Category Archives: News

ቅድስት ስላሴ ኮሌጅ የተፈጠረው ችግር ዛሬም እልባት አላገኘም

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ቅድስት ስላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ትምህርታቸው ከመጋቢት 2 ቀን 2005 ዓ.ም. ጀምሮ ተቋርጧል፡፡በተማሪዎቹ በመማር ማስተማር ሂደት ወቅት በረካታ አስተዳደራዊ በደል እየደረሰባቸው እንደሆነና ለጥቄያቸው መልስ የሚሰጥ አካል ባለመገኘቱም ምግብ የመብላትና ትምህርት የማቆም አድማ ካደረጉ እነሆ ዛሬ 15 ቀን ሆኖኗቸዋል፡፡ የምግብ አድማ ካደረጉም በኋላ መጋቢት 16 ቀን 2005ዓ.ም. የ5ኛ ዓመት ደቀመዝሙር የሆኑት አባማቲያስ፣ የ2ኛ ዓመት በኃይሉ ሰፊ እና ገብረእግዚአብሔር የተባሉ የኮሌጁ ደቀመዛሙርት ታመው ወደ ሆስፒታል መሄዳቸው ተጠቁሟል፡፡ በተጨማሪም ከጠቅላይ ቤተክህነቱ ለኮሌጁ የተመደበው በጀትም በአግባቡ ጥቅም ላይ እንደማይውልና የሙስና ወንጀል እንደሚፈፀምበት ያነጋገርናቸው ተማሪዎች አክለዋል፡፡

በተለይ ተማሪዎቹ እንደገለፁት ከሆነ የኮሌጁ አካዳሚክ ዲን መምህር ፍስሐፅዮን ደመወዝ እና የቀን ተማሪዎች አስተባባሪ መምህር ዘለዓለም ረድኤት ከቤተክርስቲያኗም ሆነ ከዓለማዊው የመንግስት የትምህርት ተቋም  የሌሉ የስነምግባር ጥሰቶች በመፈፀም ተማሪዎችን መሳደብና መምታትን ጨምሮ  በማስፈራራት እየዛቱ በመማር ማስተማሩ ሂደት ላይ ችግር እየፈጠሩ ነው የሚል ቅሬታን ሲያቀርቡ ይሰማል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ሁለቱም መምህራን ክፍያ የሚፈፀምላቸው ባስተማሩት ኮርስና ክፍለ ጊዜ መሰረት በመሆኑ ዕውቀቱና ልምዱ ያላቸው በርካታ መምህራን እያሉ አብዛኛውን ኮርስ እነሱ ብቻ እየሰጡ ሲሆን በውጤት አሰጣጥ ላይም ችግር እንደሚስተዋልበቻው ተጠቁሟል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በተፈጠረው የአስተዳደር ችግር ምክንያት የምግብ አቅርቦትና ጥራት ችግር በመስተዋሉ ለበላይ አስተዳደሩ ቅሬታ ቢቀርብም ከማስፈራራት ውጭ አዎንታዊ ምላሽ እንዳልተሰጣቸው አስታውሰዋል፡፡

ተማሪዎቹ ካነሷቸው የመብት ጥያቄ ጋር በተያያዘ የ5ኛ ዓመት ደቀመዝሙር ኃይለፅዮን መንግስቱ የተባለ ከማደሪያው በመንግስት የደህንነት ሃይሎች ሌሊት ታፍኖ ተወስዶ ቀጨኔ መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን አካባቢ በሚገኘው ፖሊስ ጣቢያ መታሰሩንና እስካሁንም አለመለቀቁ ተጠቁሟል፡፡

በመጨረሻም ደቀመዛሙርቱ ቅሬታቸውን ለኮሌጁ የበላይ ጠባቂ ብፁዕ አቡነ ጢሞቲዎስ ለመንገር ቢፈልጉም  አቡኑ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው አርብ መጋቢት 13 ቀን 2005 ዓ.ም. ቅድስት ማርያም መንበረ ፓትርያርክ ወደ ጠቅላይ ቤተክህነት በመሄድ ቅዱስ ፓትርያረኩ ብፁዕ አቡነ ማቲያስን ለማናገር ከቅዳሴ በፊት በስፍራው ብንገኝም ከውጭ አንድ ደህንነት ወደ ውስጥ በመግባት እንዳይወጡ አዟቸው ሳይወጡ ቀርተዋል፡፡ በዕለቱም ፓትርያርኩ እኛን እንዳያናግሩ በመፈለጉ ቅዳሴ እንኳ ሳይገቡ በመቅረታቸው ጥላ ይዘው ሊቀበሏቸው የሄዱ አባቶች ጥላቸውን አጥፈው ሊመለሱ መቻላቸው ተጠቁሟል፡፡ ይሁን እንጂ በነጋታው ፓትርያርኩ ጥቂት የተማሪዎች ተወካዮች እንዲያናግሯቸው ቢጠሩም አቤቱታችንን ከሰሙ በኋላ ምላሻቸው ግን ሄዳችሁ ተማሩ ብቻ ሆኗል ይላሉ ተማሪዎቹ፡፡ ይሁን እንጂ ተማሪዎቹ በድጋሚ ከአባ ሰረቀብርሃን ጋር ባደረጉት ውይይት መጋቢት 18 ቀን 2005ዓ.ም. ትምህርት መጀመራቸው ቢታወቅም አስተዳደራዊና የምግብ ችግሩ ግን እስካሁን እልባት ባለማግኘቱ በግቢው ውስጥ የሚዘጋጅ ምግብ መመገብ አለመጀመራቸው ተጠቁሟል፡፡

በመጨረሻም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የትምህርት ተቋማት የበላይ ጠባቂ የሆኑት አባ ሰረቀብርሃን ኮሌጁ ግቢ ድረስ በመምጣት ካናገሩና የተማሪዎቹ ጥያቄ በቅርቡ ምላሽ እንደሚያገኝና የታሰረው ደቀመዝሙርም በነጋታው ተፈቶ በመምጣት የመማር ማስተማሩ ሂደት እንደሚቀጥል ቃል ከገቡ በኋላ በነጋታው ሲመጡ ቃላቸውን በማጠፍ ጭራሽ ማስፈራሪያና ዛቻ በመፈፀም እንደተመለሱ አዲስሚዲያ  ያነጋገራቸው የኮሌጁ ተማሪዎች ገልፀውል፡፡ አባሰረቀ ብርሃን ከዚህ በፊት የማኀበረ ቅዱሳንን ስም በተደጋጋሚ በማጥፋት ተከሰው ዜግነታቸው አሜሪካዊ በመሆኑ ወወደ አሜሪካ በመሄድ ክሱ ተቋርጦ በፊት ከነበሩበት የቤተክርስቲያኗ ሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ የበላይ ኃላፊነት ተነስተው በአቡነጳውሎስ ፈቃድና መመሪያ የትምህርት ተቋማት የበላይ ጠባቂ እንዲሆኑ መሾማቸውምና  በቤተክርስቲያኑ የኑፋቄ ትምህርት አራማጅ ናቸው በሚልም እንደሚጠረጠሩ ይነገራል፡፡

በጉዳዩ ዙሪያ አዲስ ሚዲያ  የቤተክርስቲያኗ ቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ፀሐፊ የሆኑትን ብፁዕ አቡነ ህዝቄልን ጠይቆ ውሳኔ ለመስጠት ስብሰባ ላይ መቀመጣቸውን ከመግለፅ ያለፈ ምንም ምላሽ ሊሰጡ አልቻሉም፡፡ ከስብሰባው በኋላ የደረሱበትን ውሳኔ ለማጣራትም  በድጋሚ ብፁዕ አቡነ ህዝቄል ጋር ስልክ ብንደውልም ስልካቸውን አላነሱልንም፡፡ በኮሌጁ የቀን መርሃ ግብር ትምህርታቸውን እየተከታተሉ የነበሩት ከየ ሀገረስብከቱ የመጡ  በአጠቃላይ 180 ደቀመዛሙርት እንደሆኑም ለማወቅ ተችሏል፡፡

የነ አንዱዓለም እና ጋዜጠኛ እስክንድር ፍርድ ለሌላ ጊዜ ተላለፈ

የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ከፍተኛ አመራር አቶ አንዱዓለም አራጌ፣ አቶ ናትናኤል መኮንንና ታዋቂው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣ አቶ አንዱዓለም አያሌው፣ አቶ ክንፈሚካኤል ደበበ ፣ ሻምበል የሺዋስ ይሁንዓለም እና አቶ ምትኩ ዳምጤ ይግባኝ ውሳኔ ለዛሬ መጋቢት 18 ቀን 2005ዓ.ም. ተቀጥሮ ቢሆንም ውሳኔው ለአራተኛ ጊዜ ተላለፈ፡፡ በተለይ የክሱን ሂደት ከሚከታተሉት የፌደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች ሽመክት አሰፋ፣ በላቸው አንሺሶ እና ዳኜ መላኩ መካከል የመሐል ዳኛው ዳኜ መላኩ ከችሎት ውጭ ከጠዋቱ 3፡40 ሰዓት የተከሳሽ ጠበቆችን 6 ኪሎ በሚገኘው የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ህንፃ ቢሮ ቁጥር 9 በመጥራት ጠበቆችን “ተከሳሾቹ የተከሰሱበት ወንጀል ነፃ ናቸውና በነፃ ሊለቀቁ ይገባል የሚል ክርክር ስላነሳችሁ ውሳኔውን ለመስጠት ክሱን በደንብ እየመረመርነው ስለሆነ” በሚል ለመጋቢት 30 ቀን 2005 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀነ ቀጠሮ ሰጥተዋል፡፡

የመሐል ዳኛው ተለዋጭ ቀነ ቀጠሮ እስኪሰጡ ድረስ ተከሳሾቹ ፍርድ ቤት ያልቀረቡ ሲሆን ከቀጠሮው በኋላ ግን አቃቂ ቃሊቲ ቂሊንጦ ወህኒ ቤት የሚገኙት አቶ ናትናኤል መኮንን፣ አቶ አንዱዓለም አያሌው፣ አቶ ክንፈሚካኤል ደበበ፣ ሻምበል የሺዋስ ይሁንዓለም እና አቶ ምትኩ ዳምጤን የወህኒ ቤቱ ጠባቂዎች ይዘዋቸው ቢቀርቡም ተለዋጭ ቀነ ቀጠሮውን ችሎት ሳይገቡ በመስማታቸው ተመልሰዋል፡፡

ይህ በእዲህ እንዳለ ቃሊቲ በሚገኘው ወህኒ ቤት የሚገኙት አቶ አንዱዓለም አራጌና ጋዜጠኛ እስክንድር አልቀረቡም፡፡ ይሁን እንጂ አዲስ ሚዲያ  ባደረገው ማጣራት ተለዋጭ ቀነ ቀጠሮው የተሰጠውና እነ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋና አቶ አንዱዓለም አራጌ ያልተገኙት የቃሊቲው ወህኒ ቤት ጉዳይ አስፈፃሚ ሰርጀንት ዘውድነሽ ከጠቅላይ ፍርድ ቤት ተከሳሾቹ ለመጋቢት 18 ቀን 2005ዓ.ም. እንዲቀርቡ  የተሰጣቸውን ማዘዣ ወህኒ ቤቱ አስተዳደሮች ማዘዣው አልደረሰንም በሚል ክደው ተከሳሾቹ በቀጠሮዋቸው እንዲቀርቡ ባለመፍቀዳቸው እንደሆነ የደረሰን መረጃ አመልክቷል፡፡

ተከሳሾች በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ ወንጀል ችሎት በተከሰሱበት “ሽብር” ወንጀል ከ14 ዓመት እስከ ዕድሜ ልክ እስራት እንደተፈረደባቸው ይታወቃል፡፡

በማረሚያ ቤቱ አሰራር የፍትህ ሚኒስቴርም ሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደማያገባቸው ተገለፀ

የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ(አንድነት) አመራር አባል የሆኑትና በፌደራሉ አቃቤ ህግ በ”ሽብርተኝነት” በሚል ተከሰው በቃሊቲ ቂሊንጦ ልዩ ከፍተኛ ጥበቃ የሚደረግበት ወህኒ ቤት በእስር ላይ የሚገኙት አቶ ናትናኤል መኮንን ከሐሙስ መጋቢት 12 ቀን 2005 ዓ.ም. ጀምሮ ለአንድ ወር ምክንያቱ ባልተገለፀበት ሁኔታ ከወዳጅ ቤተሰብ እንዳይገናኝ ተከልክሏል፡፡ ይህንንም የአዲስ ሚዲያና የፍኖተ ነፃነት ዝግጅት ክፍል ከባለቤቱ ወይዘሮ ፍቅርተ ጋር በመሆን ቅዳሜ መጋቢት 14 ቀን 2005ዓ.ም. እዛው ቃሊቲ ቂሊንጦ ወህኒ ቤት በአካል በመሄድ ማረጋገጥ ተችሏል፡፡

አቶ ናትኤል መኮንን በምን የህግ አግባብ ለአንድ ወር ከወዳጅ ቤተሰቦቹ በተለይም ዘወትር ከሚጠይቁትና ስንቅ ከሚያመላልሱለት ባለቤቱና ልጁ እንዳይገናኝ እንደተደረገ የፍትህ ሚኒስቴር የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ የሆኑትን አቶ ደሳለኝ ታረቀኝን የጠየቅናቸው ሲሆን እሳቸውም “ታራሚዎች ከቤተሰቦቻቸው እንዳይገናኙ የሚያዝ ህግ የለም በይበልጥ የማረሚያ ቤቱን ኃላፊ ኮማንደር አስቻለው መኮንን መልስ ይስጠዋችሁ “ መርተውናል፡፡ ኮማንደር አስቻለው በበኩላቸው “በርግጥ እስረኞች የማረሚያ ቤቱን ስነምግባር ከጣሰ በማረሚያ ቤቱ አሰራር መሰረት ቅጣት ይኖራል፤ ነገር ግን የሚፈፀመው የማረሚያ ቤት ቅጣት ምክንያቱን ቤተሰቡና ታራሚው እንዲያውቁ ስለሚደረግ ማነጋገር ትችላላችሁ” የሚል መልስ ሰጥተዋል፡፡

የወህኒ ቤቱ ጥበቃዎችና በዕለቱ ያሉ ኃላፊዎች ግን ስንቅ ይዘው ሊጠይቁ የሄዱትን ቤተሰብ መገናኘት እንደማይችሉና የያዙትን ምግብ ይዘው እንዲመለሱ ከማዘዝ ውጭ የተሰጠ ምላሽ የለም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ “ማረሚያ ቤቱ የራሱ አሰራር ስላለው አይደለም የፍትህ ሚኒስቴርና ኮማንደር አስቻለው ቀርቶ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ቢመጡ አያገባቸውም” ሲሉ በወቅቱ ስማቸውን ማወቅ ያልተቻለ የዕለቱ የጥበቃ ኃለፊና ሁለት የጥበቃ አባላት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

አፋር ክልል በተከሰተ ርሃብ ሰዎች እየሞቱ ነው

በአፋር ክልል ዞን አንድ “ኤሊዳኣልና ቢሩ “ በሚባሉ ወረዳዎች ከፍተኛ የሆነ ርሃብ መከሰቱ ተጠቆመ፡፡ በተለይ በሁለቱ ወረዳዎች ከመጋቢት 6 ቀን 2005 ዓ.ም. ጀምሮ የረሃቡ ሁኔታ እጅግ ከመክፋቱ የተነሳ በአካባቢው ምግብና ውሃ በመጥፋቱ ለከብቶች መኖ  “አብዳ” የሚባለው መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት የሰጠውን ፉርሽካ ነዋሪዎች ጋግረው መብላት መጀመራቸውን ምንጮቻችን ከስፍራው ገልፀዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ነዋሪዎች ባለ25 ሊትር ውሃ እስከ 200 ብር እየገዛ ከመሆኑም በተጨማሪ በተከሰተው ርሃብ እስካሁን 7 ሰዎች መሞታቸውንም ከስፍራው የዓይን እማኞች ጠቁመዋል፡፡

የክልሉ መንግስት በስፍራው ቢገኝም ባልታወቀ ምክንያት እስካሁን ምንም ዓይነት የዕርዳታ ድጋፍ ባለማድረጉ ባካባቢው ነዋሪዎች ቅርሬታ ቢያቀርቡም እስካሁን ምላሽ አለመስጠቱ ተነግሯል፡፡ የፌደራሉ አደጋ መካላከል ዝግጁነት አስተባባሪ መስሪያ ቤትም እስካሁን ምላሽ አለመስጠቱ ተጠቁሟል፡፡

የዝግጅት ክፍሉም የአፋር ክልላዊ መንግስት በተጠቀሱ ወረዳዎች የተከሰተው ርሃብ ያደረሰውን ጉዳትና መንግስት እየወሰደ ያለውን እርምጃ ጠይቀን የክልሉ መንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ መሐመድ “የደረሰውን ጉዳት ገና እያጣራን ነው፣ ልዑካንን ወደ አካባቢው ልከናል፤ አደጋ መከላከል መረጃውን ስላልሰጠን ባልተጣራ ጉዳይ ላይ መረጃ ልሰጥ አልችልም “ ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

የቅድስት ስላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ተማሪዎች የትምህርት ማቆም አድማ አደረጉ

የኢትዮጵያ ኦርቶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ቅድስት ስላሴ መንፈሰሳዊ ኮሌጅ ተማሪዎች ከመጋቢት 2 ቀን 2005 ዓ.ም. ጀምሮ የትምህርት ማቆም አድማ ላይ እንዳሉ የፍኖተ ነፃነት ምንጮች ገለፁ፡፡
እንደ ምንጮቻችን ገለፃ ተማሪዎቹ በአመራር ላይ ያለው አስተዳደር ብቃት የለውም፣ የምግብ አቅርቦትና ጥራት ችግር አለ፤ ምላሽ ግን የሚሰጥም ሆነ ለማነጋገር ፈቃደኛ የሆነ አካል የለም በማለት የኮሌጁ የቀን ተማሪዎች የትምህርት ማቆም አድማ ለማድረግ ተገደዋል፡፡ ተማሪዎቹ ለኮሌጁ አስተዳደር ካነሷቸው ጥያቄዎች በተጨማሪ፣ በኮሌጁ በርካታ ኃይማኖታዊ የአሰተዳደር ችግር እንዳለ ቢጠቅሱም በአስተዳደሩ ምላሽ አለመሰጠቱን ገልፀውልናል፡፡
በነዚህ ምክንያቶች ተማሪዎቹ ጥያቄዎቻቸው እስኪመለሱ ድረስ ትምህርት እንዳቆሙና አንዳንድ ተማሪዎችም መልቀቂያ (ክሊራንስ) እየሞሉ መውጣታቸውን የፍኖተ ነፃነት ጋዜጣ ምንጮች አስታውቀዋል፡፡ ይህንንም ተከትሎ የማታ ተማሪዎችም ከሐሙስ መጋቢት 5 ቀን 2005 ዓ.ም. ጀምሮ ለኮሌጁ ደህንነት በሚል በአስተዳደሩ ትምህርት እንዲያቋርጡ መደረጋቸውን ተማሪዎቹ ለፍኖተ ነፃነት አረጋግጠዋል፡፡
የፍኖተ ነፃነት ጋዜጣ ዝግጅት ክፍልም የኮሌጁ ትምህርት የተቋረጠበትን ምክንያትና ተማሪዎቹ አነሷቸው የተባሉትን ጥቄዎች በተመለከተ የኮሌጁን አስተዳደር ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡ ሆኖም ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ፀሐፊ ብፁዕ አቡነ ህዝቄልን ጠይቀናቸው “ትምህርት መቋረጡን ገና ከእናንተ አሁን መስማቴ ነው፤ የደረሰኝ መረጃ የለም” ሲሉ ምላሽ ሰጥተውናል፡፡ ምንም እንኳ ከጠቅላይ ቤተክህነቱ ዋና ፅህፈት ቤት እስከ ኮሌጁ ድረስ ያለው እርቀት በግምት ከ600 ሜትር ባይበልጥም የቤተክህነቱ ዋና ፀሐፊ ስለትምህርት ማቆም አድማው የሰሙት እንደሌለ ገልፀውልናል፡፡
ይህ መረጃ እስከተዘገበበት መጋቢት 10 ቀን 2005 ዓ.ም. ድረስ በኮሌጁ ትምህርት እንዳልተጀመረ አረጋግጠናል፡፡