ዶ/ር ወልደመስቀል ኮስትሬ አረፉ
(አዲስ ሚዲያ) ለረጀም ጊዜ የኢትዮጵያ ረጅም ርቀት ሩጫ ውድድር አሰልጣኝ የነበሩት ዶ/ር ወልደመስቀል ኮስትሬ በህክምና ሲረዱ ቆይተው በተወለዱ በ69 ዓመታቸው ትናንት ሰኞ ግንቦት 8 ቀን 2008 ዓ.ም. ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡ ዶ/ር ወልደመስቀል ኢትዮጵያ ከነ አበበ ቢቂላ፣ ማሞ ወልዴ እና ምሩፅ ይፍጠር በኋላ በጋራም ሆነ በግል በሚገኙ አትሌቶች የድል ውጤት ዋነኛ ተጠቃሽ አሰልጣኝ ናቸው፡፡

በተለይም አትሌት ኮሎኔል ደራርቱ ቱሉ፣ አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ፣ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ፣ አትሌት ጠሩነሽ ዲባባ፣ አትሌት ብርሃኔ አደሬ፣ አትሌት ጌጤ ዋሚ፣ አትሌት ወርቁ ቢቂላ፣ አትሌት ፊጣ ባይሳ፣ አትሌት አሰፋ መዝገቡ፣ አትሌት ስልሺ ስህን፣…የመሳሰሉ ስመጥር አትሌቶችን ያፈሩ በማፍራት በርካታ የወርቅ፣ የብር እና የነሐስ ሜዳልያ ሽልማቶችን ከአትሌቶቹ በተጨማሪ ሀገሪቷም እንድታገኝ ያስቻሉ ታላቅ ሰው ነበሩ፡፡
ዶ/ር ወልደመስቀል ኮስትሬ ከ1964 ዓ.ም. ጀምሮ ለ30 ዓመታት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ የረጅም ርቀት አሰልጣኝነት ላበረከቱት አስተዋፅዖ በሀገሪቱ መንግሥትም ሆነ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የተሰጣቸው ዕውቅናም ሆነ ሽልማት ባይኖርም፤ የዓለም አቀፍ አትሌቲክ ማኀበር (IAAF) በ1998 ዓ.ም. (እ.አ.አ በ2006) ምርጥ አሰልጣኝ በሚል ተሸላሚ እንደነበሩ አይዘነጋም፡፡
አትሌት ገንዘቤ ዲባባ አዲስ የዓለም ከብረ-ወሰን በማስመዝገብ አሸነፈች
ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ገንዘቤ ዲባባ በስዊድን ስቶኮሎም የ2015 ዓለም አቀፍ የ5,000 ሜትር የቤት ውስጥ ዓለም አቀፍ ውድድር አሸነፈች፡፡ አትሌት ገንዘቤ ውድድሩን ያሸነፈችው ከዚህ ቀደም ተመዝግቦ የነበረውን ክብረ-ወሰን በማሻሻል ነው፡፡
ገንዘቤ ውድድሩን ያሸነፈችው 14 ደቂቃ ከ18 ሰከንድ ከ86 ማይክሮ ሰከንድ በመግባት ነው፡፡ በውድድሩ ከዚህ ቀደም የነበረው የዓለም ክብረወሰን 14 ደቂቃ ከ24 ሰከንድ ከ37 ማይክሮ ሰከንድ ሲሆን፤ ይህም በኢትዮጵያዊቷ አትሌት መሰረት ደፋር ተይዞ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ አትሌት ገነዝቤ ዲባባ የአትሌት ጥሩነሽ እና የአትሌት እጅጋየሁ ዲባባ ታናሽ እህት ስትሆን፤ በተለይ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ አዳዲስ የዓለም ክብረወሰን እያስመዘገበች ማሸነፏ ይታወቃል፡፡
የአለም ሻምፒዮኖቹ ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ለአለም ኮከብ አትሌትነት እጩ ሆኑ
የአለም ኮከብ እጩዎቹ ጥሩነሽ፣ መሐምድ እና መሰረት

የአለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር ባለሞያዎች ቡድን እ.አ.አ በ2013 ዓ.ም የአትሌቲክስ ውድድር አመት አትሌቶች በሩጫ፣ ውርወራ እና ዝላይ ውድድሮች ያስመዘገቧቸውን ውጤቶች እና ሌሎች መስፈርቶችን ከግምት ውስጥ በማስገባት ባደረገው የኮከብ አትሌቶች እጩዎች ምርጫ ኢትዮጵያዊያኖቹ የረጅም ርቀት ሩጫ ድንቆች ጥሩነሽ ዲባባ እና መሰረት ደፋር፣ እንዲሁም የወቅቱ የ800 ሜትር ሩጫ ኮከብ መሀመድ አማንን ጨምሮ በወንዶች 10፣ በሴቶች 10 አትሌቶችን እጩ አድርጎ አቅርቧል።
በሞስኮ አስተናጋጅነት በተካሄደው 14ኛው የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና 10 ሺህ ሜትሩን 30፡43.35 በሆነ ጊዜ በማጠናቀቅ በአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ታሪክ በርቀቱ ሶስተኛዋ በአጠቃላይ ደግሞ አምስተኛዋ የሆነው የወርቅ ሜዳሊያ ያገኘችው ጥሩነሽ ዲባባ በ10 ሺህ ሜትር ርቀት ባደረገቻቸው 11 ተከታታይ ውድድሮች አንድም ውድድር አለመሸነፏ እና በ2013 ዓ.ም በተለያዩ ርቀቶች ባደረገቻቸው ውድድሮች ጠንካራ ተፎካካሪነቷን በተደጋጋሚ ለማሳየት መቻሏ ለእጩነት አብቅቷታል።
የ 2007 ዓ.ም የአለም ኮከብ መሰረት
ሌላዋ ለአለም ኮከብነቱ እጩ የሆነችው ኢትዮጵያዊ አትሌት መሰረት ደፋር በሞስኮው የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ማጣሪያውን በቀላሉ ካለፈች በኋላ በፍጻሜው ውድድር ወቅት በተለመደው አስደናቂ የአጨራረስ ብቃቷ በመታጀብ 5 ሺህ ሜትሩን 14:50.19 በሆነ ጊዜ አጠናቃ ለሁለተኛ ጊዜ በርቀቱ የአለም ሻምፒዮን ከመሆኗ በተጨማሪ አመቱ ጥንካራ ተፎካካሪዋ ጥሩነሽ ዲባባን በዳይመንድ ሊግ ያሸነፈችበት እና በተደጋጋሚ አስደናቂ ብቃቷን ያሳየችበት ሆኖ ነው የተጠናቀቀው።
እ.አ.አ በ 2007 ዓ.ም መሰረት ደፋር እጅግ በጣም ውጤታማ አመትን በማሳለፏ በአለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር (IAAF) የአመቱ ኮከብ ሴት አትሌት ተብላ በመመረጥ ይሄንን ክብር ያገኘች በታሪክ ሁለተኛዋ ሴት አፍሪካዊት አትሌት ለመሆን ከመቻሏ በተጨማሪ ሶስተኛዋ ኢትዮጵያዊትም ለመሆን መቻሏ ይታወሳል። ከመሰረት በፊት ታላላቆቹ ሀይሌ ገብረስላሴ (1998 ዓ.ም) እና ቀነኒሳ በቀለ (2004 እና 2005 ዓ.ም) የአመቱ የአለም ኮከብ አትሌቶች ተብለው ተሸልመዋል።
በወንዶቹ በኩል ለኮከብ አትሌትነት ዘንድሮ እጩ ሆነው ከቀረቡት አስር አትሌቶች መካከል ብቸኛው ኢትዮጵያዊ መሀመድ አማን 2013 ዓ.ም እጅግ በጣም ስኬታማው አመት ነበር። በሞስኮው 14ኛው የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በድንቅ የአጨራረስ ብቃት 800 ሜትሩን በአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ታሪክ ሶስተኛው ፈጣን ሰአት ሆኖ በተመዘገበ 1:43.31 በሆነ ጊዜ አጠናቆ ለኢትዮጵያ በታላላቅ ሻምፒዮናዎች ከ5 ሺህ ሜትር በታች በሆነ ውድድር የወርቅ ሜዳሊያ ያስገኘ በታሪክ የመጀመሪያው አትሌት የሆነው መሀመድ አማን በርቀቱ የዳይመንድ ሊግ ሻምፒዮን በመሆን በፍጹም የበላይነት ነበር የዘንድሮውን የውድድር አመት ያጠናቀቀው።
እ.አ.አ ከጥቅምት 1 ቀን 2013 ጀምሮ እስከ ፊታችን ጥቅምት 27 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ *የአለም አትሌቲክስ ቤተሰብ* በኢሜል መልእክቶች በሚያደርገው የድምጽ አሰጣጥ ሂደት ከፍተኛ ድምጽ የሚያገኙ ሶስት ወንድ እና ሶስት ሴት አትሌቶች ወደፍጻሜው የሚያልፉ ሲሆን፣ ከዛ በኋላ የአለም አቀፉ አትሌቲክ ፋውንዴሽን ምክርቤት የአለም ኮከብ በመሆን የሚያሸንፉት ወንድ እና ሴት አትሌቶችን መርጦ አሸናፊዎቹ እ.አ.አ ህዳር 16 ቀን 2013 ዓ.ም ሞናኮ ውስጥ በሚካሄድ ስነ-ስርአት በይፋ ይታወቃሉ።
የዘንድሮውን የአለም ኮከብ አትሌትነት ክብር ጃማይካዊያኖቹ የአጭር ርቀት ውድድር ኮከቦች ዩሴን ቦልት እና ሼሊ-አን ፍሬዘር-ፕራይስ ይወስዱታል ተብሎ ይጠበቃል።
ዩሴን ቦልት እና አሜሪካዊቷ አሊሰን ፊልክስ የ2012 ዓ.ም የወንዶች እና ሴቶች የአለም ኮከብ አትሌቶች ተብለው መመረጣቸው ይታወሳል።
ምንጭ፡- ፍስሃ ተገኝ “ቶታል 433 “ ስፖርት
