Tag Archives: Okelo Akuay

አቶ አንዱዓለም አራጌን ጨምሮ የፖለቲካ እስረኞች ተለቀቁ

ከመስከረም 3 ቀን 2004 ዓ ም ጀምሮ በእስር ላይ የነበሩት የቀድሞ የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ (አንድነት) ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር እና የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አንዱዓለም አራጌ ፥ የፓርቲያቸው አመራር አባላት የነበሩት አቶ ናትናኤል መኮንን፥ የቀድሞ የፓርላማ አባል አቶ አንዱዓለም አያሌው የካቲት 7 ቀን 2010 ዓ ም ከእስር ተለቅዋል።
Andualem Arage
አቶ አንዱዓለም አራጌ

በተመሳሳም የቀድሞ የጋምቤላ ፕሬዘዳንት የነበሩት አቶ ኦኬሎ አኳይ፥ የመብት ተሟጋቿ ወ/ሮ እማዋይሽ አለሙ፥ የኦፌኮ/መድረክ አመራር የነበሩት አቶ ኦልባና ሌሊሳ፥ የቀድሞ መኢአድ ፕሬዘዳንት አቶ ማሙሸት አማረ፥ የመኢዴፓ አመራር የነበሩት አቶ ክንፈሚካኤል ደበበ (አበበ ቀስቶ)፥ የኢብአፓ ፕሬዘዳንት የነበሩት አቶ ዘሪሁን ገብረእግዚአብሔር፥ የቀድሞ የሰማያዊ ፓርቲ አመራር የነበረው ወጣት ብርሃኑ ተክለያሬድ፥የመብት ተሟጋቿ ጫልቱ ታከለ እና ደርቤ ኢተና፤ የሙስሊሙ መፍትህ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላትና የመብት ተሟጋቾች አህመዲን ጀበልና አህመድ ሙስጠፋ እና አርቲስት ሴና ሰለሞን ከእስር ተለቅዋል።

በተለይ አቶ አንዱዓለም አራጌ እና ወ/ሮ እማዋይሽ አለሙ ተይዘው ከታሰሩ ጀምሮ በተለያየ ክስ መዝገብ ዕድሜ ልክ እስር ተፈርዶባቸው እንደነበር ይታወቃል።

ከላይ የተጠቀሱትን ጨምሮ በተመሳሳይ ቀን ከ746 ያላንሱ የፖለቲካ እስረኞች እንደሚፈቱ የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ለመግንግሥት መገናኛ ብዙኃን ማሳወቁ ይታወሳል። ይሁን እንጂ አሁንም በርካታ የፖለቲካ እስረኞች በተለያዩ የሀገሪቱ ወህኒ ቤቶች እንደሚገኙ መረጃዎች ይጠቁሟሉ።

የነ አቶ አንዱዓለም አራጌን መፈታት ተከትሎ በርካታ ህዝብ በአዲስ አበባ ቃሊቲ ወህኒ ቤት እና በየመሮሪያ ቤታቸው በመገኘት ደስታውን ሲገልፅና እና ድጋፉን ሲያደርግ ተስተውሏል። እነ አንዱዓለምም ለመላው ህዝብ ምሥጋናችውን አቅርበዋል።

እነ ኦኬሎ ኦኳይ ጥፋተኛ ተባሉ

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት ዛሬ መጋቢት 28ቀን 2008 ዓ.ም በዋለው ችሎት የቀድሞው የጋምቤላ ርዕሰ መስተዳድር ኦኬሎ ኦኳይ እና አብረዋቸው የተከሰሱት ስድስት ተከሳሾች ጥፋተኛ ናቸው ብሎ ውሳኔ አስተላለፈ።ፍርድ ቤቱ የቅጣት አስተያየት ለመስማት ሚያዚያ 17 ቀጠሮ ስጥቷል፡፡

Okello Akuay

በሰኔ ወር 2006ዓ.ም የሽብር ክስ ተመሰርቶባቸው ክሳቸው እየታየላቸው የሚገኙት እነ ኦኬሎ ኦኳይ በየካቲት 28 ቀን 2008 ዓ.ም በዋለው ችሎት ውሳኔ ለማስተላለፍ ለዛሬ ለሶስተኛ ጊዜ ተቀጥረው ነበር፡፡ በዚህም መሰረት ዛሬ በችሎት ከተሰየሙት ሶስት ዳኞች መካካል የቀኝ ዳኛ የሆኑት አቶ ሳሙኤል ታደሰ የፍርድቤቱን ውሳኔ በንባብ አሰምተዋል፡፡

ዳኛ ሣሙኤል ታደሰ ወደ አንድ ስዓት በቆየው የፍርድ ውሳኔ ንባባቸው እንዳመለከቱት አቶ ኦኬሎና ስድስቱ ተከሳሾች የጋምቤላ ህዘቦች ነፃነት ንቅናቄ (ጋህነን) አባል በመሆን እና የጋምቤላ ክልልን ከፌደሬሽኑ ለመገንጠል ተንቀሳቅሰዋል፡፡ ከአሜሪካ ገንዘብ በማሰባሰብ እና የሽብር ቡድን ማስተባበራቸውን በንባባቸው ጠቅሰዋል፡፡

አቃቤ ህግ በነኦኬሎ ላይ ከዘረዘራቸው ክሶች መካከል ከኤርትራ መንግስት ጋር የሽብር ድርድር በማድረግ እና ከኦነግ እና ግንቦት 7 አመራሮች ጋር በተለይ ከሞት ፍርደኛው ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ጋር መገናኘት እንደሚገኙበት ዳኛ ሳሙኤል አስታውሰዋል፡፡ከዚህም በተጨማሪ ወጣቶችን ለሽብር ተግባር መመልመል፣ ወታደራዊ ስልጠና መስጠት በክሳቸው ላይ መጠቀሱን ዳኛው ተናግረዋል፡፡

ከክስ ንባብ መስማት በኃላ ወደ ሁለት አመት ያህል ፍርድቤት የተመላለሱት እነ ኦኬሎ አኳይ የክስ መቃወሚያ ካቀረቡበት ጊዜ አንስቶ ለውሳኔ እስከተቀጠሩበት ጊዜ ያለው ሂደት በዳኛው ተብራርቶ ቀርቧል፡፡
የእነ ኦኬሎ የክስ መቃወሚያ በፍርድ ቤቱ ሙሉ ለሙሉ ውድቅ መደረጉን እና የተከሰሱበትን ክስ ክደው መከራከራቸውን ያስታወሱት ዳኛ ሳሙኤል በመቀጠል አቃቤህግ ምስክሮቹን አቅርቦ ማሰማቱን አስረደተዋል፡፡
ለወራት ከዘለቀው የምስክሮች መሰማት ሂደት በኃላ ፍርድቤቱ ተከሳሾቹን እንዲከላከሉ መወሰኑን ዳኛው ጠቅሰዋል፡፡ ተከሳሾቹ በምርመራ ወቅት በከፍተኛ ጫና እና ድብደባ ውስጥ እንዳለፉ ማስመዝገባቸውን ዳኛው ጠቁመዋል፡፡

የግራና የቀኙን ክርክር ያዳመጠው እና የቀረቡለትን ማስረጃዎች የመረመረው ፍርድ ቤት በሁሉም ተከሳሾች ላይ የጥፋተኛ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡

አንደኛ ተከሳሽ ኦኬሎ አኳይ በሰው እና መማስረጃ የጋምቤላን ክልል ከፌደሬሽኑ ለመገንጠል ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር በመሆን የአመራር ሰጪ ውሳኔዎችን ሲመራ በመቆየቱ አቃቤህግ በሰው እና በማስረጃ ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዳ ዳኛው በውሳኔው አመልክተዋል፡፡ተከሳሹ በበኩሉ የተከሳሽነት ቃል ከማሰማት በስተቀር መከላከያ ምስክሮችም ይሁን ሰነዶችን አቅርቦ በበቂ ሁኔታ እንዳልተከላከለ ዳኛው ገልፀዋል፡፡
ቀሪዎቹም ተከሳሾች በምርመራ ወቅት ለፖሊስ ቃላቸውን ተገደው ስለመስጠታቸው ያሰረዱ እንጂ የቀረበባቸውን ክስ የሰው ምስክር እና የሰነድ ማስረጃ አቅርበው እንዳልተከላከሉ በዳኛው ተገልጿል፡፡
“[ተከሳሾቹ] ምስክሮቻቸው ማዕከላዊ አብረዋቸው የነበሩ፣ በሌላ ወንጀል ተጠርጥረው ያሉ እና ተዓማኒነታቸው ጥርጣሬ ውስጥ የሚገባ ከመሆኑ በተጨማሪ ከዋናው ክስ እና የክስ ማስረጃ ጋር የማይገናኙ በመሆናቸው ክሳቸውን በደንብ አልተከላከሉም” ሲሉ ዳኛው ገልፀዋል፡፡

ክሱ መታየት ያለበት በፀረ ሽብር አዋጁ ነው ወይስ አይደለም የሚለውን ፍርድቤቱ መርምሮ በአንደኛ ተከሳሽ የተመሰረተው ጋህነን፣ የጋምቤላ ህዝብን ከፌደሬሽኑ ለመገንጠል ከተለያዩ የሽብር ቡድኖች ጋር የስልጠና ትብብር መጠየቃቸው በአቃቤ ህግ የተረጋገጠ ነው ብለዋል ዳኛው፡፡ ሆኖም ድርጊቱ የአገሪቷን አንድነት የማፈራረስ ሙከራን የሚያቋቁም እንደሆነ የገለፁት ዳኛው በዚህም መሰረት ተከሳሾቹ በፀረ ሽብር አዋጁ ሳይሆን የወንጀል ህጉን 241 በመተላለፋቸው በወንጀለኛ መቅጫ ስነስርአት ህግ 149(1) የጥፋተኝነት ውሳኔ ማስተላለፉን ተናግረዋል፡፡

መጋቢት 28/2008 ዓ.ም በዋለው ችሎት የጥፋተኝነት የፍርድ ውሳኔ የተላለፈባቸው ሰባት ሰዎች ሲሆኑ፣ እነዚህም ኦኬሎ አኩዋይ፣ ዴቪድ ኦጅሉ፣ ኡቻል አፒዮ፣ ኡማን ኒኮዮ፣ ኡጅሉ ቻም፣ ኡታካ ኡዋር እና ኡባንግ ኡቡንግ ናቸው፡፡

ምንጭ፡- EHRP

ኦኬሎ አኳይ እጅና እግራቸውን ታስረው ጨለማ ክፍል መታሰራቸው ተገለፀ

-ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ከቤተሰብ ውጭ ጠያቂ ተከልክሏል

የቀድሞ የጋምቤላ ክልል ፕሬዘዳንት አቶ ኦኬሎ አኳይ

የቀድሞ የጋምቤላ ክልል ፕሬዘዳንት አቶ ኦኬሎ አኳይ

የቀድሞው የጋንቤላ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ኦኬሎ አኳይ እጅና እግራቸው ታስሮ ጨለማ ክፍል መታሰራቸውን የነገረ ኢትዮጵያ ምንጮች ገለጹ፡፡

አቶ ኦኬሎ ቂሊንጦ በእስር ላይ እንደሚገኙ የሚታወስ ሲሆን፣ ሰውዬው ከሰሞኑ የርሃብ አድማ ማድረጋቸውን ተከትሎ በእስር በሚገኙበት እስር ቤት እጅና እግራቸውን ታስረው ብቻቸውን ጨለማ ክፍል እንዲገቡ እንደተደረጉ ምንጮች ተናግረዋል፡፡

ዛሬ ጥር 1 ቀን 2007 ዓ.ም ወደ ቂሊጦ ማረሚያ ቤት እስረኞችን ሊጠይቁ ሄደው እንደነበር የገለጹት ምንጮች፣ እዚያው በእስር ላይ ካሉ ሰዎች አቶ ኦኬሎ ያሉበትን ሁኔታ መረዳታቸውን አክለው ገልፀዋል፡፡

በሌላ በኩል የ18 አመት እስር ፍርደኛው ታዋቂው ጋዜጠኛና የፖለቲካ ተንታኝ እስክንድር ነጋ ከቤተሰብ ውጭ ሌላ ሰው መጠየቅ እንደተከለከለ የነገረ-ኢትዮጵ ዘገባ አመልክቷል፡፡

%d bloggers like this: