Tag Archives: Ethiopian Human Rights

የዋልድባ መነኮሳት ክሳቸው ተቋረጦ ከእስር ተለቀቁ

በፌደራል አቃቤ ህግ በሽብር ወንጀል ተከሰው ለበርካታ ወራት ታስረው የነበሩት የዋልደባ መነኮሳት ከእስር ተፈቱ። መነኮሳቱ ከዋልደባ ገዳም ታፍነው ለበርካታ ወራት ታስረው ጉዳያቸው በፍደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት ሲታይ ቆአይቶ በመጨረሻም ክሳቸው ተቋርጦ ተፈተዋል።

Waldeba Monastry arrested monks
መነኮሳቱ ልደታ ፍርድ ቤት ሳሉ

መነኮሳቱ በአዲስ አበባ በሚገኘው ቃሊቲ ፌደራል ወህኒ ቤት ባሉ የጥበቃና የደህንነት አባላት ተደጋጋሚ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ይፈፀምባቸው እንደነበር አብቱታዎቻቸውን ለፍርድ ቤት ሲያቀርቡ እንደነበር ይታወሳል።

መነኮሳቱ አባ ገብረኢየሱስ ኪዳነ ማርያም፥ አባ ገብረሥላሴ ወልደኃይማኖት፥ መርጌታ ዲበኩሉ እንዲሁም አቶ ለገሰ ወልደሐና፥ አቶ ሀብታሙ እንየው ጨምሮ 114 የፖለቲካ እስረኞች ክሳቸው ተቋርጦ ከታሰሩበት ወህኒ ቤት ተለቀዋል።

በመጨረሻም፤ መነኮሳቱ ከእስር በመፈታታቸውን ፈጣሪን በማመስገን አሁንም በርካታ ዜጎች ፍርድ ቤት እንኳ ሳይቀርቡ ለዓመታት በውህኒ ቤት ያሉ እንዳሉ እና ሀገሪቱ ኢትዮጵያ እና ኃይማኖታቸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን እስር ላይ እንዳሉ በማስታወስ ሁሉም ከእስር ነፃ ካልወጡ ራሳቸውን ከእስር እንደተፉ እንደማይቆጥሩ ተነግረዋል።

አናፈገፍግም!

አንዱዓለም አራጌ

በቅርቡ 6 ዓመት ከ6 ወራት እስር በኋላ በድጋሚ ለ11 ቀናት ከነጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ጋር ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ያለምንም ህጋዊ መሰረት ታስሮ ብዋስ ተሰናብቷል። በእስር ከመቆየት ውጭ 11ዱም ታሳሪዎች ምንም ዓይነት ክስ አልተመሰረተባቸውም። አንዱዓለም አራጌ ምርጫ 1997 ዓ ም ጨምሮ በሥልጣን ላይ ባለው አገዛዝ በቅርቡ ለ3ኛ ጊዜ ታስሮ ክተፈታ በኋላ የሚከተለውን ማለቱ ተጠቁሟል። መልካም ንባብ።

Andualem Arage
አቶ አንዱዓለም አራጌ

“ከስድስት ዓመት ተኩል የከፋ እስር በኋላ ከዘመድ፣ ወዳጅና ደጋፊዎች ጋር መገናኘት መቻላችን በሁላችንም ዘንድ ትልቅ ደስታ ፈጥሯል። የደስታችን ተካፋዮች የሆኑ ሁሉ፣ በተለያየ መንገድ እየገለጹልን በደስታ ባህር እየዋኘን ነው። ለወትሮም ቢሆን ስሙን እንኳን በውል በማናስታውሰው ጀሞ፣ ደጋፊዎቻችን አቀባበል ሊያደርጉልን ቀጠሮ ተይዟል።

በተመሳሳይ ዕለት በሰዓታት ልዩነት የሰማያዊ ፓርቲ ከእስር ለተፈታን ግለሰቦች፣ የምሳ ግብዣ በሳሮማሪያ ሆቴል በማዘጋጀቱ ወደዚያው አመራን። የአገዛዙ ደህንነቶች ሰላማችንን እንዳያደፈርሱብን ስጋት ቢገባንም እጥር ምጥን ያለው ግብዣ፤ በጥሩ ሁኔታ ተጠናቀቀ። ሁላችንም ደስተኞች ነበርን።

ከዚህ ዝግጅት መልስ፣ የተወሰንን ከእስር ተፈቺዎችን ለማክበር የተዘጋጀውን ፕሮግራም ለመታደም፣ ብዙዎቻችን የጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ እናት መኖሪያ ቤት ወደሚገኝበት ወደጀሞ ኮንዶሚኒየም ቁጥር 1 አመራን። በቦታው ስንደርስ፤ ከመኖሪያ ህንጻው መግቢያ አጠገብ የቡና ሲኒው ተደርድሮ፣ ቄጠማ ተጎዝጉዞና የኢትዮጵያ የኢትዮጵያ የሚሸቱ ድፎ ዳቦዎች፣ ዳንቴልና ቢላዋ ደርበው የሚባርካቸውን ይጠብቃሉ። ፈንዲሻው ከተደረደሩት ሲኒዎች ጋር ተወዳጅቶ ልዩ የበዓል አይነት ድባብ ፈጥሯል። ከሁሉም በላይ ደግሞ ይቺ የአድዋ ጀግኖች ሁለንተናቸውን ያልሰሰቷት የኢትዮጵያ ሰንደቅና የአፍሪካውያን የነጻነት ብስራት አጥር ላይ በክብር ተሰቅላለች።

በእስር ቤት ገርጥተን፣ ሰውነታችን ቢጎሳቆልም ለነጻነት ያለን ህልም አልሟሸሸም፤ በውስጣችን ፈረጠመ እንጂ። መዘባበቻ ሊያደርጉን በውሸት ዶሴ ቢያስሩንም፤ በህዝብና በፈጣሪ ችሎታ እውነት ከፍትህ ሚዛን አልወደቀችም። በህዝብና ፈጣሪ ከሚገባው በላይ አከበሩን። ከህዝብ ፈቃድ ጋር መላተም እንደግብ የሚቆጥረው አገዛዝ፣ እንደወትሮው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መጫኑን እኛም በራዳራቸው ውስጥ እንደሆንን አልዘነጋንም። ሆኖም በወቅቱ ለእኛ የተዘጋጀውን ዝግጅት ህገ-ወጥ የሚያሰኝ የጊዜያዊ አዋጅ አንቀጽ አልነበረምና ዝግጅቱን በእርጋታ እንዳንከታተል እረፍት የሚነሳን ነገር አልነበረም።

ለዝግጅቱ የሚቀርብ የሚቀርብ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አንቀጽ ካለ፣ “የአደባባይ ሰልፍና ስብሰባ ተከልክሏል” የሚለው ነው። ይህንን አንቀጽ ምንም ያህል ብንለጥጠው በአንድ ኮንዶሚኒየም ስር ቡና አፍልቶ፣ ዳቦ ቆርሶና ፍንድሻ ቆርጥሞ ደስታን መግለጽ ለአገዛዙ ስጋት የሚሆንበትንና አዋጁን የሚጥስበትን መንገድ ማየት አልቻልንም። ነገር ግን፣ እንደሁልጊዜው ከህግ፣ ከሞራልና ከእውነት ያፈነገጠ የአገዛዙ አካሄድ ሊኖር እንደሚችል መገመት አያስቸግርም።

አጠር ያለው ፕሮግራማችን፣ ለተወሰንን ከእስር ተፈቺዎች የጃኖ ባህላዊ ልብስ ሽልማት በማበርከት፣ እኛም የተሸለምነውን ጃኖ እንደለበስን አጠር አጠር ያሉ ንግግሮችን በማድረግ ተጠናቀቀ። አንዳንዶች እንደለበሱት ሲሄዱ ጥቂቶቻችን በማድረግ ተጠናቀቀ። አንዳንዶች እንደለበሱት ሲሄዱ፣ ጥቂቶቻችን ልብሳችንን ለመቀየር ወደቤት ገባን። ቀይረን ስንመለስ አብዛኛው ታዳሚ ወደመጣበት ተመልሷል።

ሁለት ፖሊሶች ግን በግቢዋ ውስጥ ቆመዋል። አንደኛው ፈንጠር ብሎ የቆመ ሲሆን ሌላኛው ጠጋ ብሎ አተካራ ውስጥ ገብቷል። አጥር ላይ የተሰቀለውን ባንዲራ እያስወረደ ነው። በአንድ የመኖሪያ ቅጥር ግቢ ውስጥ የተሰቀለውን ባንዲራ ምንም ያህል ኮከብ ባይኖረው፤ ምንም ያህል የሚያስወርድበት የህግ መሠረት ባይኖረውም፣ ትዕዛዙን ተቀብለው ባንዲራውን አውርደዋል። መንጠቅ ባይገባውም ነጥቋል። ተመስገን ደሳለኝ ሊያረጋጋውም ቢሞክር እንደአንባጓሮ ቆጠረው። ብዙዎቻችን በለዘበ አንደበት ልናረጋጋው ብንሞክርም መረጋጋት እራቀው። ይስባ ብሎም፣ ከዝግጅቱ አዘጋጆች ሁለት ሰዎች እንድንሰጣቸው ጠየቁ። አሳልፈን እንደማንሰጠው አስረግጠን ነገርነው። ተጨማሪ ሀይል ይላክለት ዘንድ ወደአለቆቹ ደወለ። ተጨማሪው ሃይል ደረሰ። የተሻለና ውጥረቱን የሚያረግብ ግን ከመካከላቸው አልነበረም። ጣቢያ ሄደን እንደምንጠየቅ ተነጋገርን። መኪና አልነበራቸውምና በእግራችን እንድንቀድም ተጠየቅን። ትዕዛዛቸውን ተቀብለን ጉዞ እንደጀርመን መኪናው ደረሰ። የፖሊስ ብቻ ሳይሆን የህዝቡም ቁጥር ጨመረ። በየኮንዶሚኒየሙ መስኮት ላይ ነዋሪዎች አንገታቸውን አስግገው ትዕይንቱን ሌላ ገጽታ አላበሱት። ጸሐይ ወደማደሪያዋ ሄዳለች፤ ጨለማውም ልክ እንደፖሊሶቹ ሁሉ ዙሪያችንን እየከበበን ይገኛል።

እንደልማዳችን በውል በማናውቀው ምክንያት በቁጥጥር ስር ውለን ወደጣቢያ ተነዳን። ሆኖም በማናችንም ላይ አንዳች የመረበሽ ስሜት አልነበረም። ታስረን እናድራለን የሚል ሀሳብ በብዙዎቻችን ዘንድ አልነበረም። ፖሊስ ጣቢያ ያገኘናቸው ፖሊሶችና ሃላፊዎች የጨዋ በሚባል ሥነ-ምግባር አስተናገዱን። ቀድሞውንም ነገሩን ያወሳስብ የነበረው ፖሊስ አሁንም ከቁጥጥር ውጪ ሆኗል።

ከሌላ ፖሊስ ጋር ሆኖ፣ ኮከብ የሌለውን ባንዲራ “ጨርቁን” ለምን ያዛችሁ? በማለት ማንቋሸሽ የተሞላበት ጥያቄ ያቀርባሉ። በአድዋና በሌሎች የጀግንነት ውሎዎች ኢትዮጵውያን አባቶች ነፍስና ስጋቸውን የሰጡላትን አርማ የፖሊስ አባላት ሲያዋርዱት መስማት፤ ፍጹም የሚያሳዝንና የሚስያጨንቅ ነበር። ይኼንኑ ከነገርናቸው በኋላ መጠነኛ መረጋጋት ተፈጠረ።

በመጨረሻም፣ ወደምሽት 4፡00 ሰዓት አካባቢ ሃላፊ ኮማንደሮች ወደምንገኝበት ፖሊስ ጣቢያ ደረሱ። አንደኛው ሁኔታውን ለመረዳት የሚያስችላቸውን ጥያቄዎች አንስተው ምላሽ ሰጠናቸው። ከሁኔታቸው ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ የሚፈቱን ይመስል ነበር። ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ወደሌላ ፖሊስ ጣቢያ ሄደን እንደምንነጋገር ነግረውን ወደዚያው አመራን። እነርሱ ብቻ በሚያውቁት ምክንያት ግን ሊያስሩን ፈልገዋል። ሲነጋ በጉዳዩ ላይ እንደምንነጋርገበት እስከዚያው ግን ጣቢያው እንደምናድር ነግረውን ወደሞቀ አልጋቸው ነዱ።

ማህሌት ፋንታሁንና ወይንሸት ሞላ ወደሴቶች ክፍል ተወሰዱ፡፡ የተቀረነው እስረኞች ደግሞ በሶስት የወንዶች መታሰሪያ ክፍሎች ተመደብን፡፡

እኔና ተመስገን ደሳለኝ፣ ከሌሎች ሁለት ጓደኞቻችን ጋር ሦስተኛ ቤት ተመደብን፡፡ ሦስተኛ ቤት ‹‹ሸራተን›› በመባል ይታወቃል፡፡ በሩ ሲከፈት ከውስጥ የሚወጣውን የተደበላለቀ መጥፎ ጠረን ያዘለ እንፋሎት ወደውጪ ተንደርድሮ ሲወጣ፣ ፊታችንን ገረፈን፡፡ ወደኋላ ብናፈገፍግም ወደውስጥ የሚገፉን ፖሊሶች ከኋላችን ቆመዋል፡፡ አንደኛው፣ የአገዛዙ አፋና ሰለባዎች የሆኑ ከሰበታ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምክንያት የታሰሩ ወገኖቻችን፤ በደረቅ ወንጀል ከታሰሩ ጥቂት እስረኞች ጋር እንደፍልጥ ታስረው፣ ‹‹አስመራ ድርድር›› በሚባለው መንገድ በሩ ስር ተነጥፈዋል፡፡ በሩን በደንብ መክፈት አልተቻለም፡፡ ግድ ነውና እንደሚሰጣ ልብስ እየተጨመቅን ወደውስጥ ገባን፡፡ ለመተንፈስ የተበከለውን አየር መማግ ግድ ነው፡፡ እየተናነቀንና እያቅለሸለሸንም ቢሆን፣ የገዢዎቻችንን ትሩፋት ማግነው፡፡ የሚኮሩበት ተግባር ቢሆንም፤ የተኙ እስረኞች ላይ ላለመውደቅ በጥፍራችን ቆመን እተፍገመገምን ክፉውን ልባቸውን ፈጣሪ ይፈውሰው ዘንድ መመኘት አላቆምንም፡፡

ተመስገን፣ በወገብ ህመም ምክንያት ይሰቃይ ነበርና የሁላችንም ሀሳብ እርሱ ጎኑን የሚያሳርፍበትን መሬት መፈለግ ነበር፡፡ አንድ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የታሰሩ አባት፣ የሞት ሞታቸውን ተጠጉለትና በእርሳቸውና በሌላ እስረኛ መሃል ተሸጠ፡፡ ስንታየሁ (ቸኮል)ም በእስረኞች መሃል እንደምንም እግሮችና ጭንቅላቆቻቸውን ተሸክሞ የተጋመሰውን ሌሊት ተጋፈጠው፡፡ በደቂቃዎች ውስጥ ሁላችንም እያላበን ነው፡፡ እኔና ተፈራ ተስፋዬ ግን ጎናችንን የምናሳርፍበት ቦታ አልተገኘልንም፡፡

ተፈራ የተዘጋውን በርና የሽንት በርሜል ተደግፎ ተቀመጠ፡፡ እኔም በሌላ ወገን ግድግዳና የሽንት በርሜል ተደግፌ ተቀመጥኩ፡፡ 23 ካሬ ሜትር ላይ 56 ሰዎች ተዘግቶብናል፡፡ አንዳንዶች በመኝታ ጥበትና በሙቀት እየተጠበሱ አልፎ አልፎ ተቀምጠው ያንጎላጃሉ፡፡ ሌሎች ከእንቅልፋቸው በደንብ ሳይነቁ ሽንታቸውን ለመሽናት እስረኛውን እየረጋገጡ አጠገባቸው ወደተቀመጠው የሽንት በርሜል ይጠጋሉ፡፡ እኛ ግን መረገጥ ብቻ ሳይሆን የሽንቱን ፍንጣሪና ሽታም መታገስ ነበረብን፡፡ እንቅልፍ ከአይናችን እንደራቀ፣ የረዥሙን ሌሊት ቀርፋፋ ደቂቃዎች ስንቆጥር አደርን፡፡ በሌላ ክፍል የተመደቡ ጓደኞቻችንም ከዚህ የተለየ ዕጣ አልጠበቃቸውም፡፡ ይኼንን የመሰለው ሕይወታችንን ቀጥፏል፡፡ እንደዋዛ ያለምክንያት ታስረን ከቀናት ወደሳምንት፤ ከሳምንትም በላይ እንደሌሎች ወገኖቻችን ሁሉ ባለቤት እንደሌለው ዕቃ ተጥለናል፡፡

ለ27 ዓመታት ‹‹ የዜግነት ክብር በኢትዮጵያ ሞልቶ …›› እያለ ዳንኪራ በሚያቀልጥ አገዛዝ፣ በሀገራችንና በህዝባችን መካከል ይህን የመሰለ የአፈና ተግባር እየፈጸመብን መሆኑን ሳስብ ፍቺ የሌለው እንቆቅልሽ ይሆንብኛል፡፡

ነገር ግን፣ ነፍስና ስጋዬ ላይ እንደካስማ የተመታው መቋጫ ያጣ ግፍ፣ ልቤን በጥልቅ ሀዘን እንዲሞላ ያደርገዋል፡፡ ያም ሆኖ፣ የፍትህ፣ የነጻነትና የወንድማማችነት ዘመን ናፍቆት እንደሃይለኛ ጅረት በደም ስሬ ውስጥ ይፈሳል፡፡ የምንመኘው ዘመን እንዳይነጋ፣ እኔና ጓደኞቼ እንቅፋት ሆነን ይሆን? እያልኩ ደጋግሜ እጠይቅና ለጥያቄዬ አወንታዊ ምላሽ አጣለሁ፡፡ ታዲያ ለምን የዚህ ሁሉ ግፍ ሰለባዎች ሆንን? እያልኩ እንደጥቅጥቅ ጫካ በሆነው የእስረኛ ጢሻ ውስጥ ሆኜ አስባለሁ፡፡

እውነቱን ለመናገር፣ እኛ በተደጋጋሚ የምንታሰረው አገዛዙ ፈሪ ስለሆነ ነው፡፡ ብዙ ወንድሞቼና እህቶቼ፣ ‹‹የኢህአዴግን አገዛዝ አይነት ፈርጣማ ሃይል፣ እናንተን ሊፈራ አይችልም›› የሚል ምላሽ በምናባችሁ እንደሚቋጥር አስባለሁ፡፡ እውነታችሁን ነው፤ በፈለገበት ቦታና ጊዜ፣ በፈለገው መንገድ፣ በመዳፍ ውስጥ የሚሸንን ግለሰቦች፣ ምን የሚያስፈራ ግርማ፤ ምንስ የሚያስደነግጥ ሃይል ኑሮን ይፈራናል? ሆኖም አገዛዙ የእኛና አይነት ደካሞች የሚያሳድድ ከሆነ፣ የሚፈራውና የሚጠላው አንዳች ነገር መኖር አለበት፡፡ ወንጀልና ውሸት የሚጠላ አገዛዝ ባለመሆኑ የፍርሃት ምንጮች ይሆናሉ ብዬ አላስብም፡፡ ሙስናና ሽብርም የዙፋኑ መሠረቶች በመሆናቸው፣ ለይስሙላ ካልሆነ በስተቀር ከእኛ ዘንድ አይሻቸውም፡፡ ዘረኝነትን የሀገር ክህደትም ዋልታና ማገር ሆነው ካቆሙት አገዛዝ ውጪ፤ ሁነኛ ተጠያቂ ማቅረብ የሚቻል አይመስለኝም፡፡ ታዲያ አገዛዙን በፈሪነት እከሰዋለሁ? የሚፈራውስ ምንድን ነው?

አገዛዙ የሚፈራው እውነትን ነው፡፡ አገዛዙ የሚጸየፈው ፍትህን ነው፡፡ አገዛዙ የሚጠላው ወንድማማችነትን ነው፡፡ ለምን? የእውነት ሃይል ተድበልቡሎ የተሰራበትን ውሸት ይንድባታል፡፡ ፍትህ በነገሰባት ኢትዮጵያ፣ የአገዛዝ እስትንፋስ ይቋረጣል፡፡ ወንድማማችነት ባበበበት ሀገር፣ ህዝብን ከፋፍሎ መግዛት የጭቆና ዘመኑን ማስረዘም አይችልምና ምንም ያህል ደካሞች ብንሆን እውነትን ለመያዝ እንጥራለን፡፡ ምንም ያህል የተናቅን ብንሆን፤ ለሁላችንም የምትቀትርን የፍትህ ጸሐይ እንናፍቃለን፡፡ የምንታሰርና የምንሞት ሆነን ሳለ፣ የማይሞትና የማይታሰር ህልም ባለቤቶች ነን፡፡ እየታሰርን እናሸንፋለን፤ እየሞትን እንበዛለን፤ የማይሞት ታሪክ እንጽፋለን፡፡ የአገዛዙ ግብግብ ከእኛ ጋር የሚመስላችሁ ካላችሁ አይደለም፡፡ ግብግቡ ከእውነት፣ ከፍትህና ከወንድማማችነት ጋር ነው፡፡ የማይታሰሩትን ያሰረ እየመሰለው፣ በአፈ-ሙዝ አጥሮ ይጠብቀናል፡፡ በስብዕና ቡልኮ እንዳልተጠቀለልን፤በጎሳ ወረንጦ ይለቅመናል፡፡

ፈርኦን እስራኤልን ይለቅ ዘንድ ወደአስራ አንድ ያህል ቅጣቶችን ተቀጥቷል፡፡ ሆኖም ፈርኦን ለመስማት ፈቃደኛ አልነበረም፡፡ ወደቀይ ባህር ልብ እስኪወርድ ድረስ በእንቢተኝነቱ ጸንቷል፡፡ ከዚህ አገዛዝ ጋር ያለው ንጽጽር ይደንቀኛል፡፡ ለህዝብ ፈቃድ ከመገዛት ይልቅ፤ ህዝብን በጅምላ መግደልና ማሰር መፍትሄ ይመስለዋል፡፡ የአገዛዙ እብሪት፣ እየመጣ ያለውን አደጋ እንዳያይ ጋርዶታል፡፡ ፍርሃት አጥንት ውስጥ ገብሮ ያንዘፈዝፈዋል፡፡ ከፍርሃቱ የተገላገለ እየመሰለው ይጠላል፣ ያስራል፣ ይገድላል፡፡ የፍርሃት መንገድ ፍርሃትን ይቀፈቅፋል እንጂ አይቀንስም፡፡ የፍርሃት ማርከሻው ለእውነት፣ ለፍትህና ለፍቅር እጅ መስጠት ነው፡፡ የፍርሃት መንገድ መጨረስ የቀይ ባህር ልብ ነው፡፡ ፍቅር፣ ፍትህና እውነት የተራበው ህዝብ ግን በደረቅ መሬት ይሻገራል፡፡

እስር አይደለም ሞት የታጋዩን ዓላማ አይገድለውም፡፡ ይልቅስ ዓላማው በብዙሃን ልብ ውስጥ ይዘራል፤ ተንዠርግጎም ይበቅላል፡፡ አገዛዙ ይኼንን እውነት ሳይውል ሳያድር ሊቀበል ይገባዋል፡፡ ያለአንዳች ማቅማማት ለእርቅ፣ ለወንድማማችነትና ለብሄራዊ ወይይት እራሱን ሊያዘጋጅ ይገባዋል፡፡ በእስር ቤት በሚፈጸምብኝ ግፍ፤ ከትግል መሸሽ ሳይሆን ወደትግል እንድስፈነጠር ይገፋኛል፡፡ እስር ቤት ውስጥ የማየው የሰብዓዊነት አዘቅት፤ ወደትግሉ ኮረብታ እንድወጣ ያነሳሳኛል፡፡ አነሳስቶኛል፡፡ የጓዶቼም ዓላማ ይኼው ይመስለኛል፡፡ አገዛዙ ግልጽ ሊሆንለት የሚገባው ከዚህ በኋላ ‹‹ህዝብን በማሰርና በማስፈራራት አገዛዜን አስረዝማለሁ›› የሚለውን የየዋህ ብሂል ይርሳው፡፡ ዘመኑ ተለውጧል፤ ሞትና እስርን የማይፈራ ትውልድ ተፈጥሯል፡፡ ይኼንን እውነት ለመማር ያሳለፍናቸው ጥቂት ዓመታት ወደኋላ ተመልሶ ማየት ብቻ ይበቃዋል፡፡ ከነጻነት፣ ከፍትህና ከወንድማማችነት ግባችን የሚያስቆመን የእስር ቤት አጥር፤ አሊያም ሞት የደገሰልን የአገዛዝ አፈ-ሙዝ ፈጽሞ አያስቆመንም፡፡ ትውልድ ከነጻነት ውጪ አይረካም፡፡ ወደኋላ አንመለስም፣ ፈጽመን አናፈገፍግም፡፡

ፍትህ እንደቀጥር ጸሐይ፣ ነጻነት እንደሃይለኛ ጅረት፣ ወንድማማችነትም እንደጉንጉን አበባ በኢትዮጵያ ላይ ይንገሥ!

በቅድሚያ ፈጣሪን፣ ቀጥሎም በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገራት የምትኖሩ፣ ከጎናችንም ለነበራችሁ በሙሉ አመሰግናለሁ፤ እናመሰግናለን።”

የዋልድባ ገዳም መነኮሳት አባ ገብረ-ሥላሴ ስና አባ ገብረ-ኢየሱስ የፍርድ ቤት ውሎ

ሀብታሙ ምናለ

የፌደራሉ ከፍተና ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ወንጀል ችሎት፤ የካቲት 30 ቀን 2010 ዓ. ም. በዋለው ችሎት የዋልድባ መነከሳት ባቀረቡት “የሰብዓዊ ጥሰት በማረሚያ ቤቱ ተፈፅሞብናል ፍርድ ቤቱ ተትዕዛዝ ይስጥልን!” ብለው ያቀረቡትን አቤቱታ ሰምቶ የማረሚያ ቤቱን ምላሽ ለመስማት ሲኾን ማረሚያ ቤቱም ምላሽ የሚለውን በደብዳቤ ለፍርድ ቤቱ አቅርቧል፡፡

ፍርድ ቤቱ ማረሚያ ቤቱ የሰጠውን ምላሽ እንደተመለከተው እና ውሳኔ እንደሚሰጥ አሳውቋል፡፡ አባ ገብረ ኢየሱስ ኪዳነ ማርያም “የተከሰስነውም የታሰርነው አንድ ላይ ቢኾነም እኔን ያለምንም ምክንያት ወደ ዞን አምስት በተለምዶ ጨለማ ወይም ቅጣት ቤት ወደሚባለው አዘዋውረውኛል፡፡ ተቀጥቼ ከኾነ ጥፋቴ ተነግሮኝ፤ ቅጣቴ ምን ያህል ቀን እንደኾነ አውቄ ቅጣቴን ልቀበል፤ ያለምንም ጥፋት ዝም ብዬ ነው፡፡ እየተሰቃየኹ ያለኹት ብዙ በደል ደርሶብናል፡፡ ከአመት በላይ ልብስ ሳንቀይር ቆይተን በቅርብ ቀን አንድ ምዕመን ልብስ አምጥቶልኝ እኔ ለመቀየር ችያለሁ፡፡

ነገር ግን አባ ገብረሥላሴ ከተያዙ ጀምሮ ምንም ልብስ ቀይረው አያውቁም። ሰዎች ልብስ ሲያመጡ ማስገባት አይቻልም፡፡ እያሉ እያስመለሱ ከአንድ ዓመት በላይ በአንድ ልብስ ብቻ ሳናወልቅ ቆይተናል፡፡ ኹለታችንም አብረን በአንድ ዞን የነበርነው ያለምክንያት በታትነውናል፡፡ ሰዎች ሊጠይቁን ሲመጡ የተለያየ ዞን በመኾናችን ጠያቂዎቻችን እክል እየገጠማቸው ነው፡፡ ወደነበርኩበት ዞን ልመለስ” ብለው ጠይቀዋል፡፡

ዳኞቹም፡- “ልብስ ለምን አይገባም?” ብለው የማረሚያ ቤቱ ኃላፊዎች ሲጠይቁ መልስ መስጠት ባለመቻላቻው “ልብስ ማነው የሚያመጣላችሁ?” ብለው ዳኞች ሲጠይቁ ችሎቱን ሲከታተሉ ከነበሩት ወጣቶች መካከል ለአንዳቸው የሚኾን የምንኩስና ልብስ ገዝተው ይዘው ነበር፡፡ ልብሱን ሲያቀርቡ ዳኞቹ፡- “ጠባቂዎቹን ፈትሹና ስጧቸው!” ቢልም ፍቃደኛ አለመኾናቸውን ሲያሳዩ ዳኞቹ በቁጣ “ተቀበሉና ፈትሻችሁ ስጡ!” በማለት ሲያዙ የማረሚያ ቤቱ ኃላፊ ወታደራዊ ሰላምታ በመስጠት ወደ ዳኞቹ ተጠግቶ ሊናገር ሲል ዳኞቹ፡- “የተባልከውን ብቻ አድርግ! ምንም ሌላ አያስፈልግም!” በማለት ልብሱ ተፈትሾ ለአባ ገ/ሥላሴ ተሰጥቷቸዋል፡፡

ፍርድ ቤቱም ያቀረቡትን አቤቱታ እና የተሰጠውን መልስ አይተው ውሳኔ ለመስጠት ለመጋቢት 5 ቀን 2010ዓ.ም ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡ መጋቢት 18 መደበኛ የክስ የሚቀጥል እና ምስክር እንደሚሰማባቸው ይታወቃል፡፡

የአምቦ ዩኒቨርስቲ መምህር፥ የመብት ተሟጋች እና ጦማሪ ስዩም ተሾመ በማዕከላዊ እስር ቤት የመብት ጥሰት ተፈፀመበት

(ዳጉ ሚዲያ) የአምቦ ዩኒቨርስቲ መምህር፥ የመብት ተሟጋች፥ የኢትዮ ቲንክታንክ እና ማኀበራዊ ገፅ ጦማሪ ስዩም ተሾመ ከሚኖርበትና ይሰራበት ከነበረው ወሊሶ ከትማ በፀጥታ ኃይሎች ታፍኖ ከተወሰደ በኋላ በዕከላዊ ወንጀል ምርመራ እስር ቤት ከፍተኛ ስቃይና እንግልት እንደተፈፀመበት ተጠቆመ።

ከየካቲት 9 ቀን 2010 ዓ. ም. ጀምሮ በድጋሚ ለ6 ወራት የሚቆይ የአቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተግባራዊ በተደረገ ሳምንት ሳይሞላው ስዩም ተሾመ ከመኖሪያ ቤቱ ታፍኖ ማዕከላዊ በሚባለው የፌደራል ወንጀል ምርመራ ማዕከል ከፍተኛ ምርመራ እየተደረገበት ሲሆን፤ የአገዛዙ መርማሪዎች አካላዊ ጥቃት በመፈፀምና በማስገደድ የሚጠቀማቸውን የኮምፒዩተርና የኢንተርኔት አገልግሎት የይለፍ ቃሎች(ፓስ ወርድ) መወሰዱም ታውቋል። መርማሪ ፖሊሶችም የፍርድ ቤት ክስ በመመስረት ተጨማሪ የ14 ቀናት የምርመራ ጊዜ በጠየቁት መሰረት እንደተፈቀደላቸውም ለማወቅ ተችሏል። ስዩም ተሾመን ማዕከላዊ ምርመራ በመሄድ ለመጎብኘት የሞከሩ ወዳጆቹ፥ የመብት ተሟጋቾችና የስራ ባልደረቦቹ እንዳይጎበኙት መከልከላቸውም ታውቋል።

ስዩም ባለፍው ለ10 ወራት ተግባራዊ ተደርጎ በነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በተመሳሳይ መልኩ ከመኖሪያ ቤቱ በገዥው ስርዓት የፀጥታ ኃይሎች ታፍኖ ከተወሰደ በኋላ በምርመራ ወቅት ከፍተኛ የአካል ጥቃት ተፈፅሞበት እንደነበርና ከተወሰኑ ወራት እስር በኋላ መለቀቁ ይታወሳል።

በሞያሌ 10 ያህል ሰላማዊ ዜጎች በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ተገደሉ

(ዳጉ ሚዲያ)ትናንት ቅዳሜ መጋቢት 1 ቀን 2010 ዓ.ም በደቡብ ኢትዮጵያ፥ቦረና ዞን የሞያሌ ከተማ በገዥው መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኮማንድ ፖስት የፀጥታ አባላት 10 ሰላማዊ ዜጎች ሲገደሉ 11 ያህሉ መቁሰላቸውን የዓይን እማኞችን እና የከተማውን ከንቲባ ዋቢ በማድረግ የአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ ዘግቧል።

ግድያውን በተመለከተ በአስቸኳይ አዋጁ መሰረት የመላ ሀገሪቱን አጠቃላይ የጠጥታ እና የተፈጥሮ ሃብትን በበላይነት እየተቆጣጠረ ያለው የኮማንድ ፖስቱ ሴክሬተሪያት በበኩሉ በተፈጠረ የመረጃ ስህተት ምክንያት 9 ሰላማዊ ዜጎች በስሩ ባሉ የፀጥታ ኃይሎች 9 ሰላምዊ ዜጎች መገደላቸውን እና 12 ያህል መቁሰላቸውን አስታውቋል።

ግድያው የተፈፀመው በከተማው በተለምዶ ሸዋበር በሚባል ሰፈር ሲሆን፤ በወቅቱ በአካባቢው ምንም ዓይነት ህዝባዊ የተቃውሞ እንቅስቃሴ ባልነበረበትና ዜጎች በተለመደ ሰላማዊ መደበኛ ዕለታዊ እንቅስቃሴ እያሉ ግድያው በጅምላ መፈፀሙን የከተማው ነዋሪዎች ተናግረዋል። በተለይ ጥቃቱ በሚፈፀምበት ወቅት በመዝናኛ ስፍራ የነበሩ፥ በምግብ ቤትና በሱቅ ግብይት ላይ የነበሩና መንገድ ላይ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ እንደሚገኙበት ተጠቁሟል።

በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ የካቲት 9 ቀን 2010 ዓ ም የታወጀው እና ለ6 ወራት የሚቆየው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተግባራዊ ከተደረገበት ቀን ጀምሮ በተለይ በኦሮሚያ ክልል ባሉ የተለያዩ ከተሞች በርካታ ሰላማዊ ዜጎች በኮማንድ ፖስቱ የፀጥታ አባላት መገደላቸው የሚታወስ ሲሆን፤ የሞያሌው የጅምላ ግድያ ተጨማሪ ጥቃት መሆኑ ታውቋል። የጅምላ ጥቃቱን ተከትሎም በርካታ የከተማው ነዋሪዎች ወደ ጎረቤት ሀገር ኬንያ ተሰደዋል።

ቀደም ሲል የመብት ተሟጋች ኢትዮጵያውያን፥ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች፥ ዓለም አቀፍ ይሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት፥ የአሜሪካ መንግሥትና የአውሮፓ ህብረት አባላት እና የገዥው መንግሥት አካል የሆኑ በርካታ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተግባራዊ እንዳይደረግ ተቃውመውት እንደነበር አይዘነጋም። ይሁን እንጂ አዋጁን ተከትሎ በሰላማዊ ዜጎች ላይ እየተፈፀመ ያለው ግድያ እና እስር ተጠናክሮ መቀጠሉ ታውቋል።

%d bloggers like this: