ማን አለ እንዳንተ፣ ታማኝ?
በፈቃዱ ዘ ኃይሉ

የሆነ ጊዜ የሰማኋት ቀልድ ትዝ አለችኝ፤ አንዳንድ የተቃዋሚ ተወካዮች ፓርላማ ውስጥ በነበሩበት በዚያ በደጉ ጊዜ ነው አሉ፡፡ አንድ ተወካይ የሻዕቢያ መንግሥት ላይ ሊደረግ ስለሚገባው እርምጃ ሲናገሩ እንዲህ አሉ፤ “አሁኑኑ ገብተን ድምጥማጣቸውን ማጥፋት አለብን፡፡ አለበለዚያ ካደሩ አይቆረጠሙም፤ እነዚያ ወያኔዎችም ያኔ ሲመሠረቱ ሳንጨፈልቃቸው ዝም ብለናቸው ነው ዛሬ አናታችን ላይ…” አሉና ያሉበት ቦታ ትዝ ሲላቸው ድንግጥ ብለው ወደአቶ መለስ መቀመጫ አማተሩ፡፡ አቶ መለስ በጥሞና ያዳምጣሉ፤ ተወካዩ እንደደነገጡ “…ልጨርሰው ወይስ ትጨርሰኛለህ?” አሉ ይባላል፡፡
የሕወሓት/ኢሕአዴግ ወታደሮች አዲስ አበባ ደርሰው “ሲቪል” መንግሥት ከመመሥረታቸው አስቀድሞ “እኩይ” ናቸው በሚል ሲቃወማቸው የነበረ እና እስካሁንም ስክነቱ ያልተለየው አክቲቪስት ታማኝ በየነ ነው፡፡ የታማኝ የአክቲቪስትነት ሪከርድ ከኮሜዲያንነቱ የሚመዘዝ ነው፡፡ በቀልዶቹ ቢጀምርም አሁን ግን በጣም ‹ሲሪዬስ› ነው፡፡
አሁን እነቪኦኤ፣ ዶቸ ቬሊ፣ ኢሳት በየቤቱ እንደሚደመጡት ከደርግ ማክተሚያ ቀደም ብሎ ብዙ ሰው በየቤቱ ‹ድምፂ ወያነ›ን በድብቅ ያደምጥ ነበር፡፡ የፕሮፓጋንዳ ሚዲያዎች አመል ነውና ያው ውሸታቸው አይጣል ነው፡፡ ታዲያ ታማኝ አዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ቀርቦ የምሩን ሲቀልድ ‹እዚህ ቦታ ይሄን ያክል ሻለቃ ጦር፣ እዚያ ቦታ ደግሞ ይሄን ያክል ሻለቃ ጦር ደመሰስን ይላሉ፡፡ ሲደመር ግን ይሄን ያክላል፡፡ ቆይ እኔ የምለው ወያኔዎቹ የሚደመስሱት ጦር ከጠቅላላ ጦሩ በለጠ እኮ፤ ከየት እያመጡ ነው የሚደመስሱት?› ዓይነት ቀልድ ተናግሮ አላገጠባቸው፡፡ ከዚያ በድምፂ ወያነ መልስ ተሰጠው፤ “ቁጥሩን አዲስ አበባ ስንደርስ እናወራርዳለን” የሚል፡፡ ዛቻ የሽፍትነት ዘመንም አመል ነበረች፡፡
ግንቦት 20/1983 – ኢሕአዴግ አዲስ አበባን ሲረግጥ፣ ሲ ኤን ኤን ካነጋገራቸው ሰዎች አንዱ ታማኝ በየነ ነበር፡፡ “በመሣሪያ ተከበናል፣ ምንም ሠላም የለም…” የሚል ነገር ለጋዜጠኛው ሲነግረው ይታያል፡፡ ታዲያ ታማኝ ሁኔታውን በቀልድ ሲያስታውስ “ጓደኞቼ ከውጪ ደውለው ‹ሲ ኤን ኤን› ላይ አየንህ ሲሉኝ፣ ወዲያውኑ እንግሊዝኛዬ እንዴት ነበር?” አልኳቸው ይላል፡፡
ታማኝ ከአዲሱ ስርዓት ጋር አብሮ መኖር በማይችልበት ሁኔታ የተቀያየመው፣ ካልተሳሳትኩ የወቅቱ ባለሥልጣናት፣ እነታምራት ላይኔ በተገኙበት ስታዲዬም ውስጥ በቀለደው ቀልድ ነው፡፡ እንደማስታውሰው ቀልዱ በማንነት ላይ የተመሠረተ እና ለኢሕአዴግ የማንነት ብያኔ የማይበገር ዓይነት ቀልድ ነው፡፡
ፍቃዱ ማሕተመወርቅ፣ የቀድሞዋ ዕንቁ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ነበር፡፡ በመጽሔትና ጋዜጦች አከፋፋይነትም ይታወቃል፡፡ አሁን መጽሔቱ ተዘግቶ “በታክስ ስም” ፍርድ ቤት እየተመላለሰ ይገኛል፡፡ ፍቃዱ ነጻው ፕሬስ ሲጀመር ጀምሮ ምኅዳሩን ያውቀዋል፤ እናም “እናንተ በደጉ ጊዜ ነው የመጣችሁት” እያለ ይቀልድብኛል፡፡ ያኔ (ማለትም የመጀመሪያው አንቀጼ ላይ ‹ደግ› ባልኩት፣ ለፍቃዱ ግን ‹ክፉ› ግዜ) አንድ ሰው ስርዓቱን የሚያስቀይም ንግግር ሲናገር፣ እንዳሁኑ በሕግ ሥም ፍርድ ቤት አይመላለስም፣ የደረሰበት ይጠፋና ከአራት አምስት ወር በኋላ ተመልሶ ይመጣል፡፡ እንዳይሞት እንዳይሽር ተቀጥቅጦ ማለት ነው፡፡ እንግዲህ ከዚያ ወዲህ ያሻሻልነው ነገር ቢኖር ፍርድ ቤት የመቅረብ ዕድል መፈጠሩ ነው ማለት ነው፡፡ የሆኖ ሆኖ ይህን ያነሳሁት ታማኝ ላይ የደረሰውም እንዲህ ያለው ነገር ነው ለማለት ነው፡፡
ታማኝ ተሰደደ፡፡ ብዙዎች ሲሰደዱ አቅላቸውን ያጣሉ፡፡ የሀገር ቤት ናፍቆት መመለስ ካለመቻሉ ጋር ተደማምሮ ይሁን፣ የሄዱበት አገር ኢሕአዴግ የማይደርስባቸው ከመሆኑ በተጨማሪ የሚያዩት ነጻነት ስለሚያስቀናቸው አላውቅም ብቻ ጠርዝ ይይዛሉ፡፡ ጥቂቶች ብቻ ሚዛናቸውን በጥፍራቸው ቆንጥጠው ይቆማሉ፡፡ ታማኝ ለኔ ከጥቂቶቹ አንዱ ነው፤ ያውም በረዥም ቆይታ ይህንን ማስመስከር የቻለ፡፡ ታማኝ አሁን አክቲቪዝሙን የሚሠራው ብዙ ጊዜ የቪዲዮ ማስረጃዎችን እያቀረበ ነው፡፡ ቪዲዮዎቹን ዩቱዩብ ላይ ሳያቸው በክምችቱ እቀናለሁ፡፡ ለረዥም ጊዜ የአገር ቤት ጉዳይን እየተከታተሉ፣ ማስረጃዎችን እየሰበሰቡ የመቆየት ፅናት የገቡበትን ጉዳይ ርዝመት እና ክብደት ከመረዳት ይመነጫል፡፡
የማስረጃ ነገር ከተነሳ አይቀር፣ አሁን እነ ታማኝ ማስረጃ ዶት ኮም (masreja.com) የተባለ ድረአምባ ፈጥረዋል፡፡ ድረአምባው በአሁኒቷ ኢትዮጵያ ውስጥ በሕግ የበላይነት ፈንታ ራሳቸው ከሕግ የበላይ ሆነው ወንጀል የሚፈጽሙ ሰዎች ላይ ማስረጃ የሚሰበሰብበት ነው፡፡ እንደእውነቱ ከሆነ እኔ በይቅርታ አምናለሁ፤ እስከዛሬ አዲሱ ያለፈውን እየቀጣ የመጣበት ዑደት ቢያንስ የእኛ ትውልድ ላይ ቢቆም እያልኩ እመኛለሁ፡፡
ይህንን በተመለከተ ጓደኛዬ ሶሊያና “ይቅርታ ከፍትሕ ጋር መጋጨት የለበትም” ብላ ሞግታኛለች፡፡ ልክ ነች፤ በወቅቱ የሰጠችኝን ምሳሌ ከወቅታዊው ሁኔታ ጋር አዋህጄ ልናገር፤ “#OromoProtests ላይ ልጇ የተገደለባት እናት የስርዓት ለውጥ ቢመጣ እና ለገዳዩ ወታደር ይቅርታ አድርጊለት ብትባል ፍትሕ ተደረገልኝ ብላ ታምናለች?” በወቅቱ፣ ሶሊም እኔም ጥያቄውን ከመጠየቅ በቀር መልስ መስጠት አልቻልንም፡፡ እርግጥ ነው ልጁ የሞተው የመጣው ለውጥ እንዲመጣ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን በምሳሌያችን መሠረት አወዛጋቢው ማስተር ፕላን ቢሰረዝ እንኳን ልጁ የለውጡ እሸት ተጋሪ ላይሆን አልፏል፡፡ ይቅርታ ለአገሪቱ ቀጣይ ዕጣ ፈንታ ያስፈልግ ይሆናል፤ የቤተሰቡን አባል ወይም ወዳጁን ላጣው ግለሰብ ግን ፍትሕ ሆኖ ይሰማዋል ማለት አይቻልም፡፡ የሆነ ሆኖ፣ ለይቅርታውም ቢሆን ማስረጃውን መሰብሰብ አስፈላጊ ነው፡፡ አጥፊው ጥፋቱን እንዳይክድ፣ ይቅርታ ጠይቁኝ ባዩም በማስረጃ እንዲሞግት፡፡
ማስረጃ መሰብሰብ ሕገ-ወጥ መስሏችሁ የምትፈሩ ካላችሁ አትሳሳቱ፡፡ ሕጋዊ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው መንግሥት ራሱ በፀረ-ሙስና ኮሚሽን በኩል አላግባብ የተገኘ ሀብት ካለ በሚል የባለሥልጣናቱን ሀብት ምንጭ ሳይቀር የማጣራት ማንዴት አለው፡፡ ቁርጠኝነቱ ስለሌለ አልተሳካላቸውም፤ እኛ ግን ይሳካልናል፡፡ በየቀኑ ከታችኛው እርከን (ወረዳ) እስከ ላይ ድረስ የምንጠየቃቸውን ጉቦዎች፣ ባለሀብቱና ባለሥልጣናቱ (ሁለቱም አንድ ናቸው) ኢ-ርትዓዊ በሆነ መንገድ የሚያካብቱትን ሀብት፤ ከትላልቆቹ እስከ ትናንሾቹ ሹመኞች በሕዝብ ላይ የሚፈፅሙትን ግፍ፤ ትንንሽሽም፣ ትልልቅም ሠላማዊ ተቃውሞዎች በተነሱ ቁጥር በንፁሐን ዜጎች ነፍስ ላይ የሚሰነዘሩትን የኃይል እርምጃዎች የሚያጋልጡ ማስረጃዎች ባገኘን ቁጥር ለማስረጃ ዶት ኮም በመላክ ለኢትዮጵያችን የወደፊት መልካም ዕጣ ፈንታ ሲባል እንዲከማቹ የበኩላችንን እናድርግ፡፡ ማስረጃዎቹን መሰብሰቡ ሌላው ቢቀር አጥፊዎቹን ስለሚያስፈራቸው በደላቸውን ሊያላሉልን ይችላሉ፡፡
ቪቫ ላ ታማኝ!!!
Source: http://befeqe.blogspot.se/2015/12/Tamagn-and-masreja-dot-com.html
ሰማያዊ ፓርቲ እና መድረክ በጋራ ሰላማዊ ሰልፍ ጠሩ
ሰማያዊ ፓርቲ እና የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) አዲስ አበባ ላይ በጋራ ሰላማዊ ሰልፍ መጥራታቸውን የሰማያዊ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ነገሰ ተፋረደኝ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልፀዋል፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ እና መድረክ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመስራት መስማማታቸው የሚታወስ ሲሆን እሁድ ታህሳስ 17 ቀን 2008 ዓ.ም. በጋራ ሰልፍ መጥራታቸውን አቶ ነገሰ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልፀዋል፡፡
ሰማያዊ ፓርቲና መድረክ የጠሩት ሰልፍ በዋነኛነት ከማስተር ፕላኑ ጋር በተያያዘ መንግስት እየወሰደው ያለውን እርምጃ፤ እንዲሁም መንግስት ለሱዳን አሳልፎ ለመስጠት ያቀደውን መሬቱ እንዳይሰጥ ለመቃወም ያለመ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ሰልፉ ላይ በሰብአዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ላይ መንግስት እየወሰደው ያለውን እፈና እና እርጃዎቸ እንደሚያወግዙ ምክትል ሊቀመንበሩ ተገልፆአል፡፡
ሰማያዊ ፓርቲ እና መድረክ በጋራ የሚያደርጉት ሰልፍ መነሻውን ፒያሳ ራስ መኮንን ድልድይ አድርጎ፣ በቸርቺል አደባባይ የሚያልፍ ሲሆን መዳረሻው ኢትዮ-ኩባ አደባባይ መሆኑን ታውቋል፡፡ መንግስት እየወሰዳቸው ባሉ የተሳሳቱ እርምጃዎች ሀገራችን አጣብቂኝ ውስጥ መሆኗን የገለፁት አቶ ነገሰ ተፋረደኝ ሀገራችን ካለችበት ችግር ለማውጣት ኢትዮጵያውያን በጋራ እንዲቆሙና በሰልፉም እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ሰልፉ እሁድ ታህሳስ 17 ቀን 2008 ዓ.ም. ከጠዋቱ 3 ሰዓት ፒያሳ ራስ መኮንን ድልድይ ላይ እንደሚጀምር ለማወቅ ተችሏል፡፡
ምንጭ፡- ነገረ ኢትዮጵያ
ኦሮሞ ነኝ!! ኢትዮጵያዊ ነኝ!! አሸባሪ አይደለሁም!!
ገመቹ መረራ ፋና

*
ይኼንን የምፅፈው በብዙ ነገሮች ስለተረበሽኩ ነው፤ ጎኔን ከፍራሼ በጊዜ ባዋድድም እንቅልፍ ሊወስደኝ ስላልቻለ ከተጋደምኩበት ተነስቼ ነው። በየቀኑ የምሰማው እና የማየው ነገር እነ1984ን እና Hunger Gamesን አይነት ፊልሞች የምመለከት እንጂ የምር እየኖርኩት ያለሁት ነገር እየመሰለኝ አይደለም። መጪው ጊዜ ብሩህ አይደለም!!! ጭለማ እና አስፈሪ ሆኖብኛል።
* * *
ይሄ ሌሎች ሰዎች ላይ የደረሰ ሳይሆን በኔው በራሴው ላይ የደረሰና የኖርኩት ገጠመኝ ነው፦
አምቦ፣ ሕዳር 1998 ዓ/ም።
ከትምህርት ቤት ሲወጡ እዚያው ትምህርት ቤት በር ላይ ስለተገደሉት የ10ኛ ክፍል ተማሪዎች አላወራላችሁም። በሰላማዊ መንገድ ያለምንም ሁከት ተቃውሟቸውን ያሰሙ ልጆች ላይ ፊት ለፊት ጥይት ስለሚተኩሱ «ሰላም አስከባሪዎች»ም አልተርክም። አዎ የተገደሉት ከተገደሉ በኋላ በአንድ ዝም ባለ ቀን የተደረገ ነገር ነው።
በዚህ ዕለት አሁን በሕይወት የሌሉ አያቴን እያስታመምኩ ለማደር ከሰፈር ወጥቼ አያቴ ወደተኙበት ወደ አምቦ ሆስፒታል እያመራሁ ነበር። ወደዋናው የአስፓልት መንገድ ልደርስ አንድ ቅያስ ሲቀረኝ በስፍራው የነበሩት ሁለት ፌዴራል ፖሊሶች ጠሩኝ። ምርጫ አልነበረኝም፤ እየቀፈፈኝ ወደቆሙበት ጥግ ሄድኩ።
«መታወቂያ!» ሲል ጮኸብኝ አንደኛው ፌዴራል ፖሊስ ዱላውን እያሽከረከረ። አረንጓዴዋን የቀበሌ መታወቂያዬን ከኋላ ኪሴ አውጥቼ ሰጠሁት። ያሽከረክረው የነበረውን ዱላውን ትከሻዬ ላይ አሳረፈው። «ማን ይሄን ጠየቀህ?! የኦነግ መታወቂያህን አውጣ!» ሲል ጮኸብኝ።
«ኧረ የለኝም…» ንግግሬን አልጨረስኩም። የሁለተኛው ፖሊስ ዱላ አረፈብኝ። የተለያዩ መልስ የማይፈልጉ ጥያቄዎች እየጠየቁ በእግራቸው ተቀባበሉኝ። ሲበቃቸው «ሂድ ከዚህ ጥፋ፣ እናንተ ናችሁ ያስቸገራችሁት..» አሉኝ። ተነስቶ ለመሄድ የሚያስችል አቅም ግን አልነበረኝም፤ ይሄም ለሌላ ዱላ ዳረገኝ። እንደምንም ታክሲ ይዤ ሆስፒታል ደረስኩና አደርኩ። ያንን ድብደባ የማልረሳበት ሌላም ምክንያት አለኝ።
* * *
ይሄ መንገድ እየሄድኩ ሳለሁ የገጠመኝ ነገር ነው። ለተቃውሞ ድምፁን ያሰማ ሰው ደግሞ ምን ሊደርስበት ነው? መገመት ነው። ኦሮሞ ስለሆንኩ፣ ጥያቄ ስለጠየቅኩ፣ አንገቴን ቀና አድርጌ ስለሄድኩ «ኦነግ» የሚል ታፔላ በማንም እንዲሰጠኝ አልፈልግም!!! ሰው ነኝ!!! ኢትዮጵያዊ ነኝ!!! ኦሮሞ ነኝ!!! አሸባሪ ግን አይደለሁም!!! አባቶቼ ለዚህች አገር እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ደምተዋል። ቅድም አያቴ ትግራይ ድረስ ሄደው ዘምተው የሃገራቸውን ዳር ድንበር ሲያስከብሩ ተሰውተዋል። ከማንም ያልበለጥኩ፣ ከማንም ያላነስኩ የዚህች አገር ዜጋ ነኝ።
* * *
ይሄንን እና ሌሎችም ነገሮችን በጭንቅላቴ እንደሰነግኩ ነው እንግዲህ ወደ መቐለ ዩኒቨርሲቲ ለትምህርት የሄድኩት። እዚያ እንደደረስኩም ብዙ ሳንቆይ ነበር የብሔር ግጭት የተነሳው። በኋላ ላይ ሲጣራ አንዲት ልጅ አፍቅሮ ራሱን ባጠፋ አንድ የአዳማ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ምክንያት ነበር «እኛም አንድ ኦሮሞ መግደል አለብን» ተብሎ በጠራራ ፀሃይ የተዘመተብን። እኚህ ጥቂት የተማሩ ደደቦች የፈፀሙት ድብደባና ሌሎች አስፀያፊ ድርጊቶች የትግራይን ወይም የመቐለን ሕዝብ ይገልፁት ነበር? በፍጹም!!!
ለአራት አመታት የኖርኩበት ይህ የትግራይ ሕዝብ ከተማሪው ሸሽቶ ከዩኒቨርሲቲው ጊቢ በመውጣት በደመነፍስ ወደ ሃይማኖት ተቋማት እና ሌሎች ስፍራዎች የሸሸውን የሌላ ክልል ተማሪ ምግብና መጠለያ ሰጥቶ ክፉ ቀኑን ያሳለፈለት ደግ ሕዝብ ነው!! ታምሜ ለሳምንት በተኛሁበት አጋጣሚ በአካል እንኳን ሳታውቀኝ መታመሜን ስትሰማ «ወይኔ ልጄን» ብላ በልጇ ምግብና ማር የላከችልኝን እናት ያገኘሁበት ሕዝብ ነው!! ምንም የማያውቀኝን እኔን ተቀብሎ ቤቴ ያለው እንዲመስለኝ አድርጎ የተንከባከበኝ፣ ከአባቴ ያላነሰ ገንዘብና ሞራል እየሰጠ ለአራት አመታት ከአጠገቤ ያልተለየ አባት ያገኘሁበት ሕዝብ ነው!! የዚህን ሕዝብ ደግነት በጥቂቶች ድድብና በዜሮ ላባዛው? የተወሰኑ ፖለቲከኞች አሊያም «አክቲቪስቶች» ድርጊትና ንግግር ይሄንን እውነት ይሰውርብኝ? ፈጽሞ!!!!!!
አዎ እንዲህ አይነት የደግነት ታሪኮች በሌሎች አካባቢዎችም ብትሄዱ በብዙ ትሰማላችሁ። በተቸገረ ሰው ጨክኖ «ብሔሩ ምንድነው?» የሚል ሕዝብ የትም ቦታ የለም። ስለኖርኩብትና ስላሳደገኝ ስለደጉ የኦሮሞ ሕዝብ ሌላ ጨምሬ የምናገረው ነገር የለኝም። በተለያዩ ጊዜያትና አጋጣሚዎች በበቂ ሁኔታ ተነግሯል። በቅርቡ፣ በጣም በቅርቡ ግን በረባውም ባልረባውም በዘር መከፋፈል ነው የማየው። የሃይማኖት ጉዳይ ሆኖበት «የክርስቲያን/የሙስሊም ስጋ አልበላም» ይል የነበረው ማህበረሰባችን «የኦሮሞ/አማራ/ትግሬ ስጋ አልበላም» የሚልበት ጊዜ የመጣ እስኪመስል ድረስ ልዩነት በባትሪ ይፈለጋል። እርስ በርስ የሚያባላን የከፋ ችግር የለብንም። እንደሌላው ዓለም የዘር (race) ችግር የለብንም፤ ሁላችንም ጥቁር ነን። ተመሳሳይ ኑሮ የምንኖር፣ የመግባቢያ ችግር የሌለብን፣ ለዘመናት ስንጋባና ስንዋለድ የኖርን ሕዝቦች ነን። አንዱ «ብሔር» ከአንዱ «ብሔር» በከፋ ሁኔታ፣ አንዱ ሃይማኖት ከሌላኛዎቹ ሃይማኖቶች በተለየ ሁኔታ በተለያዩ ሥርዓቶች የተገፋበትን ሁኔታ አይተናል። አዎ ሥርዓቶች፣ መንግስታት/ገዢዎች ያልፋሉ፣ በሌላም ይተካሉ፤ ይህ ያለና የነበረ የተፈጥሮ ሥርዓት ነው። ሕዝቦች ግን አያልፉም።
ብሔር አጣርተው አይደለም ወላጆቻችን ለጎረቤታቸው ችግር ሲደርሱ እና ሲደረስላቸው የኖሩት። ብሔር ተጠያይቀን አይደለም እዚህ የደረስነው። ብሔር ቆጥረን አይደለም ምርጥ ጓደኞቻችንን ያፈራነው። ሰውነታችንን አስቀድመን ነው!!! ዛሬ በማወቅም ባለማወቅ የሚደረጉ የብሔር የርስ በርስ ግጭት ውስጥ መግባት የለብንም። ያ እንደ ብሔርም ሆነ እንደ ሃገር የማንወጣው አዘቅት ውስጥ ነው የሚከተን። አሁን ያለንበትንም ይሁን ያለፍንበትን ልዩነት በእጅጉ የሚያስመኝ ክፉ አዘቅት ውስጥ!!!
ተዋጠልንም አልተዋጠልን ተዋልደናል። ተዋደናል። ተዛምደናል። ተጋምደናል። የተሻለችዋን ነገኣችንን ልንፈልግና ልናገኝ የምንችለው አንዲት የሁሉንም ሰው መብት እና ሰብዓዊ ክብር በምትጠብቅ ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ነው። ከታሪክ ልንማር ይገባል ምናምን አልልም። አይናችንን አንስተን ደቡብ ሱዳንን ማየት በቂአችን ነው። ከሱዳን እስክትገነጠል ድረስ ፅኑና የሚገርም ትግል ለዓመታት አድርጋለች። ከተገነጠለች በኋላ ግን የሆነችውን ሆናለች። የኛም የተናጠል ጉዞ መድረሻው ያው ነው። አማራ ቢገነጠል ጎጃም፣ ጎንደር፣ ወሎ፣ ሸዋ እያለ ይናከሳል። ኦሮሚያ ብትገነጠል ሸዋ፣ ሐረርጌ፣ ወለጋ፣ አርሲ እያለ ይባላል። ትግራይ ቢገነጠል ተምቤን፣ እንደርታ፣ ዓድዋ፣ ሽሬ እያለ ይጫረሳል። «ታግሎ» ሲያበቃ «ነፃ» ባወጣት «ሃገር» የሚፈጠረው ቀውስ የዳር ተመልካች መሳቂያ ያደርገዋል።
* * *
አይን የሌለው ኢፍትሃዊነትን በሚተገብር እና ግፍ በሚፈፅመው አካል ሳይሆን ዳር ሆኖ ያንን ድርጊት በሚደግፈው ሰው ልቤ ትደማለች። ከክቡሩ የሰው ልጅ ሕይወት ይልቅ በተራ የንብረት መውደም የሚብሰከሰከውን ብኩን ሳይ ነፍሴ ክፉኛ ታዝናለች። ልጁን በሞት ካጣ ወላጅ ሃዘን ይልቅ ወደፊት ምናልባት ኪሴ ሊገባ ይችላል ብሎ ለሚያስበው ሽራፊ ሳንቲም በሚቆረቆር «ሰው» ንቀቴ ይበረታል። ትናንት እርሱ ላይ ሲጫን የነበረውን የበደል ቀንበር ዛሬ ባለቀን ሆኖ ሌላው ላይ አክብዶ በሚጭነው ላይ ጥላቻዬ ይከራል። አንድ ሕሊና ያለው ሰው እንዴት በባዶ እጅ በወጣ ሰልፈኛ ላይ ቀጥታ የተተኮሰን ጥይት ደግፎ ሊናገር ይችላል? አንድ ችግር የኛን ቤት እስኪያንኳኳ ድረስ የባለቤቱን ያህል ላይሰማን ይችላል፣ ነገር ግን እንዴት በተቃራኒ ያስቆማል? አላውቅም። የዚህ አይነት አስተሳሰብ አይገባኝም።
* * *
Rabindranath Tagore «Gitanjali» በተሰኘው መድብሉ ውስጥ በጣም የምወድለት እንዲህ የምትል የልመና/የፀሎት ግጥም አለችው፦
Where the mind is without fear and
the head is held high;
Where knowledge is free;
Where the world has not been broken
up into fragments by narrow domestic walls;
Where words come out from the depth of truth;
Where tireless striving stretches its arms towards perfection;
Where the clear stream of reason has not
lost its way into the dreary desert of
dead habit;
Where the mind is led forward by Thee
into ever-widening thought and action—
Into that heaven of freedom, my Father,
let my country awake.
አሜን!!
* * *
ኦሮሞ ነኝ!! አሸባሪ አይደለሁም!!
#OromoProtests
#StopKillingCivillians
#StopKillingUnarmedProtesters
እነ ሀብታሙ አያሌው የጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ሰብሳቢ ዳኛ ከችሎት እንዲነሱ ጠየቁ
• አቶ ዳንኤል ሺበሽ በእስር ቤት በደል እየተፈጸመበት መሆኑን ተናግሯል
በፌደራል አቃቤ ህግ የሽብርተኝነት ክስ ተመስርቶባቸው የነበሩና በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ነሀሴ 14/2007 ዓ.ም የቀረበባቸውን ክስ መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነጻ እንዲሰናበቱ ተወስኖላቸው ሳለ አቃቤ ህግ ይግባኝ ጠይቆባቸው ጉዳያቸው በፌደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት እየተከታተሉ የሚገኙት እነ ሀብታሙ አያሌው የይግባኝ ሰሚ ችሎት ሰብሳቢ ዳኛ ከችሎት እንዲነሱላቸው ጠይቀዋል፡፡
በዚህ መዝገብ ይግባኝ የተጠየቀባቸውና ሰብሳቢ ዳኛው፣ ዳኛ ዳኜ መላኩ ከችሎት እንዲነሱ የጠየቁት ተከሳሾች አቶ ሀብታሙ አያሌው፣ አቶ የሺዋስ አሰፋ፣ አቶ አብርሃ ደስታ፣ አቶ ዳንኤል ሺበሽ እና አቶ አብርሃም ሰለሞን ናቸው፡፡
የይግባኝ መልስ ሰጭዎቹ ሰብሳቢ ዳኛው ከችሎት እንዲነሱላቸው ለመጠየቃቸው ምክንያታቸውን ዘርዝረው በጽሁፍ ያቀረቡ ሲሆን በዋናነት ዳኛው ‹‹…ችሎቱን እየመሩበት ካለው አግባብ አንጻርም ሆነ በህግ ከሚጠበቅባቸው ገለልተኝነት አንጻር እርሳቸው እንደ አንድ ዳኛም ሆነ እንደ ሰብሳቢ በሚሳተፉበት ችሎት ትክክለኛ ፍትህ እናገኛለን ብለን ስለማናምን›› የሚል ነው፡፡
እነ ሀብታሙ አያሌው ነሀሴ 15 ቀን 2007 ዓ.ም የፌደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተረኛ ችሎት በጻፈው እግድ ምክንያት እስካሁን በእስር ላይ ይገኛሉ፡፡
በሌላ በኩል ቃሊቲ ማረሚያ ቤት በእስር ላይ የሚገኘውና በዚሁ መዝገብ የተካተተው የቀድሞው የአንድነት ፓርቲ ምክትል የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ አቶ ዳንኤል ሺበሽ በእስር በሚገኝበት ቃሊቲ ማረሚያ ቤት አስተዳደር በደል እየተፈጸመበት እንደሆነ ለችሎቱ ገልጾዋል፡፡ አቶ ዳንኤል ለፍርድ ቤት ክርክር ያዘጋጀው ወረቀት ተቀምቶ እንደተቀዳደደበትና በአስተዳደሩ ከፍተኛ ዛቻም እየተፈጸመበት መሆኑን ለችሎቱ ተናግሯል፡፡ ‹‹እዚህ ቤት አስክሬንህ ነው የሚወጣው›› እያሉ ይዝቱብኛል ያለው አቶ ዳንኤል፣ ‹‹ከሌላው እስረኛ እኩል የማልታየው ለምንድነው? እኔስ ዜጋ አይደለሁምን?›› ሲል ጠይቋል፡፡
ፍርድ ቤቱ መልስ ሰጭዎቹ ባቀረቡት የሰብሳቢው ዳኛ ይነሳልን አቤቱታ ላይ ብይን ለመስጠት ለታህሳስ 15 ቀን 2008 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
ዘገባው የነገረ ኢትዮጵያ ነው፡፡
የቃሊቲ ማረሚያ ቤት ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋን በምስክርነት እንደማያቀርብ አሳወቀ
የቃሊቲ ማረሚያ ቤት በእነ ዘላለም ወርቃገኘሁ የክስ መዝገብ በመከላከያ ምስክርነት የተጠቀሰውን ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ በምስክርነት እንደማያቀርበው ለልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በደብዳቤ አሳውቋል፡፡ ማረሚያ ቤቱ ታህሳስ 4 ቀን 2008 ዓ.ም ለልደታ ፍርድ ቤት በላከው ደብዳቤ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ‹‹የ18 አመት ፅኑ እስራት የተፈረደበት በመሆኑና ከአሁን ቀደም ምስክር ሆኖ ከማረሚያ ቤቱ ወጥቶ መስክሮ ስለማያውቅ ለመስክርነት ለማቅረብ እንቸገራለን›› ብሏል፡፡

እስክንድር ነጋ ለእነ ዘላለም ወርቃገኘው በመከላከያ ምስክርነት ከተቆጠረ በኋላ ከህዳር 13 ቀን 2008 ዓ.ም ጀምሮ ለአራት ቀጠሮዎች በምስክርነት ሳይቀር የቀረ ሲሆን ዛሬ ታህሳስ 6 ቀን 2008 ዓ.ም ማረሚያ ቤቱ በላከው ደብዳቤ መሰረት ሳይቀርብ ቀርቷል፡፡ ከአንድ አመት በፊት ከ6 ሰዓት እስከ 6 ሰዓት ተኩል ለ30 ደቂቃ ሲጠየቅ የነበረው እስክንድር ነጋ በአሁኑ ወቅት እንዳይጠየቅ ተከልክሏል፡፡ በተጨማሪም ማረሚያ ቤቱ በተደጋጋሚ እስክንድር ነጋ የታሰረበትን ክፍል በመፈተሽ መፅሃፍ ቅዱስን ሳይቀር መነጠቁም ይታወሳል፡፡
ምንጭ፡- ነገረ ኢትዮጵያ