የአባይ ወንዝ ናፍቆት እና የታላቁ ህዳሴ ግድብ
ካሊድ ኢብራሂም
አባይ ወንዝ ለእኛ ለኢትዮጵያውያን የተፈጥሮ ፀጋ ብቻ ሳይሆን፤ ዜማ፥ ቅኔያችን እና መኩሪያችንም ጭምር ነው። ለግብፅና ለሱዳን ደግሞ ከፈጣሪ በታች የሚያዩት ግን የማያናግራቸው ገዥ ነው። ወንዙ በዓለም ላይ ካሉ ረጅም ጉዞ መዳረሻ ካላቸው ታላላቅ ወንዞች አንዱ ሲሆን፤ በውሃ ሃብት የፖለቲካ ምልከታ ደግሞ ከሩቅ ምስራቁ ጎጀብ እና ከደቡብ አሜሪካው አማዞን ወንዝ ያልተናነሰ ገናና ታሪክ እና እደምታ ያለው ትልቅ ሃብት ነው። በሀገራችን በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በሱዳኖች እና በግብፆችም ለዘመናት የተዜመለት ነው። ይሁን እንጂ ሀገራችን እስካሁን ከወንዙ መጠቀም የቻለቸው ሊሰጥ ከሚችለው አገልግሎት ከ 1% አይበልጥም። ነገር ግን የሚቀርብለት አድናቆት፥ ቅኔ፥ ዜና፥ ስምና መወድስ ግን እንደ አዋሽ ካሉ ዘርፈ ብዙ አገልግሎት እየሰጡ ካሉ ታማኝ ወንዞች እንኳ የላቀ ሥፍራ የተሰጠው ነው።
እንደ ታሪክ ድርሳናት መረጃ ከሆነ የዛሬዎቹም ሆኑ ጥንታውያን ግብፆች እና የቀድሞ ኑባውያን የስልጣንያቸው ምንጭ ተደርጎ ይወሰዳል። ኢትዮጵያውያን ነገስታት በተለይ ከ12ኛ ክፍለ ዘመን ጀምሮ ወንዙን ለመጠቀም ፍላጎት ቢኖርም በታሰበው ልክ አገልግሎት ላይ ለማዋል የአቅም ችግር ዋነኛ ምክንያት ነው። ኢትዮጵያ የአባይ ወንዝ አመንጪና ባለቤት ስትሆን ፤ ግብፅ የእና ሱዳን ደግሞ ተጠቃሚ ሆነው ቆይተው ነበር። በተለይ የአባይ ወንዝ ብቻውን ዓመታዊ የአማክይ ፍሰት መጠን 54 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ሲሆን፤ ለናይል ወንዝ 62 % ድርሻ ወይም አበርክቶት አለው።
የተፈጥሮ ሀብትን በአግባቡ ለመጠቀም ፍላጎት በተግባር ካልተደገፈ ብቻውን ምንም ነው። ኢትዮጵያውያን የአባይን ወንዝ ለመጠቀም ፍላጎት ቢኖረንም ዛሬም ድረስ ያለን ተግባራዊ እንቅስቃሴ ግን እዚ ግባ የሚባል አይደለም። በርግጥ እስካሁን ካሉ የኢትዮጵያ መንግሥት መሪዎች የቀዳማዊ አጼ ኃይለስላሴን ያህል ለተግባራዊነቱ የተንቀሳቀሰ መሪ የለም። ወንዙን ለዜጎች ሁለንተናዊ ጥቅም ለማዋል ሳይንሳዊ ጥናት አስጠንተው ለተግባራዊነቱ ረጅም ርቀት የተጓዙትና በተወሰነ መልኩም ቢሆን ተግባር ላይ መዋል የጀመረው በአጼ ኃይለሥላሴ ዘመን ነው። ለዚህም በአባይ ወንዝ አንዱ ገባር የሆነው የፍንጫ ግድብን ማንሳት ይቻላል።
ፎቶ፡ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ገፅታ (ጸጋዬ ሐጎስ 2017)
የነበረው የፊውዳል ሥርዓት በዚህ ዘመን በበጎ የማይወሳ ቢሆንም፤ ከስሙ በስተቀር የዛሬውን የአባይን ግድብ ጨምሮ በርካታ የኤሌክትሪክ፥ የመስኖ፥ የመንገድ መሰረተ ልማት እና የዘመናዊ ከተሞች ግንባታና አስተዳደር ጥናቶች የተሰሩት በቀዳማዊ እጼ ኃይለሥላሴ ዘመን ነበር። የአዲስ አበባው የቀለበት መንገድን ጨምሮ ማለት ነው። ተግባር የዋሉት ጥናቶችም እንደዛሬው ለርካሽ ፖለቲካ ፍጆታ ታስበው የሚሰሩ ርካሽና መናኛ ሳይሆኑ ትውልድ የቀጣይ ትውልድን ተጠቃሚነትንም ታሳቢ ያደረጉ ነበሩ። በዛ ኋላቀር ፊውዳላዊ አስተዳደር ውስጥ ትውልድ ተሻጋሪ ስራዎች ዛሬም ህያው ምስክር ናቸው። ከከተማ እቅዶች በደርግ ያልተተገበረውና በኢህአዴግ ለሌቦች የገቢ ምንጭነት ታስቦ ትውልድ እና ታሪክ ነቃይ ተደርጎ በኢህአዴግ የተበለሻሸው የአዲስ አበባ መሪ ፕላን፥ ከሞላ ጎደል ተግባራዊ የተደረጉት የባህርዳርና የአዋሳ ከተማን መሪ እቅድ ጥናትን መጥቅስ ይቻላል። ከመስኖ ግድቦች መካከል ለግማሽ ምዕተ ዓመት ያህል አገልግሎት እየሰጡ ያሉትን የወንጂ፥ መተሐራ እና ፊንጫ መስኖ ግድቦችን ጥናትና ተግባርንም መጥቀስ ይቻላል። ይህ ሲባል ግን የነበረው ሥርዓት በሁሉም ዘርፍ ፍፁም ምሉዕ ነው ማለት አይደለም። በአስተዳደር በኩል እጅግ ኋላቀር ቢሆንም፤ የተሰሩ ፕሮጀክቶችና ጥናቶች ግን ዛሬም ድረስ የምንኮራባቸውና ትውልድ ተሻጋሪ መሆናቸውን ለመጠቆም እንጂ። ምክንያቱም ዛሬ የሌቦች አገዛዝ መፈንጫ የሆነው እና የምንናፍቀው የዛሬው የህዳሴው ግድብም የዛ ዘመን ጥናት ውጤት ነው።
በአሜሪካውያኑ የዘርፉ ባለሙያዎች በ1956 ዓ. ም. .ከነበሩ የአባይ ወንዝ ልማት ጥናቶች መካከል አንዱ የሆነው የዛሬው የህዳሴ ግድብ የወቅቱን የተፈጥሮ ሁኔታ እና አቅምን ከግምት ሳያስገባ ወደተግባር የተገባ ይመስላል። በተለይ የነበውን የአረቡን ዓለም አብዮት ተከትሎ መጋቢት 2003 ዓ. ም. ወደ ስራ እንደተገባ ይፋ የተደረገው እና ብዙ ተስፋ የተጣለበት ይህ የአባይ (የህዳሴ) ግድብ ፕሮጀክት የሀገሪቱን ባለሙያዎችና የሚመለከታቸውን ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ አልነበረም። ከዛ ይልቅ ከፕሮጀክቱ ተቋራጮች እስከ ግብዓት አቅራቢዎች በሙሉ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ እስከ ዕለተ ሞታቸው ድረስ በሥልጣን ላይ የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ የኔ ከሚሏቸው አካላት በስተቀር ሌላው ማኅበረሰብ ገንዘብ ከማዋጣት ባለፈ ሌላ ተሳትፎ የለውም። በብዙ መልኩ የፕሮጀክቱ ሂደት በኢኮኖሚ ደረጃ በቀጥታ የህወሓት አገዛዝ እና የኔ የሚሏቸውን የጥቅም ተጋሪዎቻቸውን ተጠቃሚ ማድረጉ ግልፅ ነው። ከአዋጭነት፥ ጥቅል አካባቢያዊ ተፅዕኖ ግምገማ ላይም ግልፅነት የጎደለው ነው። በመሆኑም ከተግባራዊ ሥራው ይልቅ የፖለቲካ ፍጆታ ጫጫታው በብዙ ዕጥፍ ይልቃል። ለዚህም ይመስላል። በ 5 ዓመት ተጠናቅ አገልግሎት ይሰጣል ሲባል የነበረውና በርካታ ፖለቲካዊ ፍጆታ ሲባል ብቻ ይገለፁ ከነበሩ ይህን ያህል % ተጠናቀቀ ከሚል የመረጃ ጋገራ ሰለባ መሆኑ እሙን ነው። ይሄ ሁሉ ወቅቱን ባገናዘበ መልኩ ትውልድ ተሻጋሪ አሳታፊ ጥናት ተደርጎበት የተጀመረ ፕሮጀክት አልነበረምና።
የህዳሴው ግድብ ሥራው ሲጀመር ለሀገራችን ኢትዮጵያ ያለው አዋጭነት እና አገልግሎቱን በሚመለከት በንጉሱ ዘመን ወቅቱን ታሳቢ ደርጎ የተጠናውን ጥናት ከብተመንግሥት ዶሴ መዞ ከመተግበር ባለፈ አሁን ያለውን የመልከዓምድር፥ አቅም እና ነባራዊ ሁኔታውን ታሳቢ ያደረገ ተጨማሪ ጥናት ሳይካሄድ ተግባራዊ መደረጉን የሚያሳብቁ ጥቂት ምሳሌዎችን ማንሳት ይቻላል። የግድቡ ፕሮጀክት ይፋ ሲደረግ ሥራው ሲጠናቀቅ ግድቡ 5,250 ሜጋ ዋት ያመነጫል ተባለ። ከሶስት ዓመታት በኋላ ፕሮጀክቱ ተሻሽሎ 6,000 ሜጋ ዋት ነው የሚያመነጨው በሚል አገዛዙ ብዙ ተደሰኮረ። በዚህ ሳያበቃ ለምን እና እንዴት እንደሆን ነጋ በሌለበት ሁኔታ ባለፈው 2010 ዓ.ም. ደግሞ ግድቡ ሲጠናቀቅ 6,540 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪ ያመነጫል ተባለ። የጉድ ሀገር። ነግስ ሌላ ማሻሻያ አዲስ “ጥናት” ዕቅድ ይነገረን ይሆን? ከተቻለማ ግድቡ በስኬት ተጠናቆ ከዚህም በላይ ቢያመነጭ ደስተኞች ነን። መልካም ነገርን ማን ይጠላል? በተለይ 70 % ያህሉ የሀገራችን ዜጋ የኤሌኬትሪክ አገልግሎት ለማግኘት በሚናፍቅበት ሀገር የተባለው እውን ሆኖ በርካታ ወላጆቻችን በተለይ እናቶቻችን ከዱር እንጨት ለቀማና በጭስ ከመታፈን ቢገላግልልን ደስታውን አንችለውም ነበር። ነገር ግን ግድቡ በተባለው ጊዜ አልተጠናቀቀም። ኽረ እንደውም ሆድ ይፍጀው ተብሎ እንጂ ግድቡ የኤሌክትሪክ ግድብ እንኳ በቅጡ የማያውቁ፥ የፕሮጀክ ምንነትና አስተዳደር ከተራ ስርቆትና ዝርፊያ መለየት የተሳናቸው ሁሉ ያለከልካይ የሚናኙበት የ “ልማት‘” መርሃ ግብር ተደርጎ እንደነበር የቀድሞ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ኃላፊዎች ገመና ህያው ምስክር ነው።
ግድቡ ከፍተኛ የውሓ መጠንን በማከማቸት የሀገራችን ትልቁን እና ተፈጥሯዊውን ጣና ሐይቅ በሁለት እጥፍ የሚበልጥ ሰው ሰራሽ ሐይቅ እንደሚፈጥር ነው የተነገረው። ከአገልግሎቱ አኳያ ስናይ ኤሌክትሪ ማመንጨቱ ጥሩ ነው። ይበረታታል። ከዓሳ ምርትና መዝናኛ በስተቀር ሌላ ተጨማሪ አገልግሎት እንዳለው የሚያመለክት ጥናትም ሆነ መረጃ የለም። ግን ለምን? የፕሮጀክቱ አንዱ ክፍተት የተለያዩ የሚመለከታቸው አካላት ያልተሳተፉበት ብቻ ሳይሆን ግድቡ አጠቃላይ አዋጭነቱ ላይ በርካታ የተሸፋፈኑ ነገሮች ይስተዋላል። ምናልባት ከብሔራዊ ጥቅምና ደህንነት አኳያ የተወሰኑ ነገሮች በአመራሮችና በፕሮጀክቱ መሪዎች ሊያዙ ይችል ይሆናል። ነገር ግን ከብሔራዊ ጥቅምና ደህንነት ውጭ ዜጎቼ ሊያውቁት የሚገባ ጉዳይ ዛሬም የሚነሳ አይመስልም።
ግድቡ ወደፊት በሀገራችን ላይ ተጨማሪ ወጪ እንዳያስከትል ከወዲሁ በቂ የሆነ የአካባቢ ጥበቃ ስራ አልተከናወነም። ለዚህም ማሳያ ግድቡ ከመጀመሩ በፊት ጀምሮ በጣና ሐይቅ ላይ በከፍተኛ ደረጃ እየተራባ ያለው ባዕድ የውሃ አረም “እንቦጭ” ከጣና ሐይቅ በተጨማሪ የህዳሴው ግድብ ላይ ዋነኛ ስጋት ሊሆን እንደሚችል የፔሮጀክቱ ባለቤት የኢትዮጵያ ኤልክትሪ ኃይልን ጨምሮ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ቦታ የሰጡት አይመስልም። ምክንያቱም ዋነኛው አባይ ወንዝ ምንጭ ከግሽ አባይ ተራራ ይነሳ እንጂ አቋርጦ የሚያልፈው ጣና ሐይቅን ነው። በዛ ላይ ጣና ሐይቅ ለአባይ ወን 10 % ውሃ ያበረክታል። እንቦጭ አረሙ ደግሞ በከፍተኛ ደረጃ ውሃ በመያዝ በተፈጥሮ ያለውን የውሃ ፍሰት መጠን ከመቀነስ በተጨማሪ የግድቡን ኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራ የማስተጓጎል አቅም አለው። የጣና በለስ ግድብም ላይም ተመሳሳይ አደጋ ነው የተጋረጠው። ይሁን እንጂ ከሚምመለከተው መንግሥትና የፕሮጀክቱ ባለቤት ይልቅ ምስኪን ገበሬዎችና የአካባቢው የመብት ተሟጋቾች በስተቀር ትኩረት አልተሰጠውም። ስለዚህ በአባይ ወንዝ ላይ እየተገነባ ያለው የህዳሴ ግድብ ቀጣይት ከወዲሁ አደጋ ተጋርጦበታል። መንግሥት በበኩሉ በሐሰት የተጋገረ መረጃን በማሰራጨት ተጠምዶ ባለፈው ዓመት ይህ ከታሰበለት ጊዜ በላይ የዘገየው ፕሮጀክት “63%” ተጠናቋል ተብሏል። ምድር ላይ ያለው መረጃ ግን ይህን አያሳይም። እውነት ነው፤ ብሳሊኒ ኩባንያ እየተሰራ ያለው የሲቪል ምህንድስና ግድቡ ግንባታ የተባለውን ያህል ባይሆንም ጥሩ በሚባል ደረጃ ቢሆንም ከግድቡ ጋር የተያያዙ የተለያዩ ሥራዎች ግን ዛሬም ምን ላይ እንዳሉ አይታወቅም። ምክንያቱም ትኩረቱም ሆነ እንቅስቃሴው ሁሉ ይታይ የነበረው የኃይል ማመንጫ ተርባይኖች የሚገጠሙበት የምህንድስና ግንባታ ብቻ ነውና። ይሁን እንጂ ሰው ሰራሽ ሐይቅ /ውሃ ማጠራቀሚያ ያለው የውሃ ኃይል ፕሮጀክት ግንባታ የአገልግሎቱ ጥራቱ ቀጣይነት ይኖረው ዘንድ የተለያዩ ባለሙያዎች የሚሳተፉበት በርካታ ሥራዎች ያሉት ዘርፍ ነው።
አሁንም ቢሆን መንግሥት ቢዘገይም ግድቡ ቢያንስ በታሰበለት ጊዜ ባይጠናቀቅም፤ በተሻላ ጥራት በተሳካ ሁኔታ ይጠናቀቅ ዘንድ ከግድቡ ባለቤት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በተጨማሪ ሌሎች የሚመለከታቸው ባለሙያዎች ቢጎበኝና ምክረ ሐሳብ ቢታከልበት የበለጠ ስኬታማ ይሆናል። በተለይ ዘርፍ ያሉ ኢትዮጵያውያን የምህንድስና፥ የውሃ ሃብት፥ የአካባቢና የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃና እንክብካቤ፥ የማኅበራዊና ኢኮኖሚ ባለሙያዎችን በውጭም ይሁን በሀገር ውስጥ ያሉ ቢያንስ አንጋፋ ባለሙያዎችን ጋብዞ ቢያስጎበኝ፥ ከዛም አጋዥ/ደጋፊ ተጨማሪ ጥናትና ምክረ ሐሳቦች ቢታከሉበት የበለጠ ውጤታማ መሆን ይችላል። እስካሁን የተሰበሰበውና ጥቅም ላይ የዋለው የህዝብ ገንዘብም ቢሆን በተወሰነ ደረጃ በግልፅ ለህዝብ ቢገለፅ (ዝርፊያ እንደተፈፀመበት ቢታወቅም) ተጨማሪ ድጋፍ ለማግኘት ጥሩ ዕድል ሊፈጥር ይችላል። ግድቡ ለሀገሪቱ ያለው ጠቀሚታ ዘርፈ ብዙ ከመሆኑ አኳያ በፕሮጀክቱ ዙሪያ ያሉ ግልፅነትና ተጠያቂነት ጉዳይ ግን በጊዜ ሊፈተሽና ሊታረም ይገባዋል። ምክንያቱም የአባይ ወንዝ ለእኛ ለኢትዮጵያውያን በሀገር ውስጥ ያለ ግን ደግሞ በቁጭት የሚወሳ ተናፋቂ ወንዝ በመሆኑ ግድብ ሃብት ብቻ ሳይሆን የዘመናት በወንዙ ውሃ አልምቶ የመጠቀም ቁጭት የመፍትሄ አካል ተደርጎ የሚወሰድም ጭምር ነውና።