Tag Archives: Andualem Aragie

በአዲስ አበባ እና በባህርዳር ጋዜጠኞች፥ የመብት ተሟጋቾች እና ፖለቲከኞች ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ለቀናት በአደራ እስር ላይ ይገኛሉ

(ዳጉ ሚዲያ) በቅርቡ የተደረገውን የፀረ አገዛዝ ህዝባዊ ተቃውሞን ተከትሎ ከዓመታት እስር በኋላ የተለቀቁ ጋዜጠኞች፥ የመብት ተሟጋቾች፥ ፖለቲከኞችን ጨምሮ ሌሎች የመብት ተሟጋቾችን ጨምሮ ያለ በቂ ምክንያት ከመጋቢት 16 ቀን 2010 ዓ.ም.ጀምሮ በጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ቤተሰብ መኖሪያ ቤት ከነበሩበት የምሳ እና የ “እናመሰግናለን” ግብዣ ላይ በነበሩበት ወቅት በድጋሚ ታስረዋል።

በድጋሚ ከታሰሩት መካከል ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፥ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ፥ አቶ አንዷለም አራጌ፥ ጦማሪ ዘላላም ወርቃገኘው፥ ወ/ት ወይንሸት ሞላ፥ ጦማሪ ማህሌት ፍንታሁን፥ ጦማሪና ጋዜጠኛ በፍቃዱ ሀይሉ፥ አቶ ስንታየሁ ቸኮል፥ አቶ ይድነቃቸው አዲስ፥ አቶ አዲሱ ጌታነህ፥ አቶ ተፈራ ተስፋዬ በአዲስ አበባ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ልዩ ስሙ ጎተራ ፖሊስ በእስር ላይ የሚገኙ ሲሆን፤ ከመደበኛ ሥራቸው ተይዘው ከታሰሩት መካከል የአምቦ ዩኒቨርስቲ መምህር፥ የመብት ተሟጋችና ጦማሪ ስዩም ተሾመ እንዲሁም የመብት ተሟጋች እና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የፍትህ ቢሮ የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ታዬ ደንደዓ በማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ ወህኒ ቤት ታስረው ይገናሉ።

Ethiopian re-arrested political Prisoners
በቅርቡ ለእስር የተዳረጉ የፖለቲካ እስረኞች መካከል በከፊል

በተያያዘ ዜና የአማራ ህዝብን ከአገዛዙ ጥቃት ለመከላከል በሚል በህጋዊ መንገድ የተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅት ለመመስረት በይፋ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የነበሩ የአካባቢ አስተባባሪዎች መካከል ከሌሎች ወዳጆቻቸው ጋር በመሆን በጋራ በመሆን ሰኞ መጋቢት 17 ቀን 2010 ዓ ም ባህርዳር ከተማ ተሰብስበው እራት ሲመገቡ በፀጥታ ኃይሎች ታፍነው ከታሰሩ በኋላ ድብደባ እንድተፈፀመባቸው ተጠቆመ። ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ድረስ በበእስር ላይ የሚገኙት ምሁራን፥ ፖለቲከኞች እና በዕለቱ በጓደኝነት እራት ግብዣው ላይ የተገኙ ጋዜጠኞች በባህርዳር ከተማ 9ኛ ፖሊስ ጣቢያ ታስረው ይገኛሉ።

በባህር ዳር ከተማ ተይዘው ከታሰሩት መካከል ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ (ባህርዳር ዩንቨርሲቲ መምህርና የጣና ደህንነትና የአካባቢ ጥበቃ ማህበር ፕሬዚደንት እና ተመራማሪ፣ ረዳት ፕሮፊሰር)፥ ጋሻው መርሻ (የአንጸባቂው ኮከብ መጽኃፍ ከታቢ፤ አዲስ አበባ በማስተማር ሙያ ላይ ይገኛል)፥ የሱፍ ኢብራሂም (ወሎ ዩኒቨርሲቲ መምህር የነበረና በአሁንኑ ወቅት ጠበቃ)፥ ተመስገን ተሰማ (ወሎ ዩኒቨርሲቲ መምህር፤የወሎ ዩኒቨርስቲ የህግ ትምህርት ቤት መስራች፣ ረዳት ፕሮፊሰር እና አማራ ነን የሚለው መዝሙርም ገጣሚ)፥ በለጠ ሞላ ( ተባባሪ ፕሮፊሰር ፡አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር)፥ ጋዜጠኛ ንጋቱ አስረስ (የአማራ ቴሌቪዥን ጋዜጠኛ(አርታኢ)፤ከ1997 እስከ 1999 የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የአማራ ተማሪዎች ማህበር ፕሬዜዳት፤)፥ ጋዜጠኛ በለጠ ካሳ (የቀለም ቀንድ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ የነበረ)፥ አቶ ሲሳይ አልታሰብ( ሲቪል ኢንጅነር)፥ አቶ ዳንኤል አበባው፥ አቶ መንግስቴ ተገኔ፥ አቶ ቦጋለ አራጌ፥ አቶ ካሱ ኃይሉ (የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ መምህር፡የማህበረሰብ ሳይንስ ተመራማሪ)፥ አቶ ተሰማ ካሳሁን፥ አቶ ድርሳን ብርሃኔ፥ አቶ በሪሁን አሰፋ፥ አቶ ፍቅሩ ካሳው፥ አዲሱ መለሰ (የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ መምህር)፥ አቶ ተመስገን ብርሃኑን ጨምሮ አንድ ስማቸው ያልተጠቀሰ ግለሰብም በእስር ላይ ይገኛሉ።

በአዲስ አበባ እና በባህርዳ ይታሰሩት ሁሉም ተከሳሾች ክስ እንዳልቀረበባቸውና የታሰሩበትም ምክንያት እንዳልታወቀ የተገኘው መረጃ አመልክታል። ይህንንም ተከትሎ ሐሙስ ምሽት መጋቢት 20 ቀን 2010 ዓ ም የተለያዩ ማኀበራዊ ሚዲያን በመጠቀም #ሁሉም_የፖለቲካ_እስረኞች_ይፈቱ የሚል ዘመቻ የተደረገ ሲሆን፤ ከአሰራቸው የመንግሥት አካል ግን የተሰጠ ምላሽ የለም።

በቅርቡ ከእስር ከተፈቱት መካከል ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ እና አቶ አንዱዓለም አራጌን ጨምሮ 11 ሰዎች በድጋሚ ታሰሩ

(ዳጉ ሚዲያ) እሁድ መጋቢት 16 ቀን 2010 ዓ.ም. የአዲስ አበባ ወጣቶች በቅርቡ ከእስር ለተፈቱት ጋዜጠኞች፥ የመብት ተሟጋቾች እና ፖለቲከኞችን “እናመሰግናለን” በሚል በጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ቤተሰብ መኖሪያ ቤት በተዘጋጀ መርሃ ግብር ላይ ተገኝተው ከነበሩት መካከል 11 ያህሉ በፖሊስ ታግተው መቆየታቸው ታውቋል። ፖሊስም ታጋቾቹን ከጋዜጠና ተመስገን ደሳለኝ ቤተሰብ መኖሪያ ቤት በበርካታ የፖሊስ ኃይል በማጀብ በአዲስ አበባ ንፋስ ስልክ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ስር በሚገኘው ጀሞ ፖሊስ ጣቢያ የወሰዷችው ሲሆን፤ ከምሽቱ 4፡30 ሰዓት ላይ ጎተራ ወደ ሚገኘው ፖሊስ መምሪያ ወስደው እንዳሰሯቸው ለማወቅ ተችሏል።

Andualem-Eskindir
አቶ አንዱዓለም አራጌ ኤና ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ

እንደምንጮች መረጃ ከሆነ፤ ለእገታው ምክንያት የሆነው በመርሃ ግብሩ ላይ የገዥው ስርዓት መለያ የሌለበት የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ተሰቅሎ በማየታቸው በተቆጡ የአገዛዙ ፖሊሶች በፈጠሩት አለመግባባት መሆኑ ተጠቁሟል። በተለይም በስፍራው የነበረው መርሃ ግብር ከተጠናቀቀ በኋላ በስፍራው ደርሰው የነበሩ ሁለት ፖሊሶች ሰንደቅ ዓላማውን ከተሰቀለበት በግድ ነጥቀው በመውሰድ ድርጊቱን ስብሰባ አድርጎ በመቁጠር ለምን አላስፈቀዳችሁም በሚል ለድርጊቱ ኃላፊነቱን የሚወስድ አካል ማናገር እንፈልጋለን በማለት ፖሊሶቹ ታዳሚውን ለማስፈራራት ሞክረዋል። ይህንንም ተከትሎ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝም የነበረው መርሃ ግብር የተለመደ የማኀበራዊ ወዳጅነት እንጂ ስብሰባ አይደለም፥ ለማኀበራዊ ወዳጅነት ፈቃድ እያስፈልግም ሲል ምላሽ በመስጠቱ በተለይ ሲያናግረው የነበረውን ፖሊስ እንዳስቆጣ ለማወቅ ተችላል።

በጋዜጠኛው ምላሽ ደስተኛ ያልነበረው ፖሊስ ጉዳዩን በማክረር ኃላፊነቱን የሚወስዱ 3 ሰዎችን ማናገር እንፈልጋለን ወደሚል እልህ ውስጥ መግባቱን ተከትሎ አቶ አንዱዓለም አራጌ ጉዳዩን ለማረጋጋት በሚል ፖሊሱን ለማግባባት ቢሞክርም፤ ፖሊሱ ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል። በመጨረሻም አቶ አንዱዓለም አራጌ ለፖሊሱ ” ችግር አለ ብላችሁ ምታምኑት ነገር ካለ እና ማናገር ከፈለጋችሁ ሁላችንንም ወስዳችሁ ማናገር ትችላላችሁ፤ ከዛ ውጭ በተናጥል ኃላፊነት የሚወስድም ሆነ የሚያናግር የለም” የሚል ምላሽ ይሰጣል።

በተሰጣቸው ምላሽ ደስተኛ እና ፈቃደኛ ያልሆነው ፖሊስ በመርሃ ግብሩ ላይ ከተሳተፉት መካከል በወቅቱ በስፍራው የነበሩትን እንዳይንቀሳቀሱ በማስገደድ፤ በያዘው የፖሊስ መገናኛ ሬዲዮ ወደበላይ አለቆቹ በመደወል በአካባቢው ከፍተኛ ችግር እንዳለ እና ለዚህም በርካታ የፖሊስ ኃይል እንዲታዘዝለት ጥሪ ያስተላልፋል። ከተወሰኑ ደቂቃዎች በኋላም በተሽከርካሪ መኪና ተጭነው የመጡ በርካታ ፖሊሶች የጦር መሳሪያዎቻቸውን በመደገን አካባቢውን በመቆጣጠር በስፍራው በቅርቡ ከእስር ከተፈቱት እና በወቅቱ የ “እናመሰግናለን” ሽልማት መርሃ ግብር ከተጠናቀቀ በኋላ በስፍራው የነበሩትና ከእስር ተለቀው የነበሩ 11 የፖለቲካ እና የህሊና እስረኞች አቶ አንዱዓለም አራጌ፥ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፥ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ፥ ጋዜጠኛ እና ጦማሪ በፈቃዱ ኃይሉ፥ ጦማሪ ማህሌት ፋንታሁን፥ ጦማሪ ዘለዓለም ወርቅአገኘሁ፥ የመብት ተሟጋች ወጣቶች አቶ ስንታየሁ ቸኮል፥ አቶ አዲሱ ጌታነህ፥ ወ/ት ወይንሸት ሞላ፥ አቶ ይድነቃቸው አዲስ እና አቶ ተፈራ ተስፋዬ በድጋሚ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለዋል።

ፖሊስ አግቶ ያሰራቸውን 11 ሰዎች ለምን እንደሆነ እስካሁን በይፋ የሰጠው ማብራሪያም ሆነ ምክንያት የለም። ይሁን እንጂ የታገቱት ጋዜጠኞችና የመብት ተሟጋቾች ታፍነው ተወስደውበት ከነበረው ጀሞ ፖሊስ ጣቢያ ማምሻውን ጎተራ ፊትለፊት ወደሚገኘው የንፋስ ስልክ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ እንደታሰሩ ለማወቅ ተችሏል። ጋዜጠኞቹ እና የመብት ተሟጋቾቹ በታሰሩብት ዕለት ቀደም ሲል በቅርቡ በሀገሪቱ ላለፉት 3 ዓመታት ጀምሮ ያልተቋረጠውን የፀረ ጭቆና አገዛ ህዝባዊ ተቃውሞን ተከትሎ በቅርቡ ከእስር ከተፈቱት በርካታ የፖለቲካና የህሊና እስረኞች ጋር የሰማያዊ ፓርቲ ባዘጋአጀው ተመሳሳይ መርሃ ግብር ላይ ተሳትፈው ካጠናቀቁ በኋላ ተጨማሪ በሌሎች በጎ ፈቃድ ወጣቶች ባዘጋጁት መርሃ ግብርን አጠናቀው ርስ በርስ በመጨዋወት ላይ እያሉ መታሰራቸውን ለማወቅ ተችሏል።

በአሁን ወቅት ሀገሪቱ ለ6 ወራት በሚቆይ የአስቸኳይ አወጅ ስር ሆና በወታደራዊ ዕዝ ቁጥጥር ስር መውደቋ ይታወቃል።

አቶ አንዱዓለም አራጌን ጨምሮ የፖለቲካ እስረኞች ተለቀቁ

ከመስከረም 3 ቀን 2004 ዓ ም ጀምሮ በእስር ላይ የነበሩት የቀድሞ የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ (አንድነት) ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር እና የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አንዱዓለም አራጌ ፥ የፓርቲያቸው አመራር አባላት የነበሩት አቶ ናትናኤል መኮንን፥ የቀድሞ የፓርላማ አባል አቶ አንዱዓለም አያሌው የካቲት 7 ቀን 2010 ዓ ም ከእስር ተለቅዋል።
Andualem Arage
አቶ አንዱዓለም አራጌ

በተመሳሳም የቀድሞ የጋምቤላ ፕሬዘዳንት የነበሩት አቶ ኦኬሎ አኳይ፥ የመብት ተሟጋቿ ወ/ሮ እማዋይሽ አለሙ፥ የኦፌኮ/መድረክ አመራር የነበሩት አቶ ኦልባና ሌሊሳ፥ የቀድሞ መኢአድ ፕሬዘዳንት አቶ ማሙሸት አማረ፥ የመኢዴፓ አመራር የነበሩት አቶ ክንፈሚካኤል ደበበ (አበበ ቀስቶ)፥ የኢብአፓ ፕሬዘዳንት የነበሩት አቶ ዘሪሁን ገብረእግዚአብሔር፥ የቀድሞ የሰማያዊ ፓርቲ አመራር የነበረው ወጣት ብርሃኑ ተክለያሬድ፥የመብት ተሟጋቿ ጫልቱ ታከለ እና ደርቤ ኢተና፤ የሙስሊሙ መፍትህ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላትና የመብት ተሟጋቾች አህመዲን ጀበልና አህመድ ሙስጠፋ እና አርቲስት ሴና ሰለሞን ከእስር ተለቅዋል።

በተለይ አቶ አንዱዓለም አራጌ እና ወ/ሮ እማዋይሽ አለሙ ተይዘው ከታሰሩ ጀምሮ በተለያየ ክስ መዝገብ ዕድሜ ልክ እስር ተፈርዶባቸው እንደነበር ይታወቃል።

ከላይ የተጠቀሱትን ጨምሮ በተመሳሳይ ቀን ከ746 ያላንሱ የፖለቲካ እስረኞች እንደሚፈቱ የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ለመግንግሥት መገናኛ ብዙኃን ማሳወቁ ይታወሳል። ይሁን እንጂ አሁንም በርካታ የፖለቲካ እስረኞች በተለያዩ የሀገሪቱ ወህኒ ቤቶች እንደሚገኙ መረጃዎች ይጠቁሟሉ።

የነ አቶ አንዱዓለም አራጌን መፈታት ተከትሎ በርካታ ህዝብ በአዲስ አበባ ቃሊቲ ወህኒ ቤት እና በየመሮሪያ ቤታቸው በመገኘት ደስታውን ሲገልፅና እና ድጋፉን ሲያደርግ ተስተውሏል። እነ አንዱዓለምም ለመላው ህዝብ ምሥጋናችውን አቅርበዋል።

ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፥ አቶ አንዱዓለም አራጌ፥ እና ሌሎችም …

ብስራት ወልደሚካኤል

ረቡዕ መስከረም 3 ቀን 2004 ዓ. ም. በግምት ከቀኑ 10 ሰዓት አካባቢ ሰላማዊ ሰዎች ከመደበኛ ዕለታዊ እንቅስቃሴዎቻቸው እንደወንጀለኛ ታድነው የታሰሩበት ቀን ነው።

Andualem-Eskindir
ፎቶ፡ ከማኅበራዊ ገፅ

ረቡዕ መስከረም 3 ቀን 2004 ዓ. ም. በግምት ከቀኑ 10 ሰዓት አካባቢ ሰላማዊ ሰዎች ከመደበኛ ዕለታዊ እንቅስቃሴዎቻቸው እንደወንጀለኛ ታድነው የታሰሩበት ቀን ነው።

አንዱዓለም አራጌ በወቅቱ የአንድነት ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ እና ምክትል ሊቀመንበር ነበር። ሀገር ሊያቀና ሲኳትን የነበረው አንዱዓለም ሰላማዊ የመብት ትግልን ስራው አድርጎ መንቀሳቀስ የጀመረው ገና የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪ ሳለ ነው።

መስከረም 3 ቀን 2004 ዓ. ም. ሰቆቃ አላልቅ ወዳለበት ማዕከላዊ እና ቃሊቲ ወህኒ ቤት ከገፋቱ በፊት ጠዋቱ የመጀመሪያ ልጁን ሩህ አንዱዓለምን ለመጀመሪያ ጊዜ ትምህርት ቤት አድርሶት ወደ አንድነት ፓርቲ መደበኛ ስራው ገብቷል። በዕለቱም ከመቼው ጊዜ በላይ ደስ ብሎት ይታይ ነበር። ምክንያቱ ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ የአብራኩን ክፋይ ፥ልጁን እጁን በመያዝ ወደ ትምህርት ቤት የወሰደበት ቀን ነውና። ይሄንን ደስታውንም በወቅቱ እዛ ለነበርን ሰዎች ሁሉ ሲያጋራ አስታውሳለሁ። ደስ የሚል ደስታ፥ በፍቅር የተሞላ ፈገግታ፥ የምርም ደስስስስ ይል ነበር። ማታ ወደ ቤት ተመልሶ የልጁን የትምህርት ቤት የመጀመሪያ ቀን ውሎ ምን እንደሚመስል እና የተሰማውን ስሜት ለማጣራትም ያቺ የአንዲት ቀን ጉማጅ እንደረዘመችበት አስታውሳለሁ።

ግን ምን ዋጋ አለው? የዛሬን አያድርገውና ፤በዕለቱ በግምት ከቀኑ 8 ሰዓት አካባቢ ከአውራምባ ታየምስ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል (ከዳዊት ከበደ እንደተደወለለት እንደነገረኝ ትዝ ይለኛ) ስልክ ተደወለለት። ስልኩንም አነሳ። ከዛም በዛሚ ኤፍ ኤም ሬዲዮ አንዱዓለምን፥ ፍኖተ ነፃነት ጋዜጣና ይዛ በወጣችው ሐሳቦች ዙሪያ በዛሚ ኤፌ ኤም ሬዲዮ “የጋዜጠኞች ክብ ጠረጴዛ” በሚለው የዕለቱ የቀትር መርሃ ግብር ነገር እየተቦካ እንደሆነ እና እንዲያደምጥ ተነገረው።

በወቅቱ ቢሮው ውስጥ መደበኛ ሬዲዮ አገልግሎት ስለሌለና በስልኩም አገልግሎቱን ማግኘት ስላልቻለ ቢሮው ከሚገኝበት ፎቅ በመውረድ የሰማውን ነገር ነገረኝ። ያቺ ደካማ ስልኬ ሬዲዮ እንደምትሰራ ጠየቀኝ። እኔም በስልኬ መሰል አገልግሎት አልባነት እየሳቅሁ የስራ ባልደረባዬ የነበረውን ጋዜጠኛ ብዙአየሁን ጠየቅኩት። የእሱም ስልክ እንደኔው የሬዲዮ አገልግሎት አልነበረውም። ከዛም የጋዜጣው ፀሐፊዎች የነበሩትን የሺን እና ብርቱካንን ጠየቅን እና ከአንዳቸው አገኘን። በመጨረሻም ከማን እንደሆነ ለጊዜው ባላስታውስም በተገኘው ስልክ በነ ሚሚ ስብሃቱ (ዛሚ ኤፍ ኤሜ ሬዲዮ) “የጋዜጠኞች ክብ ጠረጴዛ” በሚለው የዕለቱ መርሃ ግብር ላይ ስለ አንዱዓለም አራጌ፥ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ እና “ፍኖተ ነፃነት” ጋዜጣ የማክሰኞው መስከረም 2 ቀን 2004 ዓ. ም. ዕትም ይዘት ላይ ጭምር በነ ሚሚ ስብሃቱ፥ መሰረት አታላይ ፥ ፀጋልዑል መኮንን? እና ሁለት ሌላ ባልደረቦቻቸው በአደባባይ ሲቦጭቁ፥ ሲዘረጥጡና ሲወነጅሉ ሰማናቸው።

ሁላችንም በተደረገው የስም ማጥፋት እጅግ አዘንን፥ ተናደድን። ምክንያቱም እነ ሚሚ ምንም ያህል ለህወሓት/ኢህአዴግ ወግነው ጥብቅና የሚቆሙ፤ ኽረ እንደውም ከጳጳሱ ቄሱ ቢሆኑ እንኳ እንደዚህ በአደባባይ የሌለና ያልተፈፀመ እንዲሁም ያልተባለን ነገር ሽብር እንደተነዛና እንደተፈጠረ ተደርጎ መቅረቡ በጣም ያም ነበር። በርግጥ አሁንም ያው ናቸው። ውንጀላቸው በ “ፍኖተ ነፃነት” ጋዜጣ ላይ የወጡ ይዘቶችን፤ በተለይም የአንዱዓለም ቃለ መጠይቅ እና የጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ የአረቡን አብዮት በተመለከተ በአንድነት ፓርቲ በተደረገለት ግብዣ ያቀረበውን ትንታኔና ውይይት በተመለከት ነበር።

በነገራችን ላይ በአገዛዙ እና በአገዛዙ ወዳጆች በግል ሚዲያ ስም ድጋፍ እንደ ተቋቋመና እስካሁንም ሙሉ በጀቱ እንደሚሸፈንለት የሚነገረው የነ “ሚሚ ስብሃቱና ባለቤቷ ዘሪሁን ተሾመ” ዛሚ ኤፍ ኤም ሬዲዮ፤ “የጋዜጠኞች ክብ ጠረጴዛ” የሚለው የእሁድና ረቡዕ የሚዘጋጅ መርሃ ግብር አለ። ይህ ኤፍ ኤም ጣቢያ የህወሓትን ጥቅም ይጎዳሉ ተብለው የሚታሰቡ ጋዜጠኞች፥ ህዝባዊ ቅቡልነትና ከፍተኛ ድጋፍ አላቸው የሚባሉ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፥ አንዳንዴም የህወሓትን ክፉ ስራና ድርጊት ይገዳደራሉ ተብለው የሚታሰቡ በስሩ ያሉ አንዳንድ የኢህአዴግ መሪዎችም ጭምር ለህወሓት የበቀል እስርና እርድ የሚታጩበት ልዩ የቁጩ መርሃ ግብር ነው።

በዕለቱ ረቡዕ መስከረም 3 ቀን 2004 ዓ. ም. የነ ሚሚ ስብሃቱ ዛሚ ኤፍ ኤም ከህወሓት ደህንነት ጋር ቀጥታ ግንኙነት ብቻ ሳይሆን ተልዕኮም ተሰጥቷቸው እንደሚሰሩ ለመጀመሪያ ጊዜ ያረጋገጥኩትም ያኔ ነው። እውነት ለመናገር ልክ የነሱ ውንጀላ ከተጠናቀቀ በኋላ እጅግ በጣም ተሰማኝ፥ ተናደድኩ። ብቻ እንዴት እንደምገልፀው አላውቅም። ምክንያቱም የጋዜጠኝነት ሙያ ለእንዲህ ዓይነት ርካሽ ተግባር ሊውል እንደሚችል በፍፁም ገምቼ አላውቅም ነበርና።

የነ ሚሚ ውንጀላ ከተጠናቀቀ በኋላ በግምት ከ 30 ደቂቃ በኋላ የአንድነት ፓርቲ ኤዲቶሪያል ቦርድ ኃላፊ እና በፓርቲው የፍኖተ ነፃነት ጋዜጣ የበላይ ተጠሪ የነበረው አቶ በላይ ፈቃዱ ይመጣል። አቶ በላይም ሁላችንንም ሰላም ብሎን ስለጋዜጣዋ ዕትም ግርድፍ አስተያየት ( ማበረታቻና እርምት) ሰጥቶ ከአንዱዓለም ጋር ወደ ቢሮ ይገባሉ። ከተወሰኑ ደቂቃዎች በኋላም አንዱዓለምና በላይ ተያይዘው በበላይ መኪና እዛው ቀበና ባለው የአንድነት ዋናው ቢሮ አካባቢ ወደሚገኝ ካፌ ሻይ ቡና ለማለት ይሄዳሉ።

በወቅቱ ሁላችንም በሁኔታው ስለተናደድን ጥሩ ስሜት ላይ ባለመሆናችን የዕለቱን የከሰዓት በኋላ የኤዲቶሪያል ቦርድ ውይይት በይደር ለበነጋታው ሐሙስ አስተላልፈን ነበር። ስለሆነም ስለ ሚሚ ስብሃቱና በወቅቱ ስለወነጀሉ “ጋዜጠኞች” እንዲሁም ስለ ዛሚ የኋላ መረጃ ለመቃረም (በግሌ) ልምድ ወዳላቸውና ወደ ማውቃቸው ሰዎች አመራሁ። ይሁን እንጂ እኔ በወፍ በረር ከማውቀው የተለየ መረጃ አላገኘሁም። ከዛም ስለ ዛሚ ኤፍ ኤም ከኢንተርኔትና ብሮድካስት ባለስልጣን ድረ ገፅ የተሻለ መረጃ ባገኝ ብሞክርም ከማውቀው የተለየና ሚነግረኝን አጣሁ። ከዛም ስልኩ ቀደም ሲል ቢኖረኝም ለመጀመሪያ ጊዜ ደውዬ ላስቸግረው ወደ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ጋር ደወልኩ። ስልኩ ይጠራል አያነሳም። ያው ስራ ላይ ሆኖ ይሆናል በሚል ትንሽ ቆይቼ ደወልኩ፤ ስልኩ ይጠራል አይነሳም። በመጨረሻም ነገ እደውልለታለሁ ብዬ ወደ መኖሪያ ቤቴ አመራሁ።

ከዛም ለቀጣዩ ማክሰኞ ህትመት የሚሆን አዳዲስ መረጃ ከተገኘ በሚል ወደ ተወሰኑ የክፍለ ሀገር የመረጃ ምንጮች ጋር በመደወል ትንሽ ካወጋን በኋላ ሁለቱ በኢንተርኔት የመረጃ ሳጥኔ ውስጥ አዲስ መልዕክት እንደተውልኝ በምንግባባበት ቋንቋ ነገሩኝ። እኔም አመሻሹ ላይ ከቤቴ ሰፈር ካለ የኢንተርኔት ካፌ ደንበኛዬ ጋ እያመራሁ ሳለ አንድ ስልክ ከወንድሜ ተደወለ። አነሳሁ። የት ነህ? አለኝ። እዚሁ ሰፈር ነኝ አልኩት። ከዛም፤ ሰማህ? አለኝ። ምኑን? አልኩት። እነ እስክንድርና አንዱዓለም ታሰሩ፥ ዜናው በኢቴቪ ተለቋል አለኝ። አትቀልድ! ከአንድ ሰዓት በፊት ከአንዱዓለም ጋር ነበርኩ፤ ምንድነው ምታወራው? አልኩት። በቃ አትራቅ ብሎ ስልኩን ዘጋው። ውሽቱን መሰለኝ። ርግጥ ነው ማንም ቢሆን ሊያምን የሚችል አይመስለኝም።

ጋዜጠኛ እስክንድርን በተለይ በ1997 ዓ. ም. ቀውጢ ወቅት የክፍለ ሀገር ኮሌጅ ተማሪና ተመራቂ ብሆንም ሐዋሳ ለግሉ ፕሬስ ንባብና ገበያ እንግዳ አልነበረችም። ያኔ እስክንድርን በስራው አውቀዋለሁ። በዕድሜ ከኛ ላቅ ያሉ የምንግባባቸው አንዳንድ ሰዎች ደግሞ በደንብ በአካል የሚያውቁት ያህል አድናቂዎቹ እንደነበሩ አስታውሳለሁ። የመታሰራቸውን ዜና ያረዳኝ ወንድሜ ደግሞ በተመሳሳይ ዓመት አዲስ አበባ ተማሪና ተመራቂ ብቻ ሳይሆን ያን የጦዘ የተስፋ ፖለቲካና ሚዲያ ከተወሰነ ኩርኩም ጋር ስለቀመሰ ከእኔ በተሻለ እስክንድርን ያውቀዋል። ሲያደንቀውም ሰምቻለሁ። ነገር ግን በአካል የሚተዋወቁ አይመስለኝም። አንዱዓለምን በፖለትካው ተሳትፎው በሚዲያ ያውቀዋል እንጂ በአካል አያውቀውም።

ጋዜጠኛ እስክንድር ምኒልክ፥ አስኳል እና ሳተናው የሚባሉ ጋዜጦችን ለንባብ በማብቃት፥ በጋዜጠኝነት ስራውም ብዙ ዋጋ የከፈለ ሰው ነው። በኢትዮጵያ ፕሬስ ታሪክ በአንድ አገዛዝ ብቻ ተደጋጋሚ በደሎች ከደረሰባችውና ብዙ ዋጋ ከከፈሉ የሀገራችን ጋዜጠኞች ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል። በዛ ላይ ትሁት፥ ሰው አክባሪና ጠንቃቃ ነው። አሳዳጆቹንና አሳሪዎቹን እንኳ ጠንቅቆ ያውቃል፤ ግን ቦታ አይሰጣቸውም። ስለሀገራችን ኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታና ከእኛ ታሪክና የመንግሥት ምስረታ እጅግ የሚራራቅ የቅርብ ጊዜ ታሪክ ያላቸው ግን በተሻለ ሁኔታ ቀድመውን ከሄዱ የሌላው ዓለም ሀገሮች ጋር ያለንን ልዩነት ሲያወራ በቁጭት ነው። የጥሩ ስብዕና እና አርዓያ ባለቤት ነው፤እስክንድር።

አንዱዓለም አራጌ፤ ከጥላቻ፥ የበቀልክና ክፋት ፖለቲካ ማርከሻ እና ለእኛ ትውልድ መሪ ቢሆኑ ብዬ ከምመኛቸውና ከማውቃችው እጅግ ጥቂት ግለሰቦች አንዱዓለም አራጌ ዋነኛው ነው። መልካምነቱን፥ ቅንነቱን፥ ለሰዎች ያለውን አክብሮትና ፍቅር፥ ታታሪነቱን፥ብቃቱን፥ ለሀገርና ለወገን ያለውን ፍቅር እና መልካም ስብዕናውን በቅርብ አውቃለሁ። ህልሙን እና ፍላጎቱንም አይደብቅም። ሲብዛም ግልፅ ነው።

በጣም የሚገርመው አንዱዓለም በብዙ ነገር መልካም አርዓያ ነው። አንዱዓለም ከማንበብ በስተቀር ከማንኛውም ጎጂ ደባል ሱስ ነፃ ነው። በዚህ ሁሉ እደመማለሁ። ውሸትና ማስመሰል ደግሞ አይታይበትም። ሲበዛ የዋህ ነው። በየዋህነቱና በቅንነቱም በግፍ ከመታሰሩ በተጨማሪ በሌሎች ክፉዎች ወጥመድ ውስጥ ሁሉ ገብቶ እንደነበር አስታውሳለሁ (ይሄንን ከለውጥ በኋላ ጊዜ ሲደርስ እነግራችኋለው)። ይሄንንም ለምቀርባቸው ብቻ ሳይሆን እንደው በሀገራችን ፖለቲካ ዙሪያ ወሬ ከገረብን እና በመሪዎች ጉዳይ ሲወራ አንዱዓለምን በመልካም ምሳሌነት አነሳዋለሁ። ዛሬም ቢሆን እንዲሁ። ያንን ወንድሜ ያቃል። ስለዚህ ወንድሜ እንዴት ሰላማዊና መልካም አርዓያ የሆኑ ሰዎችን በተመለከተ መጥፎ የውሸት መርዶ ይነግረኛል? የሚል ጥርጣሬ አሳደረብኝ። እንዲህ ዓይነት ቀልድ ደግሞ ደስ አይልም፤ ያው ቀልድ ስለመሰለኝ።

ከዛ ወዲያው ወደ አንዱዓለም ጋር ስልክ ደወልኩ፤ ስልኩ ይጠራል ግን አይነሳም። በተደጋጋሚ ደወልኩ አይነሳም። እስክንድርም ጋር ደወልኩ አይነሳም። ዛሬ የምን ነጃሳ ቀን ነው እያልኩ ጥሩ ባልሆነ ስሜት ወደ ደንበኛዬ ኢንተርኔት ካፌ ደረስኩ። እሱም ዜናውን ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ተለቆ ሰምቶ ኖሯል ተናዷል፥ በጣም ተከፍቷል። እነኝህ ጅቦች አሰሯቸው አይደል? አለኝ፤ ገና ከመግባቴ። አሁንም ኢንተርኔት ከፍቼ እስካይ አላመንኩም። ብቻ የንዴት ስሜቴ እየናረ ሄደ። ወንበር ሳብኩና በተረበሸ ስሜት ጥግ ወዳለችው ኮምፒዩተር መነካካት ጀመርኩ። ስድስት ኪሎ ያለ አንድ የቅርብ ወዳጄ የእስሩን የመርዶ ዜና ከቁጭት ጋር አጋርቶ አየሁ። ደነገጥኩ። ማመን አልቻልኩም። ከዛ ገለልተኛ የሚዲያ ወግ ከሚናፍቀው ኢቴቪ የተጋራውን ዜና ሰማሁ። በጣም ስሜታዊ ነበርኩ፤ነኝም። የንዴትና ቁጭት ለቅሶ ፈንቅሎ ወጣ። ቀደም ሲል የክፍለ ሀገር መረጃዎችን ለማየትና ለመገረብ ከቤት ብወጣም በሰዓቱ እነኛን መረጃዎች ማየት አልፈለኩም። ጭራሽ ሌላ በርካታ መልዕክቶች እንደተላኩ የመረጃ ሳጥኔ ያሳየኛል። እኔ ግን በዛ ስሜት ውስጥ ሌላ መረጃ ማየትም ሆነ ማጋራት አልፈለኩም። በምን ስሜት? ከዛም በርካታ የስልክ ጥሪዎች መጡ ማንሳት አስጠላኝ።

የኢንተርኔት ካፌው ባለቤት ረዳት ሆና ምትሰራው ልጅ ስሜታችን ግራ ቢገባት በተሸማቀቀ የፍርሃት ስሜት ታየናለች። ባለቤቱም በሁኔታው ስለተናደደ ያለወትሮው ከአምስት ደቂቃ በኋላ ቤቱን ስለሚዘጋ ሌሎች መደበኛ ደንበኞቹ ቶሎ ጨርሰው እንዲወጡ ትብብር ይጠይቃቸዋል። ሰራተኛዋንም ነገ በስራ ሰዓቷ እንድትመጣና በወቅቱ ወደ ቤቷ መሄድ እንደምትችል ይነግራታል። እኔና እሱ ብቻ ቀረን፤ በንዴትና ቁጭት ስሜት ውስጥ …. ። ትንሽ ካወራን በኋላ ኢንተርኔት ካፌውን ዘግተን ሁለታችንም ወደየቤታችን ሄድን። ቤት ስገባም በምሽት ድጋሚ ዜናውንና ድራማውን አየሁ። ህልም ሁሉ መሰለኝ። ምክንያቱም ለእንዲህ ዓይነት የጭካኔ ድራማ ምልከታ ገና እንግዳ ነበርኩና።

ለካ የዛን ዕለት እነ ሚሚ ስብሃቱ “በጋዜጠኞች ክብ ጠረጴዛ” መርሃ ግብራቸው ሲነግሩን የነበረው በህወሓት ደህንነት የታቀደና ያለቀ የእስር መርዶ ነበር፤ ወይ አለማወቅ!?

በዕለቱ እስክንድር ልጁ ናፍቆትን በራሱ መኪና ሰላም ባይኖርም፤ እንደወትሮው ሀገር አማን ብሎ ልጁን ከትምህርት ቤት ወደ መኖሪያ ቤቱ ይዞት እየመጣ ሳለ በበርካታ ፖሊሶች፥ የደህንነት ባልደረቦችና የህወሓት ካሜራማኖች ተደርድረው መንገድ ላይ ያውም አደባባይ ላይ እንደወንጀለኛ አስቁመው የያዙት። ምን ይሄ ብቻ፤ በህፃን ልጁ ፊት እጆቹን በካቴና አስረው ነው ያንገላቱት። በወቅቱ በስፍራው የነበሩ እንደነገሩኝ ከሆነ በህወሓት የወንጀል ድራማ ልጁ ናፍቆት ተደናግጦ አምርሮ ሲያልቅስ እንደታዘቡ በሀዘን አጫውተውኛል። ተመልከቱ! በሚያድግ ህፃን ልጅ ፊት እንደዛ ያለ ነውር ነው የፈፀሙት።

ያኔ የህፃን ኖላዊ እና ሩህ አባት አንዱዓለም አራጌ እና የህፃን ናፍቆት አባት ጋዜጠኛ እስክንድር በግፍ ታሰሩ። ባልዋሉብት፥ በሚጠሉትና በሚታገሉት መንግሥታዊ ሽብር ጭራሽ ተወነጀሉበት። ከዚያም የግንቦት 7 አባል ናችሁ ተብለው ፤ ጋዜጠኛ እስክንድር ላይ 18 ዓመት፥ አቶ አንዱዓለም አራጌ ላይ ደግሞ ዕድሜ ልክ ፈረዱባቸው።

በነገራችን ላይ በተመሳሳይ ክስ በዛው ቀን እዛው አዲስ አበባ ከእስክንድርና አንዱዓለም በተጨማሪ ከአንድነት ፓርቲ መምህር ናትናኤል መኮንን እና አሳምነው ብርሃኑ፤ ከመኢዴፓ አቶ ክንፈሚካኤል ደበበ (አበበ ቀስቶ) እና አቶ ዘመኑ ሞላ ታስረው ነበር። ከክፍለ ሀገር ደግሞ የአንድነት ፓርቲ አመራር የነበሩት ሻምበል የሺዋስ ይሁንዓለም፥ አቶ ዮሐንስ ተረፈ፥ እና አቶ ሻማ ነበሩበት። ይሁን እንጂ አቶ አሳምነው ብርሃኑ፥ ዘመኑ ሞላ እና አቶ ሻማ (የቤተ እስራኤል ማኅበረሰብ አባል እንደሆነ እና ወደ እስራኤል ለመሄድ ጉዞ ዝግጅት ላይ እያለ የታሰረ) አብረዋቸው በታሰሩት ላይ በግድ እንዲመሰክሩ ተደርገው ተለቀዋል።

የአንድነቱ መምህር ናትናኤል መኮንን አቶ አንዱዓለም አራጌ ላይ በሐሰት ” የግንቦት 7 አመራር ነው፥ ተዕልኮ ሰጥቶች ሀገር ልናሸብርን ተነጋግረን ወስነናል በል” ተብሎ ልክ እንደ አቶ አሳምነው ብርሃኑ መስክሮ እንዲወጣ ተደጋጋሚ ማስፈራሪያ፥ ድብደባና ዛቻ ደርሶበታል። ይሄንንም በተደጋጋሚ ፍርድ ቤት ችሎት ላይ ቢያመለክትም ሲመለሰ ከበፊት በከፋ መልኩ ተደብድቧል፥ ለ21 ቀናትም ራቁቱን ውጭ ላይ ቀዝቃዛ ውሃ እየተደፋበት ተገርፏል፥ ብዙ ስቃይ ደርሶበታል። ግን እንዳሉት በሐሰት ለመመስከር ፈቃደኛ ሳይሆን በመቅረቱ 25 ዓመት እስር ፈርደውበት እዛው ወህኒ ቤት ይገኛል። መምህር ናትናኤል ደግሞ ከስራ ወደቤቱ በአምበሳ የከተማ አውቶቡስ ውስጥ ከስራ ወደቤቱ ሲያመራ ነው በፖሊሶች መኪና ከበባ ተሳፋሪው በሙሉ ታግቶ ተይዞ የታሰረው።

አቶ ክንፈሚካኤል ደበበ የአሁኑ እስርና ስቃይ ብቻ ሳይሆን ከዚህ በፊት ልክ እንደሌሎቹ ብዙ ስቃይ እንደደረሰበት ፍርድ ቤት ተናግሯል። ስለሱ ማውቅ የሚፈልጉ የበለጠ የኤርምያስ ለገሰ “የመለስ ትሩፋቶችና ባለቤት አልባ ከተማ” የሚለው መፅሐፍ ላይ የተወሰነ ነገር ያገኛሉ። ሌላው ክንፈሚካኤል ደበበ (አበበ ቀስቶ) በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በሚያስብል ድፍረት ንጉስን በመፈንቅለ መንግሥት ለመጣል ሙከራ አድርገው የከሸፈባችውና አርዓያ የነበሩት የወንድማማቾቹ የነ ጀነራል መንግሥቱ ነዋይ እና አቶ ግርማሜ ነዋይ የቅርብ የሥጋ ዘመድም ነው።

በሙያው የሶስት ዓለም አቀፍ የፕሬስ ሽልማቶች ባለቤት የሆነው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ከዚህ በፊት 7 ጊዜ ታስሮና ቶርቸር ተደርጎ የተለቀቀ ሲሆን፤ አሁን 7ኛ ዓመቱን እስር ላይ እያሳለፈ ያለው ለ8ኛ ጊዜ ከታሰረ በኋላ ነው። አቶ አንዱዓለም አራጌ ደግሞ በ1997 ዓ ም በነበረው ምርጫ ግርግር ከወቅቱ የቅንጅት አመራሮች ጋር ታስሮ በተመሳሳይ ዕድሜ ልክ ፈርደውበት ነበር። ከሁለት ዓመት በኋላም ከሌሎች የቅንጅት አመራሮችና ጋዜጠኞች ጋር ከተለቀቀ በኋላ ነው ድጋሚ የታሰረው።

አሳዛኙ ነገር፤ ” መንግሥት” በቅርቡ በሀገሪቱ ህዝብና በዓለም አቀፍ ምኅበረሰብና ተቋማት በደረሰበት ጫና የህሊና እና የፖለቲካ እስረኞችን እንደሚፈታ ቃል ገብቶ ነበር። ይህንንም ተከትሎ ባለፈው አንጋፍውን የኦፌኮ/መድረክ ፓርቲ አመራር ዶ/ር መረራ ጉዲናን ጨምሮ በርካታ ዜጎችን ከእስር መልቀቁ ይታወቃል።
ሰሞኑን ደግሞ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ እና አንዱዓለም አራጌን ጨምሮ የቀሩ በርካታ የህሊና እና የፖለቲካ እስረኞች በቅርቡ እንደሚፈቱ ይፋ አድርጓል። መንግሥት ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፥ አቶ አንዱዓለም አራጌ፥ አቶ ክንፈሚካኤል ደበበ ባልተቀበሉት፥ በተከሰሱአበትና በተፈረደባችው ክስ ” የግንቦት 7 አባልና አመራር ነበርኩ፥ በፈፀምኩት የሽብር ተግባር ተፀፅቻለሁ፥ መንግሥትንና ህዝቡን ይቅርታ እጠይቃለሁ” ብላችሁ ፈርሙና ውጡ ማለቱ ተሰምቷል። ይሁን እንጂ የመንግሥት የወንጀል ይቅርታ ጥያቄው በነ እስክንድር ተቀባይነትን ሊያገኝ አልቻለም።

በእስር ያሉ የሙስሊሙ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴዎችም በተመሳሳይ ጥያቄ ” በፈፀምነው የሽብር ተግባር ተፀፅተናል፥ መንግሥትና ህዝቡን ይቅርታ እንጠይቃለን” ብላችሁ ፈርሙና ውጡ የሚለው የመንግሥት ተማፅኖ ተቀባይነት አላገኘም። ይፈታሉ ከተባሉ የህሊና እና የፖለቲካ እስረኞች በተጨማሪ እነ አቶ በቀለ ገርባ እና አቶ ኦልባና ሌሊሳን ጨምሮ በርካታ ሰዎች አሁንም እስር ላይ እንደሆኑ ይታወቃል።

በርግጥ አንድ እውነት አለ። መንግሥት በደረሰበት ጫና እንጂ ለእስረኞ አዝኖ ወይም እስረኞችን በግፍ ስላሰቃያቸው ተፀፅቶና ርህራሄ ተሰምቶት አይደለም የለቀቃቸውና ሊለቃቸው የፈለገው። አሁን ያለው የሀገር ውስጥ የፖለቲካ ድባብ፥ የህዝቡ ዛሬም ያልተቋጨ ትግልና የዓለም አቀፉ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ጫና በርትቶበት እንጂ። ስለዚህ መንግሥት ጊዜ ያለፈበትን የፖለቲካ መቆመሪያ ቅድመ ሁኔታ ትቶ ሁሉንም በሚባል ደረጃ የህሊና እና የፖለቲካ እስረኞች የመለቀቁ ጉዳይ ቀጥይ እንደሚሆን ይገመታል። ከለው ተለዋዋጭ የሀገሪቱ የፖለቲካ ትኩሳት አኳያ ከህሊና እስረኞች መለቀቅ በኋላስ የሚለውን የሀገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታ በተመለከተ ያው ጊዜ ይፈተዋል ከማለት ውጭ መተንበይ አስችጋሪ ነው።

ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ እና አቶ አንዱዓለም አራጌ 5 ዓመት እስር እንደዋዛ

ጋዜጠኛና ጦማሪ እስክንድር ነጋ እና የሰላማዊ ትግል አቀንቃኝ ፖለቲከኛ አቶ አንዱአለም አራጌ በሽብር እና በሃገር ክህደት ወንጀል ፅኑ እስራት ተፈርዶባቸው እስር ቤት ከገቡ መስከረም 3 ቀን 2009 ዓ.ም ድፍን አምስት ዓመት ሆናቸው፡

እስክንድር “ንፁህ ስለሆንኩኝ፣ የቀረበብኝ ማስረጃ የሌለ በመሆኑ እንዲሁም ፍርድቤቶችን የሚያህሉ የተከበሩ ተቋማት የበቀል የአፈናና የጭቆና መድረክ መሆን ስለሌለባቸው በነፃ እንድለቀቅ የተከበረውን ፍርድቤት እጠይቃለሁ” ብሎ በፌደራል ጠቅላይ ፍርድቤት ይግባኙን በነሐሴ 2004 ዓ.ም ያቀረበ ቢሆንም የከፍተኛው ፍርድቤት የፈረደበትን የአስራ ስምንት ዓመት ፅኑ እስራት እና አምስት አመታት ህዝባዊ መብቶች እግድ ጠቅላይ ፍርድቤቱም አፅንቶበት የፍርዱን ሩብ አመታት በእስራት አሳልፏል፡፡

በፌደራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር አዲስ አበባ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት አምስት አመታትን በእስር ሲያሳልፍ ዘንድሮ የ48 አመት ጎልማሳ የሚሆነው ጦማሪው እስክንድር ነጋ በየኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራያዊ ግንባር /ኢህአዴግ/ መንግስት ለሰባተኛ ጊዜ ሲታሰር በበርካታ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብተ ተሟጋች ድርጅቶች እስራቱ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደሆን ደምፃቸውን ከፍ አድርገው አምስቱንም አመታት ለኢትዮጵያ መንግስት ውትወታቸውን አስምተዋል፡፡
ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ የፍርድቤት የችሎት ሂደቱን በመከታተል ላይ እያለ በግንቦት ወር 2004ዓ.ም ፔን አሜሪካ ከተባለ አለማቀፍ ድርጅት በአደገኛ የመገናኛ ብዙሐን ድባብ ውስጥ ሆኖ በመፃፍ ላደረገው አስታዋፅኦዖ “የመፃፍ ነፃነት ሽልማትን” አግኝቷል፡፡ በዚሁ አመት አለማቀፉ የሰብዓዊ መብት ተማጋች ድርጅት አምነስቲ ኢንተርናሽናል እስክንድር ነጋ የህሊና እስረኛ ስለመሆኑ አውጇል፡፡

ለሰባተኛ ጊዜ ለእስር በተዳረገ በአንድ አመት ከአራት ወራት ጊዜ ውስጥ በታህሳስ 2005ዓ.ም ደግሞ የሂውማን ራይትስ ዎች የነፃ ንግግር ሽልማት አሸናፊ ከመሆኑ በተጨማሪ በ36ተኛው አለማቀፍ የፀሃፊዎች ፌስቲቫል ላይ እስክንድር ነጋ የፔን ካናዳ “የአንድ ስብዓዊነት ሽልማት” አሸናፊ ሆኗል፡፡

በጋዜጠኝነት ሙያው በሚሰራው ስራ የኢትዮጵያ የፀረ ሽብር አዋጅ ቀደምት ሰለባ የሆነው ጋዜጠኛ እስክንድር በ1997 ዓ.ም የተደረገውን አገር አቀፍ ምርጫ ተከትሎ መንግስት በአገር ክህደት፣ አመፅ በመቀስቀስ፣ህገ መንግስት እና ህግ መንግስታዊ ስርዓቱን በሃይል በመናድ ወንጀል ተከሶ ፍርድ ቤት የፈረደበት ቢሆንም አንድ አመት ከአምስት ወራት እሰራት በኃላ ክሱ ተቋርጦ መለቀቁ ይታወሳል፡፡

የኢንተርናሽናል ወመንስ ሚዲያ አሶሴሽን “የብርቱ ጋዜጠኛ” ሽልማት አሸናፊ የጋዜጠኛ እስክንድር ባለቤት ጋዜጠኛ ሰርክዓለም ፋሲልም የ1997 ዓ.ም ምርጫን ተከትሎ ከባለቤቷ ጋር በተመሳሳይ ክስ በአንድነት ታስራ በቃሊቲ እስር ቤት ሳለች የመጀመሪያ እና ብቸኛ ልጃቸውን ናፍቆት እስክንድርን ተገላገላለች፡፡

የያኔው ስድስተ አመት ህፃን ልጁን ከትምህርትቤት ወደ ቤት እያመጣ ሳለ በድንገት ያለምንም ማስጠንቀቂያ በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋለው እስክንድር ነጋ እነሆ ዛሬ አብረውት ከተከሰሱት 23 አባሪዎቹ ጋር አምስት አመትን ሲደፍን የቀደሞ የአንድነት ፓርቲ ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበርና የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አንዷለም አራጌም የእድሜ ልክ እስራቱን በቃሊቲ ማረሚቤት እየገፋ ይገኛል፡፡

‹ምርጫ 97ን›› ተከትሎ ወህኒ ከወረደው የቅንጅት አመራር አንዱ የነበረው የያኔው ወጣት የአሁኑ ጎልማሳ፣ በብዙዋች ዘንድ የሰላማዊ ትግል አርበኛ ተበሎ የሚወደሰውአንዷለም አራጌ የቅጥት ማቅለያ እንዲያቀርብ በፍርድቤት ሲጠየቅ አንዷለም አራጌ እንዲህ ብሎ ነበር ማቅለያውን ያቀረበው፡፡ “እኔም ለልጆቼ፣ ለወገኖቼ፣ ለአገሬ እና ለራሴ በመረጥኩት ሰላማዊ ትግል ስታገል ቆይቻለሁ፡፡ የበደልኩት ህዝብ አለ ብዬ አላምንም፡፡ ወንጀል ሰርቻለሁ ብዬ አላሰብም፡፡ ውስጤ ፍፁም ሠላማዊ ነው ከሳሾቼ የሚስጡኝን የግፍ ፅዋ ለመጠጣት ዝግጁ ነኝ፡፡”

አቶ አንዷለም አራጌ “ያልተሄደበት መንገድ” የሚል የመጀመሪያ መጸሐፉን በእስር ላይ ሆኖ ከቃሊቲ ማረሚያ ቤት ለአንባቢያን አደርሷል፡፡ በ2007 ዓ.ም ሰኔ ወር ደግሞ “የሀገር ፍቅር እዳ” የተሰኘው ሁለተኛ መጽሐፋ ዳግም ለህትመት በቅቷል፡፡

እስካሁንም ድረስ በእስር ላይ የሚገኙት እነዚህ የሰላማዊ ትግል አርበኞ አዲሱን አመት 2009 ዓ.ም የተቀበሉት አምስተኛ አመታቸውን በማሰብ ነው፡፡

እስክንድር ነጋ እና አንዷዓለም አራጌ በፍትህ እጦት አመታትን በእስር እንዲያሳልፉ ሲገደዱ እስራቸው አገሪቷ በዓለም አቀፍ ህግ መደረክ ተገዢ እሆናለሁ ብላ ቃል የገባችባቸውን የቃልኪዳን ሰነዶች ሁሉ የናደ ሰለመሆኑ የሰበዓዊ መብት ተሟጋቾች በተደጋጋሚ ሲሞግቱ አምስት አመታት አልፈዋል፡፡

ዛሬም አስራቸው ህገ መንግስቱን የጣሰ፣ አላግባብ፣ ኢፍታዊ እና የሰብዓዊ መብቶቻቸውን ያላከበረ ነው ፡፡ አንዱአለም በተለምዶው ቅጣት ቤት ተብሎ የሚጠራው ከፍተኛ ጥበቃ የሚደረግበት ክፍል ውስጥ ታስሮ ሲገኝ እስክንድር በቃሊቲ የተለያዩ ዞኖች ታስሯል፡፡ ሁለቱም እስረኞች ከቅርብ ቤተሰብ ውጪ ማንም እንዳይጠይቃቸው የተከለከሉ ሲሆን ከእስራቸው እስከ አያያዛቸው ኢሰብአዊነትን እያስተናገዱ አምስት አመት አስቆጥረዋል፡፡
ምንጭ፡- EHRP

%d bloggers like this: