በከፍተኛ የመንግሥት አመራሮች ላይ ሰኔ 15 የተፈጸመው ግድያ ዓቃቤ ሕግንና ተጠርጣሪዎችን እያወዛገበ ነው

ታምሩ ጽጌ
‹‹ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተቋሙን የማይመጥን ውሳኔ ሰጥቷል››

ተጠርጣሪዎች

‹‹የተወሰኑ ተጠርጣሪዎች በህቡዕ ተደራጅተው ጦርነት ይመሩ ነበር››

ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ

በአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች፣ በመከላከያ ሠራዊት ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹምና በጓደኛቸው ላይ ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. በተቀራራቢ ሰዓታት ውስጥ የተፈጸመው ግድያ፣ ዓቃቤ ሕግንና ከግድያው ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው የታሰሩ ተጠርጣሪዎችን ማወዛገቡ ቀጥሏል፡፡

ግድያው በተፈጸመ ማግሥት ከሰኔ 16 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ በቁጥጥር ሥር ውለው በተለያዩ ጊዜያት ፍርድ ቤት ሲቀርቡ፣ የተጠረጠሩት ከግድያው ጋር በተያያዘና የሽብርተኝነት ሕግን አዋጅ ቁጥር 652/2001 በመተላለፍ በሽብር ተግባር ወንጀል ተጠርጥረው መሆኑን የሚናገሩት ቁጥራቸው ከ30 በላይ የሚሆኑት ተጠርጣሪዎች፣ ግድያውን በሚመለከት የፌዴራልም ሆነ የክልል መንግሥት አመራሮች የተናገሩትና ያሰራቸው የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ የሚናገረው የተለያየ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ የሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. ከፍተኛ አመራሮች ግድያን በማቀነባበርና በመሳተፍ ተጠርጥረው፣ በፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት ቀርበው በፀረ ሽብርተኝነት ሕጉ 28 ቀናት የምርመራ ጊዜ ተጠይቆባቸው ቢፈቀድም፣ ፖሊስ በተሰጠው ጊዜ ምንም ዓይነት ማስረጃ ሊያቀርብባቸው ባለመቻሉ፣ ፍርድ ቤቱ ሰፊ ትንታኔ በመስጠት በዋስ እንዲለቀቁ ውሳኔ ሰጥቶ እንደነበር ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት አስረድተዋል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ በጠበቆቻቸው አማካይነት ነሐሴ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. ባቀረቡት ክርክር እንዳስረዱት፣ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ያቀረቡት የፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ዝርዝር ትንታኔ በመስጠት ለደንበኞቻቸው የጠበቀላቸውን ሕገ መንግሥታዊ የዋስትና መብት፣ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ያላግባብ ስለነፈጋቸው ነው፡፡ የከፍተኛው ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ሕገ መንግሥታዊ የሆነውን የዋስትና መብት የነፈጋቸው፣ ተቋሙን በማይመጥንና የዳኝነትን ብቃት ግምት ውስጥ ሊያስገባ በሚችል ሁኔታ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ይኼውም አንድ የፀረ ሽብር ተግባር ወንጀል ፈጽሟል ተብሎ የተጠረጠረ ዜጋ በፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 20 (3) ድንጋጌ መሠረት ምርመራ ሊፈቀድበት የሚችለው 28 ቀናት ሆኖ ተደንግጎ እያለ፣ በከፍተኛው ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በደንበኞቻቸው ላይ የተሰጠው የምርመራ ጊዜ 42 ቀናት መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ይኼ ደግሞ የሕጉን ድንጋጌ ከመጣሱም በላይ፣ ምንም ዓይነት ማስረጃ ያልቀረበባቸው ተጠርጣሪዎችን ከሕግ አግባብ ውጪ እንዲታሰሩ ማድረግ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ ዓቃቤ ሕግ፣ የፖሊስ አባል፣ የአብን አመራሮችና አባላት፣ የተቋማት ሠራተኞችና ሌሎችም ሲሆኑ፣ በመዝገብ ቁጥሮች 181966፣ 181965፣ 182124፣ 182129 እና በመዝገብ ቁጥር 182150 ተካተው በአምስት መዝገቦች ከ30 በላይ ተጠርጣሪዎች የከፍተኛው ፍርድ ቤት ውሳኔን በመቃወም በሰባት ጠበቆች ተወክለው ሰፊ ክርክር አድርገዋል፡፡

የፌዴራል መንግሥትና የአማራ ክልል የመንግሥት አመራሮች በአማራ ክልል አመራሮች ላይ የተፈጸመው ግድያ ‹‹የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ነው›› እያሉ በይፋ ከዕለቱ ጀምሮ በመገናኛ ብዙኃን ጭምር ገልጸው እያለ፣ ደንበኞቻቸውን በሽብር ተግባር ወንጀል መጠርጠር እርስ በርሱ የሚጣረስና ሕዝብንም እምነት የሚያሳጣ መሆኑን ጠበቆቹ ገልጸዋል፡፡

ፖሊስ ደንበኞቻቸውን በሽብር ተግባር ወንጀል ጠርጥሯቸዋል ቢባል እንኳን፣ በተፈቀደለት የ28 ቀናት ጊዜ ውስጥ ማን በማን ላይና ምን ዓይነት ወንጀል እንደፈጸመ በመለየት በዝርዝርና በተናጠል ለፍርድ ቤት ማቅረብ እንዳለበት በሕጉ ተደንግጎ ቢገኝም፣ 28 ቀናት ቆይቶ ፍርድ ቤት ሲቀርብ ምንም ዓይነት የምርመራ ውጤት አለማቅረቡን አስረድተዋል፡፡

የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤትም የፖሊስ ምርመራ መዝገቦችን አስቀርቦ ከመረመረ በኋላ፣ ምንም ዓይነት ለሽብር ተግባር ወንጀል የጥርጣሬ መነሻ ነገር ባለማግኘቱ፣ ተጠርጣሪዎቹ ከ2,000 ብር እስከ 5,000 ብር በሚደርስ ዋስትና ከእስር እንዲፈቱ ውሳኔ መስጠቱንም ገልጸዋል፡፡ ፖሊስ ‹‹በሽብር ተግባር ወንጀል ጠርጥሬያቸዋለሁ›› በማለት ላሰራቸው የአብን አባላት ያቀረበላቸው ጥያቄ፣ ‹‹ማንን ነው የምትረዱት? ማነው ያሰማራችሁ?›› የሚሉና ‹‹ጠርጥሬያችኋለሁ›› ካለበት መነሻ ሐሳብ ጋር የማይገናኝ መሆኑንም ጠበቆቹ ጠቁመዋል፡፡ ‹‹የአዲኃን ሥልጠና ወስዳችኋል፣ ከእነ ዘመነ ካሴ ጋር ግንኙነት አላችሁ›› የሚሉ የግለሰቦች ወይም የተወሰነ ቡድን ፍላጎትን የሚያንፀባርቁ ጥያቄዎች እንጂ፣ ከሰኔ 15 ቀን የከፍተኛ አመራሮች ግድያ ጋር የሚያያዝ ምንም ዓይነት ምርመራ እንዳልተካሄደባቸውም አስረድተዋል፡፡

አንዳንዶቹ በተለይ ዓቃቤ ሕግ አቶ የወግሰው በቀለና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ባልደረባና የልደታ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምርያ መርማሪ ዋና ሳጅን ሞገስ በቀለ፣ የባልደራስ ምክር ቤት አባል መሆናቸውን ደርሰንበታልና መረጃ ያቀብላሉ›› ከሚል ምርመራ በስተቀር፣ የሽብር ወንጀል ተሳትፏቸው ምን እንደሆነ ያቀረበው የጥርጣሬ መነሻ ማስረጃ እንደሌለም ገልጸዋል፡፡

‹‹የከፍተኛው ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ዋስትና የከለከላቸው አቋም ይዞ ነው፤›› የሚሉት የተጠርጣሪዎቹ ጠበቆች፣ ይኼንንም ሊያስብላቸው የቻለው በዋስ እንዲወጡ በፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት እያንዳንዳቸው የ5,000 ብር ዋስትና ማቅረብ እንዳለባቸው ውሳኔ የተሰጠላቸው፣ አቶ የወግሰው በቀለና ዋና ሳጅን ሞገስ በቀለ፣ ዋስትናቸው ወደ 200,000 ብር ማሳደጉ ማሳያ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ዋስትና ከተፈቀደላቸው ሳምንት ቢሞላቸውም፣ አቅማቸውን ያላገናዘበ ዋስትና በመሆኑ ከእስር ሊለቀቁ እንዳልቻሉም አክለዋል፡፡ ሌላው ጠበቆቹ ያቀረቡት ክርክር ሕጉ ግልጽ ሆኖ ሳለ፣ ለምን ተለጥጦና ለተጠርጣሪ በማይጠቅም ሁኔታ እንደሚተረጎም እንዳልገባቸው ጠቁመው፣ ከሰኔ 15 ቀን የእነ ጄኔራል ሰዓረ መኮንን ግድያ ጋር በተያያዘ፣ ‹‹የገዳዩ ሚስት ናት›› የተባለችና ከግድው ጋር ምንም ግንኙነት የሌላት ሴትም ታስራ እንደምትገኝ ገልጸዋል፡፡ ዳኞቹ የሚሠሩት ለህሊናቸውና ለሕግ ተገዥ ሆነው ቢሆንም፣ የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት በአግባቡ የሰጠውን ውሳኔ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ያገደበትና ከሕጉ ውጪ የሥራ ቀናትን ብቻ በመቁጠር በአጠቃላይ 42 ቀናት የፈቀደበት ሒደት፣ ከሕግ አግባብ ውጪ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡ ፖሊስ ራሱ ጠይቆ የነበረው 28 ቀናት እንደሚበቃው ገልጾ ሲሆን፣ ፍርድ ቤቱ 42 ቀናት መፍቀዱ ለምንና በየትኛው የሕግ አግባብ እንደሆነ ግልጽ አለመሆኑንም አክለዋል፡፡ አዴፓ ‹‹እርስ በርሳችን ተጠፋፋን›› እያለ ከ30 በላይ ንፁኃን ዜጎችን ማሰር፣ ተገቢ አለመሆኑንም ገልጸዋል፡፡ መፈንቅለ መንግሥት መሆኑ የተገለጸበትን ድርጊት የሽብር ተግባር ወንጀል በማለት ዜጎችን ያላግባብ ማሰር ሆን ተብሎ ሰብዓዊ መብታቸውን ላለማክበር የተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ጠበቆችን ጭምር በነፃነት እንዳይከራከሩና እንዳይናገሩ ጫና በማድረግ፣ በክርክሩ ወቅት ያነሷቸውን መከራከሪያ ሐሳቦች እንኳን እንዳልመዘገበላቸውም አስረድተዋል፡፡ በአጠቃላይ ደንበኞቻቸው ታስረው የሚገኙበት ጉዳይ እንኳን በሽብር ተግባር ወንጀል፣ በተራ ወንጀል እንኳን ሊያስጠረጥር እንደማይችል የተጠርጣሪዎቹ ጠበቆች በክርክራቸው አስረድተዋል፡፡

ከሰኔ 15 ቀን ከፍተኛ የመንግሥት አመራሮች ግድያ ጋር በተያያዘ በሽብር ተግባር ወንጀል ተጠርጥረዋል ስለተባሉትና ይግባኝ ስለጠየቁት ተጠርጣሪዎች፣ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ቀርቦ ምላሽ የሰጠው (የተከራከረው) የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል መርማሪ ሳይሆን ዓቃቤ ሕግ ነው፡፡ በዕለቱ የቀረቡት ሁለት ዓቃቢያነ ሕግ እንዳስረዱት፣ እያንዳንዳቸው ተጠርጣሪዎች ከሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. በፊት ሲደራጁ ቆይተው፣ በተለያዩ አቅጣጫዎች በመንቀሳቀስ ግድያው እንዲፈጸም አድርገዋል፡፡ ይኼ ሁኔታ በተፈጸመበትና ፖሊስ ስለሁኔታው በማጣራት ላይ እያለ፣ የፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ተጠርጣሪዎቹ በዋስ እንዲወጡ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

ፍርድ ቤቱ ድርጊቱን ‹‹ተራ የፖለቲካ ሽኩቻ ነው›› በማለት የዳኛውን ገለልተኛነት የሚያጠራጥር መሆኑንም አክለዋል፡፡ ዓቃቢያነ ሕጉ እንዳብራሩት የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት የምርመራ መዝገቡን ወስዶ ለሳምንት ማቆየቱና አልመልስም በማለቱ፣ እጃቸው ላይ በነበረ ሰነድ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ ብለው፣ የተጠርጣሪዎቹ የዋስትና መብት እንዲታገድ ማድረጋቸውን አስረድተዋል፡፡ በተለይ አራት ተጠርጣሪዎች በኅቡዕ ጦር እየመሩ እንደነበርና መረጃ ሲለዋወጡበት የነበረን ማስረጃ ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ጠይቀው በመጠባበቅ ላይ እያሉ፣ ዋስትና መፍቀድ ተገቢ አለመሆኑንም ዓቃቢያነ ሕጉ ተናግረዋል፡፡

በግለሰብ እጅ ሊገባ የማይችል የጦር ሜዳ መነጽር መገኘቱንም ገልጸዋል፡፡ በአዲስ አበባ በወታደራዊ አመራሮች ላይ ግድያ ሲፈጸም የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲቋረጥ ግዳጅ የተሰጣቸው፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ሠራተኞች መያዛቸውንም ገልጸዋል፡፡ የጦር መሣሪያ መግዛቱንና 6,000 ጥይቶች ቢኖሩትም ከጎንደር እንዴት እንደሚያሳልፈው ምክክር ሲያደረግ የነበረ ተጠርጣሪና ሌሎችም፣ በኅቡዕ ተደራጅተው በእነማን ላይ ዕርምጃ እንደሚወስዱ ሥልጠና ጭምር የወሰዱ ተጠርጣሪዎች መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡ ይኼ ሁሉ ባለበት ገና በምርመራ ላይ እንደሆኑ እየገለጹ የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ዋስትና መፍቀዱ ተገቢ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡ በአጠቃላይ ከሰኔ 15 ከፍተኛ አመራሮች ግድያ ጋር በተያያዘ የሽብር ተግባር ስለመፈጸሙ ከተለያዩ የመንግሥት ተቋማት ጋር እየሠሩ እያለ፣ የወንጀል ተግባሩን በመቀየር ዋስትና መስጠቱም ተገቢ አለመሆኑን ዓቃቢያነ ሕጉ ደጋግመው አስረድተዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ በመሀል፣ ‹‹በመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት በእያንዳንዱ ተጠርጣሪ ላይ ለወንጀል ጥርጣሬ መነሻ የሚሆን የምርመራ ውጤት አቅርባችሁ ነበር?›› የሚል ጥያቄ ለዓቃቢያነ ሕጉ አቅርቦላቸው፣ ማን ከማን ጋር ግንኙነት እንደነበረው በቂ መጠርጠሪያ ማቅረባቸውን ተናግረዋል፡፡ ቀሪ መረጃና ማስረጃ በመሰብሰብ ላይ እንደሆኑም ማስረዳታቸውን ከኢትዮ ቴሌኮም፣ ከባንክ፣ የባልደራስ ምክር ቤትን እንደ ሽፋን በመጠቀም ወንጀል መፈጸማቸውን ለማሳየት ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት መረጃ መጠየቃቸውን ቢገልጹም፣ ፍርድ ቤቱ እንዳልተቀበላቸው አስረድተዋል፡፡

ከፍተኛው ፍርድ ቤት ግን ያቀረቡትን የይግባኝ አቤቱታ በሚገባ ከተመለከተ በኋላ፣ ዋስትናውን እንደሻረውም አክለዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ በመቀጠል፣ ‹‹እናንተ (ዓቃቢያነ ሕጉ ወይም ፖሊስ) 28 ቀናት የምርመራ ጊዜ ጠይቃችሁ ከፍተኛው ፍርድ ቤት እንዴት ከዚያ በላይ ሊፈቅድ ቻለ?›› በማለት ሲጠይቃቸው፣ ችሎቱ የበዓል ቀናትን ትቶ የሥራ ቀናትን ብቻ በመቁጠር መስጠቱን ጠቁመው ስህተት ከሆነ ሊታረም እንደሚችል ተናግረዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ በመቀጠል፣ ‹‹ከሰኔ 16 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ በምርመራ ላይ ከሆናችሁ እንዴት እስካሁን አልጨረሳችሁም? አሁንስ በምን ላይ ናችሁ?›› የሚል ጥያቄ አቅርቦላቸው፣ ተጠርጣሪዎቹ ሲዘጋጁ የከረሙት ከጥቅምት ወር 2011 ዓ.ም. ጀምሮ መሆኑን፣ በቤንሻንጉል ጉምዝ ዋና ከተማ በአሶሳና በአዲስ አበባ የተፈጸመውን ሁሉ ማጣራት ስላለባቸው፣ እየሠሩና የጠየቁት ለመረጃ እስከሚመጣላቸው እየጠበቁ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የተጠርጣሪዎቹ ጠበቆች በተሰጣቸው ድጋሚ የመከራከሪያ ዕድል እንዳስረዱት፣ ዓቃቤያነ ሕጉ የምርመራ መዝገቡ በመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ስምንት ቀናት በዳኛ ዕግድ መቆየቱን ለችሎቱ መግለጻቸው፣ ከአንድ ከፍተኛ የሕግ ተቋም የማይጠበቅ ምላሽ ከመሆኑም ባለፈ ግምት ውስጥ የሚከት መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ፖሊስ የራሱን ዋና የምርመራ መዝገብ ይዞ ለፍርድ ቤት የሚያቀርበው ደግሞ ግልባጩን (ኮፒ) መሆኑን ጠቁመው፣ መዝገቡ ዳኛው ዘንድ ስምንት ቀናት መቆየቱንና ‹‹አልሰጥም አሉኝ›› የሚል ሰበብ ማቅረብ ተገቢ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡

ሌላው ዓቃቢያነ ሕጉ የምርመራ መዝገቡ አካል ያልሆነን ጉዳይ ‹‹አሶሳ ከተማ የተፈጸመን ድርጊትም እየመረመርኩ ነው›› ማለቱ የማይገናኝ ነገር ለማገናኝት መሞከር መሆኑንም አክለዋል፡፡ የጦር ሜዳ መነጽር ይዘው ተገኝተዋል በማለት ዓቃቢያነ ሕጉ ተጠርጣሪዎቹን ለመወንጀል ያደረገው ጥረት፣ ‹‹መነጽር አይደለም ታንክ ይዘው ቢገኙ ሽብር ነው ማለት ነው?›› በማለት ጠይቀው፣ ፍርድ ቤቱ መዝገቡን አስቀርቦ እንዲያይላቸው ጠይቀዋል፡፡ ተገኘ የተባለው የጦር ሜዳ መነጽር የዩኒቨርሲቲ ማስተማሪያና ከመምህር ቤት የተገኘ መሆኑንም አክለዋል፡፡ በኅቡዕ ተደራጅተው ጦር ሲመሩ ነበር የተባሉት ደንበኞቻቸው ጫማ የሚጠርጉ ሊስትሮዎች፣ የቤት ሠራተኞችና የፖለቲካ ድርጅት አባላት መሆናቸውንም አክለዋል፡፡

ግድያው ሰኔ 15 ቀን ተፈጽሞ ደንበኞቻቸው ሰኔ 16 ቀን መያዛቸው የሚገርም እንደሆነ የገለጹት ጠበቆቹ፣ ይኼ የሚያሳየው እነሱን ለመያዝ ዝርዝር ተይዞና ቀደም ብሎ ዝግጅት መኖሩ የሚያረጋግጥ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት የሽብር ተግባር ወንጀል አያስቀጣም ሳይሆን፣ በአዋጅ ቁጥር 652/2011 አንቀጽ (19) መሠረት ሊያስጠረጥራቸው የሚችል ማስረጃ እንዳልተገኘባቸው ወይም ፖሊስ በተሰጠው የ28 ቀናት የምርመራ ጊዜ ሊያቀርብ እንዳልቻለ መግለጹ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ ዓቃቢያነ ሕጉ ተጠርጣሪዎቹ የጦር ሥልጠና ሲያደርጉ እንደነበር መግለጻቸው ስህተት መሆኑን ጠበቆቹ ጠቁመው፣ መንግሥት ራሱ በጀት መድቦ ሲያሠለጥናቸው የነበሩ መሆናቸውን አክለዋል፡፡ በአጠቃላይ ፖሊስ እንኳን ማስረጃ ሊያቀርብባቸው ቀርቶ ቃላቸውን እንኳን እንዳልተቀበላቸውም ጠቁመዋል፡፡

ተጠርጣሪው ዓቃቤ ሕግ አቶ የወግሰው በቀለ ለሥር ፍርድ ቤቶች ከታሰረ 50 ቀናት እንደሞላው ሲያስረዳ፣ ፍርድ ቤቱ ለምን ምርመራ እንዳልጨረሰ ፖሊስን ሲጠይቀው፣ የባልደራስ ምክር ቤት አባል መሆኑን ስለደረሰበት እያጣራ መሆኑን እንደገለጸም አስታውሰዋል፡፡

የግራ ቀኙን ክርክር የሰማው የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት መርምሮ ውሳኔ ለመስጠት ለነሐሴ 22 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

Ethiopian Reporter

Leave a comment