የአዲስ ጉዳይ መፅሔት ጋዜጠኞች ተሰደዱ
በመንግስት በደረሰባቸው ጫና እና ክስ ምክንያት የ”አዲስ ጉዳይ” መፅሔት ማኔጂንግ ዳይሬክተር እንዳልካቸው ተስፋዬ፣ ምክትል ዋና አዘጋጅ ኢብራሂም ሻፊ፣ ከፍተኛ አዘጋጅ እንዳለ ተሺ እና አዘጋጅ እና የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች መድረክ (ኢጋመ) ገንዘብ ያዥ ሀብታሙ ስዩም ሀገር ጥለው ተሰደዱ፡፡ ጋዜጠኞቹ የተሰደዱት፤ የፍትህ ሚኒስቴር አቃቤ ህግ በኢቴቪ አዲስ ጉዳይ መፅሔትን ጨምሮ 5 መፅሔቶች እና አንድ ጋዜጣ ላይ ክስ መመስረቱ ይፋ መደረጉን ተከትሎ ቢሆንም፤ ቀደም ሲል በመንግስት ደህንነትና ፀጥታ ኃይሎች ተደጋጋሚ ጫና ይደርስባቸው እንደነበርም ተጠቁሟል፡፡
ከአዲስ ጉዳይ መፅሔት ከፍተኛ አዘጋጅ አስማማው ኃይለጊዮርጊስ እና የፎቶ ጋዜጠኛ አዚዛ መሐመድ በቅርቡ መታሰራቸውና ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡ የተሰደዱ ጋዜጠኞች ቁጥርም እየጨመረ ሲሆን፤ በቅርቡ የኢትዮጵ ጋዜጠኞች መድረክ ፕሬዘዳነት ጋዜጠኛ በትረ ያዕቆብ እና የህዝብ ግንኙነቱ ዘሪሁን ሙሉጌታን ጨምሮ እስካሁን የተሰደዱ ጋዜጠኞች ቁጥር ከ15 በላይ መሆኑን መረጃዎች አመልክተዋል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ሌሎችም ጋዜጠኞች ከፍተኛ ጫና ላይ መሆናቸው ታውቋል፡፡