Tag Archives: Seyoum Teshome

በአዲስ አበባ እና በባህርዳር ጋዜጠኞች፥ የመብት ተሟጋቾች እና ፖለቲከኞች ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ለቀናት በአደራ እስር ላይ ይገኛሉ

(ዳጉ ሚዲያ) በቅርቡ የተደረገውን የፀረ አገዛዝ ህዝባዊ ተቃውሞን ተከትሎ ከዓመታት እስር በኋላ የተለቀቁ ጋዜጠኞች፥ የመብት ተሟጋቾች፥ ፖለቲከኞችን ጨምሮ ሌሎች የመብት ተሟጋቾችን ጨምሮ ያለ በቂ ምክንያት ከመጋቢት 16 ቀን 2010 ዓ.ም.ጀምሮ በጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ቤተሰብ መኖሪያ ቤት ከነበሩበት የምሳ እና የ “እናመሰግናለን” ግብዣ ላይ በነበሩበት ወቅት በድጋሚ ታስረዋል።

በድጋሚ ከታሰሩት መካከል ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፥ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ፥ አቶ አንዷለም አራጌ፥ ጦማሪ ዘላላም ወርቃገኘው፥ ወ/ት ወይንሸት ሞላ፥ ጦማሪ ማህሌት ፍንታሁን፥ ጦማሪና ጋዜጠኛ በፍቃዱ ሀይሉ፥ አቶ ስንታየሁ ቸኮል፥ አቶ ይድነቃቸው አዲስ፥ አቶ አዲሱ ጌታነህ፥ አቶ ተፈራ ተስፋዬ በአዲስ አበባ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ልዩ ስሙ ጎተራ ፖሊስ በእስር ላይ የሚገኙ ሲሆን፤ ከመደበኛ ሥራቸው ተይዘው ከታሰሩት መካከል የአምቦ ዩኒቨርስቲ መምህር፥ የመብት ተሟጋችና ጦማሪ ስዩም ተሾመ እንዲሁም የመብት ተሟጋች እና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የፍትህ ቢሮ የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ታዬ ደንደዓ በማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ ወህኒ ቤት ታስረው ይገናሉ።

Ethiopian re-arrested political Prisoners
በቅርቡ ለእስር የተዳረጉ የፖለቲካ እስረኞች መካከል በከፊል

በተያያዘ ዜና የአማራ ህዝብን ከአገዛዙ ጥቃት ለመከላከል በሚል በህጋዊ መንገድ የተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅት ለመመስረት በይፋ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የነበሩ የአካባቢ አስተባባሪዎች መካከል ከሌሎች ወዳጆቻቸው ጋር በመሆን በጋራ በመሆን ሰኞ መጋቢት 17 ቀን 2010 ዓ ም ባህርዳር ከተማ ተሰብስበው እራት ሲመገቡ በፀጥታ ኃይሎች ታፍነው ከታሰሩ በኋላ ድብደባ እንድተፈፀመባቸው ተጠቆመ። ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ድረስ በበእስር ላይ የሚገኙት ምሁራን፥ ፖለቲከኞች እና በዕለቱ በጓደኝነት እራት ግብዣው ላይ የተገኙ ጋዜጠኞች በባህርዳር ከተማ 9ኛ ፖሊስ ጣቢያ ታስረው ይገኛሉ።

በባህር ዳር ከተማ ተይዘው ከታሰሩት መካከል ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ (ባህርዳር ዩንቨርሲቲ መምህርና የጣና ደህንነትና የአካባቢ ጥበቃ ማህበር ፕሬዚደንት እና ተመራማሪ፣ ረዳት ፕሮፊሰር)፥ ጋሻው መርሻ (የአንጸባቂው ኮከብ መጽኃፍ ከታቢ፤ አዲስ አበባ በማስተማር ሙያ ላይ ይገኛል)፥ የሱፍ ኢብራሂም (ወሎ ዩኒቨርሲቲ መምህር የነበረና በአሁንኑ ወቅት ጠበቃ)፥ ተመስገን ተሰማ (ወሎ ዩኒቨርሲቲ መምህር፤የወሎ ዩኒቨርስቲ የህግ ትምህርት ቤት መስራች፣ ረዳት ፕሮፊሰር እና አማራ ነን የሚለው መዝሙርም ገጣሚ)፥ በለጠ ሞላ ( ተባባሪ ፕሮፊሰር ፡አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር)፥ ጋዜጠኛ ንጋቱ አስረስ (የአማራ ቴሌቪዥን ጋዜጠኛ(አርታኢ)፤ከ1997 እስከ 1999 የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የአማራ ተማሪዎች ማህበር ፕሬዜዳት፤)፥ ጋዜጠኛ በለጠ ካሳ (የቀለም ቀንድ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ የነበረ)፥ አቶ ሲሳይ አልታሰብ( ሲቪል ኢንጅነር)፥ አቶ ዳንኤል አበባው፥ አቶ መንግስቴ ተገኔ፥ አቶ ቦጋለ አራጌ፥ አቶ ካሱ ኃይሉ (የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ መምህር፡የማህበረሰብ ሳይንስ ተመራማሪ)፥ አቶ ተሰማ ካሳሁን፥ አቶ ድርሳን ብርሃኔ፥ አቶ በሪሁን አሰፋ፥ አቶ ፍቅሩ ካሳው፥ አዲሱ መለሰ (የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ መምህር)፥ አቶ ተመስገን ብርሃኑን ጨምሮ አንድ ስማቸው ያልተጠቀሰ ግለሰብም በእስር ላይ ይገኛሉ።

በአዲስ አበባ እና በባህርዳ ይታሰሩት ሁሉም ተከሳሾች ክስ እንዳልቀረበባቸውና የታሰሩበትም ምክንያት እንዳልታወቀ የተገኘው መረጃ አመልክታል። ይህንንም ተከትሎ ሐሙስ ምሽት መጋቢት 20 ቀን 2010 ዓ ም የተለያዩ ማኀበራዊ ሚዲያን በመጠቀም #ሁሉም_የፖለቲካ_እስረኞች_ይፈቱ የሚል ዘመቻ የተደረገ ሲሆን፤ ከአሰራቸው የመንግሥት አካል ግን የተሰጠ ምላሽ የለም።

የአምቦ ዩኒቨርስቲ መምህር፥ የመብት ተሟጋች እና ጦማሪ ስዩም ተሾመ በማዕከላዊ እስር ቤት የመብት ጥሰት ተፈፀመበት

(ዳጉ ሚዲያ) የአምቦ ዩኒቨርስቲ መምህር፥ የመብት ተሟጋች፥ የኢትዮ ቲንክታንክ እና ማኀበራዊ ገፅ ጦማሪ ስዩም ተሾመ ከሚኖርበትና ይሰራበት ከነበረው ወሊሶ ከትማ በፀጥታ ኃይሎች ታፍኖ ከተወሰደ በኋላ በዕከላዊ ወንጀል ምርመራ እስር ቤት ከፍተኛ ስቃይና እንግልት እንደተፈፀመበት ተጠቆመ።

ከየካቲት 9 ቀን 2010 ዓ. ም. ጀምሮ በድጋሚ ለ6 ወራት የሚቆይ የአቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተግባራዊ በተደረገ ሳምንት ሳይሞላው ስዩም ተሾመ ከመኖሪያ ቤቱ ታፍኖ ማዕከላዊ በሚባለው የፌደራል ወንጀል ምርመራ ማዕከል ከፍተኛ ምርመራ እየተደረገበት ሲሆን፤ የአገዛዙ መርማሪዎች አካላዊ ጥቃት በመፈፀምና በማስገደድ የሚጠቀማቸውን የኮምፒዩተርና የኢንተርኔት አገልግሎት የይለፍ ቃሎች(ፓስ ወርድ) መወሰዱም ታውቋል። መርማሪ ፖሊሶችም የፍርድ ቤት ክስ በመመስረት ተጨማሪ የ14 ቀናት የምርመራ ጊዜ በጠየቁት መሰረት እንደተፈቀደላቸውም ለማወቅ ተችሏል። ስዩም ተሾመን ማዕከላዊ ምርመራ በመሄድ ለመጎብኘት የሞከሩ ወዳጆቹ፥ የመብት ተሟጋቾችና የስራ ባልደረቦቹ እንዳይጎበኙት መከልከላቸውም ታውቋል።

ስዩም ባለፍው ለ10 ወራት ተግባራዊ ተደርጎ በነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በተመሳሳይ መልኩ ከመኖሪያ ቤቱ በገዥው ስርዓት የፀጥታ ኃይሎች ታፍኖ ከተወሰደ በኋላ በምርመራ ወቅት ከፍተኛ የአካል ጥቃት ተፈፅሞበት እንደነበርና ከተወሰኑ ወራት እስር በኋላ መለቀቁ ይታወሳል።

የአምቦ ዩኒቨርስቲ መምህር እና ብሎገር ስዩም ተሾመ ታሰረ

ስዩም ተሾመ

seyoum-teshome

በአምቦ ዩኒቨርስቲ ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ወሊሶ ግቢ መምህር እና ብሎገር ስዩም ተሾመ ታሰረ፡፡ መምህር እና ብሎገር ስዩም ተሾመ ከሚኖርበትና ከሚሰራበት ወሊሶ ከተማ ዛሬ ቅዳሜ መስከረም 21 ቀን 2009 ዓ.ም. በፀጥታ ኃይሎች ታፍኖ ከተወሰደ በኋላ መታሰሩ ተጠቁሟል፡፡ ስዩም ተሾመ በአምቦ ዩኒቨርስቲ ወሊሶ ግቢ የማናጅመንት ትምህርት ክፍል ኃላፊ እና መምህር ሲሆን፤ ከማኀበራዊ ሚዲያ በተጨማሪ በ ”ኢትዮቲንክታንክ” እና የገዥው ስርዓት ደጋፊ እንደሆነ በሚታወቀው ”ሆርንአፌይርስ” ድረ-ገፅ ጭምር በመፃፍ ይታወቃል፡፡

በተለይ ከህዳር 2008 ዓ.ም. ጀምሮ በመንግሥት እና በህዝቡ መካከል በተፈጠረው አለመግባባት ችግሮች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ እና ሌሎች ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የተለያዩ መፍትሄ ሊሆኑ ይችላሉ ያላቸውን ምክረ ሐሳቦችን በመሰንዘርም ይታወቃል፡፡

10ኛ ወሩን ባስቆጠረው የኦሮሚያ ህዝባዊ ተቃውሞን ተከትሎ በአማራ እና በደቡብ ኮንሶ ተከታታይ ህዝባዊ ተቃውሞች መቀጠላቸውን ተከትሎ ከ820 ያላነሱ ሰላማዊ ዜጎች በፀጥታ ኃይሉ ወታደራዊ ርምጃ ሲገደሉ፤ በሺህዎች የሚቆጠሩ ቆስለው፣ በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ታፍነው ታስረዋል፡፡ ከተገደሉ፣ ከቆሰሉና ከታሰሩት መካከል ህፃናት እና አዛውንት፣ መምህራን፣ ጋዜጠኞችና ብሎገሮች፣ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች እና ተማሪዎች ይገኙበታል፡፡ በተለይ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ድረስ፤ በተለያዩ ኦሮሚያ እና አማራ ክልል ከተሞችና ወረዳዎች የመንግሥት ግድያና እስር እንደቀጠለ ነው፡፡

%d bloggers like this: