Tag Archives: EOTCMK

ቅዱስ ሲኖዶስ: ፓትርያርኩ ሕግ አክብረውና መዋቅር ጠብቀው እንዲሠሩ አስጠነቀቃቸው፤ በወቅታዊ ሰላም ጉዳዮች መግለጫ አውጥቷል

• በማኅበረ ቅዱሳን ላይ ያስተላለፏቸው መመሪያዎችና የጠሯቸው ስብሰባዎች ሕገ ወጥ ተብለዋል
• ቋሚ ሲኖዶስ፥ የስምዐ ጽድቅን የፀረ ተሐድሶ ጽሑፍ ጨምሮ የተደረጉ መጻጻፎችን ይመረምራል
• የፓትርያርኩ ጉዞዎች፥ ስፖንሰር ተገኘ በሚል ሳይኾን በቋሚ ሲኖዶሱ ማስወሰን ይኖርባቸዋ

EOTC Holy Synod

ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ፣ የቤተ ክርስቲያንን አስተዳደራዊ መዋቅር ጠብቀው በሕገ ቤተ ክርስቲያን መሠረት ተግባራቸውን እንዲያከናውኑና ሓላፊነታቸውን እንዲወጡ በቅዱስ ሲኖዶስ ማስጠንቀቂያ ተሰጣቸው፡፡
ቅዱስ ሲኖዶሱ፣ ባለፈው ሳምንት ዓርብ የካቲት 27 ቀን 2008 ዓ.ም. ከቀትር በኋላ ባካሔደው ድንገተኛ ልዩ ስብሰባ፣ በማኅበረ ቅዱሳን ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ የፀረ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ጽሑፎች ላይ ቀርበዋል ለተባሉ አቤቱታዎች የነበራቸውን አያያዝ፣ የወሰዷቸውን አቋሞችና የሰጧቸውን ምላሾች ገምግሟል፡፡

ፓትርያርኩ አቤቱታዎቹን ለመመልከት በሚል በራሳቸው የጠሯቸው የኮሌጆችና የጠቅላይ ጽ/ቤቱ መምሪያዎች ሓላፊዎች ስብሰባዎች፤ ማእከላዊ አሠራርን ያልጠበቁና አድሏዊ እንደነበሩ ጉባኤው ተችቷል፡፡ ከዚኽም ጋር በተያያዘ ፓትርያርኩ፣ ከልዩ ጽ/ቤታቸው በተጻፉ ደብዳቤዎች በማኅበረ ቅዱሳን ላይ ያስተላለፏቸው የክሥና የቅስቀሳ መመሪያዎች የቅዱስ ሲኖዶስን የምልዓተ ጉባኤ ውሳኔ መንፈስ የሚፃረሩና ሕገ ወጥ መኾናቸውን ያረጋገጠ ሲኾን በስብሰባዎቹ ወጥተዋል የተባሉ የአቋም መግለጫዎችም ተቀባይነት እንደማይኖራቸው ተገልጧል፡፡

ፓትርያርኩ ዛሬ ለተጀመረው ዐቢይ ጾም ባለፈው ሳምንት ዓርብ መግለጫ በሰጡበት አጋጣሚ፣ ቋሚ ሲኖዶሱ በብፁዕ ዋና ጸሐፊው አማካይነት በጠራው በዚኹ ድንገተኛ ልዩ ስብሰባ፣ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱን በኃይለ ቃል ለማሸማቀቅ ሞክረዋል፤ ማኅበሩንም በተመለሱ ጥያቄዎችና በአሉባልታዎች ወንጅለዋል፡፡ “የማኅበሩ አባላት ናችኹ፤ ሒዱ ስላላችኹ ነው የመጣችኹት” በማለት የተናገሩት ፓትርያርኩ፣ ማኅበሩንም “ሀብታሞች ኾነዋል፤ ከመንግሥትም ገንዘብ ይሰበስባሉ፤ መንግሥት ይረዳቸዋል፤” እስከ ማለት ደርሰዋል፡፡
ተንኮል የተሸረቡባቸውንና በክፋት የተሞሉ መረጃዎችን ሳያጣሩና ሳይመዝኑ እንደተነገራቸው የሚያስተጋቡት ፓትርያርኩ፣ እኒኽን ኃይለ ቃላት የተናገሩበት የረፋድ ወኔ ግን አብሯቸው አልዘለቀም፡፡ ስብሰባው ከቀትር በኋላ ሲጀመር አንሥቶ ከፍተኛ መደናገጥ ታይቶባቸዋል፡፡ ማእከላዊ አሠራርን ሳይጠብቁ የፈጸሟቸውን መተላለፎች፣ ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ በዝርዝር ለጉባኤው ያሰሙ ሲኾን በማኅበሩ ላይ ለሰነዘሯቸው ክሦችም ማስረጃቸውን እንዲያቀርቡ ጠይቀዋቸዋል፤ የማኅበሩ ዋነኛ የድጋፍ ምንጭ የአባላቱ አስተዋፅኦ መኾኑን የጠቀሱት ብፁዕነታቸው፣ በሒሳብ አሠራሩም ጠቅላይ ጽ/ቤቱ ከማኅበሩ ብዙ የሚማረው እንዳለም አልሸሸጉም፡፡

ለመዋቅራዊ መተላለፋቸውም ኾነ ከማኅበሩ አንጻር ለቀረቡላቸው የተጨባጭነት ጥያቄዎች በቂ ምላሽ ያልሰጡት ፓትርያርኩ፣ ማእከላዊ አሠራርን ባለመጠበቅ በፈጸሟቸው ተግባራት በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ “አዋረዱን፤ አፈርንብዎ” እስከመባል የደረሰ ቅሬታ ቀርቦባቸዋል፤ በከፍተኛ ደረጃም ተገሥጸዋል፡፡
ፓትርያርኩ ከመዓርገ ክብራቸው አኳያ ከመሰል የደብዳቤ መጻጻፎች እንዲታቀቡ ጉባኤው በጥብቅ አስጠንቅቋቸዋል፤ የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ አደጋ በኮሌጆች የሚገኝበትን አስከፊነት አስመልክቶ የስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ በዳሰሳ ጥናት ላይ ተመሥርቶ ያወጣውን ጽሑፍ ተከትሎ ፓትርያርኩ የሰጧቸው መመሪያዎችና ከማኅበሩ ጋር የተመላለሷቸው ደብዳቤዎችም በቋሚ ሲኖዶሱ እንዲመረመሩ በጉባኤው ተወስኗል፡፡ በይቀጥላልም ጉባኤው፣ ፓትርያርኩ በመሰል ጉዳዮች አስፈጻሚ የአስተዳደር አካላትን በቀጥታ መሰብሰባቸው ስሕተት በመኾኑ፣ ከብፁዕ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና ከብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ ጋር እየተነጋገሩና በቋሚ ሲኖዶስ እየመከሩ ሕጉን አክብረውና መዋቅሩን ጠብቀው ከአድልዎ የጸዳ አመራር መስጠት እንደሚኖርባቸውም በጥብቅ አሳስቧቸዋል፡፡

ግለ ታሪካቸውን ከማበላሸት አልፎ በክፉ ምክሮችና በሕገ ወጥ ደብዳቤዎች ቤተ ክርስቲያንን እያሳጣና እያስነቀፈ የሚገኘው የልዩ ጽ/ቤታቸው አሠራር ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱን በእጅጉ አሳስቧል፤ የልዩ ጸሐፊው ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃና የክፋት ተባባሪዎቹ ጉዳይም አስቸኳይ እልባት እንደሚያስፈልገው ከድንገተኛ ልዩ ስብሰባው በተጓዳኝ በስፋት የተመከረበትና አቋም የተያዘበት ወቅታዊ ነጥብ ኾኗል፡፡

Pat. Abune mathias-and-nebured Elias
የፓትርያርኩ የሀገር ውስጥም ኾነ የውጭ ጉዞ፣ ቋሚ ሲኖዶስ አስቀድሞ እያወቀው በዕቅድ መከናወን ያለበት ቢኾንም “የራሳችንን ወጪ ሸፍነን ቅዱስነታቸውን እናጅባለን” በሚሉ አማሳኝ ግብረ በላዎች ጭምር የቤተ ክርስቲያን ገንዘብ ያለዕቅድ እየወጣ የሚባክንበት፤ ፓትርያርኩ እንደ ርእሰ መንበር ሐዋርያዊ ተልእኳቸውንና አባታዊ ሓላፊነታቸውን ቤተ ክርስቲያኒቱን ለመወከል በሚያበቃ መልኩ የሚወጡበት ከመኾን ይልቅ “ስፖንሰር ተገኘ” በሚል ብቻ ከፍተኛ ስሕተት(የፕሮቶኮልም) የሚፈጸምበትና ክፋት የሚመከርበት እየኾነ እንደመጣም በጉባኤው ታይቷል፡፡

በመኾኑም ማንኛውም የፓትርያርኩ ጉዞዎችና የሚመደቡ ልኡካን፣ በሕገ ቤተ ክርስቲያኑ መሠረት ለቋሚ ሲኖዶስ ቀርቦ አስፈላጊነቱ ታምኖበት ሲወሰን የቤተ ክርስቲያኒቱን ጥንተ ክብርና ሉዓላዊነት እንዲኹም የመንበረ ፕትርክናውን ፕሮቶኮል በጠበቀ ደረጃ እንዲፈጸም ጉባኤው አሳስቧል፡፡
ቅዱስ ሲኖዱሱ በነበረው ድንገተኛ በቅርቡ ከዚህ ዓለም በተለዩት የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል ምትክ የሶማሌ/ ጅግጅጋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ያሬድ ደርበው እንዲሰሩ የተመደቡ ሲሆን፤ ብፁዕ አቡነ ያሬድም ከጅግጅጋው ሀገረ ስብከት በተጨማሪ የአርሲ ሀገር ስብከት አገልግሎትን ደርበው እንደሚሰሩ ተጠቁሟል፡፡

ስለ ተቃጠሉ አብያተ ክርስቲያናት ከጠቅላይ ቤተ ክህነትና ከሚመለከታቸው አህጉረ ስብከት በሚመደቡ ልኡካን ተጨማሪ ማጣራት እንዲካሔድና አስፈላጊው የመልሶ ማቋቋም ድጋፍ እንዲደረግ የወሰነው ቅዱስ ሲኖዶሱ፣ በአገራችን ወቅታዊ የሰላም ጉዳዮች ላይም የመከረ ሲኾን በየካቲት 29 ቀን 2008 ዓ.ም. በነበረው ዕለትም በድንገተኛ ልዩ ስብሰባው ቃለ ጉባኤዎች ላይ በመፈራረም ስለሰላምና ስለወቅታዊ ሁኔታ መግለጫ ሰጥቷል፡፡
ሙሉ መግለጫው ቀጥሎ ይመልከቱ፡-

synod-declaration-yek2008a

ምንጭ፡- ሐራ ዘተዋሕዶ

ማኅበረ ቅዱሳን ለፓትርያርኩ መምሪያ ምላሽ ሰጠ፤ የስምዐ ጽድቅ ጽሑፍ የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔ የማሳወቅ ግዴታችን አካል ነው፤ ደብዳቤውም መድረክ ስለተነፈገንና ፍትሕ ስለተጓደለብን ነው

• የጋዜጣው ጽሑፎች፣ «መንፈሳዊ ኮሌጆቹ በአጠቃላይ የመናፍቃን መፈልፈያ ናቸው» አይሉም
• በጋዜጣው አጻጻፍ አንዳንድ የቃላት አጠቃቀሞች ላይ ቅሬታ ካለ ለመወያየት ዝግጁዎች ነን
• ጉዳዮቹን እንድናስረዳና የተፈጠረውንም ችግር ለመረዳት የውይይት መድረክ ይዘጋጅልን
• በተለያየ መንገድ እንደጠየቅነው፣ በአካል የመወያያ ዕድል ማጣታችን በእጅጉ ያሳዝነናል
• ለሚታረም ነገር እርምት መውሰድና ስናጠፋም ይቅርታ መጠየቅ የአገልግሎታችን መርሕ ነው
* * *
• ሰዎች እንደመኾናችንና ልንሳሳት ስለምንችል፣ በማንኛውም ደረጃ ተወያይተን የሚታረም ነገር ካለ አስፈላጊውን እርምት መውሰድ እና በትክክል ጥፋት እንዳጠፋንም ስንረዳ ይቅርታ መጠየቅ አንዱና ዋነኛው የአገልግሎታችን መርሕ ነው፡

• በሀገራችን የተከሠቱትን ማኅበራዊ ችግሮች ለመፍታት ኹሉም አካል በየዘርፉ በሚረባረብበት በዚኽ ወቅት፣ ትልቅ ሓላፊነት ያለባት የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን አባትና ልጆች እንዲህ ዓይነት ደብዳቤዎችን በመጻጻፍ መጠመዳችን በእጅጉ   አሳዝኖናል፡፡

• ሕግ አውጥቶ፣ ሥርዓት ሠርቶ የሰጠን የቤተ ክርስቲያናችን የመጨረሻ ውሳኔ ሰጪ አካል የኾነው ቅዱስ ሲኖዶስ፣ በማኅበሩ አገልግሎቶች ላይ አኹንም እየተፈጠሩ ያሉት ዕንቅፋቶች እንዲታዩልንና አስፈላጊው እርምት እንዲደረግልን በታላቅ ትሕትናና አክብሮት እንጠይቃለን፡፡ (የደብዳቤውን ሙሉ ይዘት ከዚኽ በታች ይመልከቱ)

EOTC_MK 1EOTC_MK 2EOTC_MK 3EOTC_MK 4

 

ምንጭ፡- ሐራ ዘተዋሕዶ ፣ https://haratewahido.wordpress.com/2016/02/29

 

ሰበር ዜና ፡- ፈቃድ የሌላቸው የኢ.ቢ.ኤስ ፕሮግራሞች በቤተ ክርስቲያን ስም እንዳይጠቀሙ ተወሰነ፤ የ24 ሰዓት የቴሌቭዥን አገልግሎት ይጀመራል

• የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ፈቃድ እና ዕውቅና የሌላቸው የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ አቀንቃኞቹ፣ “ታዖሎጎስ” እና “ቃለ ዐዋዲ” በምልአተ ጉባኤው ውሳኔ በስም ተለይተው ተጠቅሰዋል
• በምልአተ ጉባኤው ውሳኔ መሠረት፣ በቋሚ ሲኖዶስ የተቋቋመው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን
የብዙኃን መገናኛ ቦርድ ሥራውን ለመጀመር እየተንቀሳቀሰ ነው
• በፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ ላይ የቀረቡ ማስረጃዎች የበለጠ ተጠናክረው አጀንዳው በልዩ የምልአተ ጉባኤ ስብሰባ እንዲታይ ተወስኗል
EOTC Synod 2008
የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ፣ ከማእከል የተሰጠ ሕጋዊ ፈቃድ ሳይኖራቸው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስም፣ በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ሰርቪስ(EBS) የቴሌቭዥን ጣቢያ፣ “ሃይማኖታዊ ትምህርት” የሚያስተላልፉ ፕሮግራሞች፣ የቤተ ክርስቲያንን ስም እንዳይጠቀሙ ወሰነ፡፡

ምልአተ ጉባኤው በዛሬ፣ ጥቅምት 17 ቀን 2008 ዓ.ም. ስድስተኛ ቀን የቀትር በፊት ውሎው ያሳለፈው ውሳኔ ተፈጻሚ እንዲኾን፤ የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር እና የኢ.ቢ.ኤስ ቴሌቭዥን በደብዳቤ እንዲያውቁት ይደረግ ዘንድ ትእዛዝ ሰጥቷል፡፡
በውሳኔው÷ የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ አቀንቃኞቹ፣ “ታዖሎጎስ” እና “ቃለ ዐዋዲ” በስም የተጠቀሱ ሲኾን በፕሮግራሞቹ አዘጋጅነት የሚታወቁት በተለይ የ“ታዖሎጎስ” ግንባር ቀደም ምንደኞች፣ ፕሮግራማቸው“ራሱን የቻለ የሚዲያ ተቋም” እንጂ ከቅዱስ ሲኖዶሱ ይኹን ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ጋር ተቋማዊ ግንኙነት እንደሌላቸው በይፋ በሰጡት መግለጫ ማረጋገጣቸው ይታወሳል፡፡

ምልአተ ጉባኤው ከዚኹ ጋር በማያያዝ፤ በሊቃውንት ጉባኤ ሳይመረመሩ እና በማእከል ሳይፈቀዱ በግለሰቦች እየተዘጋጁ የቤተ ክርስቲያንን ስም ይዘው ስለሚወጡ የስብከት፣ የመዝሙር እና የመጻሕፍት ኅትመቶች እንዲኹም የአዳራሽ ጉባኤያት እና ስብሰባዎች ከተወያየ በኋላ ቀደም ሲል ያሳለፋቸውን ውሳኔዎች በማጽናት ተመሳሳይ ትእዛዝ መስጠቱ ታውቋል፡፡

ቅዱስ ሲኖዶሱ፣ “ስብከተ ወንጌል እና ሚዲያን በተመለከተ” በተራ ቁጥር ሦስት በያዘው አጀንዳ፤ ቤተ ክርስቲያን ማእከላዊነቱን ጠብቆ የራስዋን ድምፅ ለዓለም የምታሰማበት እና ስብከተ ወንጌልን የምታስፋፋበት የ24 ሰዓት የቴሌቭዥን አገልግሎት እንዲጀመርም ወስኗል፡፡

ለቤተ ክርስቲያንየቴሌቭዥን አገልግሎት ስርጭት የሚያስፈልገውና በስብከተ ወንጌል እና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ አስተባባሪነት የተጠናው በጀት ባለፈው ዓመት ግንቦት በምልአተ ጉባኤው የጸደቀ ሲኾን በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ የመክፈቻ ንግግር እንደተመለከተው፤ በዚኽ ዓመት በጀቱ በአፋጣኝ ሥራ ላይ እንዲውል የቀረበውን ጥያቄ በመቀበል የፋይናንስ ምንጮቹን ወስኖ ለነገ የሚያቀርብ ሦስት አባላት ያሉት የብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት(ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ፣ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል እና ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ) ኮሚቴ በምልአተ ጉባኤ ተሠይሟል፡፡

ምልአተ ጉባኤው ባለፈው ዓመት ግንቦት ባጸደቀው የሚዲያዎች (የሬዲዮ እና የቴሌቭዥን አገልግሎት) ሥርጭት ደንብ መሠረት፤ በስብከተ ወንጌል እና ሐዋርያዊ ተልእኮ የበላይ ሓላፊ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ የሚመራ ዘጠኝ አባላት ያሉት የብዙኃን መገናኛ የሥራ አመራር ቦርድ የተቋቋመ ሲኾን ተግባሩን ለመጀመር እየተንቀሳቀሰ እንዳለ ለ34ኛው የመንበረ ፓትርያርክ የሰበካ አስተዳደር አጠቃላይ ጉባኤ የቀረበው የጠቅላይ ጽ/ቤቱ ሪፖርት ያስረዳል፡፡

በሪፖርቱ እንደተጠቀሰው፤ ቤተ ክርስቲያን ስብከተ ወንጌልን ከዐውደ ምሕረት ባሻገር በአጽናፈ ዓለም ለማስፋፋት እና ለማጠናከር ስለሚያስፈልጓት ሚዲያዎች፣ በመምሪያው አስተባባሪነት በብዙኃን መገናኛ ባለሞያዎች የተካሔደውን ጥናት መሠረት አድርጎ መተዳደርያ ደንብ፣ ኤዲቶሪያል ፖሊሲ እና የቴሌቪዥን ሥርጭት መመሪያ/ማኑዋል ተዘጋጅቷል፡፡

በተያያዘ ዜና፣“የቤተ ክርስቲያኗን ወቅታዊ ኹኔታ በጥልቀት ማየት” በሚል ዐቢይ አጀንዳ ሥር በፊደል ተራ ቁጥር 4/መ፣ “የተሐድሶ እንቅስቃሴን በተመለከተ”፤ የተዘጋጀው ሰነድ በተጨማሪ ማስረጃዎች ተስፋፍቶ እና ተጠናክሮ ራሱን በቻለ ልዩ የምልአተ ጉባኤ ስብሰባ እንዲታይ ቅዱስ ሲኖዶሱ ወስኗል፡፡

የስብሰባው ምንጮች እንደተናገሩት፤ ከፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ግንባር ቀደም መሪዎች በሚሰጣቸው ተልእኮ እና ድጋፍ በቤተ ክርስቲያናችን የአስተዳደር እና የአገልግሎት መዋቅር ውስጥ በመስረግ የኑፋቄውን አስተሳሰብ እና ድርጊት የሚያራምዱ የ66 አካላት እና ግለሰቦች የሰነድ፣ የምስል እና የድምፅ ማስረጃዎች ከኃምሳ ገጾች ማብራሪያ ጋር ተደግፎ ተዘጋጅቷል፡፡

ከቤተ ክርስቲያናችን ዐውደ ምሕረት እና የአስተዳደር መዋቅር ባሻገር፣ የኑፋቄው ግንባር ቀደም መሪዎች እና ምንደኞቻቸው በከፍተኛ ትምህርት ተቋሞቻችን(መንፈሳዊ ኮሌጆች እና የካህናት ማሠልጠኛዎች) ውስጥ በተለያየ ሽፋን የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ከፍተኛ ትኩረት እንዲደረግበት ምልአተ ጉባኤው ኮሚቴውን አሳስቧል፡፡

በመካከለኛው ምሥራቅ አህጉረ ስብከት፣ ብፁዕ ሊቀ ጳጳሱ ሳያውቁት ከሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን ውጭ በተቋቋመው የኑፋቄው መናኸርያ “ዱባይ ሚካኤል” እና “ቤርያ ቲኦሎጂካል ኢንስቲትዩት” በሚል መሪዎቹ የመሠረቱት ሕገ ወጥ ተቋም በከፍተኛ ደረጃ ያነጋገረ ሲኾን በምልአተ ጉባኤው ጥናት ተካቶ እንዲቀርብ መወሰኑ ተጠቁሟል፡፡

በተመሳሳይ ኹኔታ ጉባኤውን ያነጋገረው፣ በመንበረ ፓትርያርኩ የውጭ ጉዳይ መምሪያ በሓላፊነት የተቀመጡት መልአከ ሰላም አባ ቃለ ጽድቅ የተባሉ ግለሰብ፣ ከፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቁ አንጻር ያላቸው ሃይማኖታዊ አቋም እና ሥነ ምግባራዊ ኹኔታ ነበር፡፡ የግለሰቡ አመጣጥ እና አመዳደብም ከፓትርያርኩ ልዩ ጸሐፊ ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ ጋር ባላቸው የጥቅም ግንኙነት እንደኾነ መጠቆሙ ደግሞ ችግሩ ከግለሰቡም በላይ ልዩ ጽ/ቤቱ እንደ መዋቅር ያለበትን አስከፊ ደረጃ እና አሳሳቢነቱን ለምልአተ ጉባኤው አለብቧል፡፡
ከዚኽ ውስብስብነቱና ከሚያስፈልገው ጠንካራ ቅንጅት አኳያ፤ አጀንዳው ራሱን በቻለ አስቸኳይ እና ልዩ የምልአተ ጉባኤ ስብሰባ እንዲታይ ቅዱስ ሲኖዶሱ ሲወስን ጊዜው በመጪው ወርኃ ጥር ላይ ሊኾን እንደሚችል ከወዲኹ የተጠቆመ ቢኾንም በኮሚቴው ውጤታማ እንቅስቃሴ ላይ እንደሚመሠረት ነው፣ በብዙኃን የምልአተ ጉባኤው አባላት ዘንድ መግባባት የተደረሰበት፡፡

በሕገ ቤተ ክርስቲያን የቅዱስ ሲኖዶስ የስብሰባ ሥነ ሥርዐት መሠረት፤ አስቸኳይ እና ድንገተኛ ጉዳይ ሲያጋጥም ቅዱስ ፓትርያርኩ ወይም ቋሚ ሲኖዶሱ ወይም የቅዱስ ሲኖዶሱ ዋና ጸሐፊ በሚያደርጉት ጥሪ የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ሊካሔድ ይችላል፤ ከዐራቱ እጅ ሦስቱ እጅ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት በተገኙበት ስብሰባም ምልዓተ ጉባኤ ይኾናል፡፡ ቅዱስ ሲኖዶሱ በማናቸውም ስብሰባ ላይ ውሳኔዎችን ሲያሳልፍም፣ ሃይማኖትንና ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን የሚመለከት ከኾነ በሙሉ ድምፅ ያልፋል፤ በሃይማኖት እና በቀኖና ጉዳይም ድምፀ ተዓቅቦ ማድረግ አይቻልም፡፡

ምንጭ፡- ሐራ ዘተዋሕዶ