Category Archives: News

የጋምቤላ ክልል የልዩ ኃይል ፖሊስ አዛዥን ጨምሮ በርካታ ባለሥልጣናት ተከሰሱ

በታምሩ ፅጌ

-79 ሰዎች መሞታቸውና 13,034 ነዋሪዎች መፈናቀላቸው በክሱ ተጠቅሷል

 

ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ወደ ጋምቤላ ክልል በመሄድ በማዣንግ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች በሕጋዊ መንገድ ሠፍረው ለበርካታ ዓመታት ሲኖሩ የነበሩ የሌላ ብሔር ተወላጆችን በአካባቢው አጠራር ‹‹ደገኞች›› የሚሏቸውን በመግደል፣

ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት በማድረስና በማፈናቀል የተጠረጠሩ፣ የጋምቤላ ክልል የልዩ ኃይል ፖሊስ አዛዥን ጨምሮ 17 ባለሥልጣናትና ሌሎች 20 ተጠርጣሪዎች ላይ ክስ ተመሠረተ፡፡

ተጠርጣሪዎቹ በክልሉ ተወላጆችና በደገኞቹ መካከል ያለውን የመሬት አጠቃቀም በሚመለከት ከሚያዝያ 2006 ዓ.ም. እስከ ሐምሌ 2006 ዓ.ም.፣ ማዣንግ ዞን ጐደሬ ወረዳ ሜጢ ከተማ ውስጥ በተለያዩ የመሰብሰቢያ አዳራሾች የወረዳ አመራሮችንና ኅብረተሰቡን በመሰብሰብ ውይይት ማድረጋቸውን የፌዴራል ከፍተኛ ዓቃቤ ሕግ፣ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት ታህሳስ 22 ቀን 2006 ዓ.ም. ያቀረበው ክስ ያስረዳል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ በጠሩት ተደጋጋሚ ስብሰባ ላይ፣ ‹‹ደገኞቹ በማዣንግ ዞን ውስጥ የያዙትን የእርሻና የቡና ተክል መሬት ለማዣንግ ብሔር ተወላጆች ሊያካፍሉ ይገባል፡፡ የማያካፍሉ ከሆነ ከአካባቢያችን ለቀው መውጣት ይኖርባቸዋል፤›› በሚል አጀንዳ ላይ ተወያይተው መመርያ ማስተላለፋቸውን ክሱ ይገልጻል፡፡

ከተለያዩ አካባቢዎች በሕጋዊ መንገድ ወደ ክልሉ ሄደው የሠፈሩትና ለበርካታ ዓመታት ኖረዋል የተባሉት በአካባቢው አጠራር ‹‹ደገኞች›› የሚባሉት የሌላ ብሔር ተወላጆች፣ ተጠርጣሪዎቹ ያስተላለፉትን መመርያ ‹‹አንቀበልም›› ማለታቸውንም ክሱ ጠቁሟል፡፡

‹‹ደገኞቹ›› መመርያውን እንደማይቀበሉ ሲያሳውቁ የማዣንግ ብሔር ተወላጅ የሆኑ አንዳንድ የዞኑ የፖሊስና የሚሊሻ ታጣቂ አባላትን በማደራጀትና በማስታጠቅ፣ ጥቃት እንዲፈጽሙ (በደገኞቹ ላይ) ትዕዛዝ በመስጠትና ራሳቸውም በመሳተፍ፣ ከሐምሌ 17 ቀን 2006 ዓ.ም. እስከ መስከረም 18 ቀን 2007 ዓ.ም. ድረስ ባሉት ቀናት፣ በብሔሩ ተወላጆችና በ‹‹ደገኞች›› መካከል ደም አፋሳሽ ግጭት እንዲከሰት ማድረጋቸውን የዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡

በማዣንግ ዞን በተለይ በመንገሺና ጐደሬ ወረዳዎች፣ ከተሞችና ቀበሌዎች ውስጥ ግጭቱ እንዲከሰት በመደረጉ፣ ክሱ እስከሚመሠረት ድረስ የታወቀው የሞቱት ሰዎች ቁጥር 79 መሆኑን ክሱ ይገልጻል፡፡ 27 ሰዎች ከፍተኛ የአካል ጉዳትና ቀላል የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው፣ 273 መኖሪያ ቤቶች መቃጠላቸው ንብረትም መውደሙና 13,034 ዜጐች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውን ክሱ ያብራራል፡፡

ተጠርጣሪዎቹና ያልተያዙ ግብረ አበሮቻቸው በማዣንግ ብሔር ተወላጆችና በ‹‹ደገኛው›› ማኅበረሰብ መካከል በተፈጠረው የእርስ በርስ ግጭት ውስጥ የጦር መሣሪያዎችን ማለትም ክላሽኒኮብ፣ ጦርና የተለያዩ ሥለቶችን በመጠቀም ዜጐችን መግደላቸውን፣ አካል ማጉደላቸውን፣ ማቁሰላቸውንና ቤቶችን በማቃጠል ንብረት በማውደማቸው፣ በወንጀሉ ድርጊት በቀጥታ ተሳትፎ ማድረጋቸውን የዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ የአምስትና የ12 ዓመት ሕፃናትን፣ ጐልማሶችንና ወጣቶችን በጥይት ደብድበው፣ በሥለት ወግተውና አርደው ከመግደላቸውም በተጨማሪ፣ የስምንት ወር ነፍሰ ጡርንና ሌሎች ነዋሪዎችን ወደ ቤት ውስጥ እንዲገቡ በማዘዝ፣ ቤታቸውን በእሳት በመለኮስ አቃጥለው የገደሏቸው መሆኑን የዓቃቤ ሕግ ክስ በዝርዝር ያስረዳል፡፡

ዓቃቤ ሕግ በተጠርጣሪዎቹ ላይ በቡድንና በተናጠል 30 ክሶችን መሥርቶ ታህሳስ 22 ቀን 2007 ዓ.ም. ችሎት ያቀረበ ቢሆንም፣ የክስ ዝርዝሩ ለተጠርጣሪዎች ሳይደርስ ቀርቷል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ከክሱ ጋር የዓቃቤ ሕግ ምስክሮች ዝርዝር ተያይዞ በመቅረቡ ዓቃቤ ሕግ የምስክሮቹ ዝርዝር ከተሰጠ ለደኅንነታቸው እንደሚያሠጋቸው በመግለጽ እንዳይሰጥ በማመልከቱ ነው፡፡

በወንጀል ድርጊቱ የተጠረጠሩት የጋምቤላ ክልል ልዩ ኃይል ፖሊስ አዛዥ ኮሚሽነር ያዕቆብ ሸራተን ታኪካን፣ የማዣንግ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ትንሳኤል ራንጃን ኮንዜን፣ የጐደሬ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዮናስ ማርቆስ፣ ምክትል አስተዳዳሪው አቶ ጌታቸው ደቢሊው ተልቲካ፣ የጐደሬ ወረዳ ፖሊስ አዛዥ ረዳት ኢንስፔክተር አብዮት ሮኬት ኮርኮት፣ የማዣንግ ዞን ፖሊስ መምርያ ወንጀል መከላከል ዘርፍ ዋና ኃላፊ ኢንስፔክተር ማቴዎስ ማጥኦት ሀኪ፣ የክልሉ ፕሬዚዳንት የአስተዳደርና ማኅበራዊ ጉዳዮች አማካሪ አቶ አብርሃም ማይክል፣ የጐደሬ ወረዳ አስተዳዳሪ አማካሪ አቶ ያኬት ሪካ፣ የጐደሬ ወረዳ ሚሊሻ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍቅሬ ተፈራ፣ የዞኑ ፀጥታ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ይማም ፋሪስ፣ የሜጢ ከተማ ማዘጋጃ ቤት የግዥና ፋይናንስ ኃላፊ አቶ  ደንገቱ ረጳሽ፣ የጐደሬ ወረዳ ጤና ጥበቃ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ይስሐቅ አብረሃም፣ የዞኑ ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ ስምዖን ኮኛንንና ሌሎችም ተጠርጣሪዎች በድምሩ 37 መሆናቸውን ሪፖርተር ዘግቧል፡፡

በኢትዮጵያ የግል የሬዲዮ ጣቢያዎች ፈርሰው ከመንግስት ቻናል እንዲከራዩ ለማድረግ ታቅዷል

በኢንተርኔት የሚሰራጩ  ፅሑፎችን፣ ምስሎችንና ቪዲዮዎችን ለመቆጣጠር ታስቧል

 ebaበኢትዮጵያ የሬዲዮና የቴሌቪዥን ስርጭቶችን ለመቆጣጠር ከስምንት ዓመት በፊት በታወጀው ህግ ላይ አዳዲስ ቁጥጥሮችን የሚጨምርና እንዲሁም የኢንተርኔት ስርጭቶችንና ድረገፆችን የሚያካትት ህግ ተዘጋጀ፡፡

ከተለያዩ የሚዲያ ተቋማት ጋር ከትናንት በስቲያ ሃሙስ ውይይት የተካሄደበት ረቂቅ ህግ፣ ነባሩ አዋጅ ውስጥ የሰፈሩ የባለቤትነትና የፈቃድ አሰጣጥ ቁጥጥሮችን የሚዘረዝር ሲሆን፤ በኩባንያ መልክ እንጂ በግለሰብ የሬዲዮ ወይም የቴሌቪዥን ድርጅት ማቋቋም እንደማይቻል ይጠቅሳል፡፡ የዝምድና ወይም የጋብቻ ግንኙነት ያላቸው ሰዎች ለብቻቸው ባለአክሲዮን የሆኑበት ኩባንያ ፈቃድ እንደማይገኝም ተደንግጓል፡፡  ምንም እንኳ እስከዛሬ ተግባራዊ ባይሆንም በ1999 ዓ.ም በወጣው ህግ፣ የግል የቴሌቪዥን ጣቢያ ለማቋቋም ፈቃድ እንደሚሰጥ ተገልፆ የነበረ ሲሆን፤ አሁን በተረቀቀው ህግ ግን የቴሌቪዥን ጣቢያ በግል ማቋቋም እንደማይቻል ይደነግጋል፡፡

መንግስት የቴሌቪዥን ማሰራጫ ኔትዎርክ እንደሚዘረጋ የሚገልፀው ይሄው አዲስ አዋጅ፤ የግል ኩባንያዎች ከመንግስት ቻናል እየተከራዩ ለመስራት ማመልከትና ፈቃድ መጠየቅ ይችላሉ ይላል፡፡

የግል ኩባንያዎች ለጊዜው የራሳቸው የሬዲዮ ጣቢያ ለማቋቋም ፈቃድ የሚያገኙበት እድል ሊኖር እንደሚችል አዲሱ ህግ ይጠቁማል፡፡ ወደፊት ግን በግል ባቋቋሙት የማሰራጫ ጣቢያ ሳይሆን ከመንግስት የማሰራጫ ጣቢያ ቻናል እየተከራዩ እንዲሰሩ ይደረጋል ተብሏል፡፡ ለዚህም መመሪያ እንደሚዘጋጅ በረቂቁ ህግ ተጠቅሷል፡፡

በረቂቁ ህግ ከተካተቱ 60 አንቀፆች መካከል አብዛኞች በሬዲዮና በቴሌቭዥን ስርጭት ቁጥጥር ላይ ያተኮሩ ሲሆን፤ በኢንተርኔት የሚሰራጩና በድረገፅ የሚቀርቡ መረጃዎችን ለመቆጣጠር የታቀዱ ሦስት አንቀፆች ተጨምረውበታል፡፡ የሬዲዮና የቴሌቪዥን የግል ድርጅቶች ስለዲሞክራሲና ስለ ኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች የመዘገብ ግዴታ በህጉ የተጣለባቸው ሲሆን፤ በኢንተርኔትና በድረገፅ የሚሰራጩ መረጃዎች እንዲህ አይነት ግዴታ ባይኖርባቸውም ትክክለኛነታቸው ያልተረጋገጡ መረጃዎችን ማቅረብና ሌሎች በአንቀፅ 33 የተዘረዘሩ ድርጊቶችን ከፈፀሙ ተጠያቂ እንደሚሆኑ ረቂቅ ህጉ ይገልፃል፡፡

አመፅና፣ ግጭትና ጦርነት መቀስቀስ፣ እንዲሁም የሰውን ስምና ነፃነትን የሚያጠፋ መረጃ ክልክል መሆኑን የሚዘረዘረው አዲሱ ህግ፤ ምን ማለት እንደሆነ በግልጽ ባይብራራም የሃይማኖትን፣ የዘርን፣ የፆታን ክብር መንካት ክልክል ነው ይላል፡፡  በደፈናው ስነምግባርን የሚፃረርና የልጆችን አስተሳሰብ ወደአልተፈለገ አቅጣጫ እንዲያዘነብል መገፋፋትም ህገወጥ መሆኑን ይገልፃል፡፡

እንደ ፌስቡክ እና ቲዊተር የመሳሰሉትን ጨምሮ አብዛኞቹ ድረገፆች በውጭ አገር የሚገኙ በመሆናቸው እንዴት ሊቆጣጠራቸው እንዳሰበ ሲጠቁም፣ በፅሁፍ ማስጠንቀቂያ እንደሚሰጥና ድረገፁ ከሚገኝበት አገር መንግስት ጋር በመተባበር እርምጃ እንደሚወስድ ህጉ ይገልፃል፡፡
ብዙዎቹ ድረገፆች በሚገኙበት በአሜሪካ “ሃሰት አሰራጨህ ወይም ወዳልተፈለገ አቅጣጫ ትገፋፋለህ” የሚል የአስተሳሰብ ቁጥጥር እንደሌለ ይታወቃል፡፡

ምንጭ፡- አዲስ አድማስ ጋዜጣ

ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝን ጨምሮ ዝዋይ የታሰሩ 16 የፖለቲካ እስረኞች ጠያቂና ምግብ እንዳይገባላቸው ተከለከሉ

  • የሰማያዊ ወጣቶችና የነገረ ኢትዮጵያ ባልደረባ እንዳይጠይቁ ተከልክለዋል

zeway1ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝን ጨምሮ በዝዋይ የፌደራል ማረሚያ ቤት ታስረው የሚገኙ 16 የፖለቲካ እስረኞች ባልታወቀ ምክንያት ጠያቂና ምግብ እንዳይገባላቸው ተከለከሉ፡፡

ዛሬ ታህሳስ 28/2007 ዓ.ም የሰማያዊ ፓርቲ ወጣቶችና የነገረ ኢትዮጵያ ም/ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ በላይ ማናዬ የገናን ዋዜማ ዝዋይ ከሚገኙ እስረኞቹ ጋር ለማሳለፍ ከአዲስ አበባ ተነስተው ወደ ዝዋይ አቅንተው የነበር ቢሆንም ሊጠይቋቸው ያስጠሯቸው የፖለቲካ እስረኞች ‹‹በማንኛውም አይነት ሰው መጠየቅ አይችሉም፡፡ ምግብም አይገባላቸውም፡፡›› ተብለው ሳይጠይቁ ለመመለስ ተገደዋል፡፡

ጠያቂዎቹ ‹‹የመጠየቅ መብት አለን›› በሚል ወደ ውስጥ ለመግባት ግፊት በማድረጋቸው ፖሊሶች ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ፣ ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ፣ አበበ ቀስቶ፣ ናትናኤል መኮንን፣ በቀለ ገርባ፣ ጄኔራል አሳምነው ጽጌና ጀኔራል ተፈራ ማሞን ጨምሮ ጠያቂና ምግብ እንዳይገባላቸው የተከለከሉትን የ16 የፖለቲካ እስረኞችን ስም ዝርዝር አሳይተዋቸዋል፡፡

የሰማያዊ ፓርቲ ወጣቶችና የነገረ ኢትዮጵያ ባልደረባ ለእስረኞቹ ምግብና ጠያቂ እንዳይገባ የተከለከለበትን ምክንያት ለማጣራት ቢሞክሩም ፖሊሶች ‹‹የሚጣራ ነገር ስላለ ነው፡፡ እሱ እየተጣራ ነው፡፡›› ከማለት ውጭ ምክንያቱን በግልጽ ሊነግሯቸው አልቻሉም፡፡

ክልከላው እስከመቼ እንደሚቆይ በውል የታወቀ ነገር የሌለ ሲሆን ከአዲስ አበባ ተነስቶ የገናን በዓል ዋዜማ ከእስረኞቹ ጋር ለማሳለፍ ወደ ዝዋይ ካቀናው የሰማያዊ ፓርቲ ልዑክ በተጨማሪ የእስረኞቹ ቤተሰቦችም በክልከላው ምክንያት ሳይጠይቁና ምግብ ሳያስገቡ ተመልሰዋለል፡፡

ምንጭ፡- ነገረ-ኢትዮጵያ

አቃቤ ህግ በብሎገሮቹ እና ጋዜጠኞቹ ላይ የቀረበውን ክስ በድጋሚ እንዲያሻሽል ታዘዘ

zonበእነ ሶልያና ሽመልስ የክስ መዝገብ የሽብር ክስ ተመስርቶባቸው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ የሚገኙት የዞን 9 ጦማርያን እና ጋዜጠኞች ዛሬ ታህሳስ 27 ቀን 2007 ዓ.ም ለ14ኛ ጊዜ በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት የቀረቡ ሲሆን ፍርድ ቤቱ ቀደም ብሎ የቀረበውን የክስ ማሻሻያ በተመለከተ ብይን ሰጥቷል፡፡

ፍርድ ቤቱ የተሰየመው ቀደም ብሎ በጦማርያኑ እና ጋዜጠኞች ላይ የተመሰረተው ክስ እንዲሻሻል ባዘዘው መሰረት የፌደራል አቃቤ ህግ ክሱን ፍርድ ቤቱ በሰጠው ትዕዛዝ መሰረት አሻሽሏል ወይስ አላሻሻለም በሚለው ጉዳይ ላይ መርምሮ ብይን ለመስጠት ነበር፡፡ በመሆኑም ፍርድ ቤቱ የተከሳሽ ጠበቆች ተሻሻለ የተባለው ክስ በፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ መሰረት አለመሻሻሉን ያቀረቡትን አቤቱታ እና አቃቤ ህግ ይህንኑ አቤቱታ በተመለከተ የሰጠውን መልስ አገናዝቦ የሰጠውን ብይን በንባብ አሰምቷል፡፡

በመሆኑም አቃቤ ህግ ተከሳሾች በጸረ ሽብር አዋጁ ላይ ከተመለከቱት የሽብር ተግባራት የትኞቹን ፈጸሙ የሚለው በክሱ ላይ አልተጠቀሰም በተባለው ጉዳይ ላይ ያቀረበውን ማሻሻያ እና ፍርድ ቤቱ የተከሳሾቹ የ‹ሽብር› ድርጊት ግብና ስትራቴጂን አስመልክቶ በግልጽ ተብራርቶ ክሱ እንዲሻሻል ተሰጥቶት የነበረውን ትዕዛዝ በተመለከተ በማሻሻያው ላይ የቀረበው በቂ ነው በሚል ፍርድ ቤቱ እነዚህን ፍሬ ነገሮች እንደተሻሻሉ አድርጎ ተቀብሎታል፡፡

በቀሪዎቹ ነጥቦች ላይ አቃቤ ህግ ፍርድ ቤቱ በሰጠው ትዕዛዝ መሰረት ማሻሻያውን አለማድረጉን ፍርድ ቤቱ በብይኑ ላይ አመልክቷል፡፡ በተለይም ይሻሻሉ ተብለው ትዕዛዝ በተሰጠባቸው አራት ነጥቦች ላይ፣ ማለትም በተከሳሾች ተመሰረተ የተባለውን ድርጅት (ቡድን) ከተቻለ በስም በመግለጽ ወይም ከሌሎች ድርጅቶች (ቡድኖች) ለይቶ እንዲገልጽ፣ የእያንዳንዱን ተከሳሽ የውስጥ የስራ ክፍፍል ለይቶ እንዲያመለክት፣ ተከሳሾች በተከሰሱበት ጉዳይ ወሰዱ ተብሎ በክሱ የተጠቀሰው ስልጠና በማን፣ የትና መቼ እንደተሰጠ ተለይቶና ተገልጾ ክሱ እንዲሻሻል፣ እንዲሁም ለአመጽ ተግባር እንዲውል ውጭ ሀገር ከሚገኙ ገንዘብ (48 000 ብር) ተላከ የተባለውን ገንዘብ በተመለከተ፣ ገንዘቡ ከማን እንደተላከና ለምን ዓላማ እንደዋለ ተገልጾ ክሱ እንዲሻሻል የሚሉት ፍሬ ነገሮች በትዕዛዙ መሰረት አለመሻሻላቸውን ፍርድ ቤቱ በብይኑ አመልክቷል፡፡

ፍርድ ቤቱ እንዲሻሻሉ ትዕዛዝ ከሰጠባቸው ነጥቦች መካከል አብዛኞቹ በአቃቤ ህግ አለማሻሻላቸውን በብይኑ ላይ አስፍሯል፡፡ ስለሆነም አቃቤ ህግ ያልተሻሻሉ ነጥቦችን አሻሽሎ እንዲቀርብ ፍርድ ቤቱ ለጥር 6 ቀን 2007 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

ምንጭ፡- ነገረ ኢትዮጵያ

የተቀዋሚ ፓርቲዎች ምርጫ ቦርድ ያቀረበውን የፋይናንስ ክፍፍል ቀመር ውድቅ አደረጉ

ELECየገዥው ፓርቲ ቀኝ ዕጅ ተደርጐ የሚወሰደው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በዛሬው ዕለት ለፓርቲዎች የሚሰጠውን የፋይናንስ ድጋፍ ክፍፍልን አስመልክቶ በምርጫ ከሚወዳደሩ ሀገር-አቀፍ ፓርቲዎች ጋር የጠራው የውይይት ሀሳብ ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ውድቅ ተደረገ፡፡ ቦርዱም ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሞታል፡፡

በግዮን ሆቴል ጉባዔ አጠቃላይ ከ25 በላይ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች የተገኙ ሲሆን ቦርዱ ፍትሐዊ ያለውን የፋይናንስ ክፍፍል ቀመር አቅርቧል፡፡ በዚህም መሠረት ለእኩልነት መስፈርት 10% ፣ የፓርላማና የክልል ም/ቤት መቀመጫን መሰረት ያደረገ የፍትሐዊነት መስፈርት 55%፣ ባቀረቡት የእጩዎች ብዛት 25% እና የሴት እጩዎች ብዛት 10% በሚል ቀመር ቢያቀርብም ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ መልኩ እና በኢህአዴግ እንደ አጋር የሚታዩ ፓርቲዎች ሳይቀር በሙሉ ድምፅ “ኢህአዴግን ዳግም ለማንገስ የተሰራ ቀመርና የቦርዱን ገለልተኛነት ጥያቄ ያጋለጡ” በማለት ከፍተኛ ትችትና ተቃውሞ እንደቀረበበት አንድነት ፓርቲን ወክለው በቦታው የተገኙት አቶ ዳንኤል ተፈራ፣ ገልፀዋል፡፡

አንድነት በመወከል ስብሰባው ላይ የተሳተፉት የአንድነት ተወካይ አቶ ዳንኤል ተፈራ፣ እንደገለፁት “ስብሰባው ላይ ምርጫ ቦርድ ላይ የቀረበበት ውግዘትና ያቀረበው ቀመር ከኢህአዴግ ተወካይ በስተቀር የሚደግፈው ማጣቱ እንዲሁም ስርዓቱን ኢህአዴግ ይደግፍኛል ብሎ የሚተማመንባቸው ፓርቲዎች ከጉያው እየወጡ እንደሆነ የሚጠቁም አጋጣሚ ነው” ሲሉ ገልፀዋል፡፡ አያይዘውም ተሳታፊዎች ምርጫ ቦርድ ስብሰባዎችና ሀሳቦችን ከዜና ማድመቂያነት ባለፈ በተግባር ለውጦ እንዲያሳይ እና ሀገራዊ ግዴታውን እንዲወጣ በርካታ ማሳሰቢያዎች የቀረቡ ሲሆን ዳግመኛ በታሪክ ቅሌት እንዳይወድቅ ከአድሏዊ አሰራር ራሱን እንዲያላቅቅ ምክርም ተለግሶታል፡፡

በተለይም ፓርላማና የክልል ም/ቤት ባለ መቀመጫ በሚል የተመደበውን ገንዘብ በኢህአዴግ ለማስረከብ መዘጋጀቱ ተቀባይነት እንደሌለውና እንደገና ራሱን እንዲፈትሽ አብዛኛው ተሳታፊ ገልፆል፡፡

ቦርዱ ቀመሩን የሰራሁት ከ111 ሀገሮች ተሞክሮ ወስጄ ነው ቢልም፡፡ ተሳታፊዎቹ የሌሎች ሀገሮች ተሞክሮ እና የኢትዮጵያ ተሞክሮ የሚለያይ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ገዥ ፓርቲ ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ የማይጨነቅ፣ ተቃዋሚዎችን ለማጥፋት የሚሰራና የይስሙላ ምርጫ የሚያደርግ በመሆኑ ለንፅፅር የሚቀርብ አይደለም ስለዚህ ከኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ተነስተን ቀመሩን እናውጣ በማለት ምርጫ ቦርድ ያቀረበው የፋይናንስ ክፍፍል ቀመር ውድቅ ተደርጐበታል፡፡
በምርጫ ቦርድ የቀረበውን የፋይናንስ ድጋፍ ክፍፍል ተገቢ ነው የሚል ድጋፍ የሰጠው የኢህአዴግ ተወካይ ብቻ ሲሆን ሌሎች ተሳታፊዎች ተቃውሞ በማሰማትና ቀመሩን ባለመቀበል ኢህአዴግ ብቻውን የቆመበት ስብሰባ ነበር ሲል የአንድነት ፓርቲ ተወካይ አቶ ዳንኤል ተፈራ ተናግሯል፡፡ በመጨረሻም ቦርዱ የቀረበበትን ተቋም ከግምት አስገብቶ የፋይናንስ ክፍፍል ቀመሩን አስተካክሎ እንደሚቀርብ ይጠበቃል፡፡

ምንጭ፡ ፍኖተ ነፃነት