Tag Archives: Bewketu Seyoum

ባለ መሰንቆውና ባለ ወለሎው

በእውቀቱ ሥዩም

Bewketu

“ ሮድ ደሴት” በተባለ አገር ውስጥ እንደ እንደምኖር የነገርኩት ጓደኛየ“ እና ባሣ አጥማጅነት ነው የምትተዳደረው?”ብሎኛል፡፡ ሮድ ደሴት አበሻ እጥረት ክፉኛ ከሚያጠቃቸው ክልሎች አንዱ ነው ፡፡ አሁን ምድሩም ሰማዩም ሰውም ነጭ ነው፡፡

ያገር ሰው በጣም ይናፍቀኛል፡፡ የሆነ ያበሻ ዓይነ ውሃ ያለው አልፎ ሒያጅ መንገድ ላይ ካየሁ ከሚበር አውቶብስ ላይ እንደ ጅምስ ቦንድ ተወርውሬ ወርጀ ስልኩን በቃሌ እቀበለዋለሁ፡፡ ከሁለት ሱዳናውያን ጋር የተዋወቅሁት በዚህ አጋጣሚ ነው፡፡

Bewketu Seyoum book 3

ያበሻ ናፍቆቴንአናቴ ላይ ሲወጣ ወደአበሻ- ጠገብ ክልሎች እቀላውጣለሁ ፡፡ ባቡሬን ጭኘ መጭ ወደ ውሻንግቶን ዲሲ! ዲሲ የውሃና የመብራት እጥረት የሌለበት አዲስአበባ ማለት ነው፡፡
ባለፈው ሳምንት ሚኒሶታ ወረድሁ፡፡ ከተማይቱ በበረዶ ተዝረክርካ የሰነፍ ቡሃቃ መስላለች፡፡ የተፈጥሮን ጨካኝነት፤ የቶማስ አልቫ ኤዲሰንን ያለም ቤዛነት ለማረጋገጥ የሚፈልግ ሚኒሶታ ይሂድ፡፡ ወይ አዲስ አበባ! አዱ ገነት፡፡ እብድ የያዘሽ ውበት፡፡ ሰው እንዴት ጥሎሽ ይመጣል? ሰው እንዴት ከገነት ያመልጣ?

ከመኪና ማቆምያው ተሥቼ አዳራሹ ድረስ እስክገባ ድረስ የተቀበልኩት መከራ ራሱን የቻለ ሰማእትነት ሆኖ ለትውልድ ይዘከርልኝ ፡፡ ብዙ ብርድ አጋጥሞኛል እንዲህ አራት ጃኬትና ሁለት ሱሪ ገልቦ፤ አስገድዶ የሚሠር ብርድ ደርሶብኝ አያውቅም፡፡ እድል ፈንታየ ብሎ ብሎ ደም እንደ ብይ በሚጠጥርበት፤ ያፍንጫ ጸጉር እንደጃርት ወስፌ በሚቆምበት አገር ይጣለኝ?
ደሞ እቺም ኑሮ ሆና “በርገርህን እየገመጥክ ትደነፋለህ አይደል?” የሚል ብሽቅ መልክት ይልኩልኛል። ባለመልክቱ! እስቲ ያዲሳባን የጧት ጸሐይ፤ በበርገር ለውጠኝ!!

ሳይደግስ አይጣላም በህይወቴ ባካል ላገኛቸው ከምፈልጋቸው ሰዎችአንዱ የሆነውን ጋዜጠኛ ሰሎሞን ደሬሳን አገኘሁት፡፡ ሰሎሞን ፈላስፋ ነው፡፡የመጀመርያው የሥእል ሓያሲም ነው፡፡ በኦሮምኛ ፤አማርኛ እንግሊዝኛና ፈረንሳይኛ የሚራቀቅ ሊቅ ነው፡፡ ወዳጅ ባታደርገው እንኳ ለፍልምያ የምትመርጠው ሰው ነው፡፡ እንድታስብ የሚገፋፋህ ፤አርፈህ እንድትቀመጥ የማያደርግህ ሰው ማግኘት መታደል አይደል? መጣጥፎቹ ተሰብስበው በመጽሐፍ አለመውጣታቸው ያስቆጫል፡፡ ”ልጅነት ” የምትል በዘልማዳዊው የአማርኛ ስነግጥም ላይ የሸፈተች የግጥም መደብል ሲያሳትም እንደ መናፍቅ ተቆጥሯል፡፡ የትውፊት አስጠባቂው አቤ ጉበኛ በሰሎሞንን ግጥምና በዳኛቸው ወርቁ ልቦለድ ላይ ለማላገጥ “ጎብላንድ አጭበርባሪው ጦጣ”የሚል መጽሐፍ እስከማሳተም ሂዷል፡፡ የአቤ ጎብላንድ ዛሬ በታሪክ ቅርጫት ውስጥ ተጥላለች፡፡ የሰሎሞንና የዳኛቸው መጽሐፎች ግን ገቢያ ላይ በጣም ይፈለጋሉ፡፡ ለምሳሌ ስለባህል ግብዝነት በተነሣ ቁጥር ይችን የሰውየውን ግጥም ማን ይረሣታል?
በኢትዮጵያ ባልጎ መታየቱ
ሳይሆን ቂንጥር ማስቆረጡ
ህጻኗን ልጅ እንደ ቆዳ መስፋቱ
መባለጉ
ኣፉን ሞልቶ” ቂንጥር “ ብሎ መጥራቱ
የሆነ ጊዜ ላይ፤ ስብሐት ገብረእግዚኣብሄር ስለወዳጁ ስለሰሎሞን ”ከሸክስፒርና ከዳንቴ ቀጥሎ ትልቁ ባለቅኔ ሰሎሞን ነው” ብሎ ጻፈ፡፡ ላዲስ ነገር ጋዜጣ የሚሆን ቃለመጠይቅ ሳደርግለት“ሰሎሞንን በዓለም ሦስተኛ ገጣሚ አድርገህ ጽፈሐል፤ አግባብ ነው?”አልኩት፡፡
“እንደዛ ብያለሁ?”
“ኣዎ”
ስብሐት ትንሽ አሰበና መለሰ፤ “ እንዲህ ያልኩት በጣም በናፈቀኝ ሠአት መሆን አለበት“
ከሥነጽሁፉ ምሽት በበኋላ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማኅበር ”ሬድ ሲ” ሬስቶራንት ራት ጋበዙን፡፡ እንደምንም እየተንፏቀቅሁ ከሰሎሞን አጠገብ ያለውን ቦታ ያዝኩ፡፡ ይችን ብርቅ አጋጣሚ ተጠቅሜ ከልጅነት እስከ ሽበት ያሳለፈውን ገድሉን አናዝዘዋለሁ ብየ አሰብኩ፡፡አልቀናኝም፡፡ ከሰለሞን ጋር ጨዋታ እንደ ጀመርሁ ከኋላየ ባለጌ ወንበር ላይ የተቀመጠ ተስተናጋጅ፤ ባንገት ጥምጥሜ ጎትቶ ካዞረኝ በኋላ” ቢራውን ትተህ ለምን ጠንከር ያለ ነገር አትወስድም?”በሚል ጥያቄ ጠመደኝ፡፡ ቢራውን ትቸ ጠንከር ያለ ነገር የማልወስድበትን ሰባት ምክንያት ስዘረዝር ራቱ ተገባድዶ ከፍ አለ፡፡

ከእራት በኋላ አዝማሪው ወደ መድረክ ወጣና ማሲንቆውን ማስተከዝ ጀመረ ፡፡ በቤቱ ያለው ሰው በማሲንቆ ዜማ ታጅቦ ወደ ግል ወሬው ተጠመደ፡፡ “ኣንድ ኮርኔስ እዚህ ጋ ያዘዘ ማን ነው?” የሚለው ያስተናጋጇ ድምጽ ካዝማሪው እንጉርጉሮ በላይ ጠብድሎ ይሰማኛል፡፡ ሰሎሞን ከወንበሩ ተነሥቶ በዝግታ እየተራመደ ወደ መድረኩ ከወጣ በኋላ አዝማሪውን ሸልሞ አጠገቡ ቁጭ አለ፡፡ ዓይኑን ለበስ አድርጎ እልምም !! በማሲንቆው ተሳፍሮ የት ደርሶ ይሆን? ወለጋ-አዲስአበባ – ደጃች ውቤ ሠፈር- ፤ የከተማ መኮንን ክራር – ምኒልክና ጊዮርጊስ በፈረቃ ከሚጋልቡት የአራዳ ፈረስ፡፡

ልጅነት በተባለቸው መድብሉ ስለአንድ የውቤ በረሃ ጀግና በጻፈው መወድስ ውስጥ እኒህ መስመሮች ተካትተዋል፡፡
”ደኑ ርቆት፤
መንገዱ ጠፍቶት
ጓዱ ረስቶት
በጨለማ ቤቱን ስቶት“
ዛሬ እኒህ መስመሮች በግዞትና በስደት ሰጥመው የቀሩ ድንቅ ኢትዮጵያውያንን ሁኔታ የሚገልጹ አድርጌ ብተረጉማቸው ማን ይፈርድብኛል?

( ወዳጄ ገጣሚ ዮናስ አንገሶም ኪዳኔ የሰሎሞንን መጽሐፎች ስለሰደድክልኝ ምስጋናየ ይድረስህ፡፡)

%d bloggers like this: