የዋና ኦዲተር ሪፖርት የመንግሥት ተቋማት የፋይናንስ ጥሰትና አፈጻጸም ከዓመት ዓመት እየባሰበት ነው አለ
ዮናስ ዓብይ
•ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ያልተወራረደ ሒሳብ ተገኝቷል
• ጊዜው ያለፈባቸው አደገኛ ኬሚካሎች ለዜጎች እየተሸጡ ነው
• ሊብሬ ያላቸው ተሽከርካሪዎች በአካል የት እንደገቡ አይታወቅም
• የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣንና ዩኒቨርሲቲዎች ተወቀሱ

የፌዴራል ዋና ኦዲተር ጽሕፈት ቤት የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ ቤቶች የ2007 የበጀት ዓመት ሒሳብ ኦዲት ማክሰኞ ግንቦት 9 ቀን 2008 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቀረበው ሪፖርት፣ አብዛኞቹ በጀት ተቀባይ የመንግሥት ተቋማት አስደንጋጭ የተባለ የሕግ ጥሰት የተገኘባቸው መሆኑን አስታወቀ፡፡ በዚህ ሪፖርት መነሻም ፓርላማው በአስፈጻሚ አካላት ላይ ቁጣውን ገልጿል፡፡
ዋና ኦዲተሩ አቶ ገመቹ ዱቢሶ በምክር ቤቱ ተገኝተው ባቀረቡት ሪፖርት፣ ብዛት ያላቸው የመንግሥት ተቋማት በተደጋጋሚ በየዓመቱ የሚሰጣቸውን አስተያየት ተግባራዊ በማድረግ ከማሻሻል ይልቅ፣ ወደባሰ ጥፋት እየገቡ መሆናቸውንና ለዚህም ዋና ምክንያቱ ተጠያቂ ያለመደረጋቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ዋና ኦዲተር ጽሕፈት ቤት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በስተቀር በሁሉም መሥሪያ ቤቶች የኦዲት ሥራ ማከናወኑን አስታውቋል፡፡ ዋና ዋና የተባሉና ልዩ ትኩረት የሚሹ የኦዲት ግኝቶችን ዋና ኦዲተር ለምክር ቤቱ አቅርበዋል፡፡
ዋና ኦዲተሩ አቶ ገመቹ አጠቃላይ ሪፖርታቸው በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የፋይናንስና ሕጋዊነት ኦዲት፣ በክዋኔ ኦዲትና በመሠረታዊ አገልግሎቶች ከለላ ድጋፍ (PBS) ላይ ባተኮሩ ሦስት ክፍሎች የቀረበ ነበር፡፡
ምንም እንኳ ተጠያቂ መደረግ አለባቸው የተባሉ የተለያዩ ተቋማት በዝርዝር ሪፖርቱ የተካተቱ ቢሆንም፣ በኦዲት ግኝቱ ስማቸው የተነሳው የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣንና አሥር ያህል ዩኒቨርሲቲዎች ናቸው፡፡
በሕግ በተደነገገው መሠረት የሰነድ ሒሳብ በወቅቱ መወራረዱን ለማጣራት በተደረገው የኦዲት ሥራ፣ በ94 መሥሪያ ቤቶችና በ11 ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች 2.079 ቢሊዮን ብር በደንቡ መሠረት በወቅቱ መወራረድ አለመቻሉን ሪፖርቱ ያሳያል፡፡
ከዚህ ውዝፍ ሒሳብ ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ የያዙት የመንግሥት ግዢና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት፣ የትምህርት ሚኒስቴር፣ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ የአገር መከላከያ ሚኒስቴር፣ ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ፣ ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲና ሌሎችም ይገኙበታል፡፡
በተሰብሳቢ ሒሳብ ላይ የታዩ ዋና ዋና የአሠራር ችግሮች ያሉትን አቶ ገመቹ በዝርዝር ያቀረቡ ሲሆን፣ በአራት መሥሪያ ቤቶች የተሰብሳቢ ሒሳብ ተቀፅላ ሌጀር ያልተዘጋጀላቸው ሒሳብ ከ174 ሚሊዮን ብር በላይ ተገኝቷል ብለዋል፡፡
በገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ሥር ባሉ ሦስት ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶችና በሌሎች ሁለት መሥሪያ ቤቶች ከ15.9 ሚሊዮን ብር በላይ በወጪ ተመዝግቦ ሪፖርት መደረግ ሲገባው፣ ያላግባብ በተሰብሳቢ ሒሳብ ተይዞ መገኘቱን አስረድተዋል፡፡
የመንግሥት ገቢ በወጡት ሕጎች መሠረት በአግባቡ መሰብሰቡን ለማጣራት በተደረገ ኦዲት፣ በ34 መሥሪያ ቤቶችና በገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ሥር ባሉ አሥራ አምስት ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች በድምሩ 118.7 ሚሊዮን ብር፣ እንዲሁም በአንድ መሥሪያ ቤት ተማሪዎች በገቡት ውል መሠረት ግዴታቸውን ባለመወጣታቸው ያልተሰበሰበ 211,930 ዶላር ግብር፣ ቀረጥና ታክስ አለመሰብሰቡንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡
በገቢ ሰብሳቢ መሥሪያ ቤቶችና ድርጅቶች ከፍተኛ የሚባሉ ገንዘቦች አለመሰብሰባቸውን የዋና ኦዲተር ሪፖርት በዝርዝር አስፍሯል፡፡ ለአብነትም በገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ከ689 ሚሊዮን ብር በላይ በበጀት ዓመቱ አለመሰብሰቡን አሳይቷል፡፡
የገቢ ሒሳብ ሪፖርት ውስጥ ያልተካተተ ገቢን አስመልክቶ የኦዲት ግኝቱ እንደሚያስረዳው፣ ገቢ እንዲሰበሰቡ በተፈቀደላቸው ተቋማት በትክክል ተመዝግቦ በገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር መቅረቡን ለማረጋገጥ በተደረገ የኦዲት ሥራ በስድስት መሥሪያ ቤቶች ከ76.7 ሚሊዮን ብር በላይ፣ በሌሎች አምስት መሥሪያ ቤቶች በገንዘብ መጠን ያልተገለጸ የውስጥ ገቢ ባቀረቡት ዓመታዊ የገቢ ሒሳብ ሪፖርት ሳይካተት መገኘቱን አቶ ገመቹ ለምክር ቤቱ ገልጸዋል፡፡
የገቢ ሒሳብ በሪፖርት ከማያካትቱት መሥሪያ ቤቶች አብዛኞቹ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሲሆኑ፣ ይህ አሠራር በገቢ ሒሳብ ላይ የሚደረገውን ቁጥጥር በማላላት ለምዝበራ በር የሚከፍት ከመሆኑም በላይ፣ መሥሪያ ቤቶቹ በራሳቸው የሚያዘጋጁዋቸው የሒሳብ መግለጫዎች የመንግሥት አጠቃላይ ገቢና ወጪ ሒሳብ ትክክለኛ ገጽታ እንዳያሳዩ ያደርጋል ብለዋል፡፡
በወጪ ሒሳብ አያያዝ፣ በግንባታ ኮንትራት ውል፣ በግዢና ንብረት አወጋገድና አስተዳደር ከፍተኛ የሕግ ጥሰትና አግባብነት የጎደለው አሠራር በአብዛኞቹ መሥሪያ ቤት ቢታዩም፣ ከፍተኛ ችግር የታየባቸውም ሆነ በተከታታይ ዓመታት መሻሻል ያላሳዩት አብዛኞቹ ዩኒቨርሲቲዎች መሆናቸውን ዋና ኦዲተሩ ገልጸዋል፡፡
የወጪ ሒሳብን በተመለከተ በ24 መሥሪያ ቤቶች የተሟላ መረጃ ሳይቀርብ ከ221.8 ሚሊዮን ብር በላይ በወጪ ተመዝግቦ መገኘቱን የኦዲት ሪፖርቱ ያመለክታል፡፡ የተሟላ የወጪ ማስረጃ ሳይቀርብ በወጪ ከመዘገቡት መሥሪያ ቤቶች ትምህርት ሚኒስቴር 95,526,864.83 ብር፣ ሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ 26,417,436.86 ብር፣ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 10,000,000 ብር፣ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ 8,601,445.18 ብር፣ ሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ 5,100,434.00 ብር፣ ወሎ ዩኒቨርሲቲ 4,646,850.00 ብር ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡
እንዲሁም ኦዲት በተደረጉ 56 መሥሪያ ቤቶችና አራት ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ከደንብና ከመመርያ ውጪ ያላግባብ 61,397,293.70 ብር ተከፍሎ መገኘቱን የዋናው ኦዲተሩ ሪፖርት ያመለክታል፡፡
ማንኛውም ግንባታ ሲከናወን ሥራው በትክክል ስለመሠራቱ ብቃቱ ተረጋጋጦ የማማከር አገልግሎት እንዲሰጥ በሚመለከተው መንግሥታዊ አካል ፈቃድ በተሰጠው አማካሪ ድርጅት ሲረጋገጥ ብቻ፣ ክፍያዎች ሊፈጽሙ እንደሚገባ የሕግ አግባቡን ዋና ኦዲተሩ አስረድተዋል፡፡ ሆኖም በአራት መሥሪያ ቤቶች የፕሮጀክቶችን ሥራ እንዲከታተሉ የተቋቋሙ፣ ነገር ግን የማማከር ፈቃድ በሌላቸው የግንባታ ጽሕፈት ቤቶች በኮንትራክተሮች የተሠራው ሥራ ትክክለኛነት እየተረጋገጠ በሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ 717,312,735.03 ብር፣ በዲላ ዩኒቨርሲቲ 74,495,345.59 ብር፣ በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ 35,419,596.22 ብር እና በአክሱም ዩኒቨርሲቲ 7,428,032.90 ብር በድምሩ 834,655,709.74 ብር ገንዘብ ወጪ ሆኖ ተገኝቷል ሲሉም ገልጸዋል፡፡
የእነዚህን ዩኒቨርሲቲዎች ጉዳይ በተመለከተ ተጠያቂ የማድረግ ዕርምጃ ከመውሰድ በተጨማሪ የመፍትሔ ሐሳብ ያሉትንም አቶ ገመቹ ለምክር ቤቱ አስረድተዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲዎች ከዓመት ዓመት የሚፈጸሙት ስህተት እየተባባሰ በመሆኑ በትምህርት ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ፣ ግዢ፣ ግንባታንና መሰል ሥራዎችን በተመለከተ ሌላ ተቋም ማቋቋም እንደሚገባ፣ ወይም በትምህርት ሚኒስቴር ሥር ለዚህ ዓላማ አንድ ዘርፍ እንዲቋቋም በማለት ለምክር ቤቱ አሳስበዋል፡፡ ነገር ግን ትምህርት ሚኒስቴር በራሱ ብዙ የኦዲት ችግር ከተገኘባቸው መሥሪያ ቤቶች አንዱ በመሆኑ፣ ይህንን ሥራ በአግባቡ ስለመፈጸሙ በአንዳንድ የምክር ቤቱ አባላት ጥያቄ ተነስቶበታል፡፡
በሌላ በኩል የምክር ቤቱን አባላት ያስደነገጠው ሌላው ጉዳይ በግብርና ምርት ማሳደጊያዎች አቅራቢ ድርጅት፣ የአገልግሎት ጊዜያቸው ያለፈባቸው ኬሚካሎች ለአርሶ አደሮች የሚሸጡ መሆናቸው በዋና ኦዲተሩ ሪፖርት ሲቀርብ ነው፡፡ የተለያዩ የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸው ኬሚካሎች በዝርዝር የተጠቀሱ ሲሆን፣ በኦዲት ሥራው ወቅት ኬሚካሎቹ ከሁለት ወራት እስከ ሁለት ዓመታት የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ቢያልፍም በቀጥታ ለአርሶ አደሮች ሲሸጡ መታየታቸው በሪፖርቱ ተካቷል፡፡
በተጨማሪም በመድኃኒት ፈንድና አቅርቦት ኤጀንሲ የተገዙ ግምታቸው 570 ሚሊዮን ብር የሚሆኑ መድኃኒቶች፣ በዋናው መሥሪያ ቤትና በቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች በመጋዘን ተቀምጠው የመጠቀሚያ ጊዜያቸው አልፎ መገኘቱንም አቶ ገመቹ ለምክር ቤቱ አስረድተዋል፡፡
ሕፃናትን በጉዲፈቻ መልክ ወደ ውጭ መላክን በተመለከተ የዋና ኦዲተር ሪፖርት ግኝቱንም አመላክቷል፡፡ በተለይ የሴቶችና ሕፃናት ሚኒስቴር የሚመለከታቸው ኃላፊዎች ከ2004 እስከ 2007 ዓ.ም. ባሉት ጊዜያት ውስጥ በናሙና ተመርጠው በታዩት የጉዲፈቻ አስፈጻሚ ድርጅቶች፣ ወደ አሜሪካና አውሮፓ ሕፃናትን በላኩባቸው አገሮች ጉብኝት ማድረጋቸው በሪፖርቱ ተመልክቷል፡፡ ነገር ግን ኃላፊዎቹ በሄዱባቸው አገሮች ያገኙዋቸው በጉዲፈቻ የተሰጡ ሕፃናት ደኅንነታቸው መጠበቁንና የጉዲፈቻ ተጠቃሚ መሆናቸውን የጉብኝት ዝርዝር ሪፖርት ቢያቀርቡም፣ እንዲሁም ባቀረቡት ሪፖርት መሠረት አስፈላጊውን ዕርምጃ መውሰድና ግብረ መልስ ሊሰጡ የሚገባ ቢሆንም ይህ የማይፈጸም መሆኑን በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡
የገቢና ወጪ ዕቃዎችን በተመለከተ ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ ወይም እንዳይወጡ በኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ድርጅት የላብራቶሪ ውጤት፣ ወይም ዓለም አቀፍ የሦስተኛ ወገን ሠርተፊኬት አምጥተው ትክክለኛነቱ ተረጋግጦ ደረጃቸውን የሚያሟሉ መሆናቸው ተረጋግጦ፣ ንግድ ሚኒስቴር ከሕግ አግባብ ውጪ በተቃራኒው ደብዳቤ በመጻፍ እንዲለቀቁ ማድረጉን የኦዲተሩ ሪፖርት አጋልጧል፡፡ እንዲሁም በሦስተኛ ወገን ሳይረጋገጡና የላቦራቶሪ ውጤት ሳይገለጽ ምርቶች ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ እያደረገ መሆኑንም ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡
በንብረት አስተዳደርም በርካታ የኦዲት ግኝቶች ለምክር ቤቱ የቀረቡ ሲሆን፣ የፓርላማ አባላቱን በቁጭት ፈገግ ያሰኘው የኢትዮጵያ ብዝኃ ሕይወት ኢንስቲትዩት በስሙ ከተመዘገቡ ተሽከርካሪዎች ውስጥ አሥሩ ሊብሬ ቢኖራቸውም፣ ተሽከርካሪዎቹ የት እንደደረሱ ምንም የማይታወቅ መሆኑን አቶ ገመቹ ሲገልጹ ነው፡፡
ከዋና ኦዲተሩ ሪፖርት በኋላም የት እንዳሉ የማይታወቁትን አሥሩን የኢንስቲትዩቱ ተሽከርካሪዎች አስመልክተው አስተያየት የሰጡት የምክር ቤቱ አባል አቶ ዱቤ ጂሎ፣ ‹‹ባለፉት ቀናት ከ88 በላይ የኮንዶሚኒየም ሕንፃዎች ጠፉ ተባልን፡፡ ዛሬ ደግሞ አሥር ተሽከርካሪዎች ከአንድ ተቋም ከጠፉ ነገ የተገነባ መንገድ ጠፋ የማንባልበት ምክንያት ላይኖር ነው?›› በማለት አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
በዕለቱ አስተያየትና ጥያቄዎችን ሲያቀርቡ የነበሩ አብዛኛዎቹ የምክር ቤት አባላት ዋና ኦዲተሩን አቶ ገመቹን ላቀረቡት ሪፖርት ውዳሴና አድናቆት ሲያቀርቡላቸው፣ በሌላ በኩል ደግሞ የሥራ አስፈጻሚውን አካል ሲተቹ ውለዋል፡፡
ወ/ሮ ሙሉ ገብረ እግዚአብሔር የተባሉ የምክር ቤት አባል በሪፖርቱ ማዘናቸውን ገልጸው እያንዳንዱ መሥሪያ ቤት በሕግ ሊጠየቅ ይገባዋል ካሉ በኋላ፣ ‹‹ከዚህ በኋላ አንላቀቅም፡፡ ከማንኛውም አካል ጋር እንጠያየቃለን፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡ እኚሁ አባል፣ ‹‹ለብዙ ዓመታት የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ከተዘፈቀበት መውጣት አለመቻሉን ስመለከት ለእኔ ጥያቄ ብቻ ሳይሆን፣ እስከ መክሰስ የሚያደርስ ዕርምጃ መወሰድ አለበት፤›› ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲዎችንም በተለመከተ ሕግ፣ አካውንቲንግ ወይም ማንኛውንም የትምህርት ዓይነት የሚያስተምር ተቋም እንዴት የራሱን ስህተት ሊያርም አይችልም በማለት ጠይቀዋል፡፡
አቶ መሐሪ ዘለቀ የተባሉ ሌላ የምክር ቤት አባል በበኩላቸው፣ ‹‹ጊዜ ያለፈባቸውን ኬሚካሎች የሚሸጥ ተቋምን በአስተያየት ብቻ ማለፍ የለብንም፡፡ በሕግ ጭምር የግድ መጠየቅ አለበት፡፡ በሰው ሕይወት የራሱን ትርፍ ለማጋበስ የሚሞክር ተቋም ዝም ሊባል አይገባውም፤›› ብለዋል፡፡
በተደጋጋሚ ዓመታት ተመሳሳይ የኦዲት ግኝት ቀርቦባቸው መሻሻል በማያሳዩ ላይ በምክር ቤቱ በኩልም ሆነ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካይነት ዕርምጃ መወሰድ እንዳለበት፣ በርከት ያሉ የምክር ቤቱ አባላት ተመሳሳይ አቋማቸውን ሲሰነዝሩ ተስተውለዋል፡፡ ዋና ኦዲተሩ አቶ ገመቹ የመንግሥት ተቋማቱ በተደጋጋሚ የሕግ ጥሰት የሚፈጽሙት ተጠያቂ ባለመሆናቸው ምክንያት መሆኑን አስረግጠው ተናግረዋል፡፡
በምክር ቤቱ አሠራር መሠረት ለመጀመርያ ጊዜ ዋናው ኦዲተሩ ሪፖርታቸውን ሲያቀርቡ፣ የኦዲት ተደራጊ መሥሪያ ቤቶች ኃላፊዎች በምክር ቤቱ ተገኝተው ሪፖርቱን እንዲከታተሉ በአፈ ጉባዔው ጥሪ ተገኝተዋል፡፡ ነገር ግን ከሰዓት በኋላ በነበረው የጥያቄና መልስ ክፍለ ጊዜ አብዛኛዎቹ የተቋማቱ ኃላፊዎች ባለመገኘታቸው በአንዳንድ የምክር ቤቱ አባላት ትችት ተሰንዝሮባቸዋል፡፡
ምንጭ፡-ሪፖርተር ጋዜጣ
ዶ/ር ወልደመስቀል ኮስትሬ አረፉ
(አዲስ ሚዲያ) ለረጀም ጊዜ የኢትዮጵያ ረጅም ርቀት ሩጫ ውድድር አሰልጣኝ የነበሩት ዶ/ር ወልደመስቀል ኮስትሬ በህክምና ሲረዱ ቆይተው በተወለዱ በ69 ዓመታቸው ትናንት ሰኞ ግንቦት 8 ቀን 2008 ዓ.ም. ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡ ዶ/ር ወልደመስቀል ኢትዮጵያ ከነ አበበ ቢቂላ፣ ማሞ ወልዴ እና ምሩፅ ይፍጠር በኋላ በጋራም ሆነ በግል በሚገኙ አትሌቶች የድል ውጤት ዋነኛ ተጠቃሽ አሰልጣኝ ናቸው፡፡

በተለይም አትሌት ኮሎኔል ደራርቱ ቱሉ፣ አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ፣ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ፣ አትሌት ጠሩነሽ ዲባባ፣ አትሌት ብርሃኔ አደሬ፣ አትሌት ጌጤ ዋሚ፣ አትሌት ወርቁ ቢቂላ፣ አትሌት ፊጣ ባይሳ፣ አትሌት አሰፋ መዝገቡ፣ አትሌት ስልሺ ስህን፣…የመሳሰሉ ስመጥር አትሌቶችን ያፈሩ በማፍራት በርካታ የወርቅ፣ የብር እና የነሐስ ሜዳልያ ሽልማቶችን ከአትሌቶቹ በተጨማሪ ሀገሪቷም እንድታገኝ ያስቻሉ ታላቅ ሰው ነበሩ፡፡
ዶ/ር ወልደመስቀል ኮስትሬ ከ1964 ዓ.ም. ጀምሮ ለ30 ዓመታት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ የረጅም ርቀት አሰልጣኝነት ላበረከቱት አስተዋፅዖ በሀገሪቱ መንግሥትም ሆነ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የተሰጣቸው ዕውቅናም ሆነ ሽልማት ባይኖርም፤ የዓለም አቀፍ አትሌቲክ ማኀበር (IAAF) በ1998 ዓ.ም. (እ.አ.አ በ2006) ምርጥ አሰልጣኝ በሚል ተሸላሚ እንደነበሩ አይዘነጋም፡፡
77 ቢሊዮን ብር የሚያንቀሳቅሰው ስኳር ኮርፖሬሽን የገጠመው ፈተና
‹‹ለስኳር ኮርፖሬሽን መውደቅ ሜቴክ ትልቅ ድርሻ አለው› ‹‹የስኳር ኮርፖሬሽን የቀድሞ አመራሮች መጠየቅ አለባቸው››

የኮርፖሬሽኑ ከፍተኛ አመራሮች
በዮሐንስ አንበርብር
በ2003 ዓ.ም. በተካሄደው የመጀመርያ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ትልቅ ትኩረት ከተሰጣቸው ሜጋ ፕሮጀክቶች መካከል የስኳር ልማት አንደኛው ነው፡፡ አገሪቱ ለስኳር ልማት ያላትን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም አሥር ግዙፍና አዳዲስ የስኳር ፋብሪካዎችን በመገንባት በዓመት 4.07 ሚሊዮን በላይ ስኳር በማምረትና ለውጭ ገበያ በማቅረብ፣ በ2007 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ 1.2 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት በዕቅድ ተይዞ ነበር፡፡
ይሁን እንጂ ይህ ዕቅድ በጣም የተለጠጠ መሆኑ በስተመጨረሻ ሲታወቅ፣ ሰባት ፋብሪካዎችን በመጀመርያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ማጠናቀቅ ተብሎ እንዲከለስ ተደርጓል፡፡
እነዚህ አዳዲስና ግዙፍ ፕሮጀክቶች በደቡብ ኦሞ ዞን የሚገነቡት ኩራዝ አንድ፣ ኩራዝ ሁለት፣ ኩራዝ ሦስት፣ በለስ አንድ፣ በለስ ሁለት፣ ከሰም፣ ወልቃይት፣ አርጆ፣ ደዴሳና ተንዳሆ ናቸው፡፡
መንግሥት ፕሮጀክቶቹን አጠናቆ ስኳር ለውጭ ገበያ በማቅረብ በሚገኝ የውጭ ምንዛሪ ዕዳ መክፈል እንደሚችል በማሳመን ለስኳር ፋብሪካዎቹ መገንቢያ ከተለያዩ አበዳሪዎች ሁለት ቢሊዮን ዶላር ተበድሯል፡፡ ከአገር ውስጥ ባንኮችም ከፍተኛ ብድር አግኝቷል፡፡ በአጠቃላይ የስኳር ልማቱን የሚመራው የኢትዮጵያ ስኳር ልማት ኮርፖሬሽን 77 ቢሊዮን ብር በላይ እያንቀሳቀሰ የሚገኝ ቢሆንም፣ አንድም ፋብሪካ እስካሁን ተጠናቆ ወደ ሥራ አልገባም፡፡ በሌሎች አገሮች አንድ ስኳር ፋብሪካን ለማጠናቀቅ ግፋ ቢል አንድ ዓመት የሚፈጅ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ስኳር ልማት ኮርፖሬሽን ግን አንድ ዓመት ከስድስት ወራት (18 ወራት) አንድ ስኳር ፋብሪካን ለማጠናቀቅ አቅዶ የውል ስምምነቶችን ቢያደርግም፣ አንድ ፋብሪካ ሥራ ሳይጀምር ስድስተኛ ዓመት ላይ ተደርሷል፡፡
የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን የሥራ ኃላፊዎች በ2008 የበጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጸም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ለማቅረብ ባለፈው ሰኞ ግንቦት 1 ቀን 2008 ዓ.ም. ተገኝተዋል፡፡
የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነው ከተሾሙ የወራት ዕድሜን ያስቆጠሩት አቶ እንዳወቅ አብቴና ሌሎች ምክትል ሥራ አስፈጻሚዎች ያቀረቡት ሪፖርት ‹‹ተስፋ በመቁረጥና እያመመን ነው፤›› ብለዋል፡፡
ከሰባት ዓመት በፊት ግንባታው የተጀመረው ተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ በኅዳር ወር 2008 ዓ.ም. ስኳር ማምረት ቢጀምርም ጥራቱ የተጓደለ የእንፋሎት አቅርቦት፣ የፋብሪካውን ፊልተር በቆሻሻ በመዝጋቱና በተርባይን ላይ ጉዳት በማድረሱ እንዲቆም መደረጉን ገልጸዋል፡፡ ጥገና ከተደረገ በኋላ በአገሪቱ በተከሰተው ድርቅ ለፋብሪካውና ለመስኖ የሚሆን የውኃ አቅርቦት ችግር ወደ ምርት እንዳይገባ እንዳደረገው ጠቁመዋል፡፡
የተንዳሆ ቁጥር ሁለት ፋብሪካ ግንባታም ገና 27 በመቶ ላይ ይገኛል፡፡ ኩራዝ አንድ የተባለው ፋብሪካ ኮንትራት ውል የተገባው በ2003 ዓ.ም. ሲሆን፣ የውል ማሻሻያ ሰኔ 2004 ዓ.ም. ላይ እንደተደረገ አቶ እንዳወቅ አስረድተዋል፡፡
በዚህ መሠረት ግንባታውን የሚያከናውነው አገር በቀሉ የኢትዮጵያ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ፕሮጀክቱን በመጋቢት ወር 2005 ዓ.ም. አጠናቆ ማስረከብ ይጠበቅበት ነበር፡፡
ፕሮጀክቱ በመጋቢት ወር 2008 ዓ.ም. ላይ የደረሰበት ደረጃ 83 በመቶ ሲሆን፣ ሜቴክ ግን 97 በመቶ ክፍያ እንደተፈጸመለት አቶ እንዳወቅ ተናግረዋል፡፡ ኩራዝ ሁለት የተባለውን ፋብሪካ ለማስገንበት ውል የተፈረመው እ.ኤ.አ. በሐምሌ ወር 2014 ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት የፕሮጀክቱ አፈጻጸም 58 በመቶ መድረሱን ይጠቅሳሉ፡፡ በውሉ መሠረት በመጪው ሐምሌ ወር ፕሮጀክቱ መጠናቀቅ የነበረበት ቢሆንም መዘግየቱን አስታውቀዋል፡፡ የፕሮጀክቱ ኮንትራክተር የፕሮጀክቱ ማጠናቀቂያ ጊዜ እንዲራዘምለት ጠይቆ እስከ መጪው ኅዳር ወር እንዲያጠናቅቅ መመርያ እንደተሰጠው አብራርተዋል፡፡
ኩራዝ ሦስት ግንባታው የተጀመረው እ.ኤ.አ. በፌብሯሪ 2015 ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት የፕሮጀክቱ አፈጻጸም 25 በመቶ ደርሷል፡፡ ይህም ቢሆን መሆን ከነበረበት ወደ ኋላ የቀረ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ኩራዝ አምስት ስኳር ፋብሪካን ለማስጀመር ከቻይና ኩባንያ ጋር ውል የተፈጸመ ሲሆን፣ ወደ ሥራ ለመግባት ኩባንያው ዝግጅት ላይ መሆኑን አቶ እንዳወቅ ይገልጻሉ፡፡ በለስ አንድ ስኳር ፕሮጀክት ወደ ሥራ የገባው በየካቲት 2003 ዓ.ም. ነው፡፡ በሰኔ ወር 2004 ዓ.ም. የውል ማሻሻያ መደረጉንና በመጋቢት ወር 2005 ዓ.ም. ኮንትራክተሩ ሜቴክ አጠናቆ ማስረከብ የነበረበት ቢሆንም፣ የፕሮጀክቱ አፈጻጸም በአሁኑ ወቅት ገና 60 በመቶ ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡ ኮንትራክተሩ ግን 94 በመቶ የሚሆነውን ክፍያ መቀበሉን ገልጸዋል፡፡
በለስ ሦስት ፋብሪካን ለመገንባት ውል የተፈጸመው በ2003 ዓ.ም. ሲሆን፣ መጠናቀቅ የሚገባው በ2005 መጋቢት ላይ እንደነበረ ያስረዳሉ፡፡ ይሁን እንጂ ፕሮጀክቱ ገና 23 በመቶ ሲሆን፣ ኮንትራክተሩ ሜቴክ ግን 94 በመቶ ክፍያ እንደተከፈለው ያስረዳሉ፡፡
የከሰም ስኳር ፋብሪካ አፈጻጸም 96 በመቶ መድረሱን ነገር ግን ገና ሙሉ ለሙሉ ወደ ሥራ እንዳልገባ አክለዋል፡፡ ወልቃይት ስኳር ፋብሪካም ግንባታው እንዳልተጀመረና በቅርቡ ግንባታው እንደሚጀመር ገልጸዋል፡፡ ኮርፖሬሽኑ ፋብሪካዎቹን ገንብቶና ምርት ኤክስፖርት በማድረግ ዕዳውን የመክፈል ኃላፊነት የተሰጠው ቢሆንም፣ ኤክስፖርት ማድረግ ይቅርና የአገሪቱን የስኳር ፍላጎት ማሟላት አለመቻሉን ገልጸዋል፡፡
ግንባታዎቹን ለማከናወን 77 ቢሊዮን ብር የውጭና የአገር ውስጥ ብድር የተበደረ በመሆኑ፣ አንድም ፋብሪካ ወደ ምርት ባልገባበት በአሁኑ ወቅት 13 ቢሊዮን ብር ዕዳ ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ የመክፈል ኃላፊነት ከፊቱ ተጋርጧል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ ይገዙና የኮሚቴው አባላት የኮርፖሬሽኑ ችግር ምን እንደሆነ፣ ሥራው ባልተሠራበት ሁኔታ ከ90 በመቶ በላይ ገንዘብ ለምን እንደተከፈለ ማብራሪያ ጠይቀዋል፡፡
የኮርፖሬሽኑ የኢንቨስትመንትና ልማት ዘርፍ ምክትል ሥራ አስፈጻሚ አቶ አብርሃም ደምሴ በሰጡት አስተያየት፣ የአሥሩም አዳዲስ ፋብሪካዎች ኮንትራት የተሰጠው ለአገር በቀሉ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) መሆኑን አስታውሰው፣ ኮርፖሬሽኑ ፋብሪካዎቹን መገንባት እንዳልቻለ ገልጸዋል፡፡ ይህ ቢሆንም የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን አመራሮች ከሜቴክ ጋር የነበራቸው ግንኙነት በቢዝነስ ኮንትራት ሕግ የማይመራ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
‹‹አሥሩም ፋብሪካዎች በዚህ ኮንትራክተር እንዲሠሩ ነበር የተወሰነው፡፡ በኋላ ላይ የመፈጸም አቅሙ እየታየ ፕሮጀክቶቹ እየተነጠቁ አሁን እጁ ላይ ሦስት ፋብሪካዎች ናቸው የቀሩት፤›› ብለዋል፡፡
ከዚህ ኮንትራክተር (ሜቴክ) ተነጥቀው ፋይናንስ ተገኝቶላቸው ወደ ሥራ ከገቡት መካከል ከሰም ሥራ ለመጀመር ዝግጅት ላይ ሲሆን፣ ሌሎቹ ደግሞ እስከ ኅዳር ወር 2008 ዓ.ም. ይደርሳሉ ብለዋል፡፡ በሜቴክ እጅ የሚገኙት ግን መቼ እንደሚጠናቀቁ እንኳን ለማወቅ አስቸጋሪ እንደሆነባቸውና ከድርጅቱ ጋር ልቅ የሆነው ግንኙነት በውል ያልታሰረ በመሆኑ ዕርምጃ እንኳን ለመውሰድ እንዳልተቻለ ተናግረዋል፡፡
ሜቴክ በእጁ የሚገኙትን ሦስት ፋብሪካዎች በተለይም ኩራዝ አንድ ፋብሪካን በመጋቢት ወር 2007 ዓ.ም. ለማጠናቀቅ ገንዘብ እንደሚያስፈልገው ገልጾ፣ በልዩ ሁኔታ ስኳር ኮርፖሬሽን የአገር ውስጥ ብድር እንዲያገኝ ተደርጎ ሊከፈለው መቻሉን አቶ አብርሃም አስረድተዋል፡፡
‹‹ይሁን እንጂ ይህ ፋብሪካ እስካሁን አልተጠናቀቀም፡፡ እኛ ግን ዕዳ የመክፈል አደጋ ከፊታችን ተጋርጧል፤›› ብለዋል፡፡ ፋብሪካዎቹ ባለመድረሳቸው ምክንያት አጠቃላይ የስኳር ኮርፖሬሽን ወጪ እየናረ መሆኑን የሚገልጹት የሥራ ኃላፊው፣ የሸንኮራ አገዳው ቢደርስም አገዳውን ከማስወገድ ሌላ አማራጭ አለመገኘቱን ገልጸዋል፡፡
‹‹ኩራዝ ላይ 870 ሔክታር አገዳ ለማስወገድ ተቃርበናል፡፡ 300 ሺሕ ሔክታር የሸንኮራ አገዳ በለስ ላይ አስወግደናል፡፡ ይህንን ለማስወገድ በሔክታር 50 ሺሕ ብር እያወጣን ነው፤›› በማለት በምሬት ተናግረዋል፡፡
‹‹በዚህ ኮንትራክተር ላይ እንደ ማንኛውም ኩባንያ ቅጣት መጣል እንደማንችል ሁላችሁም ታውቃላችሁ፡፡ የሚያስጠይቅ ነገር ካለ ባለቤቱ ተለይቶ መጠየቅ ያስፈልጋል፤›› ብለዋል፡፡
ሌላው የኮርፖሬሽኑ አመራርም የሜቴክ ችግር በመገንባት ላይ ባሉት ፋብሪካዎች ላይ ብቻ አለመሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡ በማምረት ላይ ለሚገኙ ፋብሪካዎች መለዋወጫ የሚያቀርበው ሜቴክ መሆኑን በመጥቀስ፣ መለዋወጫ ባለማቅረቡ ምክንያት ፋብሪካዎች ለበርካታ ቀናት ምርት እንደማያመርቱ ገልጸዋል፡፡
‹‹የማይችሉትን ሁሉ እንችላለን እያሉ አገርን ዋጋ እያስከፈሉ ነው፡፡ ምክንያቱም ነባሮቹ ፋብሪካዎች ያለ ችግር ቢሠሩ ቢያንስ በውጭ ምንዛሪ ስኳር አናስገባም ነበር፤›› ብለዋል፡፡ መለዋወጫ ከሜቴክ የመግዛት ግዴታ ለአገሪቱ አዋጭ አለመሆኑን፣ ምክንያቱ ደግሞ ሜቴክ ራሱ ከውጭ ከሚገባው በላይ እየሸጠ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡ ‹‹ለምሳሌ ሮለር ከውጭ ስንገዛ ከ200 ሺሕ ብር አይበልጥም፡፡ ሜቴክ ግን 600 ሺሕ ብር ነው የሚሸጥልን፤›› ብለዋል፡፡
‹‹እንቢ ብለን እንኳን እንዳንታገል አመራሮች ያሸማቅቁናል፤›› በማለት ተናግረዋል፡፡ ቋሚ ኮሚቴው ከሌሎች አካላት ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለብቻ በሌላ መድረክ እንደሚያይ አስታውቆ አሁንም የኪራይ ሰብሳቢነት ችግር በኮርፖሬሽኑ ውስጥ መኖሩን በመጥቀስ ፋብሪካዎች ኦዲት እንዲደረጉ አዟል፡፡
ምንጭ፡ ሪፖርተር ጋዜጣ
በአዲስ አበባ ሰሚት አካባቢ ባለ 5 ፎቅ ህንፃ ተደርምሶ በንብረት ላይ ጉዳት አደረሰ
በአዲስ አበባ ከተማ ሚያዚያ 19 ቀን 2008 ዓ.ም. ባለ 5 ፎቅ ህንፃ ተደርምሶ በንብረት ላይ ጉዳት አደረሰ።

የአዲስ አበባ የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ባለስልጣን የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ንጋቱ ማሞ እንደገለጹት፥ የህንፃ መደርመስ አደጋው ዛሬ ማለዳ 12 ሰአት ላይ ነው በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 ሰሚት አካባቢ የተከሰተው።
ባለ 5 ፎቅ ህንፃው ሙሉ በሙሉ ያልተጠናቀቀ ቢሆንም ከታችኛው ወለል ላይ ሁለት ባንኮች አገልግሎት መስጠት ጀምረው እንደነበርም አቶ ንጋቱ ጠቁመዋል።
የመደርመስ አደጋው በስራ ሰዓት ቢደርስ በሰው ላይ ከባድ አደጋ ሊያደርስ ይችል እንደነበርም ነው ባለሙያው ያነሱት።
የባንኮቹ የጥበቃ ሰራተኞች ህንፃው ከመድርመሱ በፊት ከባድ ድምፅ በመስማታቸው ከአደጋው ሊያመልጡ ችለዋል።
ምንጭ፡-ፋናቢሲ
የአዋሽ ወንዝ ሊሞላ ስለሚችል የአካባቢው ወረዳዎች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ማሳሰቢያ ተሰጠ
በዚህ ሳምንት ውስጥ እንደሚጥል በተተነበየ ከመደበኛ በላይ የሆነ ዝናብ አማካይነት የአዋሽ ወንዝ ሞልቶ ጉዳት ሊያደርስ እንደሚችል፣ ብሔራዊ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አሳሰበ፡፡

ኮሚሽኑ ለሪፖርተር የላከው የቅድመ ማስጠንቀቂያ መልዕክት እንደሚገልጸው፣ ከሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ በስተቀር በአብዛኞቹ የአገሪቱ አካባቢዎች መደበኛና ከመደበኛ በላይ የሆነ ዝናብ እስከ ሚያዝያ 22 ቀን 2008 ዓ.ም. ሊጥል እንደሚችል፣ ከብሔራዊ የሚቲዮሮሎጂ ኤጀንሲ መረጃ ማግኘቱን ይጠቁማል፡፡
ከአዋሽ ተፋሰስ ባለሥልጣን በተገኘው ሌላ መረጃ መሠረትም የአዋሽ ወንዝ በቀጣዩ ሳምንት ሊሞላ ስለሚችል፣ ከዚህ ጋር ተያይዞ ጐርፍ በተፋሰሱ ባሉ አካባቢዎች ሊከሰት እንደሚችል መረጃዎች የሚያመለክቱ መሆኑን፣ በኮሚሽኑ የቅድሚያ ማስጠንቀቂያና ምላሽ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሙሉነህ ወልደ ማርያም ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም በበቾ ወረዳ፣ በዓለም ጤና ወረዳ (ሁምቡሌና ጐሮ አካባቢዎች)፣ በስሬ ወረዳ፣ በወንጂ በተለይም በቆቃ ግድብ አካባቢ የሚኖሩ፣ በመርቲ ወረዳ፣ በመተሃራ (ፈንታሌ)፣ በአሚባራ፣ በዱለቻ፣ በገላአሎ፣ በገዋኔ፣ በተንዳሆ ግድብ አካባቢ የሚኖሩ፣ በአሳይታና በአፋምቦ ወረዳዎች የሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጐርፍ ሊከሰትባቸው ስለሚችል ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ኮሚሽኑ አሳስቧል፡፡
የተጠቀሱት አካባቢዎች የመስተዳደር አካላትም በአካባቢዎቹ የሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ከወንዙ በማራቅ ከጉዳት መጠበቅ እንዲችሉ የበኩላቸውን ጥረት እንዲያደርጉም አሳስቧል፡፡
ባለፈው መጋቢት ወር መጨረሻ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል በተከሰተው የጐርፍ አደጋ ከ20 ሰዎች በላይ መሞታቸው ይታወሳል፡፡
ብሔራዊ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን በ2008 ዓ.ም. የመጀመሪያ ወራት እንደ አዲስ የተቋቋመና በሰው ሠራሽና የተፈጥሮ አደጋዎችን የመከላከልና የቅድመ ማስጠንቀቅ ሥራ የማከናወን ኃላፊነት የተጣለበት ተቋም ሲሆን፣ ተጠሪነቱም በቀጥታ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ነው፡፡
ምንጭ፡- ሪፖርተር ጋዜጣ