በወለጋ ሻምቡ ወህኒ ቤት አንድ ወታደር ሁለት አለቆቹን ገደለ
ትናንት ህዳር 24 ቀን 2006 ዓ.ም. ጠዋት በኦሮሚያ ክልል ወለጋ ውስጥ በሚገኘው ሆሮጉድሩ ወረዳ ሻምቡ ወህኒ ቤት አንድ ወታደር ሁለት አለቆቹን በመሳሪያ ገድሎ እጁን ሰጠ፡፡
ገዳዩ አለቆቹ በተደጋጋሚ በእስረኞች ላይ እና በሌሎች የበታች ሰራተኞች ላይ ጸደጋጋሚ በደል ሲፈፅሙ ይቃወም የነበረ ሲሆን ትናንት ግን እስካሁን በውል ባልታወቀ ምክንያት ሁለቱነብ አለቆቹን መግደሉን ምንጮቻችን ከስፍራው አስታውቀዋል፡፡ የወረዳው ፖሊሶች ዝርዝር መረጃውን እንዲሰጡን ተደጋጋሚ ጥረት ብናደርግም አልተሳካም፡፡
በአፍሪካ ትልቁ የንግድ ማዕከል በሆነው መርካቶ በደረሰ የእሳት አደጋ ንብረቶች ወደሙ
በአዲስ አበባ የሚገኘው የአፍሪካ ትልቁ የንግድ ማዕከል መርካቶ ዛሬ ህዳር 25 ቀን 2006 ዓ.ም. ከቀኑ 8፡00 ሰዓት በኋላ በመርካቶ ልዩ ቦታው ከምዕራብ ሆቴል ወደ በርበሬ በረንዳ በሚወስደው መንገድ ሐረር ሜትሮ ሆቴል ዓለም ሽንሽን እና ጌጣጌጥ በሚሸጡባቸው ሱቆች እና በተለምዶ ጆንያ ተራ እየተባለ በሚጠራው ቦታ በተነሳ የድንገተኛ ችሳት ቃጠሎ እስካሁን ግምቱ ያልታወቀ ንብረት አውድሟል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር እሳት እና ድንገተኛ አደጋ መከላከያ ድርጅት እሳቱን ለማጥፋት በቶሎ ባለመድረሱ ብዙ መትረፍ የሚገባቸው ንብረቶች ሊወድሙ መቻላቸው የታወቀ ሲሆን፤ ድርጅቱ በበኩሉ ወደ መርካቶ መሄጃ መንገዶች በመቆፋፈራቸው ለመዘግየቱ እንደምክንያት ተጠቅሷል፡፡ በአካባቢው ያሉ እማኞች በበኩላቸው ድርጅተሩ በከተማው መቼም ቢሆን በአፋጣን ደርሶ ውድመትን አድኖ አያውቅም፤ ብዙ ንብረት ማትረፍ ሲቻል ብዙ ጊዜ ሆን ብሎ በሚመስል መልኩ ይዘገያል የሚል ትችትን አቅርበዋል፡፡