የኢትዮ ኤርትራ ድንበር ተዘጋ

ብሩክ አብዱ

ሐምሌ 1 ቀን 2011 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በአስመራ ያደረጉትን ድንገተኛ ጉብኘት ካደረጉ በኋላ የሁለቱ አገሮች ግንኙነት በመሻሻሉ ተከፍቶ የነበረውና የኢትዮጵያና የኤርትራ ዜጎች ሲመላለሱበት የቆየው የኢትዮ ኤርትራ ድንበር፣ ከረቡዕ ታኅሳስ 17 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ መዘጋቱ ታወቀ፡፡

ድንበሩ የተዘጋበት ምክንያት ባይታወቅም በአካባቢው ያሉ ምንጮች ድንበሩን እንዲዘጋ ያደረገው የኤርትራ መንግሥት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ በዚህም ሳቢያ ከሁለቱም አገሮች የሚጓጓዙ ዜጎች የመንግሥታቸውን ፈቃድ ማግኘት እንደሚጠበቅባቸው ተነግሯል፡፡

የኤርትራ መንግሥት በመጀመሪያ በዛላምበሳ በኩል ያለውን ድንበር ሲዘጋ፣ በመቀጠልም በራማ ድንበር ላይ ተመሳሳይ ዕርምጃ መውሰዱ ታውቋል፡፡

የኢትዮ ኤርትራ ድንበር ከተከፈተ በኋላ በቀን ከ1,000 እስከ 2,000 ተሽከርካሪዎች ከኤርትራና ከኢትዮጵያ እንደሚመላለሱ፣ በየቀኑ ከኤርትራ ድንበር በማቋረጥ ወደ ኢትዮጵያ 390 ያህል ሰዎች ይገቡ እንደነበር ታውቋል፡፡ በድንበር አካባቢ ንግድ ተጧጡፎ የነበረ በመሆኑ በተለይ በዛላምበሳ፣ በራማና በቡሬ ከፍተኛ እንቅስቃሴ ይስተዋል ነበር፡፡

ድንበሩ ከተከፈተ ከስድስት ወራት ወዲህ ብቻ 27,000 ኤርትራውያን ኢትዮጵያ ገብተው ጥገኝነት እየጠየቁ መሆናቸው ታውቋል፡፡ በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩም ኢትዮጵያ ገብተው መቅረታቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
Zalanbesa town_Ethio-Eritrea border
ፎቶ፡ በድጋሚ የተዘጋው የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ድንበር ከተማ ዛላንብሳ (ሪፖርተር)

ባለፈው ሳምንት የድንበሩ መዘጋት በርካቶችን ግራ ያጋባ ሲሆን፣ በተለይ በድንበር አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች በኤርትራ በኩል በርካታ ወታደሮች በማየታቸው ግራ መጋባት እንደፈጠረባቸው ተሰምቷል፡፡

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በቅርቡ ባደረገው ሪፎርም አማካይነት በአራት ዕዞች የሠራዊት ምደባ ሲያደርግ፣ በርካታ ወታደሮች ውጥረት ከነበረበት የኢትዮጵያና የኤርትራ ድንበር አካባቢ ማንቀሳቀሱን አስታውቆ ነበር፡፡

ሐሙስ ታኅሳስ 18 ቀን 2011 ዓ.ም. በነበራቸው ጋዜጣዊ መግለጫ ስለጉዳዩ የተጠየቁት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ መለስ ዓለም፣ መረጃው እንደሌላቸው ተናግረዋል፡፡

ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ፕሬስ ሴክሬታርያት በጉዳዩ ላይ ከሪፖርተር ጥያቄ ቢቀርብም፣ መረጃው ቢኖር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን ስለሚመለከት እዚያው መጠየቅ እንደሚገባ ተገልጿል፡፡

በጉዳዩ ላይ ሪፖርተር ያናገራቸው የትግራይ ክልል የከተማ ልማት፣ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ዳንኤል መኰንን፣ የፌዴራል መንግሥት ስለድንበሩ መዘጋት ለክልሉ የገለጸው ነገር የለም ብለዋል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታም በተዘጉት ድንበሮች ወደ ኤርትራ መግባት የሚፈልግ ግለሰብ ከፌዴራል መንግሥት ፈቃድ እየተጠየቀ እንደሆነ፣ ከኤርትራም በኩል ወደ ኢትዮጵያ መምጣት የሚፈልጉት ድንበር ላይ የማለፊያ ፈቃድ ከኤርትራ በኩል እየተሰጠ እንዳልሆነ አቶ ዳንኤል ገልጸዋል፡፡

ክልሉ ከፌዴራል መንግሥት ከተወጣጡ ባለሙያዎች ጋር ሆኖ የንግድ እንቅስቃሴውን እንዴት በተገቢው መንገድ ማንቀሳቀስ ይቻላል የሚለውን አጥንቶ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) ለሚመራው ኮሚቴ ማቅረቡን ያስታወሱት ኃላፊው፣ በጉዳዩ ላይ ምንም ውሳኔ ሳይሰጥበት ድንበሩ መዘጋቱ እንዳስገረማቸው አቶ ዳንኤል ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል የኤርትራ መንግሥት ወደ ኢትዮጵያ ለሚጓዙ ዜጎቹ የመውጫ ቪዛ ግዴታ መጣሉ ተሰምቷል፡፡ ሁለቱ አገሮች ሰላም ከፈጠሩ በኋላ ዜጎች ለወራት በነፃ ሲዘዋወሩ ቢቆዩም፣ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በኤርትራ የድንበር ተቆጣጣሪዎች ኤርትራውያን ወደ ኢትዮጵያ መግባት ተከልክለዋል፡፡

በኤርትራ በኩል ወደ ኢትዮጵያ ለመጓዝ የተቀመጠው የመውጫ ቪዛ ግዴታ፣ ኤርትራውያን በከፍተኛ ቁጥር ወደ ኢትዮጵያ በመግባት ላይ በመሆናቸው እንደሆነ፣ የኢትዮጵያ ቆይታቸውን አጠናቀው ወደ ኤርትራ የመመለስ አዝማሚያቸው በመቀነሱ የተወሰደ ዕርምጃ ሊሆን እንደሚችል ምንጮች ጠቁመዋል።

ከሁለት ሳምንት በፊት የሥራ አፈጻጸምና የዓመቱን ዕቅዳቸውን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ያቀረቡት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር)፣ ከኤርትራ ጋር ለበርካታ ዓመታት የነበረው አለመግባባት ተፈቶ ኅብረተሰቡ ያለምንም ችግር የንግድና ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች እያደረገ እንደሚገኝ ተናግረው ነበር፡፡

ከኤርትራ ጋር የተፈጠረውን መልካም ጉርብትናና ትስስር አጠናክሮ ለማስቀጠል የኢሚግሬሽን፣ የንግድ፣ የታክስ፣ የመገበያያ ገንዘብ አጠቃቀምና ምንዛሪ፣ የጉምሩክና የድንበር ጉዳዮች ተቋማዊ ሆነው እንዲቀጥሉ በሁለቱ መንግሥታት መካከል ዝርዝር ውይይት በመደረግ ላይ መሆኑን ጠቁመዋል።

እስካሁን ራሳቸው የተገኙባቸው ሦስት ዙር ውጤታማ ድርድሮች መከናወናቸውን ገልጸው፣ ድርድሮቹ ተጠናቀው ስምምነት ከተፈረመ በኋላ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ በሕግ ደረጃ እንደሚፀድቅ አስረድተዋል፡፡

ሪፖርተር አዲስ አበባ ከሚገኘው የኤርትራ ኤምባሲ ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡

በብሩክ አብዱና በዳዊት እንደሻው

ምንጭ፦ ሪፖርተር

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: