በኦሮሚያ ክልል በተካሄዱ ተቃውሞዎች 67 ሰዎች ተገደሉ

ግጭቱ ከክልሉ አቅም በላይ በመሆኑ የመከላከያ ሠራዊት ተሰማርቷል

የኦኤምኤን ቴሌቪዥን ጣቢያ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ጃዋር መሐመድ የተመደበለት ጥበቃ እንዲነሳ በመባሉ በተቀሰቀሰ ውዝግብ፣ በኦሮሚያ ክልል በተካሄዱ ተቃውሞዎች የሞቱ ሰዎች ቁጥር 67 መድረሱ ተረጋገጠ፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች ሃይማኖታዊና ብሔር ተኮር ጥቃቶች ተፈጽመዋል፡፡

የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ዓርብ ጥቅምት 14 ቀን እንዳስታወቀው በክልሉ በተቀሰቀሱ ተቃውሞዎች 67 ሰዎች ተገድለዋል፡፡ ከተገደሉት ውስጥ 13 ያህሉ በጥይት፣ ቀሪዎቹ ደግሞ በተፈጸመባቸው ጥቃት ሕይወታቸው ማለፉን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ገልጿል፡፡ ከተገደሉት መካከል አምስቱ የፖሊስ ባልደረቦች እንደሆኑ ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ይህንን ቢልም ጉዳት በደረሰባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎች የተገደሉት ሰዎች ቁጥር ሊጨምር ይችላል እያሉ ነው፡፡ በአንዳንድ ሥፍራዎች የተፈጸሙት ጥቃቶች ሃይማኖታዊና ብሔር ተኮር በመሆናቸው ሳቢያ በርካቶች ጉዳት እንደደረሰባቸው ተናግረዋል፡፡

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመንግሥታቸው የበጀት ዓመቱ ዕቅዶችና በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ማብራርያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የውጭ ዜግነት ያላቸው የሚዲያ ባለቤቶች ጥላቻና ግጭትን ከሚቀሰቅሱ ሥራዎች ካልተቆጠቡ፣ መንግሥት ዕርምጃ እንደሚወስድ ማክሰኞ ጥቅምት 11 ቀን 2012 ዓ.ም. ማስታወቃቸው ይታወሳል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማስጠንቀቂያ በጥቅሉ የተነገረ ቢሆንም ጃዋር የውጭ ዜግነት ያለው ትውልደ ኢትዮጵያዊ የፖለቲካ አክቲቪስትና የሚዲያ ባለቤት መሆኑ፣ ራሱን ጨምሮ በርካቶች የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማስጠንቀቂያ በዋናነት እሱን የሚመለከት አድርገው ተገንዝበውት ነበር፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ማስጠንቀቂያ ባስተላለፉበት ዕለት አመሻሽይ ላይ ወደ ሩሲያ ተጉዘዋል፡፡ ነገር ግን በዚያው ዕለት ዕኩለ ሌሊት ለጃዋር ደኅንነት ጥበቃ እንዲያደርጉ በመንግሥት የተመደቡ ጥበቃዎች፣ በአዲስ አበባ ከተማ ቦሌ አካባቢ ከሚገኘው መኖሪያ ቤት ሥራቸውን አቋርጠው እንዲወጡ ታዘዋል በመባሉ ምክንያት አለመግባባት ተፈጥሯል፡፡

የጥበቃ አገልግሎቱ ተገቢ ባልሆነ ሰዓትና እሱ ሳያውቅ እንዲነሳ ትዕዛዝ ተላልፏል በመባሉ በጃዋር ላይ ሥጋት መፍጠሩንና ለዚህም ተጨባጭ ምክንያት ከመንግሥት ኃላፊዎች ማግኘት አለመቻሉን በመግለጽ፣ ከ1.7 ሚሊዮን በላይ ተከታዮችን ባፈራበት የማኅበራዊ ትስስር ገጽ ላይ በዚያው ሌሊት ይፋ እንዲያደርግ እንዳስገደደው ራሱ ተናግሯል፡፡

ይህንንም ተከትሎ ከጃዋር መኖሪያ ቅርብ ከሆኑ አካባቢዎች ደጋፊዎቹ ሌሊቱን ተጉዘው በሥፍራው የደረሱ ሲሆን፣ እሱ ይፋ ያደረገው መረጃም ስሜትና ጥርጣሬን እየቀላቀለ ሌሊቱን ሲሰራጭ አድሮ ‹‹ቄሮ›› በሚባል መጠሪያ የሚታወቁ ወጣቶች በማግሥቱ በበርካታ የኦሮሚያ ክልል ከተሞች ለተቃውሞ እንዲወጡ፣ ተቃውሟቸውንም መንገድ በመዝጋትና እንቅስቃሴዎችን በማስተጓጎል እንዲገልጹ አድርጓቸዋል፡፡ ተቃውሞውም እየተስፋፋ በርካታ ሥፍራዎችን አዳርሷል፡፡

ጃዋር የተመደቡለት የጥበቃ ሰዎች በዕኩለ ሌሊት እንዲነሱና ጥበቃው እንዲቋረጥ መንግሥት አድርጓል ያለውን ድርጊት ‹‹የግድያ ሙከራ›› እንደሆነ፣ ሌሎች ፖለቲካዊ ምክንያቶችንም በማያያዝ በማግሥቱ ጠዋት በራሱ ሚዲያ (ኦኤምኤን) እና በሌሎች ሚዲያዎች እንዲገለጽ አድርጓል፡፡

በመሆኑም ረቡዕ ጥቅምት 12 ቀን 2012 ዓ.ም. ማለዳ በአዲስ አበባ ዙሪያ ባሉ የኦሮሚያ ከተሞች የተጀመረው ተቃውሞ፣ በበርካታ የኦሮሚያ ከተሞችም ተስፋፍቶ ቀጥሏል፡፡ ተቃውሞው መንገድ ከመዝጋትና የተባለውን ድርጊት ከማውገዝ አልፎ በመሄድ ገጽታውን በመቀየር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማኅበራዊ መሠረታቸው በሆነው የኦሮሞ ሕዝብ ላይ ክህደት እንደፈጸሙ፣ እንዲሁም የኦሮሞ ሕዝብ ትግል ጥያቄዎች እንዳይመለሱ አድርገዋል የሚሉ ውግዘቶች ተስታጋብቶባቸዋል፡፡ በቅርቡ ያሳተሙት ‹‹መደመር›› የተሰኘው መጽሐፋቸውና ባነሮች እንዲቃጠሉ ተደርገዋል፡፡ የተቃውሞ ሠልፎቹ በተካሄዱባቸው አንዳንድ አካባዎች ለአብነትም በተለያዩ ከተሞች የሚኖሩ የሌላ ብሔር ተወላጆችና የጃዋር ደጋፊዎች በመጋጨታቸው፣ የበርካታ ሰዎች ሕይወት እንዲቀጠፍ ምክንያት ሆኗል፡፡

የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር እንደሻው ጣሰው በጃዋር ላይ ምንም ዓይነት የግድያ ሙከራ አለመቃጣቱን፣ ግለሰቡም በሥራው ላይ እንደሚገኝ ረቡዕ ቀትር ላይ በመግለጽ ለማረጋጋት ጥረት አድርገው ነበር፡፡

ለጃዋርም ሆነ ከውጭ ለገቡ ተፅዕኖ ፈጣሪ ፖለቲከኞች መንግሥት መድቦ የነበረውን የጥበቃ አገልግሎት በአገሪቱ በተፈጠረው አንፃራዊ ሰላም ምክንያት በማቋረጥ ላይ እንደነበር የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነሩ ተናግረዋል፡፡ ረቡዕ ጠዋት የተጀመረው ተቃውሞ ከቀትር በኋላም እየተስፋፋ በርካታ የኦሮሚያ ከተሞችን በግጭት ሲንጥ ውሏል፡፡

ተቃውሞዎቹ በአንዳንድ አካባቢዎች ሃይማኖታዊና የብሔር ግጭት መልክ በመያዛቸው፣ ከቁጥጥር ውጭ መሆናቸውንና የፀጥታ አስከባሪዎችም ክስተቱን ለመቆጣጠር ኃይል ወደ መጠቀም እንዲገቡ ማስገደዱን ለማወቅ ተችሏል፡፡

በዚህም ምክንያት ረቡዕ ዕለት በአምቦ ሦስት ሰዎች፣ በምሥራቅ ሐረርጌ አንድ መገደላቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በዚሁ ቀን በአዳማ ከተማ በሚገኝ አንድ ዱቄት ፋብሪካ ላይ ጥቃት ለማድረስ ሙከራ አድርገዋል በተባሉ ተቃዋሚዎች ላይ የፋብሪካው የጥበቃ ሠራተኛ ተኩስ በመክፈት ሁለት ሠልፈኞችን በመግደላቸው ምክንያት ተቃውሞው ማየሉን፣ በዚህም ሳቢያ የፋብሪካው የጥበቃ ሠራተኛ በሠልፈኞቹ ሲገደሉ፣ በፋብሪካው ቅጥር ግቢ የነበሩ 15 ተሽከርካሪዎች መውደማቸውም ታውቋል፡፡ በተመሳሳይ በድሬዳዋ ከተማ አራት ሰዎች መገደላቸውንም የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡ በድሬዳዋና በሐረር ከተሞች በነጋታው በተፈጸሙ ጥቃቶች በርካቶች እንደተገደሉ የዓይን እማኞች ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ጥቃቶቹም በጣም አስፈሪ እንደነበሩ አክለዋል፡፡

የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ረቡዕ አመሻሽ ላይ በሰጡት መግለጫ፣ የክልሉ ሕዝብ እንዲረጋጋ ጥሪ በማቅረብ የጃዋር ጥበቃዎችን ለማንሳት የተሄደበት መንገድ አግባብነት እንደሌለው ተናግረዋል፡፡

አክለውም ተቃውሞው ሌላ መልክ እንዲይዝ በማድረግ ክልሉን ለመረበሽ ዓላማ ያላቸው ኃይሎች መኖራቸውን በመግለጽ፣ የክልሉ መንግሥት በእነዚህ ላይ አስፈላጊውን ዕርምጃ እንደሚወስድ አስጠንቅቀዋል፡፡

ይሁን እንጂ ተቃውሞውንና ግጭቱን በማግሥቱም መቆጣጠር አልተቻለም፡፡ በማግሥቱ ሐሙስ ግጭቶቹ ተጠናክረው የቀጠሉ ሲሆን፣ በተለይም በመጀመርያው ቀን የነበረውን ተቃውሞ ለማስተጓጎል ሞክረዋል የተባሉ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ማንነት በመለየት ጥቃት ወደ መሰንዘር እንደተገባ ታውቋል፡፡

የዓይን እማኞች በምዕራብ ኦሮሚያ ወለቴ በተባለ አካባቢ የመጀመርያ ቀን ተቃውሞውን የማስተጓጎል ሙከራ አድርገዋል የተባሉ የሌላ ብሔረሰብ ተወላጆችን በየመኖሪያቸው በመግባት ጥቃት መሰንዘሩን ተናግረዋል፡፡ በዚህም ምክንያት በአንድ ያላለቀ ሕንፃ ላይ በጋራ ከሚኖሩ ሰዎች መካከል ሴቶቹን በመለየት፣ ወንዶቹን ከመኖሪያቻው በማውጣት ጥቃት ያደረሱባቸው መሆኑንና ጥቃት ከደረሰባቸው መካከልም ስድስት የሚሆኑት መገደላቸውን የዓይን እማኞች አስረድተዋል፡፡ በአምቦም እንደዚሁ ሰዎች ሞተዋል፡፡

በምሥራቅ ሐረርጌም ተመሳሳይ ጥቃት ሊደርስባቸው የነበሩ አንድ ግለሰብ በጦር መሥሪያ ራሳቸውን ለመከላከል ባደረጉት ሙከራ ጥቃት ሊያደርሱባቸው ከመጡት መካከል ሁለት ሰዎች መግደላቸውን፣ ይህንንም ተከትሎ ግለሰቡ ከሥፍራው ቢያመልጡም በባለቤታቸው ላይ በተፈጸመ ግድያ እንዲሁም በሌሎች ሁለት ሰዎች ላይ በተፈጸመ ጥቃት በድምሩ አምስት የአካባቢው ነዋሪዎች መገደላቸውን የአካባቢው ሰዎች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ በተመሳሳይ ዶዶላ አካባቢ ለተቃውሞ የወጡ ወጣቶች ብሔርና ሃይማኖት ለይተው በማጥቃት ድርጊት ውስጥ በመግባታቸው አራት ሰዎች እንደተገደሉ ተሰምቷል፡፡

በሁለቱ ቀናት በርካታ ሰዎች መገደላቸውን ሪፖርተር ግጭቶቹ ከተቀሰቀሱባቸው አካባቢዎች ነዋሪዎች ያሰባሰበው መረጃ ያመለክታል፡፡ የሟቾችን ቁጥር በተመለከተ የተለያዩ አኃዞች እየተሰሙ ቢሆንም፣ ከገለልተኛ አካላት ትክክለኛውን ቁጥር ማረጋገጥ አልተቻለም፡፡ ሐሙስ ከቀትር በኋላ ጃዋር ከተለያዩ የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር በመሆን በሰጠው መግለጫ፣ በተካሄዱት ተቃውሞዎች በቂ መልዕክት መተላለፉን በመግለጽ ተከታዮቹም ሆኑ ሌሎች የኦሮሞ ማኅበረሰቦች ተቃውሟቸውን በመግታት እንዲረጋጉ በኦኤምኤን ማሳሰቢያ ሰጥቷል፡፡ በተለይ ዶዶላ አካባቢ የከፋ ጥቃት ሲፈጸም እንደነበር ታውቋል፡፡ የተገደሉ ሰዎችን አስከሬን ለመቅበር የተቸገሩ ሰዎች ለመንግሥት አካላት የድረሱልን ጥሪ ሲያሰሙ ነበር፡፡ ቤቶቻቸው የተቃጠሉባቸው ሰዎችም እንዲሁ ድረሱልን ሲሉ ነበር፡፡

ይህንን ተከትሎ መለስተኛ መረጋጋት ዓርብ ዕለት ቢስተዋልም ውጥረቱ እንዳየለ ነበር፡፡ ዓርብ ዕለት የመከላከያ ሠራዊቱ በሰጠው መግለጫ የክልሉ መንግሥት ግጭቱን ለመቆጣጠር ከአቅም በላይ እንደሆነበት በመግለጽ፣ የፌደራል መንግሥትን ድጋፍ በመጠየቁ መንግሥት ሠራዊቱ ችግር በተፈጠረባቸው አካባቢዎች እንዲሰማራ መወሰኑን አመልክቷል፡፡

የመከላከያ ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነትና ኢንዶክትሪኔሽን ዳይሬክተር ሜጀር ጄነራል መሐመድ ተሰማ በሰጡት መግለጫ፣ ሠራዊቱ ወደ ክልሉ በመግባት ግጭቱን እንዲቆጣጠር ከመንግሥት በተሰጠው መመርያ መሰማራቱን አረጋግጠዋል፡፡

በዚህም መሠረት አዳማ፣ ቢሾፍቱ፣ ድሬዳዋ፣ ባሌ፣ ዶዶላ፣ አሰላ፣ ኮፈሌ፣ አምቦ፣ ሻሸመኔ፣ ሞጆና በሐረር ሠራዊቱ ከተሰማራባቸው መካከል መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በተፈጠረው ግጭት ለጠፋው የሰው ሕይወትና የንብረት ውድመት ተጠያቂ ስለሆኑ አካላት ግን፣ ለኅትመት እስከ ገባንበት ቅዳሜ እኩለ ቀን ድረስ በመንግሥት በኩል የተባለ ነገር የለም፡፡ ብዙዎች ግን የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ መንግሥትን ዕርምጃ እየጠበቁ ነበር፡፡

Source: ሪፓርተር

Leave a comment