Daily Archives: November 15th, 2013

በአዲስ አበባ የተጠራው ሰልፍ በፖሊስ ድብደባ እና እስር ተጠናቀቀ

ሰማያዊ ፓርቲ የሳውዲዓረቢያ መንግስት ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ በኢትዮጵያውያን ላይ እየፈፀመ ያለውን ግድያ፣ እስር እና እንግልት ለመቃወም ዛሬ አርብ ህዳር 6 ቀን 2006 ዓ.ም. አዲስ አበባ ወሎ ሰፈር በሚገኘው የሰውዲ ኤምባሲ ሊደረግ የነበረው የተቃውሞ ሰልፍ በፌደራል እና በአዲስ አበባ ፖሊስ ድብደባ እና እስር ተጠናቀቀ፡፡ ሰለፍ 4 ኪሎ ግንፍሌ ከሚገኘው የሰማያዊ ፓርቲ ጽህፈት ቤት ከረፋዱ 4፡00 ሰዓት ሲጀምር በበፖሊስ እገታ ተፈፅሞ ነበር፡፡ በመቀጠልም አራት ኪሎ ቅድስት ስላሴ ኮሌጅ ፊትለፊት ደግሞ በርካታ የፌደራል ፖሊሶች ዳግም እገታ ፈፀሙ፡፡

በመጨረሻም በእገታው ያልተበገረው የአዲስ አበባ ነዋሪ ወሎ ሰፈር በሚገኘው የሳውዲዓረቢያ ኤምባሲ አካባቢ ቢያመራም በ3 ፒክአፕ መኪና የመጡ የፈደራል ፖሊሶች የተገኘውን ህዝብ በያዙት ዱላ፣ በእጅ እና በእግር ድብደባ ጀመሩ፡፡ ከረፋዱ 5፡30 ሰዓት ላይ እዛውም የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች አቶ ይልቃል ጌትነት፣ አቶ ስለሺ ፈይሳ፣ አቶ ጌታነህ ባልቻ ፣ አቶ ወረታው ዋሴ፣ አቶ ብርሃኑ ተክለያሬድ፣ አቶ ዮናታን ተስፋዬ እና አቶ ሀብታሙ ደመቀ በፖሊስ ታስረው ተወሰዱ፡፡ በዚሁ ሰዓት ደራሲ አቶ አስራት አብርሃምም መታሰሩ ታውቋል፡፡

በሰልፉ ላይ ከተገኙ ነዋሪዎችም ቁጥራቸው ከ500 የማያንሱ ሰዎች ታፍሰው ላንቻ ፖሊስ ጣቢያ እና ጃንሜዳ ፖሊስ ጣቢያ መታሰራቸውን የሰማያዊ ፓርቲ የህግ ጉዳይ ኃላፊ አቶ ይድነቃቸው ከበደ ተናግረዋል፡፡ ፖሊስ ከቀኑ 10፡50 ሰዓት አካባቢ ከታሰሩት መካከል የተወሰኑትን መፍታት መጀመሩን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ይሁን እንጂ ይህ እስከተዘገበበት ሰዓት ድረስ ከተፈፀመባቸው ድብደባ በተጨማሪ የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮችን ጨምሮ በርካታ ሰዎች አሁንም እስር ላይ እንደሚገኙ ታውቋል፡፡

 በዚህ ጉዳይ ላይ የመንግስት ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ ሽመለስ ከማል እና የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ አቶ አባተ ስጦታውን ለማናገር ብንሞክርም ስልካቸውን ባለማንሳታቸው አልተሳካም፡፡ በፖሊስ ድብደባ ተፈፅሞባቸው ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው በተለይ ከላንቻ አካባቢ ካለው ከፖሊስ ጣቢያ በሚኒባስ እየተወሰዱ መሆናቸውን የዓይን እማኞች የገለፁ ሲሆን፤ ወሎ ሰፈር በሚገኘው ሳውዲዓረቢያ ኤምባሲ አካባቢ የሚገኙ ነዋሪዎችም ተባባሪ ናችሁ በሚል አሁንም እየተለቀሙ እየታሰሩ መሆኑን ምንጮቻችንን አስታውቀዋል፡፡

ይህ ሁሉ ድርጊት ያበሳጫቸው የሰልፉ ታዳሚዎች እና ታዛቢዎች መንግስት ይሄንን ስፍ እራሱ ማስተባበር የሚጠበቅበትን ዜጎች በራሳቸው ፈቃድና ተነሳሽነት ድርጊቱን በመቃም መውጣታቸው ሊበረታታ ሲገባ መከልከሉ ኢህአዴግ ኢትዮጵያውያን በሳውዲዓረቢያ መንግስት እና ፖሊስ እደረሰባቸው ያለውን ግድያ፣ እስር እና ስቃይ እንደሚደግፈው በግልፅ ያረጋገጠበት ነው ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ የፊታችን እሁድ ህዳር 8 ቀን 2006 ዓ.ም. አንድነት ከሌሎች የመድረክ አባል ፓርቲዎች ጋር ተመሳሳይ ሰልፍ በዚሁ በአዲስ አበባ ወሎ ሰፈር በሚገኘው የሳውዲዓረቢያ ኤምባሲ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ መጥራታቸውም ታውቋል፡፡

%d bloggers like this: