በሚዛን 2ኛ ደረጃ እና መሰናዶ ትምህርት ቤት ተዘጋ
በደቡብ ክልል በቤንች ማጂ ዞን በሚገኘው ሚዛን 2ኛ ደረጃ እና መሰናዶ ትምህርት ቤት ከሚያዚያ 10 ቀን 2005 ዓ.ም. ጀምሮ መዘጋቱ ታውቋል፡፡ እንደፍኖተ ነፃነት ምንጮች ገለፃ ከሆነ ከሚያዚያ 7 ቀን 2005ዓ.ም. ጀምሮ በትምህርት ቤቱ ተማሪዎችና አስተዳደር አካላት በተነሳ አለመግባባት ከፍተኛ እረብሻ በመፈጠሩ እንደሆነ ተገለፀ፡፡ ለረብሻው መንስኤው የትምህርት ቤቱ ከአሜሪካ በተሰጠው የትምህርት ዕድል የ12ኛ ክፍል የመሰናዶ ተማሪዎች መካከል በተደረገው ውድድር ከሴቶች ተማሪ መድኃኒት ስታሸንፍ ከወንዶች ደግሞ በጀመሪያ ተማሪ ጌታመሳይ ማሸነፉ ከተጠቆመ በኋዋላ በተደረገ የውጤት ማጣራት ሂደት ተማሪ ዮሐንስ ማለፉ ተጠቁሟል ፡፡ ይህንንም ተከትሎ በተለይ የውድድሩ አዘጋጅ ኮሚቴ በወንዶች ተማሪ ዮሐንስና ተማሪ ጌታመሳይ ውድድር ላይ የውጤት አሰራር ስህተት በመኖሩን በተማሪዎችና በትምህርት ቤቱ መምህራንና አስተዳደር አካላት መካከል በተፈጠረ አለመግባባት መማር ማስተማሩ ሂደት መቋረጡ ተጠቁሟል፡፡ በመጨረሻም በተደረገው የውጤት ማጣራት መሰረት በውድድሩ ያለፈው ተማሪ ዮሐንስ መሆኑንም ምንጮቻችን አስታውሰዋል፡፡
ከረብሻው ጋር በተያያዘ ሚያዚያ 11 ቀን 2005ዓ.ም. በትምህርት ቤቱ አካባቢ ተኩስ መከፈቱና በተፈጠረ ግጭትም 3 ተማሪዎች ቆስለው ወደህክምና ጣቢያ መወሰዳቸው ተገልፁዓል፡፡ ይህን ዜና እስከዘገብንበት ድረስም ትምህርት ቤቱ በፌደራል ፖሊስ መከበቡ ተጠቁሟል፡፡ ይህንንም በሚመለከት የትምህርት ቤቱ ዋና ርዕሰ መምህር የሆኑት አቶ አብዱ ካሣ ስለጉዳዩ ስናነሳላቸው አሁን ስለማልችል ከ30 ደቂቃ በኋላ መልሳችሁ ደውሉ ካሉ በኋዋላ ሽልካቻን በመዝጋታቸው ምላሻቸውን ማካተት አልቻልንም፡፡ ምክትላቸው አቶ አበራ ጉልማንም ለማናገር ጥረት ብናደርግም ስልካቸውን ጆሯችን ላይ ዘግተዋል፡፡
የነ አቶ በቀለ ገርባ ይግባኝ ክስ ለሌላ ጊዜ ተቀጠረ
የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረንስ(ኦፌኮ) ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር፣ የመድረክ ከፍተኛ አመራርና የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህር የሆኑት አቶ በቀለ ገርባ፣ የኦፌኮ አመራር አባል የሆኑት አቶ ኦልባና ሌሊሳን ጨምሮ ወጣት ወልቤካ ለሚ፣ አደም ቡላ፣ ደረጀ ከተማ፣አዲሱ ምክሬ፣ገልገሎ ጉፉ፣ መሐመድ መሉ እና ወይዘሪት ሐዋ ዋቆ በፌደራሉ አቃቤ ህግ በሽብርተኝነት ክስ ተመስርቶባቸው በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ ወንጀል ችሎት የጥፋተኝነት ውሳኔ የተወሰነባቸውን ክስ በመቃወም ይግባኝ ቢጠይቁም እስካሁን ውሳኔ አላገኙም፡፡ በዚህም ምክንያት ይግባኝ የጠየቁት ክስ 6 ኪሎ በሚገኘው በፌደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት አቶ በቀለ ገርባ ለሚያዚያ 14 ቀን 2005ዓ.ም. የተቀጠረ ሲሆን የአቶ ኦልባና ሌሊሳ ደግሞ ለሚያዚያ 16 ቀን 2005ዓ.ም. ክርክር ለማድረግ ተቀጥሯል፡፡ በዚህ የክስ መዝገብ ያሉ ሌሎች ስድስት ተከሳሾች ይግባኝ ቢጠይቁም እስካሁን የተሰጠ ቀነ ቀጠሮ አለመኖሩ ታውቋል፡፡ አቶ በቀለ ገርባ ቀደም ሲል በከፍተኛው ፍርድ ቤት የተወሰነባቸው ቅጣት 8 ዓመት ሲሆን አቶ ኦልባና ሌሊሳ ደግሞ 13 ዓመት ፅኑ እስራት መሆኑ ይታወቃል፡፡
በተያያዘ ዜና በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ ወንጀል ችሎት በፌደራሉ አቃቤ ህግ በሽብርተኝነት ክስ ተጠርጥረው በተሸለ በከሺ የክስ መዝገብ ክስ የተመሰረተባቸው አቶ ተሸለ በከሺ፣ሐሰን መሐመድ፣ አለማየሁ ጋሮምሳ፣ ልጅዓለም ታደሰ፣ ቶሎሳ በቾ እና ወጣት ሙላታ አብዲሳን ጨምሮ 69 ተከሳሾች ሚያዚያ 11 ቀን 2005ዓ.ም. የመከላከያ ምስክር ለመስማት ቀነ ቀጠሮ የተሰጠ ቢሆንም ፍርድ ቤቱ ለሰኔ 27 ቀን 2005ዓ.ም. ተለዋጭ ቀነ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ በዚህ የክስ መዝገብ የኦፌኮ አባላትን ጨምሮ የቀድሞ የፓርላማ አባል የሆኑት የተከበሩ አቶ ጉቱ ሙሊሳ ይገኙበታል፡፡ ተከሳሾቹ የፍርድ ውሳኔ ሳያገኙ ከሚያዚያ 19 ቀን 2003ዓ.ም. ጀምሮ በፍርድ ቤት እየተመላለሱ እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡
የሲዳማ አርነት ንቅናቄ(ሲአን) ምርጫ ቦርድ ገለልተኛ አለመሆኑን በተደገፈ ማስረጃ አጋለጠ
የሲዳማ አርነት ንቅናቄ(ሲአን) ሚያዚያ 11 ቀን 2005ዓ.ም. አዲስ አበባ በሚገኘው የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ(አንድነት) ዋና ጽህፈት ቤት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ገለልተኛ እንዳልሆነ በተደጉ በርካታ ማስረጃዎች አስታውቋል፡፡ ፓርቲው የሚያዚያ 2005ዓ.ም. የአዲስ አበባ፣ ድሬዳዋ አስተዳደርና የአካባቢ ምርጫ ላይ በደቡብ ክልል ሲዳማ ዞን ለመወዳደር ወደምርጫው ቢገባም በቅስቀሳው ወቅት አባሎቹ ላይ ኢህአዴግ ከፍተኛ ማስፈራራት፣ እንግልት፣ እስርና ግድያ እየፈፀመ በመሆኑ አቤቱታውን ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ወዲያው ቢያሳውቅም መፍትሄም ሆነ ምላሽ ሊሰጥ ባለመቻሉ የኢህአዴግ አምባገነንነት ተጠናክሮ መቀጠሉን አስታውሷል፡፡ በዚህም በዞኑ ለሚገኘው ዳሌ ወረዳ ምክር ቤት ዕጩ ተዋዳዳሪ የሆኑት አቶ ተሸመ ሳታና ባካባቢው ባለስልጣናት ከፍተኛ ማስፈራሪያና ከምርጫው እራሱን እንዲያገል በተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ከሰጡ በኋላ በጥይት ገድለውት የውሃ ጉድጓድ ውስጥ በመጨመር የአስከሬን ምርመራ እንኳ እንዲደረግ አጥብቀን ብንጠይቅም ፖሊስ ቶሎ እንዲቀበር አድርገዋል ሲል የተፈፀመበትን ጠቁሟል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ዕጩ ተወዳዳሪ የመንግስት ሰራተኞች ከስራ እንዲፈናቀሉ ተደርገዋል፣ ህገወጥ የስራ ቦታ ዝውውርም ተፈፅሞባቸዋል ፣ በግፍ እንዲታሰሩ ተደርገው ተፈርዶባቸዋል፤ በሲአን ስብሰባ ተካፍላችኋል በሚል 3 ሴት ተማሪዎችና 4 ወንድ ተማሪዎች ለሁለት ዓመት ከትምህርት ገበታቸው ታግደዋል፣ ሌሎችም እስራት በመፍራትም መሰደዳቸውን በመግለጫው አስታውቀዋል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ምርጫ ቦርድ ለአንድ ድምፅ ሰጭ ሁለትና ከዛ በላይ ካርድ ማደል፣ ድምፅ መስጫ ወረቀት ከድምፅ መስጫው ቀን አስቀድሞ ለካድሬዎች ማደል፣ህዝቡ ለድምፁ ዋጋ በመስጠት አዋጁ በሚፈቅደው መልኩ የሰጠውን ድምፅ እንዳይጭበረበር ከምርጫ ጣቢያው 500 ሜትር ርቆ እንዳይጠብቅ የምርጫ አዋጅን በመፃረር ቀጥታ ወደ ቤታችሁ ግቡ በማለት የምርጫ ክልል ጽህፈት ቤት በማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ትዕዛዝ መስጠቱም ኢህአዴግና ምርጫ ቦርድ ልተለያዩበትን ማስረጃ ዋቢ በማድረግ ምርጫ ቦርድ ገለልተኛ አለመሆኑን ፓርቲው በመግለጨቫው አስታውቋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ፓርቲው በመግለጫው ወቅት ለማስረጃ ኤግዝቢትነት ካቀረባቸው በርካታ የፎቶና የቪዲዮ ማስረጃ በተጨማሪ በርካታ የሰነድ ማስረጃዎችን ለጋዜጠኞች ይፋ ያደረገ ሲሆን ከቀረቡት መካከልም የ3 ዓመት እና የ7 ዓመት ህፃናት የመራጭነት ካርድ መውሰዳቸውን፣ አንድ ሰው ሁለትና ከሁለት በላይ የመራጭነት ካርድ መውሰዳቸውን፣ የነገ ሚያዚያ 13 ቀን የሚደረገው የቀበሌ የድምፅ መስጫ ካርድ የምርጫ ቦርድ ማህተምና ፊርማ ያረፈበት የድምፅ መስጫ ወረቀት ቀድሞ መውጣቱና መታደሉ፣ ከመደበኛው የተለየ የተጭበረበረ ድምፅመስጫ ካርድ አዘጋጅቶ ማደል፣ ምልክት የተደረገበት የምርጫ ካርድ በማደል ከኢህአዴግ ደጋፊ ውጭ ለሆኑ መራጮች ድምፅ እንዳይሰጡ የተበላሸ የመራጮች ካርድ መሰጠቱ፣ ምርጫ ቦርድ የፃፈው መራጮች ድምፅ ከሰጡ በኋላ ወዲያው ወደቤታቸው እንዲሄዱ ትዕዛዝ ያረፈበት ደብዳቤ፣ አንድ ለአምስት የተደረገ ጥርነፋ ለምርጫ ቃለ መሐላ የተፈፀመበት ሰነድ፣የ አካባቢው የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስፈፃሚዎች ኢህአዴግ አባል የሆኑበትንና የአባልነት መዋጮ ያዋጡበትን ሰነድን ጨምሮ በርካታ ማስረጃዎችን ማየት ችለናል፡፡
ፓርቲው በግለጫው ምርጫው የይስሙላ ያለተወዳዳሪ ፖለቲካ ፓርቲ እና አብዛኛው ህዝብ ያልተሳተፈበት ምርጫ የየትኛውንም የምርጫ መስፈርት የማያሟላ በመሆኑ ምርጫው ውድቅ እንዲደረግ ጠይቋል፡፡ በመጨረሻም በሀገራችን እውነተኛ የዴሞክራሲ ስርዓት ሰፍኖ የዜጎች የግልና የቡድን መብት እንዲከበር በእንዲህ በተናጠል በሚደረግ ትግል ውጤት እንዳይመጣ ሲአን ተገንዝቦ 33ቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሀገር አቀፍ የፖለቲካ ግንባር የሚፈጠርበትን ሁኔታ በአስቸኳይ አመቻችቶና የጋራ ትግል ስልት ቀይሶ ለሰላማዊ ትግል እንዲነሳ ጥሪውን አቅርቧል፡፡
በጎንደር እስከ ሐሙስ የመራጮች ካርድ ይታደል እንደነበር ተገለፀ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት በተለይም በጎንደር ከተማ አራዳ ክፍለ ከተማ እና አደባባይ ኢየሱስ ባሉ የምርጫ ጣቢያዎች እስከ ሐሙስ ሚያዚያ 3 ቀን 2005ዓ.ም. ድረስ የመራጮች ካርድ እየሰጠ መሆኑን የፍኖተ ነፃነት ጋዜጣ ምንጮች ገልፀዋል፡፡ ነገር ግን በብሔረዊ ምርጫ ቦርድ የጊዜ ሰሌዳ መሰረት የመራጮች ካርድ መውሰጃ ቀን የተጠናቀቀው የካቲት 1 ቀን 2005ዓ.ም. መሆኑ ይታወቃል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ አርብ ሚያዚያ 4 ቀን 2005ዓ.ም. ለምርጫ ታዛቢዎች በሚል በጎንደርና በመቀሌ ከተሞች ያሉ የቀበሌ ሰራተኞች እየዞሩ ገንዘብ ለመሰብሰብ መሰማራታቸውን የከተሞቹ ነዋሪዎችም በመታዘብ “ተወዳዳሪ በሌለበት የምርጫና ታዛቢ ለምን ያስፈልጋል?” በሚል ፊት እየነሷቸው እንዳባረሯቸው ተጠቁሟል፡፡ እስካሁን ባደረግነው የማጣራት ሙከራ በጎንደር ከኢህአዴግ ውጭ ምንም ዓይነት ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ እንደሌለና ብቻውን ለውድድር እንደቀረበ ከስፍራው ምንጮቻንን አረጋግጠዋል፡፡ ይህንንም በሚመለከት የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ምላሽ እንዲሰጠን ጸደጋጋሚ ፅረጽ ብናደርግም አልተሳካም፡፡
በሀዲያ ዞን የፍትህ ስርዓቱ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱ ተገለፀ
በሀዲያ ዞን ያለው የፍትህ ስርዓት የህዝብ አመኔታ እያጣ በመምጣቱ ወደፍርድ ቤቶች ከመሄድ የሽምግልና ስርዓትን እንደሚመርጡን ባለው የፍትህ ስርዓት መዳኘት እንደማይፈልጉ ምንጮቻችን ከስፍራው ለፍኖተ ነፃነት ገልፀዋል፡፡ከዚህ ጋር በተያያዘ በተለይ የሌሞ ወረዳ ፍርድ ቤት ፕሬዘዳንት ህግ ከማስከበር ይልቅ የህግ ጥሰት በመፈፀም በደል ያደረሱብኝ የወረዳው ፍርድ ቤት ዳኛም አንዱ ናቸው የሚል ጥቆማ ተሰምቶ ጉዳዩ ለዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የስነስርዓት ጉዳይ ላይ እንዲታይ አቤቱታም መቅረቡን ከዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዘዳንትና ምክትል ፕሬዘዳንት ማረጋገጥ ችለዋል፡፡
በተለይ በሌሞ ወረዳ ሲታይ የነበረው በመዝገብ ቁጥር 06066 በወይዘሪት ቤተልሔም ወልደመስቀል እና በአቶ ጌትነት በላቸው በተባሉ ግለሰቦች መካከል በሆሳዕና ከተማ ጎፈር ሜዳ ክፍለ ከተማ ልዩ ቦታው ሄሜ ኢንተርናሽናል ሆቴል አጠገብ በሚገኝ 400 ካሬ ሜትር ላይ ያለው ቤትና ቦታ ወራሽነት ይገባኛል በሚል በሚደረገው ክርክር ላይ የካቲት 26 ቀን 2005ዓ.ም. በዳኛ ወ/ዮሐንስ ለውሳኔ መዘጋጀቱ ተጠቁሟል፡፡ይሁን እንጂ ጉዳዩ የማይመለከታቸው በወረዳው ፍርድ ቤት ፕሬዘዳንት አቶ ተስፋዬ ሰጦሬ ተነጥቆ ውሳኔው እንዲስተጓጎል በማድረግ ህግ ተላልፈዋል በሚል ለከፍተኛ ፍርድ ቤት አቤቱታ ቀርቦባቸው በፕሬዘዳንቱ የተነጠቁት ዳኛ ወ/ዮሐንስ አይተው ውሳኔ እንዲሰጡ በዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በተላለፈው መሰረት የክሱ መዝገብ መጋቢት 11 ቀን 2005ዓ.ም. ውሳኔ መሰጠቱ ታውቋል፡፡ ነገር ግን በተደረገው ክርክር ላይ “ወራሽ ነኝ ያሉት ግለሰብ አቶ ጌትነት በላቸው እስካሁን በአካል ያልቀረቡና በወራሽነት ያለችውን ግለሰብ መብት ለማሳጣት የወረዳው ፍርድ ቤት ፕሬዘዳንት ሆን ብለው ከህግ አግባብ ውጭ በማይመለከታቸው ጉዳይ ጣልቃ በመግባት ተከራካሪ ወገኖችን እያጉላሉ ነው” በሚል በተደጋጋሚ ቅሬታ ቀርቦባቸው እንደነበር ተጠቁሟል፡፡
በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገርናቸው ውሳኔ የሰጡት ዳኛ ወልደዮሐንስ ሐንዲሶ “በርግጥ የህግ ስርዓትን ያልተከተለ ትዕዛዝ መጥቶ አላይም ብዬ በኋላ የወረዳ ፍርድ ቤት ፕሬዘዳንት አቶ ተስፋዬ ጋር ከተወያየን በኋላ ማየት እንዳለብኝ ሲነገረኝ አይቼ ለውሳኔ በተዘጋጀሁበት ወቅት ተቃውሞ በመቅረቡ ውሳኔ ሳልሰጥ ቀርቻለሁ እንጂ አልተነጠኩም፡፡ ነገር ግን ጉዳዩን የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ከመረመረ በኋላ ውሳኔውን እኔ እንድሰጥ በመደረጉ በድጋሚ አይቼ ውሳኔውን ሰጥቻለሁ ” ብለዋል፡፡ የወይዘሪት ቤተልሔም ጠበቃ አቶ ተካልኝ ጴጥሮስ በበኩላቸው “ጉዳዩን የህግ ስርዓት ያልተከተለ አሰራር በወረዳው ፍርድ ቤት ፕሬዘዳንት አሰራር ላይ ቅሬታ ስላለን አቤቱታችንን የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ማረም ችሎ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ አሁንም ቢሆን የወረዳው ፍርድ ቤት ፕሬዘዳንት በማይመለከታቸው ጉዳይ እንደ ፍትህ አካል ሳይሆን እንደባለጉዳይ ከህግ አግባብ ውጭ እየተንቀሳቀሱና እያስፈራሩ በመሆኑ አሁንም ለሚመለከተው አካል ቅሬታችንን አቅርበን ውሳኔ እየጠበቅን ነው” ሲሉ ገልፀዋል፡፡
በደል ፈፅመዋል የተባሉት የወረዳው ፍርድ ቤት ፕሬዘዳንት አቶ ተስፋዬ ሰጦሬ በበኩላቸው “እኔ ከችሎት ላይ የነጠኩት የውሳኔ መዝገብም የለም፣ ሊኖርም አይችልም፤ እንዲህ ዓይት አሰራር ከዛሬ 20 እና 25 ዓመታት በፊት እንጂ በዚህ ስርዓት የለም፡፡ በዳኞች ላይ ተቃውሞ ሲቀርብ ግን በህግ አግባብ እንዳይታይ አድርጌ ነበር፤ በመጨረሻ ከፍተኛው ፍርድ ቤት በሰጠው ብይን መሰረት ጉዳዩን የያዙት ዳኛ ወ/ዮሐንስ ውሳኔ እንዲሰጡ ተደርጓል፡፡ አስፈራርተሃል የተባለውን በተመለከተ የስም ማጥፋት ዘመቻ ነው እንጂ ያስፈራራሁት አካል የለም” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዘዳንት አቶ ለማ ገ/እግዚአብሔር በበኩላቸው ጉዳዩ ውስብስብ ቢሆንም በወረዳው ህጋው አሰራርን ያልተከተለ አሰራር ነበር ፤ በኋላ የከፍተኛው ፍርድ ቤት ጉዳዩን አይቶ እርማት ሰጥቶ ቀደም ሲል የያዙት ዳኛ ውሳኔ እንዲሰጡ ተደርጓል፡፡ ይሁን እንጂ አሁን በይግባኝ ጉዳዩ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ደርሶ እየታየ ይገኛል ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ በተለይ ከጉዳዩ ጋር እጃቸው እንዳለበት የሚጠረጠሩት የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዘዳንት አቶ ግርማ አበበ ከህግ አግባብ ውጭ የወራሽነት መብት ላይ እግድ ጥለዋል ከሚል ቅሬታ በተጨማሪ ከወረዳው ፍርድ ቤት ፕሬዘዳንት ጋር የጥቅም ትስስር ስላላቸው ጉዳዩ ላይ እግድ ጥለዋል የሚል ቅሬታ እንዳለባቸው ተጠቁሟል፡፡ አቶ ግርማ በበኩላቸው “እግድ የጣልኩት ንብረት እንዳይሸጥና እንዳይለወጥ እንዲሁም ለሶስተኛ ወገን ተላልፎ እንዳይሰጥ እንጂ የወራሽነት መብት ላይ እግድ አልጣልኩም” ሲሉ ለፍኖተ ነፃነት ገልፀዋል፡፡ በመጨረሻም የአቶ ጌትነትን ጠበቃ አቶ ኤርጃቦን ለማናገር ጥረት ብናደርግም አልተሳካም፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ሌሎች በርካታ የፍትህ መጓደል በዞኑ የተለያዩ ወረዳዎች ላይ እንደሚስተዋልና የአንዳንድ ዳኞች ሹመትም ቢሆን ከሙያ ብቃትና አገልግሎት ይልቅ የጎሳ ዝምድና ትስስር ላይ ትኩረት እንደሚደረግ ተጠቁሟል፡፡ በዚህ ዙሪያ የዞኑ ፍትህ ጽህፈት ቤትን ምላሽ ለማግኘት ተደጋጋሚ ጥረት ብናደርግም አልተሳካም፡፡