Daily Archives: December 25th, 2013

የአንድነት ፓርቲን ለመጪዎቹ አመታት የሚመራ ሊቀመንበር 3 ዕጩዎች የምረጡኝ ቅስቀሳ ጀመሩ

የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ(አንድነት) ለመጪዎቹ 3 ዓመታት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳን ተክ በመተካት ፓርቲውን በሊቀመንበርነት የሚመራ 3 ዕጩዎች የምረጡኝ ቅስቀሳ መቀጠላቸው ተገለፀ፡፡  ፓርቲው በተለይም የፓርቲውን ዓላማና ግብ በአጭር ጊዜ ከማሳካት አንፃር ትግሉን ይመራል፣ መጪውን 2007 ዓ.ም. ምርጫንም በድል ለማጠናቀቅ ይረዳ በሚል ከወዲሁ ድንገተኛ ጠቅላላ ጉባኤ በመጥራት አዲስ የፓርቲውን ሊቀመንበር እና የብሔራዊ ምክር ቤት አባላትን ሊያስመርጥ ነው፡፡ ለዚህም መጪዎቹን ዓመታት አንድነት ይመራል በሚል በዕጩነት የቀረቡት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ኬሚካል ኢንጂነሩ ረዳት ፕሮፌሰር ግዛቸው ሽፈራው፣ በፓርላማ ብቸኛው የተፎካካሪ ፓርቲ ተወካይ እና የልማት አማካሪ አቶ ግርማ ሰይፉ እና መንግስታዊ ያልሆነ በአፍሪካ የንግድ ግብይት ጥናት ድርጅት ባለሙያ የሆኑት አቶ ተክሌ በቀለ ናቸው፡፡

ImageImageImage

ኢንጂነር ግዛቸው በሙያቸው በኬሚካል ምህንድስና ማስተርስ ድግሪ ያላቸው ሲሆን፤ በፖለቲካ ህይወታቸው በመኢአድ እና በኋላም በቅንጅት ፤አሁን ደግሞ በአንድነት/መድረክ ከተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበርነት ጀምሮ አሁን ደግሞ የብሔራዊ ምክር ቤት አባል በመሆን ልምድ እንዳላቸው ይታወቃል፡፡ አቶ ግርማ ሰይፉ ደግሞ በኢኮኖሚ ፖሊሲ ትንተና የማስተርስ ድግሪ ያላቸው ሲሆን፤ በፖለቲካ ህይወታቸው በቀድሞ ኢዴሊ በኋላም በቅንጅት፤ አሁን ደግሞ የአንድነት/መድረክ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር እና ስራ አስፈፃሚ እና የብሔራዊ ምክር ቤት አባል በመሆን ልምድ እንዳላቸው ይታወቃል፡፡

ሶስተኛው እጩ ደግሞ የአንድነት ፓርቲ የጀርባ አጥንት በመሆን ሰፊ ስራ እየሰሩ ያሉት አቶ ተክሌ በቀለ በሙያቸው በማኀበራዊ ግብይት የማስተርስ ድግሪ ያላቸው ሲሆን፤ በፖለቲካ ህይወታቸው በቀድሞ ኢዴፓ በኋላም በቅንጅት አሁን ደግሞ በአንድነት/መድረክ ከሰሜን ቀጠና አደራጅነት ጀምሮ በአሁን ወቅት የማዕከላዊው ፋይናንስ ሃላፊ እና ስራ አስፈፃሚ አባል እንዲሁም የብሔራዊ ምክር ቤት አባል በመሆን ሰፊ የፖለቲካ ልምድ እንዳላቸው መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

ፓርቲው በያዝነው የፊታችን ታህሳስ 2006 ዓ.ም. መጨረሻ አካባቢ በሚያካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ የፓርቲውን ሊቀመንበር ጨምሮ በፓርቲው ከፍተኛ ስልጣን ላለው ብሔራዊ ምክር ቤት አባላትን እንደሚያስመርጥ ይታወቃል፡፡ በተለይ ዕጩ ሊቀመንበሮቹ በአሁን ወቅት በይፋ የምረጡኝ ቅስቀሳ መጀመራቸውን የፓርቲው ልሳን ያስታወቀ ሲሆን፤ በመካከላቸው ያለው ፉክክርም እጅግ ፈታኝ እና አጓጊ እንደሆነም ተጠቁሟል፡፡

 

 

መኢአድ በቦሌ መኖሪያ ቤት ከፈረሰባቸው 70 ከመቶ አባሎቼ ናቸው ማለቱ ተገለፀ

-ምትክ ቤት እንዲሰጣቸው የጠየቁ 12 የኮሚቴ አባላትም መታሰራቸው ተጠቁሟል

 በአዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 በተለምዶ ሃዲስ ሰፈር በሚባለው አካባቢ ይገነባል በሚባለው ብሔራዊ ስታዲየም ግንባታ ከታህሳስ 3 ቀን 2006 ዓ.ም. ጀምሮ በመፍረስ ላይ ከሚገኙት 534 ቤቶች ውስጥ 70 በመቶ የሚሆኑ አባወራዎች አባሎቹ መሆኑን መኢአድ እንዳስታወቀ ኢትዮ ምህዳር ባሬ እትሙ ዘግቧል፡፡

የመኢአድ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ የኢዮብዘር ዘሪሁን ለኢትዮ ምህዳር ጋዜጣ እንደገለፁት ፤ነዋሪዎቹ ከ1994 ዓ.ም. ጀምሮ በካርታ ላይ የሰፈረ ፕላን ያላቸው ሲሆን የከተማ ቦታ ሊዝ ስርዓቱ ሲታወጅም የክፍለ ከተማው እና የወረዳው አመራሮች፤ነዋሪዎቹ ከቦታው ላይ ሲነሱ ምትክ እንደሚሰጣቸው የገቡትን ቃል በማጠፍ በ7 ቀናት ውስጥ እንዲፈናቀሉ መደረጉ አግባብነት የለውም ማለታቸውን ጋዜጣው ለንባብ አብቅቷል፡፡ ከዚህ በተቃራኒ የወረዳው አስተዳደሮች ነዋሪዎቹ ያላቸውን ህጋዊነት ወደ ጎን በመተው መሬትን በመውረር ህገ ወጥ ቤት ገንብተዋል የሚል ምላሽ መስጠቱም ተጠቁሟል፡፡

የተፈናቃዮችን ቅሬታ ለከተማው ከንቲባ እና ለሚመለከተው አካል ለማድረስ 12 አባላት ያቀፈው ኮሚቴ ቦሌ ክፍለ ከተማ በሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ ቢታሰሩም፤ እስካሁን ህጋዊ የዋስ መብታቸው አለመጠበቁን እና ከቤተሰቦቻቸውም ጋር እንዳይገናኙ መደረጉን የህዝብ ግንኙነት ኃላፊውን ዋቢ አድርጎ ጋዜጣው ጨምሮ ገልፅዋል፡፡

የድምፃዊት ሚካያ በኋሉ የቀብር ስነስርዓት ተፈፀመ

በአዲስ የሙዚቃ ስልት “ሸማመተው” በሚል የሙዚቃ አልበሟ ከህዝብ የተዋወቀችው ድምፃዊት ሚኪያ በኋሉ ባደረባት ህመም በህክምና ስትረዳ ቆይታ ትናንት ታህሳስ 15 ቀን 2006 ዓ.ም. ሌሊት 36 ዓመቷ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይታለች፡፡ ድምፃዊቷ ወደ ሙዚቃው ኢንዱስትሪ ከመምጣቷ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ “በኢትዮጵያ ቋንቋዎች እና ስነ ፅሑፍ” በመጀመሪያ ድግሪ ተመርቃ በስኩል ኦፍ ቱሞሮ እና በአዲስ ኢንተርናሽናል ትምህርት ቤት በመምህርነት አገልግላለች፡፡ Image

ድምፃዊቷ ኢትዮጵያን በመወከል በደቡብ አፍሪካ በሚካሄደው “ኮራ” የአፍሪካ ሙዚቃ ውድድር ላይ ደለለኝ ደለለኝ በሚል ዘፈኗ ተወዳድሯ ምርጥ ስድስት ውስጥ ገብታ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፤ ትናንት በሞት እስክትለይ ድረስም “በዶመስቲክ ካልቸር” ጥናት የማስተርስ ትምህርቷን የመመረቂያ ፅሑፍ እየሰራች እንደነበርም ታውቋል፡፡

የድምፃዊቷ የቀብር ስነስርዓትም ዛሬ ማክሰኞ ታህሳስ 16 ቀን 2006 ዓ.ም. ቤተሰቦቿ፣ ወዳጅ ዘመድ እና አድናቂዎቿ በተገኙበት በለቡ ቅዱስ ገብርኤል የቀብር ስነስርዓቷ ተፈፅሟል፡፡ ሚካያ በኃይሉ የአንዲት ሴት ልጅ እናት ነበረች፡፡ አዲስ ሚዲያም ለሚኪያ የነፍስ እረፍትን፤ለወዳጅ ቤተሰቦቿ እና አድናቂዎቿ መፅናናት ይመኛል፡፡

%d bloggers like this: