Category Archives: News

ኢህአዴግ ብቻውን እየተወዳደረም ህገወጥ ስራ እየሰራ መሆኑ ተገለፀ

በአዲስ አበባ የሚገኙ ባለሃብቶች “ኢህአዴግ ለሚያዚያ 2005 ዓ.ም. ለሚደረገው የአዲስ አበባ፣ ድሬዳዋ አስተዳደርና የአካባቢ ምርጫ ብቻውን እየተወዳደረም ለምርጫ ቅስቀሳ በሚል በግዳጅ ገንዘብ እየጠየቀ ህገወጥ ድርጊት እየፈፀመ እንደሆነና ድርጊቱም እንዳማረራቸው ለአዲስ ሚዲያ ገለፁ፡፡ “በተለይ እኛ ሳንፈልግ ለኢህአዴግ ምርጫ ቅስቀሳ የሚሆን ገንዘብ አዋጡ የሚል እደምታ ያለውና የመንግስት መስሪያ ቤት ማኀተም ያረፈበት አስገዳጅ ደብዳቤ በየድርጅታችን ስም እየላኩ የመኖርና የመስራት ነፃነታችንን እየተጋፉ ነው “ ሲሉ ቅሬታ የተሰማቸው ያነጋገርናቸው ነጋዴዎች ለአዲስ ሚዲያ ጠቁመዋል፡፡

በተለይ በአዲስ አበባ ንፋስ ስልክ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 የኢህአዴግ ጽህፈት ቤት መጋቢት 20 ቀን 2005ዓ.ም. በወረዳው ማዘጋጃ ቤት አገልግሎት ጽህፈት ቤት ማኀተም ባረፈበትና የወረዳው ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የስልክ አድራሻን በመጠቀም የተላከው ደብዳቤ “…ባለድርሻ አካላት” ላላቸው “የኢህአዴግ አባላት፣ አጋር ድርጅቶች፣ታዋቂ ካምፓኒዎች፣ ሪል ስቴቶች፣ ግለሰቦች፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት” በሚል ከተላከው አስገዳጅ ደብዳቤ ማረጋገጥ ተችሏል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በተላከው ደብዳቤ ማጠቃለያ ላይ አስገዳጅነቱን በግልፅ በሚያሳይ ማስፈራሪያ “የዚህ ፕሮግራም ማጠቃለያ የሚሆነው ለሚመለከተው አካል ጊዜውን የጠበቀ ዘገባ ማድረግ ይሆናል፡፡ ከዚህ በመነሳት ኢህአዴግን መምረጥ የሀገራችንን ህዳሴ ወደ ሌላ ምዕራፍ ማሸጋገር ስለሆነ አገረ ባለሃብቶችና ጥያቄ የቀረበላችሁ አካላት አስፈላጊውን ታደርጉ ዘንድ ማሳወቅ ነው::” በሚል ከፈቃደኝነት ይልቅ አስገዳጅነት ያለው ደብዳቤ በመላክ ምላሽ እንድንሰጣቸው ይጠይቁናል ሲሉ ስማቸውን መግለፅ ያልፈለጉ ባለሃብቶች ከተደገፈ መረጃ ጋር አስታውቀዋል፡፡

በዚህም ምክንያት ኢህአዴግ ብቻውን ሆኖ ይህን ህገወጥ ድርጊት መፈፀሙ የከዚህ በፊቱ ልምዱን ነው የሚያሳየው፣ ይህ አዲስ አይደልም፤ እንደውም ይባስ ብሎ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት እንኳ የእሱ አጋር መሆናቸውን መግለፁ ኢህአዴግ ህገወጥ ስራ መስራቱን የሚያረጋግጥ ነው ሲሉ ያነጋገርናቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ገልፀውልናል፡፡

ይህንንም በሚመለከት ምርጫ ቦርድ ምን ይላል የሚለውን ለማረጋገጥ ጥረት ብናደርግም ለጊዜው አልተሳካም፤ ከዚህ በተጨማሪ በመንግስት ማኀተምና አድራሻ የኢህአዴግ ምርጫ ቅስቀሳ ደብዳቤ በትነዋል ከተባሉት መካከል በአዲስ አበባ የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 ዋና ስራ አስፈፃሚ የሆኑት አቶ ስለሺ ካሳ መልስ እንዲሰጡን ብንሞክርም ያልተሳካ ሲሆን በወረዳው የመንግስት ቢሮ ውስጥ የህዝብ አደረጃጀት ኃላፊ በህዝብ ደመወዝ የኢህአዴግ ጽህፈት ቤት ስራን የሚሰሩት አቶ በረከት ዮሐንስ በበኩላቸው እኛ እንዲህ አላደረግንም ቢሉም ሰነዱ ግን በዝግጅት ክፍላችን የሚገኝ ሲሆን ቅጂው ለምርጫ ቦርድ ህዝብ ግንኙነት ክፍል እንደደረሰም ተጠቁሟል፡፡ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምክትል ዋና ፀሐፊ አቶ ወንድሞ ጎላ በበኩላቸው ከላይ የተጠቀሰው ድርጊት ተፈፅሞ ከሆነ የእርምት እርምጃ እንወስዳለን ፤ መረጃውን ግን እስካሁን አላየሁትም ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

 

የአፋር ክልላዊ መንግስት 3 ባለስልጣናት ተሰናበቱ

 

በአፋር ክልላዊ መንግስት ገዥው ፓርቲ አብዴፓ ባካሄደው ጉባዔ የክክሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደርና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ የሆኑት አቶ አወል ውቲካ እና የአብዴፓ ጽህፈት ቤት ኃላፊ  አቶ መሐመድ ቡልቡል የተሰጣቸውን ኃላፊነት በአግባቡ አልተወጡም  በሚል ሙሉ በሙሉ ከስልጣናቸው ሲነሱ የክልሉ የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ስራ አስፈፃሚ አቶ መሐመድ ያዮ ከኃላፊነታቸው ዝቅ መደረጋቸው ታውቋል፡፡ በጉባዔው የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ እስማኤል አሊሴሮ ከክልሉ ህዝብ ጥቅም ይልቅ ለኢህአዴግ ስልጣን ጥቅም ብቻ ይሰራሉ በሚል እየተወቀሱ ውስጥ ውስጡን ከስልጣናቸው እንዲነሱ ቢፈለግም በኢህአዴግ ባለስልጣናት ፍላጎት ሳይወርዱ መቅረታቸውን የአዲስ ሚዲያ ምንጮቻችን ከስፍራው ጠቁመዋል፡፡

በተያያዘ ዜና በአፍር ክልል ዞን ሶስት  በሚገኙ ገዋኔ፣ አሚባራ እና ጉሩመዳች ወረዳ ከሚገኙ አርብቶ አደሮች በፌደራል ፖሊስ  ለከብቶቻቸው ጥበቃ የሚገለገሉበት የጦር መሳሪያ በፌደራል ፖሊስ ተነጥቆ ሲወሰድ የአጎራባች የሶማሌ ክልል ወረዳ ነዋሪዎችም በተመሳሳይ ተነጥቆ ከፍተኛ ቁጣን በመቀስቀሱ ወዲያው ሲመለስላቸው የአፋሮች ግን ሳይመለስ በመቅረቱ ማንነታቸው ባልታወቁ ዘራፊዎች 80 ፍየሎችና 17 የቀንድ ከብቶች እንደተሰረቁባቸው ምንጮቻችን በተለይ ለአዲስ ሚዲያ ገልፀዋል፡፡ የክልሉ ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ባልደረባ የሆኑት አቶ መሐመድ ያዮ የተደረገው ሹም ሽር አስመልክቶ፣  የአርብቶ አደሮቹ መሳሪያ መነጠቅ ላይ እና ተፈፀመባቸው ስለተባለው ዝርፊያ መልስ ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል፡፡

የነ አቶ አንዱዓለም አራጌና ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ክስ ውሳኔ በድጋሚ ተቀጠረ

በእነ አንዱዓለም አራጌ የክስ መዝገብ ለፌደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ የጠየቁት የአንድነት ፓርቲ ከፍተኛ አመራር አቶ አንዱዓለም አራጌ እንዲሁም  እውቁ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣ አቶ ናትናኤል መኮንን፣ አቶ አንዱዓለም አያሌው፣ ሻምበል የሺዋስ ይሁንዓለም፣አቶ ዮሐንስ ተረፈ፣አቶ ክንፈሚካኤል ደበበ እና አቶ ምትኩ ዳምጤ ውሳኔ ለዛሬ መጋቢት 30 ቀን 2005 ዓ.ም. ተቀጥሮ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ 6 ኪሎ የሚገኘው የፌደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የይግባኙን የመጨረሻ ውሳኔ ይሰጣል ተብሎ ቢጠበቅም ውሳኔውን ሳይሰጥ ለአምስተኛ ጊዜ ለሚያዚያ 24 ቀን 2005 ዓ.ም. ተቀጠረ፡፡

ፍርድ ቤቱም ውሳኔውን ሊሰጥ ያልቻለበትን ምክንያት ሲገልፅ የክሱን ሂደት ገና መርምሬ አልጨረስኩም በሚል ተጨማሪ ቀነ ቀጠሮ መስጠቱን አስታውቋል፡፡ በወቅቱ የፍርድ ቤቱ ዳኞች ሽመክት አሰፋ፣ በላቸው አንሺሶ እና ዳኜ መላኩ ተሰይመው ሲሆን ከከሳሽ በኩል አቃቤ ህግ ብርሃኑ ወንድማገኝ እንዲሁም ከተከላካይ ጠበቆች አቶ አበበ ጉታ፣ አቶ ደርበው ተመስገን እና አቶ ሳሙኤል አሰፋ ተገኝተዋል፡፡ ተከሳሾችም በሰዓቱ የቀረቡ ቢሆንም የነበረው በበርካታ ያልተለመደ የጦር መሳሪያ አጀብ አዲስ ያልተለመደ ክስተት ቢሆንም በተለይ የአቶ አንዱዓለም አራጌ በከፍተኛ ደረጃ መጎሳቆል የችሎት ታዳሚዎችን ሐዘን ውስጥ ከቶ ተከሳሾቹ የውሳኔ ፍርዱ ሳይሰጥ ከቀኑ 6፡30 ሰዓት ወደ የመጡበት እስር ቤት ተመልሰዋል፡፡   

 

ከቤንሻንጉል አማርኛ ተናጋሪ ዜጎችን በግፍ የማፈናቀሉ ሂደት ተጠናክሮ ቀጥሏል

-ጥቃቱ ህፃናትና አረጋውያን ላይም እየደረሰ ነውአማርኛ ተናጋሪውን ከየቦታው የማፈናቀሉ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉን የመረጃ ምንጮቻችን አስታወቁ፡፡ የፍኖተ ነፃነት ምንጮች እንደሚሉት በዚህ ሳምንት ውስጥ ብቻ ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከማይ ዞን ያሶ ወረዳ 25 ሺህ አማርኛ ተናጋሪዎች እየተደበደቡ በጭነት መኪና ተጭነው ከመኖሪያቸው ተባረዋል፡፡ የአካባቢው የዓይን ምስክሮችም ተጧሪ አረጋዊያንና ህፃናት “ውሃ፣ አምባሻ እያሉ በየመንገዱ ሲለምኑ ያለርህራሄ እየደበደቧቸው ወስደዋቸዋል፡፡” ሲሉ በቅሬታ ያስረዱሉ፡፡
ፍኖተ ነፃነት ያነጋገረቻቸው የዓይን ምስሮች እንደሚሉት መንታ የተገላገለች እመጫት ሳትቀር አስር ቀን ሳይሞላት በጭነት መኪና ላይ ወርውረዋት አከባቢውን ለቃ እንድትሄድ ተደርጓል፡፡ የዝግጅት ክፍላችን ለመረዳት እንደቻለው አብዛኞቹ ተፈናቃዮች ከ96 ዓ.ም ጀምሮ በባዶ መሬት ላይ ሠፍረው አካባቢውን ያለሙ የነበሩ ናቸው፡፡ የዘሩትን እህል ሳይሰበስቡና ንብረታቸውን ሳይዙ እየተባረሩ የሚገኙት እነዚህ የአማርኛ ተናጋሪ ዜጎች የተለያዩ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችም እየደረሱባቸው እንደሚገኝ ፍኖተ ነፃነት ከአይን እማኞች ለማረጋገጥ ችላለች፡፡ ምንጮቻችን አክለውም “ሰው መሆን እስከሚያስጠላ ድረስ በጭካኔ እየደበደቡ መሬት ለመሬት እየጎተቱ መኪና ላይ ይወረውሯቸዋል፡፡ በአካባቢው ኦሮሚኛ እና ሌላ ቋንቋ ተናጋሪዎች በተመሳሳይ ጊዜና ከዚያ ወዲህ በቅርብ ጊዜ ሠፍረው የሚኖሩ አሉ፡፡ እነሱን የሚነካቸውና የሚጠይቃቸው የለም፡፡” በማለት አማርኛ ተናጋሪዎች ላይ ያነጣጠረ ዘር የማፅዳት ዘመቻ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
ፍኖተ ነፃነት ያነጋገረቻቸው በአካባቢው በንግድ ስራ የተሰማሩ ግለሰብ እንደሚናገሩት አማርኛ ተናጋሪዎቹን ከስፍራው ለማፈናቀል ከሚሰጡት ምክንያት አንዱ “ከዚህ በፊት በክልላችሁ በነበራችሁበት ቦታ የማዳበሪያ ዕዳ አለባቸው” የሚል ነው፡፡ ግለሰቡ አክለውም “ዕዳ ካለባቸው ባሉበት በህግ መጠየቅ እየተቻለ ሁሉንም ወንጀለኞች ናቸው እየተባለ መደብደብና ማባረር ወንጀል ነው፡፡” ብለዋል፡፡ አያይዘውም ብአዴን በአማራ ህዝብ ስም ሥልጣን ላይ ተቀምጦ በአማራ ህዝብ ላይ የሚፈጸመውን እያየ እንዳላየ ዝም ብሎአል፡፡ አቤቱታ እየቀረበላቸው አንድም ነገር አላሉም፡፡ ብአዴን የአማራ ህዝብ ወኪል አለመሆኑን ሙሉ በሙሉ ያረጋገጠበት ወቅት ላይ ደርሷል፡፡” ሲሉ እጅግ አዝነው ተናግረዋል፡፡
ጉዳዩን እያስፈጸሙ ናቸው የተባሉትን የወረዳውን አስተዳዳሪ አቶ ታደሰ ሻምበልን በስልክ አግኝተናቸው ነበር፡፡ እራሳችንን አስተዋውቀን ጥያቄያችንን ልንጀምር ስንል አቶ ታደሰ ስልካቸውን ጆሮአችን ላይ በመዝጋታቸው ዜናው ሚዛናዊ ለማድረግ አልቻልንም፡፡
በዚህ ሳምንት ከወረዳው ተባረው በመጓጓዝ ላይ የነበሩ ዜጎችን ጭኖ የነበረው አንዱ መኪና ተገልብጦ 59 ሰዎች ህይወታቸው ሊያልፍ ችሏል፡፡ ህይወታቸው ካለፈው ውስጥ አብዛኞቹ ህጻናት፣ሴቶችና አረጋውያን መሆናቸውን በስፍራው የተገኙ የዓይን ምስክሮች ለዝግጅት ክፍላችን አስታውቀዋል፡፡
ምንጭ ፍኖተ ነፃነት

 

አፋር በተከሰተው ርሃብ የሟቾች ቁጥር 22 ደርሷል

በአፍር ክልል በተከሰተው ርሃብ የሟቾች ቁጥር 22 መድረሱ ተሰማ፡፡ በክልሉ ዞን ሁለት አሚባራ ወረዳን ጨምሮ በዞን አንድ በሚገኙ ኤረርሲ፣ኤልዳዓልና ቢሩ ወረዳዎች የተከሰተው ርሃብ እስካሁን ድረስ ችግሩ ሊቀረፍ ባለመቻሉ የሟቾች ቁጥር እያሻቀበ መሄዱንና ወደሌሎች የክልሉ ወረዳዎችም መዛመቱን ምንጮቻችን በተለይ ለአዲስ ሚዲያ ገልፀዋል፡፡

የአፋር ክልል የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ የስራ ሂደት ሃላፊ የሆኑት አቶ መሐመድ ያዮ ስለተከሰተው ርሃብ “በአካባቢው ጠረፋማ ወረዳዎች የተከሰተው በዋነኝነት የውሃ እጥረት ቢሆንም የምግብ እጥረቱም አለ፡፡  የክልሉ መንግስት 2 ሚሊዮበሰሜን ምስራቅ ኢትዮጵያ አፋር ክልል በተከሰተው ርሃብ የሟቾች ቁጥር 22 መድረሱ ን ብር በመመደብ ውሃ በቦቲ ተሸከርካሪ  እየወሰደ ለአካባቢው ማኀበረሰብ እያደረሰ ነው፣ ምግብ ግን በበቂ ሁኔታ በመጋዘናች ተከማችቶ የሚገኝ በመሆኑ እየተሰጣቸው ከመሆኑም በተጨማሪ በአካባቢው ያሉ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችም የበሰሉ አልሚ ምግቦችን እያዳረሱ ነው፡፡ በአሁን ወቅት ግን በአካባቢው ዝናብ በመዝነቡ የውሃውን እጥረት ችግር ተቀርፏል “ ሲሉ ገልፀዋል፡፡  አያይዘውም የእንሰሳቱን የውሃና የምግብ እጥረት ችግር ለመቅረፍ አጎራባች የአማራ ክልል ወረዳዎች ጥሩ ትብብር እያደረጉልን ቢሆንም አብዛኛው አጎራባች ቦታ ተክሎች ተተክለው  በአጥር በመከለሉ ለፀጥታ ችግር ሊፈጥር ይችላል በሚል ማሳሰቡ እንዳልቀረ ገልፀውልናል፡፡

የግብርና ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆኑት አቶ ታረቀኝ ፅጌ በበኩላቸው በሶማሌና አፋር በተለያየ ጊዜ ድርቅ ስለሚከሰት በቂ የሆነ የምግብ ክምችት ስላለ ወደስፍራ ተልኳል፡፡ የተከሰተውም ድርቅ እንጂ ርሃብ አይደልም ሲሉ አክለዋል፡፡ የአዲስ ሚዲያ መረጃዎች እንዳመለከቱት ከሆነ በአካባቢው ያለው ርሃብ እየተባባሰ ወደ አጎራባች ወረዳዎችም መዛመቱን ያስረዳል፡፡ አዲስ ሚዲያ ባለፈው በክልሉ ዞን አንድ ቢሩና ኤልዳዓል ወረዳ በተከሰተው ርሃብ የ 8 ሰዎች መሞታቸውን መዘገቧ የሚታወስ ሲሆን አሁን ግን ኤረርሲና አሚባራ ወረዳ የሚባሉ ሌላ ወረዳዎችም ችግሩ በመከሰቱ የሟቾች ቁጥር ወደ 22 መድረሱ ተጠቁሟል፡፡