የሙስሊሙ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴዎች ፍርድ በአየር ለሌላ ጊዜ ተቀጠረ
የሙስሊሙ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴዎች የመጨረሻ ፍረድ ብይን ዛሬ ህዳር 23 ቀን 2006 ዓ.ም. ይሰጣል ተብሎ ቢጠበቅም ያለምንም ችሎት በአየር ላይ ለሌላ ጊዜ መቀጠሩ ታወቀ፡፡ ቀደም ሲል ጉዳዩ ልደታ ከሚገኘው ከፍተኛው ፍርድ ቤት አቃቂ ቃሊቲ በሚገኘው ደራርቱ ቱሉ ትምህርት ቤት አካባቢ በሚገኘው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በዝግ ችሎት እየታየ የነበረ ሲሆን፤ በብዙዎች ግምት የመጨረሻ የብይን ፍርዱ ልደታ በሚገኘው ፍርድ ቤት ይሆናል ተብሎ ሲጠበቅ በሁለቱም ፍርድ ቤት ችሎት አለመሰየሙ ታውቋል፡፡
ይሁን እንጂ ጋዜጠኞች፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች እና ዓለም አቀፍ ዲፕሎማቶች ጉዳዩን እንዳይከታተሉ በዝግ ችሎት ሲያደርግ የቆየው አቃቂ ቃሊቲ የሚገኘው ፍርድ ቤት ዛሬ በመዝገብ ቤት በኩል ለአንዱ ተከላካይ ጠበቃ የመጨረሻ ይሆናል የተባለውን የፍርድ ብይን ለታህሳስ 3 ቀን 2006 ዓ.ም. ያለ ምንም ችሎት በአየር ላይ ቀነ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ ተከላካይ ጠበቆችም ከፍርድ ቤት አሰራር ውጭ ያለምንም ችሎት ቀነቀጠሮ መሰጠቱ እንዳስገረማቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡
በወለጋ ሻምቡ ወህኒ ቤት አንድ ወታደር ሁለት አለቆቹን ገደለ
ትናንት ህዳር 24 ቀን 2006 ዓ.ም. ጠዋት በኦሮሚያ ክልል ወለጋ ውስጥ በሚገኘው ሆሮጉድሩ ወረዳ ሻምቡ ወህኒ ቤት አንድ ወታደር ሁለት አለቆቹን በመሳሪያ ገድሎ እጁን ሰጠ፡፡
ገዳዩ አለቆቹ በተደጋጋሚ በእስረኞች ላይ እና በሌሎች የበታች ሰራተኞች ላይ ጸደጋጋሚ በደል ሲፈፅሙ ይቃወም የነበረ ሲሆን ትናንት ግን እስካሁን በውል ባልታወቀ ምክንያት ሁለቱነብ አለቆቹን መግደሉን ምንጮቻችን ከስፍራው አስታውቀዋል፡፡ የወረዳው ፖሊሶች ዝርዝር መረጃውን እንዲሰጡን ተደጋጋሚ ጥረት ብናደርግም አልተሳካም፡፡
በአፍሪካ ትልቁ የንግድ ማዕከል በሆነው መርካቶ በደረሰ የእሳት አደጋ ንብረቶች ወደሙ
በአዲስ አበባ የሚገኘው የአፍሪካ ትልቁ የንግድ ማዕከል መርካቶ ዛሬ ህዳር 25 ቀን 2006 ዓ.ም. ከቀኑ 8፡00 ሰዓት በኋላ በመርካቶ ልዩ ቦታው ከምዕራብ ሆቴል ወደ በርበሬ በረንዳ በሚወስደው መንገድ ሐረር ሜትሮ ሆቴል ዓለም ሽንሽን እና ጌጣጌጥ በሚሸጡባቸው ሱቆች እና በተለምዶ ጆንያ ተራ እየተባለ በሚጠራው ቦታ በተነሳ የድንገተኛ ችሳት ቃጠሎ እስካሁን ግምቱ ያልታወቀ ንብረት አውድሟል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር እሳት እና ድንገተኛ አደጋ መከላከያ ድርጅት እሳቱን ለማጥፋት በቶሎ ባለመድረሱ ብዙ መትረፍ የሚገባቸው ንብረቶች ሊወድሙ መቻላቸው የታወቀ ሲሆን፤ ድርጅቱ በበኩሉ ወደ መርካቶ መሄጃ መንገዶች በመቆፋፈራቸው ለመዘግየቱ እንደምክንያት ተጠቅሷል፡፡ በአካባቢው ያሉ እማኞች በበኩላቸው ድርጅተሩ በከተማው መቼም ቢሆን በአፋጣን ደርሶ ውድመትን አድኖ አያውቅም፤ ብዙ ንብረት ማትረፍ ሲቻል ብዙ ጊዜ ሆን ብሎ በሚመስል መልኩ ይዘገያል የሚል ትችትን አቅርበዋል፡፡
በአዲስ አበባ የተጠራው ሰልፍ በፖሊስ ድብደባ እና እስር ተጠናቀቀ
ሰማያዊ ፓርቲ የሳውዲዓረቢያ መንግስት ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ በኢትዮጵያውያን ላይ እየፈፀመ ያለውን ግድያ፣ እስር እና እንግልት ለመቃወም ዛሬ አርብ ህዳር 6 ቀን 2006 ዓ.ም. አዲስ አበባ ወሎ ሰፈር በሚገኘው የሰውዲ ኤምባሲ ሊደረግ የነበረው የተቃውሞ ሰልፍ በፌደራል እና በአዲስ አበባ ፖሊስ ድብደባ እና እስር ተጠናቀቀ፡፡ ሰለፍ 4 ኪሎ ግንፍሌ ከሚገኘው የሰማያዊ ፓርቲ ጽህፈት ቤት ከረፋዱ 4፡00 ሰዓት ሲጀምር በበፖሊስ እገታ ተፈፅሞ ነበር፡፡ በመቀጠልም አራት ኪሎ ቅድስት ስላሴ ኮሌጅ ፊትለፊት ደግሞ በርካታ የፌደራል ፖሊሶች ዳግም እገታ ፈፀሙ፡፡
በመጨረሻም በእገታው ያልተበገረው የአዲስ አበባ ነዋሪ ወሎ ሰፈር በሚገኘው የሳውዲዓረቢያ ኤምባሲ አካባቢ ቢያመራም በ3 ፒክአፕ መኪና የመጡ የፈደራል ፖሊሶች የተገኘውን ህዝብ በያዙት ዱላ፣ በእጅ እና በእግር ድብደባ ጀመሩ፡፡ ከረፋዱ 5፡30 ሰዓት ላይ እዛውም የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች አቶ ይልቃል ጌትነት፣ አቶ ስለሺ ፈይሳ፣ አቶ ጌታነህ ባልቻ ፣ አቶ ወረታው ዋሴ፣ አቶ ብርሃኑ ተክለያሬድ፣ አቶ ዮናታን ተስፋዬ እና አቶ ሀብታሙ ደመቀ በፖሊስ ታስረው ተወሰዱ፡፡ በዚሁ ሰዓት ደራሲ አቶ አስራት አብርሃምም መታሰሩ ታውቋል፡፡
በሰልፉ ላይ ከተገኙ ነዋሪዎችም ቁጥራቸው ከ500 የማያንሱ ሰዎች ታፍሰው ላንቻ ፖሊስ ጣቢያ እና ጃንሜዳ ፖሊስ ጣቢያ መታሰራቸውን የሰማያዊ ፓርቲ የህግ ጉዳይ ኃላፊ አቶ ይድነቃቸው ከበደ ተናግረዋል፡፡ ፖሊስ ከቀኑ 10፡50 ሰዓት አካባቢ ከታሰሩት መካከል የተወሰኑትን መፍታት መጀመሩን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ይሁን እንጂ ይህ እስከተዘገበበት ሰዓት ድረስ ከተፈፀመባቸው ድብደባ በተጨማሪ የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮችን ጨምሮ በርካታ ሰዎች አሁንም እስር ላይ እንደሚገኙ ታውቋል፡፡
በዚህ ጉዳይ ላይ የመንግስት ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ ሽመለስ ከማል እና የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ አቶ አባተ ስጦታውን ለማናገር ብንሞክርም ስልካቸውን ባለማንሳታቸው አልተሳካም፡፡ በፖሊስ ድብደባ ተፈፅሞባቸው ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው በተለይ ከላንቻ አካባቢ ካለው ከፖሊስ ጣቢያ በሚኒባስ እየተወሰዱ መሆናቸውን የዓይን እማኞች የገለፁ ሲሆን፤ ወሎ ሰፈር በሚገኘው ሳውዲዓረቢያ ኤምባሲ አካባቢ የሚገኙ ነዋሪዎችም ተባባሪ ናችሁ በሚል አሁንም እየተለቀሙ እየታሰሩ መሆኑን ምንጮቻችንን አስታውቀዋል፡፡
ይህ ሁሉ ድርጊት ያበሳጫቸው የሰልፉ ታዳሚዎች እና ታዛቢዎች መንግስት ይሄንን ስፍ እራሱ ማስተባበር የሚጠበቅበትን ዜጎች በራሳቸው ፈቃድና ተነሳሽነት ድርጊቱን በመቃም መውጣታቸው ሊበረታታ ሲገባ መከልከሉ ኢህአዴግ ኢትዮጵያውያን በሳውዲዓረቢያ መንግስት እና ፖሊስ እደረሰባቸው ያለውን ግድያ፣ እስር እና ስቃይ እንደሚደግፈው በግልፅ ያረጋገጠበት ነው ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ የፊታችን እሁድ ህዳር 8 ቀን 2006 ዓ.ም. አንድነት ከሌሎች የመድረክ አባል ፓርቲዎች ጋር ተመሳሳይ ሰልፍ በዚሁ በአዲስ አበባ ወሎ ሰፈር በሚገኘው የሳውዲዓረቢያ ኤምባሲ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ መጥራታቸውም ታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች የመንግስትን ማጭበርበር አጋለጡ
ኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞች ዛሬ ጥቅምት 30 ቀን 2006 ዓ.ም. ከCPJ ፣ ከዶሃ ዓለም አቀፉ የሚዲያ ነፃነት ማዕከል እና ከሌሎች ዓለም አቀፍ የሚዲያ ተቋማት ተወካዮች ጋር በአዲስ አበባ ኢሊሊ ኢንተርናሽናል ሆቴል ተገናኝተው ተወያዩ፡፡ ጋዜጠኞቹ ለ3፡30 ሰዓት ያህል ስለኢትዮጵያ ሚዲያ አፈና፣ ስለጋዜጠኛች መከራ፣ እስርና ስቃይ እንዲሁም ስደት ከነነባራዊው ሁኔታ በዝርዝር ከነ ምክንያቱ ሰፊ ምክክር ተደርጓል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ትናንት ጥቅምት 29 ቀን 2006ዓ.ም በአፍሪካ የኢኮኖሚክ ኮሚሽን የተደረገው የአፍሪካ ሚዲያ ፎረም ላይ ነፃ ጋዜጠኞች እንዳልተጋበዙ እና የመንግስት ደጋፊዎች እንዲሳተፉ መደረጉን እንዲሁም ከነፃ ሚዲያ ከ3 ያልበለጡ በእንግሊዘኛ የሚዘጋጅ ሚዲያ አዘጋጆች በሌላ አካል እንዲሳተፉ መደረጉን፣ መንግስት ሚዲያውን ከማፈኑ በተጨማሪ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣ ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ፣ ጋዜጠኛ ርዕዮት አለሙ፣ ጋዜጠኛ ዩሱፍ ጌታቸውን ጨምሮ 6 ጋዜጠኖች ከጋዜጠኝነት ስራ ጋር በተያያዘ መታሰራቸው እና በተለያየ ጊዜም የተለያዩ ጋዜጠኞች እየታሰሩ እንደሚፈቱ ተጠቁሟል፡፡
በዚህም ዙሪያ በአፍሪካ ሚዲያ ፎረም ላይ ስለተጋበዙ ስለኢትዮጵያ ጋዜጠኞች እና ሚዲያ አፈና የተሳሳተ ዘገባ እንዳያቀርቡ እውነታውን ከ15 ያላነሱ ጋዜጠኞች አብራርተዋል፡፡ በዚህም ጋዜጠኖቹ የመንግስትን ማጭበርበር በማጋለጣቸው፤ ተወካዮቹ እውነታውን ለዓለሙ ማኀበረሰብ እነምደሚያቀርቡ እና ይህንንም በይበልጥ ለለጋስ ሀገሮች እንደሚያሳውቁ በማረጋገጥ ውይይቱ በተሳካ ሁኔታ ተጠናቋል፡፡
