በቅርቡ ከእስር ከተፈቱት መካከል ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ እና አቶ አንዱዓለም አራጌን ጨምሮ 11 ሰዎች በድጋሚ ታሰሩ
(ዳጉ ሚዲያ) እሁድ መጋቢት 16 ቀን 2010 ዓ.ም. የአዲስ አበባ ወጣቶች በቅርቡ ከእስር ለተፈቱት ጋዜጠኞች፥ የመብት ተሟጋቾች እና ፖለቲከኞችን “እናመሰግናለን” በሚል በጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ቤተሰብ መኖሪያ ቤት በተዘጋጀ መርሃ ግብር ላይ ተገኝተው ከነበሩት መካከል 11 ያህሉ በፖሊስ ታግተው መቆየታቸው ታውቋል። ፖሊስም ታጋቾቹን ከጋዜጠና ተመስገን ደሳለኝ ቤተሰብ መኖሪያ ቤት በበርካታ የፖሊስ ኃይል በማጀብ በአዲስ አበባ ንፋስ ስልክ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ስር በሚገኘው ጀሞ ፖሊስ ጣቢያ የወሰዷችው ሲሆን፤ ከምሽቱ 4፡30 ሰዓት ላይ ጎተራ ወደ ሚገኘው ፖሊስ መምሪያ ወስደው እንዳሰሯቸው ለማወቅ ተችሏል።
አቶ አንዱዓለም አራጌ ኤና ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ
እንደምንጮች መረጃ ከሆነ፤ ለእገታው ምክንያት የሆነው በመርሃ ግብሩ ላይ የገዥው ስርዓት መለያ የሌለበት የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ተሰቅሎ በማየታቸው በተቆጡ የአገዛዙ ፖሊሶች በፈጠሩት አለመግባባት መሆኑ ተጠቁሟል። በተለይም በስፍራው የነበረው መርሃ ግብር ከተጠናቀቀ በኋላ በስፍራው ደርሰው የነበሩ ሁለት ፖሊሶች ሰንደቅ ዓላማውን ከተሰቀለበት በግድ ነጥቀው በመውሰድ ድርጊቱን ስብሰባ አድርጎ በመቁጠር ለምን አላስፈቀዳችሁም በሚል ለድርጊቱ ኃላፊነቱን የሚወስድ አካል ማናገር እንፈልጋለን በማለት ፖሊሶቹ ታዳሚውን ለማስፈራራት ሞክረዋል። ይህንንም ተከትሎ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝም የነበረው መርሃ ግብር የተለመደ የማኀበራዊ ወዳጅነት እንጂ ስብሰባ አይደለም፥ ለማኀበራዊ ወዳጅነት ፈቃድ እያስፈልግም ሲል ምላሽ በመስጠቱ በተለይ ሲያናግረው የነበረውን ፖሊስ እንዳስቆጣ ለማወቅ ተችላል።
በጋዜጠኛው ምላሽ ደስተኛ ያልነበረው ፖሊስ ጉዳዩን በማክረር ኃላፊነቱን የሚወስዱ 3 ሰዎችን ማናገር እንፈልጋለን ወደሚል እልህ ውስጥ መግባቱን ተከትሎ አቶ አንዱዓለም አራጌ ጉዳዩን ለማረጋጋት በሚል ፖሊሱን ለማግባባት ቢሞክርም፤ ፖሊሱ ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል። በመጨረሻም አቶ አንዱዓለም አራጌ ለፖሊሱ ” ችግር አለ ብላችሁ ምታምኑት ነገር ካለ እና ማናገር ከፈለጋችሁ ሁላችንንም ወስዳችሁ ማናገር ትችላላችሁ፤ ከዛ ውጭ በተናጥል ኃላፊነት የሚወስድም ሆነ የሚያናግር የለም” የሚል ምላሽ ይሰጣል።
በተሰጣቸው ምላሽ ደስተኛ እና ፈቃደኛ ያልሆነው ፖሊስ በመርሃ ግብሩ ላይ ከተሳተፉት መካከል በወቅቱ በስፍራው የነበሩትን እንዳይንቀሳቀሱ በማስገደድ፤ በያዘው የፖሊስ መገናኛ ሬዲዮ ወደበላይ አለቆቹ በመደወል በአካባቢው ከፍተኛ ችግር እንዳለ እና ለዚህም በርካታ የፖሊስ ኃይል እንዲታዘዝለት ጥሪ ያስተላልፋል። ከተወሰኑ ደቂቃዎች በኋላም በተሽከርካሪ መኪና ተጭነው የመጡ በርካታ ፖሊሶች የጦር መሳሪያዎቻቸውን በመደገን አካባቢውን በመቆጣጠር በስፍራው በቅርቡ ከእስር ከተፈቱት እና በወቅቱ የ “እናመሰግናለን” ሽልማት መርሃ ግብር ከተጠናቀቀ በኋላ በስፍራው የነበሩትና ከእስር ተለቀው የነበሩ 11 የፖለቲካ እና የህሊና እስረኞች አቶ አንዱዓለም አራጌ፥ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፥ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ፥ ጋዜጠኛ እና ጦማሪ በፈቃዱ ኃይሉ፥ ጦማሪ ማህሌት ፋንታሁን፥ ጦማሪ ዘለዓለም ወርቅአገኘሁ፥ የመብት ተሟጋች ወጣቶች አቶ ስንታየሁ ቸኮል፥ አቶ አዲሱ ጌታነህ፥ ወ/ት ወይንሸት ሞላ፥ አቶ ይድነቃቸው አዲስ እና አቶ ተፈራ ተስፋዬ በድጋሚ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለዋል።
ፖሊስ አግቶ ያሰራቸውን 11 ሰዎች ለምን እንደሆነ እስካሁን በይፋ የሰጠው ማብራሪያም ሆነ ምክንያት የለም። ይሁን እንጂ የታገቱት ጋዜጠኞችና የመብት ተሟጋቾች ታፍነው ተወስደውበት ከነበረው ጀሞ ፖሊስ ጣቢያ ማምሻውን ጎተራ ፊትለፊት ወደሚገኘው የንፋስ ስልክ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ እንደታሰሩ ለማወቅ ተችሏል። ጋዜጠኞቹ እና የመብት ተሟጋቾቹ በታሰሩብት ዕለት ቀደም ሲል በቅርቡ በሀገሪቱ ላለፉት 3 ዓመታት ጀምሮ ያልተቋረጠውን የፀረ ጭቆና አገዛ ህዝባዊ ተቃውሞን ተከትሎ በቅርቡ ከእስር ከተፈቱት በርካታ የፖለቲካና የህሊና እስረኞች ጋር የሰማያዊ ፓርቲ ባዘጋአጀው ተመሳሳይ መርሃ ግብር ላይ ተሳትፈው ካጠናቀቁ በኋላ ተጨማሪ በሌሎች በጎ ፈቃድ ወጣቶች ባዘጋጁት መርሃ ግብርን አጠናቀው ርስ በርስ በመጨዋወት ላይ እያሉ መታሰራቸውን ለማወቅ ተችሏል።
በአሁን ወቅት ሀገሪቱ ለ6 ወራት በሚቆይ የአስቸኳይ አወጅ ስር ሆና በወታደራዊ ዕዝ ቁጥጥር ስር መውደቋ ይታወቃል።
ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ የተፈረደበትን ፅኑ እስራት ጊዜውን አጠናቆ ወጣ
የቀድሞው ፍትህ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ የነበረው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ተፈርዶበት የነበረውን የ3 ዓመት ፅኑ እስራት አጠናቆ በጣ። ጋዜጠኛው የእስር ጊዜውን ካጠናቀቀ ሁለት ቀናት ቢያልፉትም፤ ዛሬ ጥቅምት 5 ቀን 2010 ዓ.ም. መለቀቁ ታውቋል።
ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ፎቶ_ ከማኅበራዊ ገፅ
ጋዜጠኛው ከመታሰሩ በፊት በባለቤትነት እና በዋና አዘጋጅነት ከሚያስተዳድረው ፍትህ ጋዜጣ በተጨማሪ፥ በልዕልና ጋዜጣ፥ በአዲስ ታየምስ እና በፋክት መፅሔቶች ላይም በቋሚነት ይፅፍ እንደነበር ይታወቃል።
ጋዜጠኛ ተመስገን ለእስር የተዳረገውም ቀደም ሲል በፍትህ ጋዜጣ በፃፋቸው ፅሑፎች እንደነበር ቀርቦበት የነበረው የክስ ሰነድ ያስረዳል።
በኢትዮጵያ ምንም እንኳ ጋዜጠኛ ተመስገን የተፈረደበትን የእስር ጊዜ አጠናቆ ቢወጣም ፤ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ እና ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬን ጨምሮ ሌሎች ጋዜጠኞች እና ብሎገሮች አሁንም ድረስ በእስር ላይ እንደሚገኙ ይታወቃል።
በዝዋይ ወህኒ ቤት እስር ላይ የነበረው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ አሁን የት እንዳለ አለመታወቁን ቤተሰቦቹ አስታወቁ
(አዲስ ሚዲያ) የፍትህ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ እና መስራች የነበረው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ባለፈው ህዳር 2007 ዓ.ም. በመንግሥት በተመሰረተበት ክስ የ3 ዓመት ፅኑ እስር ተፈርዶበት ዝዋይ ወህኒ ቤት የነበረ ቢሆንም፤ ከፋለፈው ማክሰኞ ህዳር 27 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ የነበረበት ዘዋይ ወህኒ ቤትን ጨምሮ ቃሊቲ፣ የአቃቂ ቂሊንጦ እና ሸዋ ሮቢት ወህኒ ቤት ጥበቃ ሰራተኞችና ኃላፊዎች፤ ጋዜጠኛ ተመስገን የት እንዳለ ከቤተሰቦቹ ለቀረበላቸው ጥያቄ በተጠቀሱት ወህኒ ቤቶች እንደሌለ በመግለፅ በአሁን ወቅት የት እንዳለ ግን እንደማያውቁ መናገራቸውን የጋዜጠኛው ቤተሰቦች ይፋ አድርገዋል፡፡
ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ፤ ፎቶ ከማኀበራዊ ገፅ
አዛውንቱ ወላጅ እናቱን ጨምሮ ሌሎች የጋዤተኛው ቤተሰቦችና ወዳጆች ቀደም ሲል ታስሮ የነበረበትን እና በፌደራል ደረጃ የሚታወቁ ወህኒ ቤቶች በሙሉ በመሄድ ያለበትን ሁኔታ ለማረጋገጥ ሙከራ ቢያደርጉም ሊያገኙት እንዳልቻሉ የተገለፀ ሲሆን፤ በተለይ በዕድሜ የገፉ አዛውንት ወላጅ እናቱ ወ/ሮ ፋንታዬ እርዳቸው በከፍተኛ ስጋትና ጭንቀት ላይ መሆናቸውን ምንጮች አስታውቀዋል፡፡ ጋዜጠኛው ቀደም ሲል በእስር ላይ እያለ በደረሰበት ህመም ምክንያት የህክምና ዕርዳታ ለማግኘት ጠይቆ በተደጋጋሚ መከልከሉ አይዘነጋም፡፡
የፌደራል አቃቤ ህግ ጋዜጠኛ ተመስገን በፍትህ ጋዜጣ ላይ በፃፋቸው ፅሑፎችን ዋቢ በማድረግ በመሰረተበት ክስ የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት 3 ዓመት ፅኑ እስራት እና የፍትህ ጋዜጣ አሳታሚ ማስተዋል ህትመትና ማስታወቂያ ድርጅትደግሞ 10 ሺህ ብር እንዲቀጣ መበየኑ ይታወሳል፡፡ጋዜጠኛ ተመስገን ከመታሰሩ በፊት መንግሥት ይፈፅማል ያላቸው የመብት ረገጣዎችና ብልሹ አሰራሮችን በግልፅ በመተቸት ይታወቃል፡፡
ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝን ጨምሮ በገዥው የኢህአዴግ መንግሥት 11 ጋዜጠኞችና 1 ብሎገር ኢትዮጵያውያን እንዲሁም 3 የውጭ ዜጋ ጋዜጠኖች በአጠቃላይ 15 ጋዜጠኞችና ብሎገር በእስር ላይ ይገኛሉ፡፡ በተለይ በእስር ከሚገኙ ጋዜጠኞች መካከል ኢትዮጵያውያኑ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣ ውብሸት ታዬ፣ ተመስገን ደሳለኝ፣ ጌታቸው ሽፈራው፣ ፈቃዱ ምርከና፣ጌታቸው ወርቁ፣ አናኒያ ሶሪ፣ ኤልያስ ገብሩ፣ በፈቃዱ ኃይሉ፣ ከድር መሐመድ፣ ዳርሰማ ሶሪ እና የደ ብርሃን ብሎገር ዘለዓለም ወርቅአገኘሁ ተጠቃሾች ናቸው፡፡
እንደ ሀገር ውስጥ የሰብዓዊና የፕሬስ ነፃነት መብት ተሟጋቾች እና እንደ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች መረጃ ከሆነ፣ ኢትዮጵያ በአሁን ወቅት የፕሬስ ነፃናት ከሌለባቸው የዓለም ሀገራት ተርታ በቀዳሚነት ከሚጠቀሱት አንዷ ስትሆን፤ በርካታ ጋዜጠኞችን በማሰር በአፍሪካ ከጎረቤት ኤርትራ ቀጥሎ በሁለተኛ ደረጃ ላይ የምትገኝ ሀገር ነች፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት ገመና
ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ
(ከዝዋይ እስር ቤት)
መሐሙድ የሱፍ የተወለደው በ1980ዓ.ም ከሶማሌ ክልል ርእሰ-መዲና ጅጅጋ 500 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በምትገኘውዶሀን ከተማ ነው፡፡ ለቤተሰቡ ሰባተኛ ልጅ ሲሆን፤ አምስት እህቶችእና ሦስት ወንድሞች አሉት፡፡ በጅጅጋ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት እስከ አስረኛ ክፍል ድረስ መዝለቁቢሳካለትም፤ ከዚህ በላይ ግን ሊቀጥል አልተቻለውም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የኢትዮጵያመንግስት የደህንነት ሠራተኞች የ1999ዓ.ም የግንቦት ሃያ በዓል በጅጅጋ ከተማ ስታዲዬም በተከበረበት ዕለት፣ የኦጋዴን ነፃአውጪ ግንባር (ኦብነግ) በሰነዘረው የቦንብ ጥቃት ተሳትፈሃል በሚል ለእስር በመዳረጉነው፡፡ ይህንን ተከትሎምከምድራችን አስከፊ ማሰቃያዎች መካከል ግንባር ቀደም በሆነውና የክልሉ ነዋሪ “ጄል-አዳብ” (የገሃነም እስር ቤት) እያለ በሚጠራው ማጎሪያ ውስጥ እጅግ በጣም የከፋ ምድራዊ መከራ እንደተቀበለሀዘን በተጫነው ድምፅ ይናገራል፡፡ በሠውነቱ የተለያዩ ክፍሎች ላይ እንደ ፍም ቀልተው የሚታዩት ጠባሳዎቹም ያሳለፈውንሥቃይ አፍ አውጥተው ይመሰክራሉ፡፡
ለአራት ወራት ያህል አንድ ክፍል ውስጥ ለብቻው ተቆልፎበት፤ ሃያ አራት ሠዓታትሙሉ እጆቹ በካቴና ተቀፍድደው፣በቀን ከአምስት ጊዜ በላይ ለምርመራ እየተጠራ ያለዕረፍት ከባድ ስቅየት (ቶርቸር)ሲፈፀምበት ቆይቷል:፡ በመጨረሻም ለአንዲትም ቀን የፍርድ ቤት ደጅ ሳይረግጥ፣ ለኦብነግ አባላት አንድ ፓኬት ሲጋራሲያቀብል እጀ-ከፈንጅ ተይዟል በሚል ክስ የጅጅጋ ዞን ፍርድ ቤት በሞት እንዲቀጣ መወሰኑን እዛው እስር ቤት ሆኖከኢትዮጵያ ሬዲዮ የዜና እወጃ እና ከቪኦኤ ሶማሊኛ ፕሮግራም ሠምቷል፡፡
ከፍርዱ በኋላም በተመሳሳይ ወንጀል ከተከሰሰ አንድ እስረኛ ጋር በካቴና ተጠፍሮ በቀን አንድ እንጀራ ለሁለት ተካፍሎእንዲበላ እንደ ውሻ እየተወረወረለት 60 ቀናትን አሳልፏል፡፡ መሐሙድ በተለይም በእንቅልፍ ወቅት እርሱ ወይምየሰንሰለት ደባሉ የተገላበጠ እንደሆነ ካቴናው የሚያደርስበትን የመለብለብ ቃጠሎ ሲያስታውስ ዓይኖቹ በእንባ ይሞላሉ፡፡በአሁኑ ወቅት በዝዋይ ማጎሪያ ከባድ ጥበቃ ለሚደረግባቸው ብቻ በተመደበ ‹‹ዘጠነኛ ቤት›› ውስጥ አስራ አንድ ሶማሊኛተናጋሪዎችን ጨምሮ በድምሩ ሰላሳ አራት ሰዎች ጋር ከዛሬ ነገ የግፍ ፍርዱ ተፈጻሚ ሊሆንብኝ ይችላል በሚል ሰቀቀንእየባነነ በስጋት ተጠፍንጎ መኖር ከጀመረ እነሆ ሰባት ዓመት ሊደፍን ሦስት ወራት ብቻ ቀርተውታል፡፡
የተዋረደው የፍትሕ ሥርዓት!. . .
ርግጥ ነው ይህ በጨረፍታ ያቀረብኩት አሳዛኝ ታሪክ የመሐሙድ የሱፍ ብቻ አይደለም፡፡ ሌሎች ሰባት ‹‹አባሪዎቹ››ስቃዩንም ሆነ የሞት ፍርዱን ይጋሩታል (በነገራችን ላይ በአንድ መዝገብ የተወነጀሉት እነዚህ ስምንት የሞት ፍርደኞች፡-መሐድ ኢብራሂም፣ አረብ ሰዋኔ ዱልባንቲ፣ ሐሰን መሐመድ ዑስማን፣ ሐሰን መሐመድ ዓሊ፣ ሙክታር መሐመድ ዓብዱላሂ፣ከድር ሽኩር ሙሳ እና ካሚል ዓብዱልናስር እንኳን በጋራ መንግሥት ላይ ሊያሴሩ ቀርቶ እርስ በርስም የተዋወቁት እስር ቤትውስጥ ነው፡፡ ከጅጅጋ ወደ ዝዋይ ‹‹ዘጠነኛ ቤት›› ተዘዋውረው በርካታ ዓመታትን ያሳለፉትም በጭካኔው ወደርእንደማይገኝለት የሚነገረው የክልሉ ፕሬዚዳንት አብዲ በአደራ እንዲቀመጡ በመተላለፋቸው መሆኑን ነግረውኛል፡፡) እንደ መሐሙድ ሁሉ እነርሱም ፍርድ ቤት ቀርበውአያውቁም፤ ምንም ዓይነት የሰውም ሆነ የሰነድ ማስረጃ አልተቆጠረባቸውም፡፡ እዚህ ጋ የማነሳው አሳዛኝ ገጠመኝከመካከላቸው አንዳቸውም ራዲዮ ስላልነበራቸው የተጣለባቸውን የሞት ፍርድ ውሳኔ የሠሙት፣ ዜናው ከተላለፈ ከበርካታቀናት በኋላ ሬዲዮ ካላቸው እስረኞች መሆኑ ነው፡፡
ይህ እጅግ አሳፋሪና አስደንጋጭ መንግሥታዊ ውንብድና በደንብ ይብራራ ዘንድ ለተከሳሶቹ ከተሰጣቸው ባለ አንድገፅ የክስ ቻርጅ የሁለቱን ብቻ በአዲስ መስመር እጠቅሳለሁ፡-‹‹በሶማሌ ክልላዊ መንግሥት ጠቅላይ አቃቤ ሕግና ፍትሕቢሮ በሶማሌ ክልላዊ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት ጅጅጋ የዐ/ሕግ/መ/ቁ 90/2000
ከሳሽ፡- ዐ/ሕግ
ተከሳሽ፡- ሐሰን መሐመድ ዑስማን (ሐንን መድቤ)
ዕድሜ፡- 21 ሥራ፡- ተማሪ አድራሻ፡- ጅጅጋ ከተማ፡- 06 ቀበሌ ወንጀል በ1996ዓ/ም የወጣውን የኤ.ፌ.ዴ.ሪ የመ.መ.ሥ.ሥ.ህ.ቁ. 240(3) እና 251(መ) ላይ የተመለከተውን በመተላለፍ፣
የወንጀል ዝርዝር
ተከሳሽ ከመስከረም 1999 ዓ.ም. ጀምሮ እራሱን ኦ.ብ.ነ.ግ. እያለ ከሚጠራው ተቃዋሚና አሸባሪ ድርጅት ጋር በራሱፈቃድ በዚሁ በጅጅጋ ከተማ ከላይ በተጠቀሰው ዓመተ-ምህረት አባል በመሆን በጫካ በዚሁ አካባቢ ከሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ጋርበከተማም
ሆነ በጫካ በመገናኘት በኢኮኖሚ ረገድ የሚያስፈልጋቸውን፡- ጫማ፣ ልብስ የመሳሰለውን እዚያው ድረስ ሄዶ በማቀበልአብሮ ሲንቀሳቀስ በመቆየቱ ተከሶ ቀርቧል፡፡››
ሁለተኛው የክስ ቻርጅ ደግሞ እንዲህ ይነበባል፡-
‹‹በሶማሌ ክልላዊ መንግሥት ጠቅላይ አቃቤ ሕግና ፍትሕ ቢሮ
በሶ/ክ/መ/ ጅጅጋ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት
ጅጅጋ
የዐ/ሕ/መ/ቁ 90/2000
ከሳሽ፡- ዐ/ሕግ
ተከሳሽ፡- መሐድ ሼክ ኢብራሂም
ዕድሜ፡- 28፣ሥራ፡- የለውም አድራሻ፡- ጅጅጋ ከተማ፡- ቀበሌ 05
1ኛ ክስ፣ወንጀሉ፡-
በ1996 ዓ/ም የወጣውን የኤ.ፌ.ዴ.ሪ የመ/መ/ህ/ ቁ. 241 እና 251(መ) ላይ የተመለከተውን በመተላለፍ፣
የወንጀሉ ዝርዝር
ተከሳሹ በ1998 ዓ.ም. ወራትና ቀኑ በውል ካልታወቀ ጊዜ ጀምሮ እራሱን ኦ.ብ.ነ.ግ. እያለ ከሚጠራው ተቃዋሚ የፖለቲካ
ድርጅትና አሸባሪ ጋር በራሱ ፈቃድ አባል በመሆን ከዚህ ሕገ-መንግሥቱን ከሚፃረር ድርጅት በቀጥታ ፌዴሬሽኑእንዲከፋፈል፣ ክልሉን
የመገንጠል ዓላማ ለማሳካት ይህንኑ ድርጅት ከዚሁ በጅጅጋ ከተማ ለጊዜው ካልተያዘ ግብረ-አበሩ ጋር በመሆን ይህንኑአሸባሪ ድርጅት
በሚያስፈልገው ማቴሪያል ሁሉ፡- ጫማ፣ የፖሊስ የደንብ ልብስ፣ መድሃኒት. . . የመሳሰለውን በማቀበሉ፡፡
2ኛ ክስ፣ወንጀሉ፡-
በ1996ዓ/ም የወጣውን የኤ.ፌ.ዴ.ሪ የመ/መ/ህ/ ቁ. 36 (ለ) ላይ የተመለከተውን በመተላለፍ፣
የወንጀሉ ዝርዝር
ተከሳሹ ከ1996 ዓ.ም. ጀምሮ የተለያዩ መ/ቤቶች ማለትም፡- የክልሉ ት/ቢሮን፣ የቀብሪ-ደሐር ት/ቢሮን፣ እንዲሁም የMSF እና የተለያዩ መሥሪያ ቤቶችን እና የትምህርት ተቋማትን ማህተም በማስመሰል አትሞ እና የኃላፊዎችን ፊርማ ዓይነትአስመስሎ በማስፈር ሐሰተኛ ሰነድ አዘጋጅቶ በመገኘቱ ተከሶ ቀርቧል፡፡›› (ሁሉም የክስ ቻርጆች ማኅተም እና አንጋው አፈወርቅ ምንተስኖት የተባለ የክልሉ ዐቃቤ ሕግ ፊርማ አላቸው) እነሆም ያለአንድ ምስክር፣ ያለምንም የሰነድ ማሰረጃ፣ አንድም ቀን ችሎት ቀርበው የእምነት ክህደት ቃል ሳይጠየቁ እና ሳይከራከሩ (ያውም የዞን ፍርድ ቤት) በነዚህ በስም በጠቀስኳቸው በስምንቱ ኢትዮጵያውን ላይ የሞት ቅጣትን የመሰለየመጨረሻ ውሳኔ እንደቀልድ አስተላልፎባቸዋል፡፡ (በነገራችን ላይ ሌሎች 13 የኢትዮጵያ-ሶማሌ ተወላጆችም በተመሳሳይ የሐሰትውንጀላ የዕድሜ ልክ እስር ተፈርዶባቸው ዝዋይ ይገኛሉ፡፡ የሚገርመው ጉዳይ ደግሞ ም ቢሆኑ መጀመሪያ ተጠርጥረው በተያዙበት ወንጀልአይደለምየተጠየቁት፡፡ ጉዳዩ ጭራሽኑ በምርመራም ወቅት አልተነሳም) መቼም በዚህ መልኩ በተቀናበረ የውሸት ክስ ከ20-27 ዓመት የሚገኙ ወጣቶችን በሲኦላዊ እሳተ-ነበልባል ስቅየት ውስጥ እንዲያልፉ ከማድረግም በዘለለ፣ ብሩህ ቀናቸውን አጨልሞ ላይመለሱወደመቃብር የሚሸኝ ቅጣት ሲጣል ከመመልከት የበለጠ የትኛውንም ዜጋ የሕሊና ስቃይ ውስጥ ከትቶ፣ አንገት አስደፍቶ፣ በቁጣ ቀስቅሶ ወደአደባባይ የሚያወጣ ገፊ-ምክንያት አለ ብዬ አላምንም፡፡
ማነው ተጠያቂው?
በእነዚህ ንፁሃን ኢትዮጵያውያን ላይ ‹በጄል-አደብ› የደረሰባቸው በነውረኝነት የታጀለ ኢ-ፍትሐዊ ፍርድ እና ስቅየት፣ የሥርዓቱን እውነተኛ ማንነት ገሃድ የሚያወጣ ተጨባጭ ተግባር መሆኑ ባይካድም፡ ይህንን አረሜናዊ ድርጊት በፊት-አውራሪነት የመሩት፡- ኮሎኔል ሞኒ መንገሻ በጊዜው የክልሉ የፀረ-ሽብር ግብረ-ኃይል ዋና ኃላፊ የነበረ አሁን ወደአዲስ አበባ ተቀይሮ‹ሕገ-ወጥ የሠው ዝውውር ወንጀል መከላከል› ኃላፊ፣ ቢኒያም የተባለ የክልሉ የደህንነት ኃላፊ፣ ሻለቃ ዘገየ በክልሉ የፌዴራል ፖሊስኃላፊ፣
ወልደአራዌ የክልሉ ፖሊስ ም/ኮሚሽነር፤ እንዲሁም ሻለቃ ወንድሜ፣ ሻለቃ በለጠ እና ታሰረ የተባሉ ኃላፊነታቸውንለይተው የማያስታውሷቸው ግለሰቦች መሆናቸውን ግፉአኖቹ በተሰበረ ልብ፣ ምሬት በሞላው ድምፅ፣ ተስፋ በቆረጠ ስሜትሲተርኩልኝ ዓይኖቼ ላይ የተቋጠረው የእንባ ከረጢት ገንፍሎ እንዳይፈስ ብርቱ ትግል ማድረጌን አልሸሽግም፡፡
የሆነው ሆኖ እነዚህ የሥርዓቱ ሹማምንት የፍርድ ቤት ደጅ ሳይረግጡ፣ የሞት ቅጣት እንዲተላለፍባቸው ባደረጓቸው ምስኪኖች ላይ የማሰቃያ ጥበቦቻቸውን በሙሉ ከሞከሩባቸው በኋላ፡- ‹‹ሞት እንፈርድባችኋለን!!›› እያሉ ያስፈራሯቸውናይዝቱባቸው ነበር፤ እነርሱም፡- ‹‹እናንተ ፍርድ ቤት ናችሁ እንዴ?›› ብለው በግርምትና ባለማመን ሲጠይቋቸው፣ ማናአህሎኝነትያሳበጣቸው የፀጥታ
ኃላፊዎች እንዲህ በማለት አስረግጠው መልስ መስጠታቸውን ሰምቻለሁ፡-
‹‹አዎን! ፍርድ ቤት ማለት እኛ ነን!!››
በርግጥ ከዚህ ሁሉ መከራ በኋላ የተላለፈባቸው ውሳኔ፣ ያውም በሞት እንዲቀጡ የሚል መሆኑን ስናስተውል የዛቻውን መነሾ መረዳቱ አዳጋች አይሆንብንም፡፡ በአናቱም በምርመራ ወቅት ዕድል ፊቷን ያዞረችበትን ተጠርጣሪ እዛው እስረኛ ፊትበሽጉጥ ግንባሩን በርቅሰው እንደ መናኛ ነገር ሜዳ ላይ ይዘረጉት እንደነበረ የዓይን እማኞች ይመሰክራሉ፡፡
በጥቅሉ ይህ ሁነት በሀገሪቱ አለቅጥ የተንሰራፋውን የፍትሕ እጦት፣ የሠብአዊ መብት ጥሰት፣ ዳኞች ከሕግ ይልቅ ከቤተ- መንግሥት በሚላክላቸው የፍርድ ውሳኔ ንፁሃኑን ለምድራዊ ስቃይ ከመዳረግም አልፈው ተርፈው በጭካኔሕይወታቸውንም እንደሚነጠቁ በቂ ማስረጃ ይመስለኛል፡፡
‹‹ጄል-አዳብ››
የክልሉ ኗሪዎች ‹‹ጄል-አዳብ›› (የገሃነም እስር ቤት) እያሉ የሚጠሩት የጅጅጋው ማሰቃያ ቤት ክፍሎች የተሠሩት አራትመቶ ታሳሪዎችን እንዲይዙ ታስቦ ቢሆንም፣ አብዛኛውን ጊዜ ከአራት ሺህ በላይ ታሳሪዎች እንደሚታጎሩበት አረጋግጫለሁ፡፡ይህም አንድ ሰው ከአንድ ሰዓት በላይ በእንቅልፍ ማሳለፍ እንዳይችል አድርጎታል፡፡ ምክንያቱም ቦታውን ለተረኛው የመልቀቅ ግዴታአለበትና፡፡
ምናልባት እንቅልፍ ቢጥለው እንኳ ተረኞቹ ቀስቅሰው (ጎትተው) ያስነሱታል፡፡
ከ‹‹ጄል-አዳብ›› በሕይወት ተርፎ የሚወጣ ሰው ዕድለኛ ተደርጎ ይቆጠራል፡፡ በዚህ ቦታ ከቤተሰብ ጋር መገናኘት ጭራሽ አይሞከርም፡፡ ማሰቡ እንኳ እንደ ቅንጦት ነው የሚታየው፡፡ በእስር ቤቱ አጥር ሦስት መቶ ሜትር ክልል ርቀት ዙርያ ውስጥመገኘትም ለከባድ ስቃይ (አንዳንዴም ለሞት ቅጣት) ይዳርጋል፡፡ በሃያ አራት ሰዓት አንዴ፣ አንድ እንጀራ ለሦስት እየተቃመሱለአምስት ዓመት በዛ እስር ቤት ያሳለፈ ምስኪን አጋጥሞኛል፡፡ ይህ ወጣት በ2004ዓ.ም መጨረሻ አካባቢ ሦስት ዓይነት ተላላፊ በሽታ (ተቅማጥ፣ ሰውነትን የሚያሳክክና ጉሮሮን አሳብጦ ለአዕምሮ መቃወስ የሚዳርግ) ተከስቶ በቀን እስከ አስራ አራት ሰው ድረስ ይሞትእንደነበር ያስታውሳል፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ሕክምና ብሎ ነገር አልነበረም፡፡
እንዲያውም በግልባጩ የክልሉ አስተዳዳሪዎችጭካኔያቸውን (ኢ-ሠብአዊነታቸውን) ወለል አድርገው የሚያሳብቁ ድርጊቶች መፈፀማቸውን አላቋረጡም፡፡ ለማሳያ ያህልም እስረኛው ከሌሊቱስድስት
ሰዓት ላይ በአንድ ድምፅ እንዲህ የሚል መፈክር እንዲያሰማ መገደዱን እዚህ ጋ መጥቀስ ይቻላል፡-
‹‹መለስ ዜናዊ ሐኖላዶ!›› (መለስ ዜናዊ ለዘላለም ይኑር!)
‹‹አብዲ ሑመድ ዑመር ሐኖላዶ!››
‹‹ኢትዮጵያ ሐኖላዶ!››
ኦብነግ ሐዳኦዶ!›› (ኦብነግ ይውደም!)ሌላው አስገራሚ ጉዳይ ቤተሰብ ታሳሪ ልጁ በሕይወት ይኑር ይሙት የሚያውቀውከማጎሪያው በስንት ጊዜ አንዴ የሚፈታ ሰው ሲገኝ ብቻ የመሆኑ እውነታ ነው፡፡ እናም ድንገት በአንዲት ‹ዕድለኛ› ቀን አንድ ታሳሪ ከ‹‹ጄል-አዳብ›› የተለቀቀእንደሆነ ወሬው ከመቅጽበት ይዛመትና ለሳምንታት አሊያም ለወራት የእስረኛው ቤት በእንግዶች እስከ አፍ-ገደፉ ጢም ብሎ ይውላል፡፡የተለመደ ነውና እሱም ያለመታከት የቀረበለትን ጥያቄ በሚከተለው መልኩ ሲመልስ ይከርማል፡- ‹‹ኦ!… እገሌ ከሞተ እኮ ሁለት ዓመት አለፈው›› ፤ “እገሌማ ሲያሳዝን! ካረፈ ገና አንድ ወሩ ነው”፤ “ኦ! እገሌ ለወደፊቱ እግዜር ይጠብቀው እንጂ እስካሁን በሕይወት ይገኛል…” ወዘተ ወዘተ. . .