በባህርዳር በተደረገ የተቃውሞ ሰልፍ የሰው ህይወት ሲጠፋ፤ በአዲስ አበባም ተቃውሞ ተደርጓል
ዛሬ አርብ ታህሣሥ 10 ቀን 2007 ዓ.ም. ባህርዳር ከተማ ቀበሌ 04 እየተባለ የሚጠራው አካባቢ የሚገኘውን የጥምቀት ባህር ታቦት ማደሪያ መንግስት ለባለሀብት ይሰጣል መባሉን ተከትሎ ህዝቡ ለተቃውሞ አደባባይ ላይ ቢወጣም፤ የመንግስት ፖሊሶች በሰላማዊ ሰለፈኞቹ ላይ በከፈቱት ተኩስ እስካሁን 3 ዜጎች መገደላቸው ሲነገር፣ አዛውንት መነኩሴን ጨምሮ በርካቶች ከመንግስት በተተኮሰ ጥይት መቁሰላቸውን ምንጮች ከስፍራው አስታውቀዋል፡፡ ለተቃውሞ የወጡ ሰላማዊ ሰልፈኞቹ ከመነሻው እየዘመሩ ወደ ጥምቀተ ባህር ታቦት ማረፊያ ሲሄዱ የመንግስት ፖሊሶች ሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፉን ለማስቆም በሚል በወሰዱት የተኩስ ኃይል እርምጃ አማረ ያዜ የተባለ ወጣት ወዲያው ሲሞት፤ ሌሎች 2 ሰዎችም ሆስፒታል ደርሰው መሞታቸው ተጠቁሟል፡፡ እንደ ባህርዳር ሆስፒታል ምንጮች ጥቆማ ከሆነ የሟቾች ቁጥር ከ3 ወደ 5 እንዳሻቀበ የተገለፀ ሲሆን፤ ከ8 ያላነሱ ቆስለው የመጀመሪያ የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው እንደነበር አስታውቀዋል፡፡
የአማራ ክልል አስተዳደር የቤተ ክርስቲያን ንብረት የሆነውን የታቦት ማደሪያ ከፊሉን ለመንገድ ማስፋፊያ ቀሪውን ለባለሃብትና ለጥቃቅንና አነስተኛ ሱቆች መስሪያ እንዲነጠቅ ማዘዙን ተከትሎ በቤተ ክርስቲያኗ በተደረገ ጥሪ የተቃውሞ ሰልፉ መካሄዱን መረጃዎች አመልክተዋል፡፡ ይሁን እንጂ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፉን ለማስቆም ፖሊስ በወሰደው ሰልፍ በወጣው ምዕመናን ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱ ታውቋል፡፡ በመጨረሻም የአማራ ክል መስተዳደርና የባህርዳር ከተማ መስተዳደር በጋራ በተሸከርካሪ መኪና በመንቀሳቀስና ባርዳር በሚገኘው በአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት በተለይም በሬዲዮ በጥምቀተ ባህር ታቦት ማረፊያ ስፍራው ሊካሄድ የታሰበው የመንግድ ማስፋፊያ ቀርቷል ሲል ማወጁ ተጠቁሟል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የፌደራል መንግስት በበኩሉ በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቴቪ) ባሰተላለፈው ዜና በተፈጠረው ችግር አንድ ሰው ብቻ መሞቱን ሲያምን የሌሎች ሟቾችንና ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸውን በተመለከተ ያለው ነገር የለም፡፡ እንደ ዓይን እማኞች ገለፀ ከሆነ የሟቾችና ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ቁጥር ከተጠቀሰው እንደሚጨምርና በሰልፉ ላይ ከነበሩት መካከል ከ30 የማያንሱ ሰዎች በፖሊስ ታፍሰው ወዳልታወቀ ስፍራ ለእስር መወሰዳቸውን እማኞች ለአዲስሚዲያ ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ የፌደራል መንግስት በበኩሉ ቀደም ሲል በ2፡00 ሰዓት የዜና እወጃው ላይ ካስተላለፈው ዜና በተቃራኒ ስራው ሊከናወን የነበረው ከኋይማኖቱ አባቶች ጋር በተደረገ መግባባትና ስምምነት እንደሆነ እና የጥምቀተ ባህር ታቦት ማረፊያን እንደማይነካ ከየትኛው ደብርና ገዳም እንደሆኑ ያልተገለፁ የተወሰኑ ቀሳውስትን ምስል በማሳየት ስራው ሊቀጥል እንደሚችል ፍንጭ ሰጥቷል፡፡ በዜና እወጃው በሰልፉ የተገኙትንም ሆነ ጉዳት የደረሰባቸውንም ሲወነጅል ተሰምቷል፡፡
በተያያዘ ዜና በአዲስ አበባ ፒያሳ አካባቢ በሚገኘው ኑር (ቤኒ) መስኪድ ህዝበ ሙስሊሙ ድንገት በመንግስት ላይ ተቃውሞ ማሰማቱ ታውቋል፡፡ ለዓመታት የቆየው ህዝበ ሙስሊሙ የመንግስት በኃይማኖት ጣልቃ ገብነት በሰላማዊ መንገድ በተከታታይ ያሰማ የነበረውን ተቃውሞ ለተወሰነ ጊዜ ረገብ ያለ ቢመስልም ዛሬ አርብ ታህሣሥ 10 ቀን 2007 ዓ.ም. የተለመደ ሰላማዊ ተቃውሞውን ማሰማት ቀጥሏል፡፡ ህዝበ ሙስሊሙ መንግስት በኋይማኖት ጉዳይ ጣልቃ መግባቱን እንዲያቆም ከጥር 1 ቀን 2004 ዓ.ም. ጀምሮ ሲካሄድ የነበረው ሰላማዊ ተቃውሞ ምላሽ ባለመገኘቱ ዛሬም ድንገት ሰላማዊ ተቃውሞ መቀጠሉ ታውቋል፡፡ መንግስት ከሙስሊሙ ማኀበረሰብ ተወካዮቻቸው ጋር ለተወሰነ ጊዜ ሲደራደር ቆይቶ በመጨረሻ የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴዎቹን በሙሉ አስሮ ክስ መመስረቱንና እስካሁንም እልባት እንዳልተገኘለት አይዘነጋም፡፡
ብሎገሮቹ እና ጋዜጠኞቹ ተጨማሪ 20 ቀናት ቀነ ቀጠሮ ተሰጣቸው
∙ተሻሻለ በተባለው ክስ ላይ አስተያየት ተሰጥቶበታል
በሶልያና ሽመልስ የክስ መዝገብ የሽብር ክስ ተመስርቶባቸው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ የሚገኙት የዞን 9 ጦማርያን እና ጋዜጠኞች ተጨማሪ 20 ቀናት ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቶባቸዋል፡፡
ዛሬ ታህሳስ 7 ቀን 2007 ዓ.ም ለ13ኛ ጊዜ በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት የቀረቡት ጦማርያኑና ጋዜጠኞች በጠበቆቻቸው አማካኝነት ቀደም ብሎ ተሻሽሎ በቀረበባቸው ክስ ላይ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
የተከሳሽ ጠበቆችም ተሻሻለ በተባለው ክስ ላይ አስተያየታቸውን በጽሑፍ አቅርበዋል፡፡ ጠበቆቹ አስተያየታቸውን በጽሑፍ ከማቅረባቸው በተጨማሪ በቃል ለችሎቱ ለማስረዳት ጠይቀው የነበር ቢሆንም ፍርድ ቤቱ፣ ‹‹በጽሑፍ ካቀረባችሁ በቃል መድገም አያስፈልግም›› በሚል ሳይፈቅድላቸው ቀርቷል፡፡
ጠበቆቹ ‹‹ተሻሻለ የተባለው ክስ ምንም መሻሻል የለውም›› በማለት ለፍርድ ቤቱ ለማስረዳት ቢሞክሩም፣ ችሎቱ ንግግራቸውን አቋርጦ ‹‹ክሱ በታዘዘው መሰረት መሻሻል አለመሻሻሉን መርምሮ የሚወስነው ፍርድ ቤቱ ነው›› ሲል አስረድቷል፡፡
በዚህም መሰረት ፍርድ ቤቱ በተከሳሽ ጠቦቆች የቀረበውን አስተያየትና ቀደም ብሎ ለአቃቤ ህግ ክሱን እንዲያሻሽል የሰጠውን ትዕዛዝ በማገናዘብ ጉዳዩን መርምሮ ክሱ በምን አግባብ እንደተሻሻለ አይቶ ብይን ለመስጠት ለታህሳስ 27 ቀን 2007 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል ሲል የነገረ- ኢትዮጵያ ዘገባ አመልክቷል፡፡
መድረክ በአዲስ አበባ የጠራው የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ተጠናቀቀ
የ6 የፖለቲካ ድርጅቶች ግንባር የሆነው የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሚክራሲያዊ አንድነት ግንባር (መድረክ)እሁድ ታህሣሥ 5 ቀን 2007 ዓ.ም. በአዲስ አበባ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ አደረገ፡፡ መድረክ ሰልፉን ያደረገው ከጠዋቱ 3፡00 ሰዓትት ጀምሮ ሲሆን፤መነሻውን ከ4 ኪሎ ግንፍሌ ድልድይ አድርጎ በአዋሬ አልፎ መዳረሻውን በየካ ክፍለ ከተማ ልዩ ቦታው የጥምቀተ ባህር ታቦት ማደሪያ አካባቢ በሚገኘው ኳስ ሜዳ ላይ መከናወኑ ተጠቁሟል፡፡
የግንባሩ መረጃዎች አንንደሚያመለክቱት በሰልፉ ላይ ከ8 ሺ በላይ የአዲስ ኣበባ ነዋሪዎች መሳተፋቸው ተጠቁሟል፡፡ በሰልፉ ላይ ከተጋበዙ ፓርቲዎች መካከል የአንድነት ፓርቲ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዘዳንት አቶ ተክሌ ና የፓርቲው አመራርና አባላትን ጨምሮ ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲ አባላትም መሳተፋቸው ተጠቁሟል፡፡ የመድረኩ ሰላማዊ ሰልፍ በወጣቶች የመድረክ አመራር፣ የሴቶች ተወካይ፣ አቶ ቡልቻ ደመቅሳና የወቅቱ የመድረክ ሊቀ መንበር ፕሮፌሰር በየነ ዼጥሮስ ባሰሙት ንግግሮች መጠናቀቁን ምንጮች ከስፍራው አስታውቀዋል።
ሰላማዊ ሰልፉ የኢህኣዴግ መንግስት ሊያርማቸው የሚገቡ፣ መመቻቸት ያሉባቸው ፖለቲካዊ ምህዳር፣ መወገድ ያለበት የፀረ ሽብር ህግ ፣የ2007 ዓ.ም. ምርጫ ፍትሃዊ እንዲሆን ሊያደረጉ የሚገቡ ስራዎች እንዲሰሩ፣ በየቦታው እያጋጠመ ያለው አፈና፣ እስርና እንዲሁም ግድያዎች እንዲቆሙ በሰልፉ ላይ ከተሰሙ መፈክሮች በተጨማሪ የመድረኩ አመራሮች ጥሪ ማቅረባቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡
አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) ጠቅላላ ጉባዔ ተጠናቀቀ
አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) ከታህሣሥ 3-4 ቀን 2007 ዓ.ም. ያደረገው አስቸኳይ ልዩ ጠቅላላ ጉባዔ ተጠናቀቀ፡፡ ፓርቲው በተከታታይ ቀናት መዋቅሩን ከዘረጋባቸው ከአራቱም የሀገሪቱ አቅጣጫዎች በመጡ አባላቱ ባደረገው ልዩ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ የተለያዩ አጀንዳዎችን በማፅደቅ ውሳኔዎችን ያሳላፈ ሲሆን፤ በተለይም የቀድሞው የፓርቲው ፕሬዘዳንት ኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራው በገዛ ፈቃዳቸው ስልጣናቸውን ከለቀቁ በኋላ በፓርቲው ብሔራዊ ምክር ቤት የተመረጡትን ፕሬዘዳንት አቶ በላይ ፈቃዱን ስልጣን ከነ ስራ አስፈፃሚዎቹ አፅድቋል፡፡ ሌላው ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የጠቅላላ ጉባዔ አባላትን ቁጥር በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ በአባላቱ ተወስኖና የፀደቀው ደንቡ ላይ ሰፍሮ ይቅረብልኝ ባለው መሰረት ተወስኖ እንዲሰፍር መደረጉ ተጠቁሟል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከዋና አጀንዳዎቹ መጠናቀቅ በኋላ ፓርቲው በአመራር አባላቱ ለጠቅላላ ጉባኤ አባላት በሀገሪቱ ነባራዊ ሁኔታዎች(የአርሶ አደሩ ፤የከተማው ነዋሪ፤የባለሐብቱ ሁናቴ) በዳግማዊ ተሰማ፣ የተማሪውና የምሁሩ ነባራዊ ሁኔታ በጋዜጠኛ አናንያ ሶሪ፣ የአንድነት የምርጫ ስትራቴጂ ግብ በፓርቲው ፕሬዝዳንት አቶ በላይ ፈቃዱ መቅረቡ ታውቋል፡፡

በመቀጠልም የስልጠናው ተሳታፊዎች ጥያቄና አስተያየት በመስጠት ስልጠና ተጠናቆ፣ በፓርላማ ብቸኛው የተፎካካሪ ፓርቲ ተወካይና የአንድነትፓርቲምክትል ፕሬዝዳንት የተከበሩ አቶ ግርማ ሰይፉ በምርጫ ስትራቴጂ ዙሪያ ስልጠና ሰጥተዋል፡፡አባላቱ የፓርቲው የህግና ሰብአዊ መብት ጉዳይ ምክትል ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ገበየሁ ይርዳው የአባላት መብትና ግዴታ ከፓርቲው ደንብና ከፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ አንጻር ስልጠና ከሰጡ በኋላ መድረኩ ለውይይት ክፍት ሆኖ በስልጠናዎቹና ወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት መደረጉን የደረሱን መረጃዎች አመልክተዋል፡፡

በመጨረሻም የፓርቲው ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ተክሌ በቀለ የጉባኤውን የመዝጊያ ንግግር በማድረግ አንድነት በብሔርም ሆነ በህብረብሔር ፓርቲዎች ጋር አብሮ ለመስራት መዘጋጀቱንና ከአንድነት ፓርቲ ጋር ተመሳሳይ የፖለቲካ ፕሮግራም ላላቸው ፓርቲዎች ሁሉ የውህደት ጥያቄ ማቅረባቸው ተጠቁሟል፡፡ አቶ ተክሌ አንድነት ፓርቲ የ2007 ዓ.ም. ምርጫን በአሸናፊነት ለመወጣት እየሰራ እንደሚገኝና አባላቱም በያሉበት ጠንክረው የበኩላቸውን እንዲወጡ በማሳሰብ ጉባዔው በስኬት መጠናቀቁን ፓርቲው አስታውቋል፡፡
የታሰሩት የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና አባላት በመታወቂያ ዋስ ከእስር ተፈቱ
መንግሥት ያስተላለፈውን ጥብቅ ትዕዛዝ በመተላለፍ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለመጣስ ሙከራ አድርገዋል በሚል ተጠርጥረው ከታሰሩ በኋላ ከሰባት እስከ 14 ቀናት ተጨማሪ ጊዜ ቀጠሮ የተጠየቀባቸው ከዘጠኝ ፓርቲዎች የተውጣጡ አመራሮችና አባላት፣ ታኅሣሥ 1 እና 2 ቀን 2007 ዓ.ም በመታወቂያ ዋስ ከእስር ተፈቱ፡፡
የሰማያዊ ፓርቲና የዘጠኙ ፓርቲዎች ጥምረት ሊቀመንበር ኢንጂነር ይልቃል ጌትነትን ጨምሮ፣ በአምስት ፖሊስ ጣቢያዎች ታስረው የሰባት፣ አሥርና 14 ቀናት ጊዜ ቀጠሮ የተጠየቀባቸው 84 እስረኞች በሁለቱ ቀናት ውስጥ የተፈቱ ሲሆን፣ ከአንድ መቶ በላይ የሚሆኑ ለሰላማዊ ሠልፉ ወጥተው ታስረው የነበሩ ሰዎች ሁኔታቸው እየተጣራ ኅዳር 28 እና 29 ቀን 2007 ዓ.ም. መፈታታቸውም ታውቋል፡፡
ህዳር 27 ቀን 2007 ዓ.ም. ከቀኑ ስድስት ሰዓት ጀምሮ እስከ ኅዳር 28 ቀን 2007 ዓ.ም. ከቀኑ ስድስት ሰዓት ለ24 ሰዓታት፣ የዘጠኙ ፓርቲዎች ጥምረት ሊያደርግ ለነበረው ሰላማዊ ሠልፍ ቅስቀሳ ወጥተው የታሠሩ ሦስት የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ግን አለመፈታታቸው ታውቋል፡፡ የሰማያዊ ፓርቲ የአዲስ አበባ ምክር ቤት ጸሐፊ አቶ ማቲያስ መኩሪያ፣ የምርጫ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ አባል አቶ ባህሩ እሸቱና አቶ ሲሳይ ዘርፉ ናቸው፡፡
ሦስቱ የፓርቲው አባላት የታሰሩት ለሰላማዊ ሠልፉ ቅስቀሳ ወጥተው በመሆኑ ሌሎቹ ሲፈቱ መፈታት ቢኖርባቸውም፣ ፖሊስ ለሁለተኛ ጊዜ የሰባት ቀናት ተጨማሪ ጊዜ ጠይቆባቸው አለመፈታታቸው ተገልጿል፡፡
የታሰሩት የፓርቲዎቹ አመራሮችና አባላት በወቅቱ ከፍተኛ ድብደባ እንደደረሰባቸውና እንደተጎዱ የተገለጸ ቢሆንም፣ የሰማያዊ ፖርቲ አባላት ከሆኑት አቶ ብርሃኑ ተክለያሬድና ወ/ሪት እየሩስ ተስፋው በስተቀር፣ ሌሎቹ ደህና መሆናቸው ታውቋል፡፡ ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት ሰውነታቸው ጉዳት እንዳለውና ሕመም እንደሚሰማቸው ከመናገራቸው ውጪ የከፋ ጉዳት እንዳልደረሰባቸው የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበርና የምርጫ ጉዳይ ኃላፊ አቶ ስለሺ ፈይሳ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ምንጭ፡- ረፖርተር