የማለዳ ወግ…ለተሃድሶ ጀማሪዎች ለጅዳ ቆንሰል ተማጽኖየ !
* ፖለቲካውን እንደርስበታለን መብት በማስከበሩ ላይ በርቱ
ሰሞነኛ ወጋችን ፍተሻ ፣ አሰሳ ፣ ማጣራት ሆነና ልብን በሃዘን የሚሰብሩት ጩኸት እንዳይረሳ ሰጋሁ ። ለነገሩ የሳውዲ መገናኛ ብዙሃን በሚለቋቸው መረጃዎች ልክ መረጃ ተለዋውጠናል ባይባልም ፣ ያለፈውን አመትና የቆየውን ሁከት የሚያሳይ የቆየ ተንቀሳቃሽ ምስል እየለጠፉ የቆየነው አዲስ ነው ሳይሉና ሳያሳውቁን መረጃውን የሚለቁ የራሳቸን ሰዎች ተበራክተዋል። በዚህም ፍተሻ አለ የለም ወደሚለው አተካራ እየተዶልን ይመስላል። ተወደደም ተጠላ የሰው ሃገር የሰው ነው ፣ ሳውዲዎች በሃገራቸው ሰማይ ስር እንኳንስ በአደባባይ በተናገሩት ጊዜ ባሻቸው ጊዜ ህገ ወጥ ያሉትን ይዘው የማባረር መብት አላቸው ። አለመቀደም ነው እንጅ ሲላቸው ም የጠራረጉትን ጠራርገው ሲያበቁ ሁሉ ትተው የምህረት አዋጅ ሲሉ እናውቃለን ። ይህ ሲወርድ ሲዋረድ የምናውቀው አሰራራቸው ነው ። የዘንድሮውን ለየት የሚያፈርገው ” የምህረት አዋጅ የሚባል ነገር አይታሰብም “ማለቱ አይደለም ። ይልቁንም ስራቸውን በጣም በተረጋጋ ሁኔታ የመብት ጥሰት እንዳይኖርና ማህበራዊ ገጾች ጥሰቱን እየተቀባበሉ እንዳያወግዟቸው በጥንቃቄ እየተሰራ መሆኑን ልብ ብለን የግንባር ስጋ ከመሆን ካመለጥን መልካም ነው !
ከሰሞነኛው መረጃ ቅበላ ጎን ለጎን በተለያዪ አላባቢዎች ያሉ ወዳጆቸ ከሚያደርሱኝ መረጃዎች መካከል ሰሞነኛው የአፈሳ ፣ እስራት ፣ ማጣራቱ መረጃ ከአዕምሮየ አላዳፍን ያላቸውን የሚያሙ ግን ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገባ ጉዳዮችን ማንሳት ወደድኩ ! ለዚህ የማለዳ ወግ መነሻ የሆነኝ ባሳለፍነው ሳምንት የዲያስፖራ ምክር ቤት የሚሉትን ለማቋቋም ከተሰበሰቡት የድርጅት ሰዎች አጠራርና የህዝብ ውክልና ጉዳይ ነው። ከአንድ አፍቃሬ ህወሃት ወዳጀ ጋር በዚህ ዙሪያ ስናወጋ ” ያን ሰሞን ተሃድሶ አድራጊውን ቆንስል እንዳላመሰገንክ ዛሬ በዲያስፖራው ጉዳይ ነካከህው! ” ነበር … ቀድሞውንም አሁንም በማይረባውና በማንግባባበትን የፖለቲካ ጉዳይ እንደርስበታለን መብት በማስከበሩ ላይ ግን ኢህአዴግ ምንቴስ ሳንል እንትጋ ፣ በርቱ እንበርታ ስል ባደረግነው ማሳረጊያ ተገወባባን … እናም ሰሞነኛ የመረጃ ግብአቱ ቦታውን ሳያጣብበው ለተገፋት የወገኖቻችን መብት እንደጋገፍ እንበርታ ስል የደረሰኝን መረጃ ተከትሎ በውስጤ ከሚጉላሉት ብዙ አሳዛኝ ታሪኮችን በጨረፍታ ዳስሸ መብት በማስከበሩ ረገድ መስማት የጀመሩት የጅዳ ቆንስል ተወካዮቻችንን ለመብታችን መከበር ጽኑልን ስለ መማጸን ፈለግኩ …
የሰሚራ ጉዳት …
ባሳለፍነው አንድ ቀር ገደማ በጥይት ተመታ በቢሻ ሆስፒታል በጥይት ተመታ ቆስላ በሆስፒታል ስለምትገኘው እህት ጉዳይ በማህበራዊ መረጃ መረቡ በኩል መረጃው ሲሰራጭ እኔም እጅ ገባ ። ብዙም ሳይቆይ በየድህረ ገጾች ተለቀቀ ። እኔም መረጃውን ለማጣራት ያፈረግኩት ሙከራ በተሳካ ማግስት በጅዳ የጅዳ ቆንስል መስሪያ ቤት ወደ ቦታው በማቅናት ተጎጅዋን ማግኘታቸውን፣ ማነጋገራቸውንና ጉዳዩን እየተከታተሉት የመሆኑን የምስራች አበሰሩን ፣ ደስም አለን! ምስጋናም አቀረብን !
ይህ ከሆነ ከሳምንት በኋላ የሰሚራን ጉዳይ ለመከታተል ስሞክር በመረጃ አሰባሰቡ ዙሪያ ያልጠበቅኩት ችግር መከሰቱን ሰማሁ ፣ ረፋዱ ላይ ወደ ጅዳ ቆብስል ጎራ በማለት ጉዳዩን ከያዙት ዲፕሎማት የደረሰኝን መረጃ መሰረት በማድረግ ለማጣራት ብሞክርም ሃላፊው ለስራ ስለወጡ ማግኘት አልቻልኩም ። ያም ሆኖ በቦታው ላገኘኋቸው መልዕክቴን አስተላልፊ ተመለስኩ ! ይህ በእንዲህ እንዳለ በጉዳዩ ዙሪያ ያናከርኩት አንድ ወዳጀ በደረሰኝ መረጃ ዙሪያ አንድ ወንድም ዘርዘር ያለ መረጃ ያለው መልዕክት ከነ ተንቀሳቃሽ ፊልም ጭምር የያዘ መረጃ ማስተላለፉን ጠቆመኝ ። መረጃውን ከያዘው ወንድም መረጃ ትመለከቱት ዘንድ ከዚህ ገሰር አያይዠዋለሁ !
ሩቅያ …
ከወራት በፊት እዚህ ጅዳ ውስጥ በአንድ ት/ቤት የቅርብ ርቀት በተከሰተ የመኪና አደጋ የአሰሪዎቿን ልጆች ለማዳን ስትል ለከባድ አደጋ የተጋለጠች ሩቅያ የተባከች እህት አሳዛኝ ታሪክ አውቃለሁ። የሩቅያ ታሪክ በአረብ መገናኛ ብዙሃን ሳይቀር ቀርቧል። ከአደጋው በኋላ ራሷን የማታውቀው ሩቅያ በአንድ ሆስፒታል ለወራት ስትታከም ቆይታ ” ከህመሟ አገግማለች !” ተብሎ ከሆስፒታል ወጥታለች ። ያለ ወገን ደገሰፊ አምስት እህት ወንድሞችዋን የምታስተምር ትጉህ ክጅ አግር ናት ሰሚራ። ለህክምና ብትወጣም እርዳታ በማድረግ አንዳንድ ኢትዮጵያውያን ነዋሪዎች ግን አልረሷትም ። አደጋ ያደረሰባት ደግሞ ከእስር ወጥቷል ። እንዴት ወጣ አይታወቅም ። በውል ቋሚ የሆነ የሚደግፍ የሚረዳት ግን የለም ። ጉዳዩን በፊት ገጼ ካቀረብኩት በኋላ ለጅዳ ቆንስል አሳውቄ ነበር ። በወቅቱ ሄደው ጠይቀዋታል።እየተመላለሱም ጉዳዩን የተከታተሉ መሆኑን የገለጹልኝ የጅዳ ቆንስል ባለደረባ የሩቅያን ጉዳይ እንዳልረሱት ከቀናት በፊት አጫውተውኛል ። ይሁን … ብዙዎች ግን የሩቅያ ጉዳይ ተድበስብሶ እንዳይቀር እንማጸናለን !
መሐመድ …
መሃመድ ይባላል ፣ በ3 አመት የብላቴና እድሜው ድክ ድክ እያለ ለቀላል ቀዶ ህክምና ወደ ሃኪም ቤት ገባ ፣ ከቀዶ ጥገናው ክፍል ከገባ ከሰአታት በኋላ ከቀዶ ህክምናው ቢወጣም አልነቃ አለ። ሰአታት ተቆጠሩ ፣ ቀኖች ሲከተሉ ጉዳይ አስደንጋጭ እየሆነ መጣ ! ወላጅና የቤተሰብ አባላት የሚይዙ የሚጨብጡት ጠፋባቸው። ህክምናውን ያከናወኑት የሚሰጡት የተስፋ መልስ ጭብጥ እውንት ጠፋበት … ቀናት በቀናት ተተክተው ሳምታት ወርን ሲወልዱ የብላቴናው አለመንቃት በሆስፒታሉ ሃኪሞች ስህተት እንደሆነ ይፋ ተነገረ ! ይህ ሲሆን ታዲያ ከሆስፒታሉ የተሰጠው ምላሽ አስደንጋጭ ነበር ። የሶስት አምት ልጃቸው መሃመድ በህክምና ስህተት ማደንዘዣ በዝቶበት እንዳልነቃነና ይህን ስህተት የፈጸመው ዶር ከስራው መባረሩ ተገልጾላቸው መሃመድ እስኪነቃ አስፈላጊ ህክምናና ክፍል ተሰጥቶት ህክምናውን በነጻ እንደሚቀጥል ለወላጆች መርዶ ተነገራቸው ! ይህንን በደል ለማሰማት ወላጆቹ ከጅዳ ቆንሰል ከፍ እስካሉ የመንግስት መ/ቤቶች ቢደርሱም ሰሚ አላገኙም። እንዲያ ሆኖ ብላቴናው ከሰመመንና ከተኛበት አልጋ ሳይነቃ 11 ኛ አመቱን ዘንድሮ ይዟል …
ጉዳዩ አሳዛኝ ነው ከማለት በላይ ነው … ይህ በደል ወደ ሳውዲ ከፍተኛ የመንግስት አካላት ስለመታወቁ ግን አሁንም እጠራጠራለሁ ፣ ይህንኑ ለማጣራት አምድ ወዳጀ ከቤተሰብ አባላቱ ጋር ሊያገናኘኝ ቃል ገብቶልኛል። ያ ሙሉ አሳዛኙን መረጃ በዝርዝር እናወጋዋለን ! .. ባሳለፋቸው የብላቴናውና የወላጆቹ አስከፊ የጨለማ የመከራ አመታት ብላቴናውን የአልጋ ቁራኛ ህክምና በሚሰጠው ክፍል ሄጀ ለማየት ካንድም ሁለት ሶስቴ በሩ ላይ ደረስ ደርሸ ህመሙን መቋቋም ሳልችል ቀርቸ ሳላየው ተመልሻለሁ ! መውለድ ከባድ መሆኑንም የተረዳሁት ያኔ ነበር … የመሃመድ ጉዳይ በአንባሳደር ተክለአብ በአንባሳደር መርዋን እና በቆንስል ጀኔራል ዘነበ እየታወቀ እልባት የሚሰጥ የሚከታተለው ጠፍቶ ጉዳዩ ተድበስብሶ እዚህ ደርሷል ። ይህም ያማል ! ዘንድሮ ግን በቆንስሉ ትጉህ የተሃድሶው መሪዎች መፍትሔ ያገኙለት ዘንድ እንማጸናለን !
ስላለፈው ወቃሹ ታሪክ እንጅ እኛ አይደለንም፣ አንወቃቀስም …
የጀዛኑን ካልድ ለሶስት አመታት የቀጠለ አበሳ ሰሞኑን እልባት ሊያገኝ መሆኑን ሰምቻለሁ ፣ በካልድም ጉዳይም ሆነ በስም አይጠሬውን የአንድ እህት ሬሳ ታሪክ የምናወራው ዛሬ አይደለም ፣ አልነካካውም ! ስላለፈው መብት ጥሰትና የመብት ጥበቃ ጉድለት መረጃዎችን ከመሰብሰብ አልፈን ፣ ያለፈውን ጉዳይ እያነሳን መወቃቀሱ አይጠቅምም !
ዛሬ ሌላ ቀን ነው ፣ ላለፉት 11 ዓመታት እልባት ካልተሰጠው ከመሃመድ ጉዳይ ጀምሮ እስከ ጀዛኑን ካልድ ፣ በአሰሪዋ የፈላ ውሃ የተደፋባትና ላለፉት አንድ አመት ጉዳዩዋን በጅዳ ቆንስል ሆና የምትከታተለው የሄለን ጉዳይ ፣ በቅርብ በጥይት ከተመታችው የሰሚራ ጉዳይ እና መኪና ተገጭታ አካሏ እስከ ጎደለው ሩቅያ የዜጎችን መብት ለማስከበር የመንግስት ተወካዮች የተከፈተው በር እንዳይዘጋ ስንማጸን ፣ መረጃዎችን በማሰባሰቡ ረገድ ግልጽ መረጃ በመለዋዎጥ የመንግስት ተወካዮች መብታችም ያስከብሩልን ዘንድ ደጋግሜ እማጸናችኋለሁ !
በኢትዮጵያ መንግሥት የሳይበር ጥቃት መፈፀሙ ይፋ ተደረገ
የኢትዮጵያ መንግስት የመረጃ ጠለፋ መፈጸሙን እንደገፋበት ሂዩማን ራይትስ ዎች ተናገረ፡፡ የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ ድርጅት ዛሬ ይፋ አንዳደረገው ከሆነ መንግስት ቀስ በቀስ ጋዜጠኞችን ጸጥ ያደርጋል እንዲሁም የዲጂታል ጥቃት ይፈጽማል ሲል ገልጿል፡፡
ባለፈው አመት “ዘይ ኖው ኤቭሪቲንግ ዊ ዱ፤የኢንተርኔትና የቴሌኮም ስለላ በኢትዮጵያ” ሲል ቡድኑ ባወጣው ዘገባ የኢትዮጲያ መንግስት በዜጎቹ ላይ የቴሌኮምና የመረጃ መረብ እያንዳንዱን ሚስጥራቸውን ይበረብራል ማለቱ አይዘነጋም፡፡
ዘንድሮም በተመሳሳይ መንግስት ይህን ድርጊት መፈጸሙን አጠናክሮ እንደቀጠለ የሚናገረው ቡድኑ በውጪ የሚኖሩ ነጻ ጋዜጠኞች ላይ ሳይቀር የሳይበር ጥቃት ይፈጽማል በማለት አትቷል፡፡
መሰረቱን በካናዳ ቶሮንቶ ያደረገ አንድ ገለልተኛ አጥኚ ቡድን ሰሞኑን በአንድ የሚዲያ ተቋም ላይ መንግስት የሳይበር ጥቃት መፈጸሙን ማረጋገጡን የሚገልጸው ሂዩማን ራይትስ ዎች ለኢትዮጵያ መንግስት የመረጃ መረብ መጥለፊያና ጥቃት መፈጸሚያ ምርቶችን የሚሸጡ አለም አቀፍ ኩባኒያዎች ድርጊቱን እንዲያጣሩ፤ድርጊቱን ፈጻሚው መንግስትም በአስቸኳይ ከድርጊቱ እንዲታቀብ አሳስቧል፡፡
ይህን የሂዩማን ራይትስዎች መረጃ ተከትሎ በርካታ አለም አቀፍ ሚዲያዎች ባወጡት ዘገባ የኢትዮጵያን መንግስት አውግዘዋል፡፡
ባለፈው አመት የኢትዮጵያ መንግስት ከአንድ የጣሊያን የደህንነት ተቋም በውጪ የሚኖሩ ጋዜጠኞችን ለመሰለል የሶውትዌር ምርት እንደገዛ በአንድ ገለልተኛ ቡድን ምርመራ መረጋገጡን በመጥቀስ ዘገባውን የሚጀምረው ማዘርቦርድ የተባለው የወሬ ምንጭ ይሁን እንጂ ዘንድሮም በተመሳሳይ መንግስት የሳይበር ጥቃቱን ቀጥሎበታል ሲል ያትታል፡፡ በዚህም ሰለባ ከሆኑት መካከል የኢትዮጵያ ሳተላይት ሬዲዮና ቴሌቪዥን(ኢሳት) እንዲሁም በውጭ የሚኖሩና በስራ ላይ ያሉ የኢትዮጵያውያን ነፃው ፕሬስ ጋዜጠኞች እንደሚገኙበት መዘገቡ አይዘነጋም፡፡
ይህን በሚመለከት ተመሳሳይ ዘገባ ይዞ የወጣው ዋሽንግተን ፖስት በበኩሉ የኢትዮጵያ መንግስት በውጪ ያሉ ነጻ ጋዜጠኞችን በሽብር ይከሳል አልፎ ተርፎም የሚያሰራጯቸውን የሚዲያ አገልግሎቶች ጃም በማድረግና በሳይበር ጥቃቶች ለማፈን ይሞክራል ማለቱን ድሬ ቲዩብ ዘግቧል፡፡
በአዲስ አበባና በክልሎች በርካታ ኢትዮጵውያን ሙስሊሞች በመንግሥት እየታሰሩ መሆኑ ተሰማ
ከጥር 2004 ዓ.ም. ጀምሮ በሀገር አቀፍ ደረጃ በይፋ የኃይማኖት ነፃነት መብትና ህገ-መንግሥቱ እንዲከበር፤ በሰላማዊ መንገድ እየጠየቁ የሚገኙት የኢትዮጵያ ሙስሊሙ ማኀበረሰብ የመንግሥትን ህገወጥ እርምጃ ተቃውሞ መቀጠሉን ተከትሎ፤አሁንም በያዝነው የካቲት 2007 ዓ.ም. ከየቤቱና ከስራ ቦታ ጭምር የጅምላ እስሩ ተጠናክሮ መቀጠሉን ከአዲስ አበባና ከተለያዩ የክልል ከተሞች የሚመጡ መረጃዎች ጠቁመዋል፡፡ በተለይ በአዲስ አበባ የመንግሥትን ያይል እርምጃ እና የኃይማኖት ነፃነት መብታቸው እንዲከበርና መንግሥትም ከኃይማኖት ጣልቃ ገብነት እንዲወጣ በተደጋጋሚ መጠየቃቸውን ተከትሎ ሰሞኑን የጅምላ እስር እየተካሄደ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
የጅምላ እስሩ እየተከናወነ የሚገኘው መንግሥት በመጪው ምርጫ 2007 ዓ.ም. ከሙስሊሙ ማኀበረሰብ ድጋፍ እንደሌለው በመረዳቱና በርካቶችም የድምፅ መስጫ በረቀት መውሰዳቸው የደረሰው መረጃ አስደንግጦት እንደሆነ ቢጠቆምም፤ ከመንግሥት በኩል ግን እየተወሰደ ስላለው የጅምላ እስር የተሰጠ ምንም ዓይነት ማብራሪያም ሆነ ምላሽ ማግኘት አልተቻለም፡፡ በተለይ ሰሞኑን በተወሰደውና እየተወሰደ ባለው የጅምላ እስር ተጠናክሮ መቀጠሉን ከመጠቆም ባለፈ፤እስካሁን ምን ያህል ሰዎች እንደታሰሩ ግን ለማወቅ አልተቻለም፡፡
ከዚህ ቀደም መንግሥት የኢትዮጵያ ሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴው ጋር ሲደራደር ቆይቶ፤ በመጨረሻም በጅምላ በማሰር የሽብር ክስ መስርቶባቸው የኮሚቴው አባላት ያለምንም ፍትህ እስካሁን በእስር ላይ እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡
በየመን የኢትዮጵያ ኤምባሲ፤ ዜጎች ወደ ሀገር መግባት የምትፈልጉ ተመዝገቡ ሲል ጥሪ አስተላለፈ
ግሩም ተ/ኃይማኖት
(ከየመን)

በየመን ሰነዓ ያለ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጥሪ አስተላለፈ፡፡ “..አሁን በየመን ውስጥ ያለው ሁኔታ አስጊ ነው፡፡ ማኛውችሁም ወደ ሀገር መግባት የምትፈልጉ ዜጎች ሁሉ ተመዝገቡ እና ተዘጋጅታችሁ ተቀመጡ፡፡ ችግር በሚነሳ ሰዓት ወደ ሀገር እንድትገቡ ኤምባሲው አገልግሎት ይሰጣል፡፡ ዜጎቹን በትኖ ኤምባሲው ስለማይዘጋ አለን…ተመዝገቡ፤ እስከ መጨረሻው ዜጋዎቻችንን ሳናወጣ ኤምባሲውን አንዘጋም…” ማለታቸው በየመን በስደት ለሚኖሩ ኢትዮጵውን ደስታ እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡
በአሁኑ ሰዓት የመን ያለችበት የከፋ የፖለቲካ ውጥረት አስፈሪ እና በከፍተኛ ሁኔታ የእርስ በእርስ ጦርነት ያስከትላ ተብሎ ተፈርቷል፡፡ አንዳንዶች ከሶማሊያ በከፋ ሁኔታ በዘር፣ በጎሳ የመከፋፈል ግጭት ይካሄዳል ብለው ይገምታሉ፡፡ በእርግጥም አይቀሬ አይነት እየሆነ ነው ያለው፡፡ ከ16 በላይ ኤምባሲዎች ዘግተው ወጥተዋል፡፡ UNHCR ስደተኛውን በትኖ ሰራተኞቹን አውጥቷል፡፡ ጥቂት የመናዊያን ሰራተኞች ብቻ ናቸው ያሉት፡፡ ማንኛውም መንግስታዊ ተቋማት ወለም ዘለም፣ አገም ጠቀም አይነት ነው አስራራቸው፡፡ ፈራ ተባ እያሉ…ነው ሂደታቸው፡፡
ተቃውሞውና ድጋፉ በማይለይበት ሁኔታ ሰላማዋ ሰልፈኞች በከተማዋ በተለያየ አቅጣጫ ብቅ ጥልቅ ይላሉ፡፡ መሳሪያ በታጠቁ ወታደሮች እና የሁቲ አማጺሚሊሻዎች ከተማዋ ተወጥራ የሞት አረማሞዋን የምታዜም…የማትወልደው ምጥ የምታምጥ መስላለች፡፡ ይህ ሁኔታ ፍርሃት ያልፈጠረበት ሀገር ዜጋ የለም፡፡ አሜሪካን የመን ሰነዓ ከተማ ውስጥ የነበረውን ሼራተን ሆቴል ተከራይተው ወታደራዊ ቤዝ አድርገው የነበሩ ወታደሮቻቸውን አንስተው ኤምባሲውን ዘግተው ያላቸውን መረጃ ሁሉ አጥፍተው ወጥተዋል፡፡ ሌላው ቀርቶ አውሮፕላን ማረፊያ ድረስ በሰው አልባ የጦር ጀት ታጅበው ነው የሄዱት፡፡ በሰላም ከየመን ምድር ወጥተዋል፡፡ ሌሎች ሀገራትም ተመሳሳይ ዜጎቻቸውን የማውጣት ስራ ሰርተዋል እየሰሩም ነው፡፡ ኢትዮጵያ ኤምባሲም ዜጎቼ ሆይ ሲል መልዕክት አስተላልፏል፡፡ በየመን በርካታ ኢትዮጵያውያን በስደት ላይ እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡
በየመን ሰነዓ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ኤምባሲን ጥሪ አስመልክቶ ጋዜጠኛ ግሩም ከየመን “በእውነቱ ይህ እሳቤ ራሱ የሚያስመሰግን መሆኑ አይካድም፡፡ ሁሉ ዜጎቹን የበተነ ላለመሆን ይህ በጎ ጅምር ነው፡፡ ‘..ኑ!! ተመዝገቡ፡፡..’ የሚለው ጥሪ ለቦንድ ወይም ለእከሌ ልማት ማህበር ክፈሉ ለማለት ሳይሆን ህይወታችሁን አድኑ በመሆኑ ከልብ ያስመሰግናል፡፡” ሲል በፌስ ቡክ ገፁ አስፍሯል፡፡
የኢትዮጵያ ቤተ እስራኤላውያን ሴቶች የወሊድ መከላከያ እንዲወስዱ ተገደዋል መባሉን እስራኤል አመነች
ከኢትዮጵያ የተወሰዱ ቤተ እስራኤላውያን ሴቶች ለረዥም ጊዜ የሚያገለግለውን ዴፖ ፕሮቬራ የተባለ የወሊድ መቆጣጠሪያ መድሃኒት ለመወጋት ካልተስማሙ ወደ እስራኤል ሊገቡ እንደማይችሉ ይነገራቸው እንደነበር ይታወቃል።
ክሊኒኩን ያስተድድር የነበረው “Joint Distribution Committee” እና የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ውንጀላውን ማስተባበላቸው የሚታወስ ቢሆንም ዛሬ በወጣው ሪፓርት የእስራኤል መንግስት ውንጀላውን አምኗል።
በርካታ ሴቶች፣ በኢትዮጵያ ጊዜያዊ መጠለያ ውስጥ ሳሉ በክትባት መልክ የሚሰጠውን የወሊድ መቆጣጠሪያ መድኃኒት እንዲወስዱ እንዴት ያግባቧቸውና ያስፈራሯቸው እንደነበር ተናግረዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን ቤተ-እስራኤላውያኑ ሲገልፁ “የማትወስዱ ከሆነ ወደ እስራኤል አትሄዱም፤ እርዳታና ህክምናም አታገኙ ተባልን፡፡ ይሄኔ ፈራን፤ ምንም ምርጫ አልነበረንም፡፡ ያለ እነሱ እርዳታ መውጣት አንችልም ነበር፡፡ ስለዚህ ክትባቱን ለመወጋት ተስማማን፡፡” ሲሉ ቤተ-እስራኤላውያን መናገራቸውን የሀገሪቱ መገናኛ ብዙኃን በመጥቀስ ዎርልድ ቡሌቲን ዘግቧል፡፡ ቤተ-እስራኤላውያኑ ከዚህ ቀደም በእስራኤል መንግሥትና ቀድመው እስራኤል በገቡ ዜጎች ከተለያዩ ማኀበራዊ የመንግሥት አገልግሎቶች ጭምር ይገለሉ እንደነበር መዘገቡ አይዘነጋም፡፡




