2010 ድረስ በምክትልና በዋና ሥራ አስፈፃሚነት ጥረትን ሲመራ ቆይቷል፡፡ ጥረት በተለያዩ ውጣ ውረዶች አልፎ፣ በተለይም የለውጥ እንቅስቃሴ ከጀመረበት ከ2ዐዐ2 ዓ.ም ጀምሮ ፈጣን እድገት አስመዝግቧል፡፡ ጥረት ሲመሠረት ከድርጅቱ የተሰጠው መነሻ ሀብት ሃያ ሚሊዮን ብርና 31 አሮጌ ተሽከርካሪዎች ብቻ ናቸው፡፡ ለተኩን አመራሮች ያስረከብነው ከ11 ቢሊዮን ብር በላይ ሀብት ያላቸው 20 ኩባንያዎችን ነው፡፡ ጥረትን የመራነው ከእያንዳንዱ እንቅስቃሴያችን እየተማርን ነው፡፡ የኢንቨስትመንትና ቢዝነስ አመራር እውቀትና ልምድ ደካማ በሆነበት አገር ውስጥ ሆነን፣ የጥረት አመራር የተለየ ምጥቀት የሚጠበቅበት አይደለም፡፡ ከፕሮጄክት አመራረጥ ጀምሮ ትግበራ ድረስ ብዙ መደነቃቀፎች ያጋጥማሉ፡፡ በሸርክና አፈፃፀም ላይ ስኬትም ጉድለትም ይከሰታል፡፡ መክሰርና ማትረፍ የቢዝነሱ አለም ክስተቶች ናቸው፡፡ ጥረትን ስንመራ እነዚህና መሰል ችግሮች አልታዩም ብለን አናውቅም፣ ይልቁንም በየጊዜው ጉድለቶቻችንን እየገመገምንና እያስተካከልን፣ ውጤታማ የአሠራር ስርዓት፣ ተቋማዊ ፖሊሲዎች፣ ወቅታዊ እቅዶችና የአፈፃፀም መመሪያዎችን እያወጣን በመጓዝ፣ በክልሉ ውስጥ ፈጣን እድገት በማስመዝገብ አርአያ የሆነ ኮርፖሬት ፈጥረናል፡፡ በርግጥ የክልሉ ሕዝብ ከሚጠብቀውና ከሚገባው አኳያ የሠራነው ብዙ ነው ብለን አንመፃደቅም፡፡ ከብዙ ውስጣዊና ውጫዊ እንቅፋቶች ጋር እየታገልን በክልሉ ኢኮኖሚያዊ ልማት ላይ አስተዋኦ አድርገናል፡፡
የመንግሥት ግዴታቸውን በአግባቡ የሚወጡ፣ ጥሩ ግብርና ብድር ከፋዮች የሆኑ ኩባንያዎችን አደራጅተናል፡፡ ከመንግሥት የገዛናቸውን አክሳሪ የነበሩ ኩባንያዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ አትራፊነት መቀየር ችለናል፡፡ በአመራርና በአፈፃፀም ላይ የነበሩና ካሁን በፊት ያልታዩ አዳዲስ ጉድለቶች አሉ ከተባሉ፣ ሂስ ለመቀበልና አስፈላጊውን እርምት ለማድረግ አንቸገርም።
እግረ መንገዳችንን ግን አንዳንድ ጥያቄዎችን እናንሳ፡፡ የክልሉ ቃል አቀባይ ለአማራ ብዙሐን መገናኛ መግለጫ ሲሰጡ፣ “የብአዴን አመራር በተለያየ ጊዜ ተጣርተው በቀረቡለት የኪራይ ሰብሳቢነትና የሙስና ችግሮች ላይ የቅጣት ውሳኔ ሲሰጥ ቆይቷል፣ የአሁኑም የዚሁ አካል ነው” ሲሉ ሰምተናል፡፡ /ቃል በቃል አይደለም የጠቀስነው/ ከዚህ በፊት በጥረት አመራሮች ላይ የቀረበው ጥቆማና የአጣሪ ኮሚቴዎች ሪፖርት ታደሰና ሌሎች የማኔጅመንት አባላትን እንጂ በረከትን የሚመለከት አልነበረም፡፡ የማኔጅመንቱ አባላት በወቅቱ መልስ ሰጥተው፣ ማእከላዊ ኮሚቴውም ውሳኔ ሰጥቶበት ያለፈ እንደነበር ይታወቃል፡፡ በበረከት ላይ ምንድን ነው ተጣርቶ የቀረበው አዲስ ጥፋት? ተጣርቶ የቀረበ ካለ በረከት ሳይጠየቅና ማእከላዊ ኮሚቴው የአጣሪዎችንና የተጠርጣሪውን ግራ ቀኝ ሃሳብ ሳይሰማ እንዴት በአዳፍኔ ይፈረዳል? ይህ በማእከላዊ ኮሚቴው ውስጥ ያጠላው የቂም በቀል፣ የጥላቻና የዘረኝነት አዚም፣ ምክንያታዊ የሆኑ አስተሳሰቦችን ማራመድ ለሚፈልጉ የማይመች እንደሆነ ከማመልከት በስተቀር ሌላ ትርጉም የለውም።
ማእከላዊ ኮሚቴው እኛን ከማእከላዊ ኮሚቴ አባልነት ለማገድ ምን አስፈለገው? ምንስ አስቸኮለው? የሚለው ሌላው መልስ የሚሻ ጥያቄ ነው፡፡ ከሦስት አመት በፊት በተካሄደው የብአዴን 11ኛ ድርጅታዊ ጉባኤ የማእከላዊ ኮሚቴ ሆነን መሥራት አንፈልግም እያልን፣ አባላት ፍላጎታችንን በመጋፋት እንደመረጡንና፣ ሳንፈልግ ብንመረጥም አንሠራም ብለን ስናንገራግር ቆይተን፣ የተሃድሶው መጀመር ተስፋ ስለፈጠረልን ግለሂስ ወስደን መመለሳችን ይታወቃል፡፡ መስከረም ይካሄዳል በሚባለው ጉባኤ በማእከላዊ ኮሚቴ አባልነት ለመመረጥ ፍላጎቱም፣ ዝግጁነቱም እንደሌለን ሁሉም የማእከላዊ ኮሚቴ አባል ያውቃል፡፡ አንድ ወር መታገስ ለምን ተሳነው? ቃል አቀባዩ የነገሩን አመራሩ ብአዴንን ለማልበስ የሚፈልገው አዲስ ልብስ፣ የቂም በቀል፣ የጥላቻና የዘረኝነት፣ ነፃ አቋም የሚይዙ ነባርም ሆነ አዳዲስ አባላቱን የማጥቃት፣ የማሸማቀቅና የማግለል ሸማ መሆኑን ከማመልከት በቀር ሌላ ምን ትርጉም ሊሰጠው ይችላል።
ኤርትራ በመመሸግ ስርአቱን በትጥቅ ሲታገሉ ከነበሩ ኃይሎች ጋር በይቅርታና በፍቅር በመተሳሰር፣ በሰላማዊ መንገድ አብሮ ለመሥራት የተስማማ አመራር፣ በድሉም ሆነ በችግሩ አብረውት ሲታገሉና ሲጓዙ የነበሩ ጓዶቹን ለምን ፍቅር ይነፍጋል? የብሔራዊ ማንነት መመዘኛ፣ ግለሰቡ የተገነባበት ሥነልቦና ሳይሆን የደም ሐረጉ ከየት ይመዘዛል የሚለውን አድርጎ የሚወስድ አመራር ለአማራ ክልልም ሆነ ለኢትዮጵያ ይበጃል ብለን አናምንም። ከኤርትራ ከመጡት ቤተሰቦቹ ጎንደር ከተማ ላይ ተወልዶ፣ በጎንደሬ ስነልቦና ተገንብቶ ያደገውን በረከት፣ ከእናትና አባትህ የወሰድከው ደም ኤርትራዊ ስለሆነ አማራ አይደለህም፣ የአማራ ሕዝብን አትወክልም፣ የአማራ ድርጅትን መምራት አትችልም ማለት አሁን ያለው የብአዴን አመራር ከአስተዋዩና በዘር እየለየ ማፈናቀልን ከማያውቀው የአማራ ህዝብ አኩሪ ባህልና ታሪክ ምን ያህል እንዳፈነገጠ የሚያስገነዝብ ነው። ኮረም አካባቢ የተወለደውና በወሎየነት ስነልቦና ያደገውን ታደሰ፣ ወላጆችህ የአማራ፣ የአገውና የትግራይ ደም ቅልቅል ስላለባቸው አማራ አይደለህም የሚል አስተሳሰብም ተመሳሳይ ስህተት ነው።
እኛ ከታዳጊነት እስከ ጎልማሳነት እድሜ የኢትዮጵያ ህዝቦች የሚጠቀሙና የሚከበሩበት ሥርዓት እንዲገነባ ስንታገል ቆይተን፣ እነሆ አዛውንቶች መሆን ጀምረናል፡፡ ስንታገል የኖርነው ትግሉ የሚጠይቀውን ሁሉንም ዓይነት መስዋዕትነት በመክፈል ዓላማችንን ለማሳካት ነው፡፡ ለሥልጣን፣ ለግል ኑሮ መደላደል አልታገልነም። ሥልጣንና ከሥልጣን የሚገኝ ጥቅም አያማልለንም፡፡ ከተመክሮና ከሥራ ብቃት አኳያ ከመሥራቾችና ከእኛ ከነባር አመራሮች ያነሰ ደረጃ ላይ የነበሩትን አስቀድመን ወደ ሥልጣን በማውጣት እንጂ፣ ለሥልጣን በመንሰፍሰፍ አንታወቅም፡፡ በየጉባኤው ለማእከላዊ ኮሚቴ አባልነት ስንመረጥ የነበረውም፣ አባላት ይመሩናል ብሎ ስለአመነብን እንጂ፣ በሎቢ ወይም በኔትወርክ እንዳልነበረ ታሪካችን ይመሰክራል፡፡ በትግል ላይ በቆየንባቸው አርባ ዓመታት የሚቆጨን መጥፎ ሥራ አልሠራንም፡፡ የእኛም ሆነ የኢሕዴን/ብአዴን ነባር ታጋዮች ታሪክ፣ ውስጠ ድርጅት ፀረ ዴሞክራሲን፣ መርህ አልባ ግንኙነትን፣ ዘረኝነትን አምርሮ በመታገል የደመቀ ነው። እንደዚህ ዓይነት ጉድለቶችን በታገልን ቁጥርም በተለያየ ጊዜ ስም ማጥፋት፣ ዛቻ፣ አልፎ ተርፎም እስራት ደርሶብናል፡፡ ዛሬም ዝምታ አይበጅም ብለን፣ ሐቁን በይፋ መናገር ስንጀምር፣ አንዳንድ ፅንፈኛ የብአዴን ማእከላዊ ኮሚቴ አባላት በተለያዩ ርምጃዎች ሊበቀሉን እንደሚነሱ ለመገመት አይከብደንም። ነገር ግን በማናቸውም ዓይነት ርምጃ እንደማንበረከክ ለማረጋገጥ እንወዳለን፡፡
በመድረክ የተናገርነውንና አምነንበትን የያዝነውን አቋም፣ በማህበራዊ ሚዲያ ወይም በሌላ መንገድ በሚሰነዘርብን ማስፈራሪያ የምንለዋውጥ ድኩማን አይደለንም፡፡ እንዳንዶች “እንዳያልፉት የለም”፣ “ያልተንበረከክነው” የመሳሰሉትን ዘመን ተሻጋሪ የፅናት መዝሙሮቻችን ጊዜ ያለፈባቸው ቢሏቸውም፤ ዛሬም እንደ ትናንቱ ጊዜያዊ ፈተናዎችን በፅናት አልፎ፣ በደሙ በላቡ ደማቅ ታሪክ የፃፈው ትውልድ አካላት ነን፡፡ ጥቂቶች ሆነን ለአንዳችም ፈተና ሳንምበረከክ ሚሊዮኖችን ማፍራት የሚችሉ ቆራጥ ታጋዮችን አደራ የተቀበልን ታጋዮች ነን፡፡ ብዙ ምርጥ ጓዶቻችንን ቀብረን፣ በእድል ተርፈን፣ ትርፍ ሕይወት የምንኖር፣ የስልጣንና የሀብት ጉጉት የሌለን ሰዎች ነን፡፡ በዚህ ወቅት የሚያሳስበንና እንቅልፍ ነስቶ የሚያሳድረን ዋነኛ ጉዳይ የብአዴን መሪዎች አካሄድ ከክልሉ አልፎ በኢትዮጵያ ላይ ሊያስከትል የሚችለው መዘዝ ነው። የብአዴን መሪዎችም ሆኑ አባላቱ ይህን ልብ ብለው እንዲያጤኑትና ይህን ታላቅ ህዝብ ወደጥፋት እንዳያመሩት ከአደራ ጭምር እናሳስባለን። በበኩላችን ክልላችንና አገራችን ሃላፊነት በጎደለው መንገድ ሳይሆን በተጀመረው መልካም አቅጣጫ እንዲጓዙ የምንችለውን በጎ አስተዋፅኦ ለማድረግ ምንጊዜም ቢሆን ዝግጁዎች ነን። ችግሮች በመወጋገዘ ሳይሆነ በነፃና ገንቢ ሙግት እየተለዩ በመግባባት ሊፈቱ ይገባል ብለን እናምናለን። ስለሆነም በእኛና በማዕከላዊ ኮሚቴው መካከል ባለው ልዩነት ላይ በየትኛውም የመገናኛ ብዙሃን ቀርበን ከጠቅላላው አመራርም ሆነ ከሚወክላቸው ግለሰቦች ጋር ለመከራከር እና በህዝብ ብይን ለመዳኘት ዛሬም እንደወትሮው ዝግጁዎች መሆናችንን ለመግለፅ እንወዳለን።
የብአዴን እና የአማራ ክልላዊ መንግሥት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን:-
አቶ ንጉሱ ጥላሁን
ሰሞኑን የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ አቶ በርከትን እና አቶ ታደሰን ከማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነታቸው ማገዱን ተከትሎ አቶ በረከት ለተለያዩ ሚዲያዎች ውሳኔው:-
=> በስብሰባው ለመታደም ዋስትና ስላልተሰጠኝ መገኘት አልቻልኩም፣
=> ውሳኔው መሰረተ ቢስ ነው፣
=> የኤርትራ መንግስት እጅ እና ፍላጎት ስለላበት በኤርትራ መንግስት ትዕዛዝ የተፈፀመ ነው፤ እኔ እርምጃ የተወሰደብኝ ኤርትራዊ ዘር ስላለኝ ነው፣
=> አቶ ደመቀ ጠቅላይ ሚንስትር እንዳይሆን ስለታገልኩት በቂም ነው፣
=> እኔ ከኦሮሞ አንድ አመራር ወደ ሀላፊነት(ጠቅላይ ሚንስትርነት)እንዲመጣ ፍላጎት ነበረኝ ታግያለሁም፣
=> የአማራ አመራር አቅም የሌለው በመሆኑ የወጣቱን ጥያቄ ስላልመለሰ አቅጣጫ ለማሳት ከሱዳን፣ ከትግራይ እና ከአፋር እያጋጨ ነው፣ ሲሉ ብአዴንን በመክሰስ እና ማንንም ሊያሳምንልኝ ይችላል ያሉትን ሁሉ ጠጠር በመወርወር ላይ ናቸው ፡ ፡
===
ይህንን ሰምተን እና እዳምጠን አቶ በረከትን በዕድሜያቸው አክብረን እውነትን ሲያዛቡ እና በተንኮል መንገዳቸው ሲነጉዱ ለግንዛቤ ይሆን ዘንድ ጥቂት ነገር ማለት ፈለግን ::
===
አቶ በረከት የጠየቁት ዋስትና የአማራ ወጣቶች እንዳያጠቋቸው በመፍራት እንደሆነ ገልፀዋል :: እሳቸውን የመሰለ አድራጊ ፈጣሪ፣ የፈለጉትን አንጋሽ እና አውራጅ ሰው ወደ ዋስትና ጠያቂነት ሲለወጥ ዋስትናውን ከመጠየቅ ለምን ወጣቱ ይህንን አለ፤ ምንስ አጠፋሁ ? ብሎ ራስን መመርመር የሚበጅ ስለመሆኑ እሳቸውን መምከር “ልጅ ለእናቷ ምጥ አስተማረች ” ስለሚሆን እንተወው:: ግን ግን በየወረዳው መድረክ ፈጥረን ባወያየንባቸው መድረኮች ሁሉ ወጣቱ ” በረከት የአማራን መብት አስረግጧል፣ ህዝቡን አስቀጥቅጧል፣ አማራን አንገቱን እንዲደፋ አድርጏል … ወዘተ “ብሎ ሲሞግተን እኛም ወጣቱን ስንመክር የሚወርድብንን ትችት ቢያዩት አቶ በረከት አመራሩን ባልኮነኑ እንላለን::
===
ውሳኔውን በተመለከተ አቶ በረከት መሰረተ ቢስ ነው አሉት እንጂ እኛ ደግሞ ብአዴንም ሆነ አመራሩ መወቀስ ካለበት ውሳኔውን በማዘግየቱ ን እና ከልክ ያለፈ ትዕግስት ማሳየቱ ነው:: አቶ በረከት ማዕከላዊ ኮሚቴው ስለ ክልሉ ህዝብ ተጠቃሚነት እንዳይወያይ በማድረግ የንትርክ እና የጭቅጭቅ ኮሚቴ ካደረጉት እኮ ከአምስት አመታት በላይ ሆኗቸዋል:: በብአዴን ውስጥ ብቃት ያለው አመራር እንዳይወጣ እና የአማራ ህዝብ ጥያቄ በአግባቡ እንዳይነስ ትንሽ ሀሳብ ብልጭ ያደረገን ሰው ከሌሎች ጋር ሆነው “ትምክህተኛ፣ ነፍጠኛ” በማለት አጎብዳጅ እና ተላላኪ ሆነን እንድንኖር ታግለዋል:: እሳቸውውን የታገሉትን ህይወታቸው እንዲመሰቃቀልም ቁልፍ ሚና ተጫውተዋል:: ጥረትንም የተጨመላለቀ የቤተሰብ እና የጏደኛ ጎጆ መውጫ አድርገውታል ተብሎ መገምገሙን በሶስትና አራት ወራት አይረሱትም:: ስለሆነም ውሳኔው የዘገየ ከበቂ በላይ ፖለቲካዊ መሠረት ያለው ነው እንላለን:: በህግ የመጠይቅን ጉዳይ በተመለከተ ህግ ይየውም እንላለን::
===
” ውሳኔው የኤርትራ መንግስት እጅ አለበት፤ እኔም ኤርትራዊ ስለሆንኩ ነው ” ያሉት ነገር እርስ በእርሱ የሚጣፋ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ አቶ በረከት ብአዴን በሌላ ውጫዊ አካል የሚታዘዝ ድርጅት ነው እያሉንም ስለሆነ “እሱ አክትሟል፤ እንኳን ከሌላ አገር በብእእዴንም ውስጥ ባዕድ ሀሳብ ሊጭን ይእሚችል ሀይል የሚሸከም ትከሻ የለም ” ልንላቸው እንወዳለን:: እኛም ወደ ኤርትራ የሄድንበትን ምክንያት ህዝብ ስለሚያውቀው ውሀ እንደማይቋጥር እሳቸውም አይጠፋቸውም :: በነገራችን ላይ የአማራ ብሄራዊ ክልል ምክር ቤት ልዑክ መስከረም 3 ቀን 2011 ዓ.ም ወደ ኤርትራ ይጏዛል::
===
አቶ ደመቀን በተመለከተ “ጠቅላይ ሚንስትር እንዳይሆን ስለታገልኩት ነው ” ላሉት ደግሞ ምክንያታቸው ደካማው ነው:: ምክንያቱም አቶ ደመቀ በእጩነትም እንዳይያዙ ለምክር ቤት አቅርበው እንደነበረ እና ምክንያታቸውም አዲስ አመራር እንዲመጣ ፍላጎት ስላላቸው መሆኑ ያደባባይ ሚስጥር ከመሆኑም በላይ የአቶ ደመቀን ትልቅነትና አስተዋይነት ያሳየ የወራት ትውስታ ስለሆነ ይህም ውሀ አይቋጥርም:: ለነገሩ አቶ በረከት በብአዴን መድረክ የአመራር ሽግሽግ አጀንዳ በማቀንቀን እሳቸው የሚያዙት አሻንጉሊት ሊቀመንበር ለማስቀመጥ አምርረው ታግለዋል፣ ጉዳዩንም እስክ ደምፀ ውሴኔ አድርሰዋል:: ሀሳባቸውም ውድቅ ተደርጏል:: አቶ በረከት ኦሮሞ ወደ ስልጣን ይምጣ ብለው እንደሞገቱ እና እንደታገሉ ገልፀዋል :: ነገር ግን ዶክተር አብይ ሊቀመንበር ሆነው እንዲመረጡ ብአዴን ሲታገል ” አብይ ኢትዮጵያንም ኢህአዴግንም አይመጥንም ” ብለው የታገሉት አብይ የየትኛው ብሄር እና ድርጅት መሪ መስለዋቸው ይሆን? ምን አልባት በአልባት በሁለቱ ህዝቦችና ድርጅቶች መካከል ቅራኔ እንዲፈጠር ታስቦ ከሆነ ይሄ አልፎበታል:: ለነገሩ ባለፈው አመት በባህር ዳር የኦሮሞ እና አማራ ህዝብ የጋራ መድረክ ስንፈጥር አቶ በረከት እና መሰሎቻቸው ” መርህ አልባ ግንኙነት ነው” ብለው መድረኩ እንዳይካሄድ እስከ ዋዜማው ጥረት ማድረጋቸው እና ትምክህትና ጥበት ያልተቀደሰ ጋብቻ መሰረቱ ብለው እንደወረዱብን ለምናስታውስ ጉዳዩ የቆየ እና ባህሪያዊ ስለሆነ እንደተለመደው እናልፈዋለን::
===
በመጨረሻም የአሁኑ የአማራ ክልል አመራር ደካማ ነው ሲሉ አመራሩን አጣጥለዋል :: ለመሆኑ ይሄ አመራር ደካማ ቢሆን ኖሮ እንዴት እሳቸውን ያህል ጉምቱ ፖለቲከኛ እና የተቀናቀኑትን መቀመቅ የሚያወርዱ ሰው ተቋቋመ? እንዴትስ ለእርሶ አላጎበድድም አለ? እንዴትስ ያልተደፈሩትን የአማራን ህዝብ ጥያቄዎች ደፍሮ ተሟገተባቸው? ባለፉ ጥቂት ወራት በነበሩን ስብሰባዎችስ ብአዴን ላይ ተስፋ አለኝ አላሉምን ? አሁን ያለው አመራር የወጣቱን የስራ ዕድል ይፈጠርልኝ ጥያቄ አይመልስም ሲሉ ለመሆኑ ይህ አመራር ይህንን ጥያቄ ለመመለስ ምን እየሰራ እንደሆነስ ያውቁ የለም ? የአማራ ወጣት ጥያቄ ስራ እና ዳቦ ብቻ ነው እንዴ ? ጥያቄው እኮ ከዳቦ በላይ ነው:: ጥያቄው ነፃነት፣ እኩልነት፣ ፍትሀዊ ተጠቃሚነት፣ ማንነት ነው:: ለነገሩ እነዚህ ጥያቄዎች አማራ ሲያነሳቸው ለእርስዎ ትምክህት ናቸው:: እነዚህን ያነሱ የብአዴን አመራሮችን አሳደው መምታትዎትን መናገር እርስዎን መድፈር ስላልሆነ እንናገረዋለን:: አመራሩስ ደካማ ቢሆን ማን መራው፣ ማን አሰለጠነው፣ ማን ገመገመው ቢባል ቀዳሚው ሰው አቶ በረከት መሆንዎ አይቀርምና የአመራር አያያዜ ምን ይመስል ነበር ብሎ ራስን መፈትሽ ከእውነት ያስታርቃል::
ታዲያ ይህንን ስል የትንታኔ ብቃቶትን፣ የትግል ድፍረቶትን እና እድሜዎትን በመድፈር አይደለም :: ቢያድልዎት ኖሮ ልክ እንደ አንዳንዶቹ የድርጅታችን መስራቾች “ቦታውን የያዘው አመራር በራሱ መንገድ ይምራ፣ እኛ ገብተን አንፍትፍት ” ብለው መድረኩን ለባለመድረክ ቢልቁ መልካም ነበር እንላለን:: እርሶን ያህል የኢትዮጵያን ሚዲያዎች ያሾር የነበረ ሰው አንድ ድብቅ አላማ ያነገብ እውደድ ባይ ግለሰብ የሚዘውራት እዚህ ግባ ማትባል ቦታ መገኘትዎትም እርስዎን አይመጥንም እና ይቅርብዎት እንልዎታለን::