Category Archives: Social and Culture

ድምፃዊ ቴዲ አፍሮ ከሃገር እንዳይወጣ ታገደ

Teddy_Afroበአውሮፓና በተለያዩ መካከለኛው ምስራቅ ሀገራት በርካታ የሙዚቃ ኮንሰርቶቹን ለማቅረብ ወደ ባህር ማዶ ሊጓዝ የነበረው ታዋቂው ድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ከሀገር እንዳይወጣ መታገዱ ተገለፀ። ቴዲ አፍሮ የሙዚቃ ኮንሰርቱን በፊንላንድ ሄልሲንኪ በነገው ዕለት ማቅረብ ይጀምራል ተብሎ ተጠብቆ ነበር፡፡ ለዚህም የሙዚቃ ባንዱ አባላትና ማናጀሩ ዘካርያስ ጌታቸው እዛው ፊላንድ ቢገቡም፤ ቴዲ ከሃገር እንዳይወጣ በደህንነቶች በመታገዱ ምክንያት የነገው የፊንላንድ ኮንሰርት መሰረዙን አዘጋጆቹ ከፊንላንድ ሄልሲንኪ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታው ቀዋል።

ከጥቂት ወራት በፊት ለቴዲ አፍሮ የበርካታ ወራት እስር በመንግስት በምክንያትነት የተገለፀችው ቢ ኤም ደብልዩ የቤት አውቶሞቢል ከገቢዎችና ጉሙሩክ ቀረጥ ጋር በተያያዘ ክፍያ ሳይፈፀም ወደ ሶስተኛ ወገን በሽያጭ አስተላልፏል በሚል ክስ ተመስርቶበት በዋስ ከተለቀቀ በኋላ ወደ አሜሪካ ሊሄድ ሲል እንዲሁ በደህነንቶች ተይዞ በቦሌ ኤርፖርት ሲጉላላ ከቆየ በኋላ የተለመደ የኮንሰርት ስራውን ቀጥሎ ወደ ሀገሩ መመለሱ አይዘነጋም፡፡ ይሁን እንጂ ህዳር 26 ቀን 2007 ዓ.ም. አርቲስቱ ከሀገር እንዳይወጣ ፓስፖርቱ በደህንነቶች ለጉዞ ዝግጅት ላይ እያለ ድንገት መነጠቁን እና ይህ እስከተዘገበበት ድረስም የጉዞ ሰነዱ እንዳልተመለሰለት መረጃዎች አመልክተዋል። ድምፃዊ ቴዲ አፍሮ ለምን ከሃገር እንዳይወጣ እንደታገደ እስካሁን የተገለፀ ነገር የለም:።

በሄል ሲንኪ ፊላንድ የቴዲ አፍሮን ኮንሰርት ለመታደም ትኬቱን የገዙ በርካታ ታዳሚዎች በጉጉት ይጠባበቁ የነበረ ሲሆን፤ከአቅም በላይ በተፈጠረ ችግር ኮንሰርቱን በዕለቱ ማቅረብ ስለማይቻል መሰረዙን አዘጋጁ ቲ-ፕሮሞሽን ከሄልሲንኪ ፊንላንድ አስታውቋል ። ይሁን እንጂ አዘጋጆች ኮንሰርቱ በመሰረዙ ምክንያት ትኬቱን የገዙ ሰዎች ገንዘባቸው ክፍያ በፈፀሙበት መንገድ እንደሚመለስላቸው እና በቅርቡም የታሰበው ኮንሰርት እንደሚካሄድ በመጠቆም፤ ችግሩ የተፈጠረው ከአርቲስቱና ከአዘጋጆቹ አቅም በላይ በሆነ ችግር በመሆኑ አዘጋጁ ይቅርታ ጠይቋል፡፡ ለኮንሰርቱ መሰረዝ የሆነው ችግር እንደተፈታም የሙዚቃ ድግሱ እንደሚቀጥል ተጠቁሟል፡፡

አመክሮና በቀለ ገርባ

Zelalem Kibret

የኦሮሞ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኦፌዴን) ምክትል ሊቀመንበርና የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ መድረክ ስራ አስፈፃሚ የነበሩት “ህጋዊ የፖለቲካ ፓርቲን ሽፋን በማድረግ  የአሸባሪ ቡድን የሆነው ኦነግ አባል ሆነዋል” በሚል ክስ ተመስርቶባቸው የ8 ዓመት እሥር የተበየነባቸው ሲሆን፤ ይግባኝ ጠይቀው እስሩ ወደ 3 ዓመት ከ7 ወር ዝቅ ተደርጎላቸዋል፡፡

bekele-gerbaከ3 ዓመት ከ7 ወር የእስር ጊዜ ውስጥም 3ቱን ዓመት በመጨረሳቸው በአመክሮ ይፈቱ ዘንድ ለማረሚያ ቤቱ ያመለከቱ ሲሆን ማረሚያ ቤቱም ‹አመክሮ መስጠትም አለመስጠትም መብታችን ነው›  በማለት እስከአሁን ሊፈታቸው አልቻለም፡፡ ይህም ብዙ ጥያቄዎችን አስነስቷል፡፡

አንዳንድ ህጋዊ ሁኔታዎች ስለጉዳዩ፡

አመክሮ ምንደር ነው?
ሌላውን ትርጉም ትተን የኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ ‹በተወሰነ ጊዜ በአመክሮ መፈታት› በሚለው ክፍል በተለይም በአንቀፅ 202 እንደደነገገው፡
“ተቀጭው ከተወሰነበት የእስራት ጊዜ ከሶስት እጅ ሁለቱን እጅ ወይም ፍርዱ የእድሜ ልክ እስራት ሲሆን ሀያ ዓመት በፈፀመ ጊዜ አግባብ ባለው አካል ወይም በጥፋተኛው አሳሳቢነት ጥፋተኛውን ከቅጣቱ ነፃ ያወጣዋል፡፡” ይህም ማለት አመክሮ 2/3ኛውን የቅጣት ጊዜውን የጨረሰ ታራሚ ከእስር የሚፈታበት አሰራር ነው፡፡

አመክሮ ለማግኝት ምን መስፈርት ማሟላት ያስፈልጋል?

የኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ ከላይ በጠቀስነው አንቀፅ 202 ላይ አመክሮ ለማግኝት አንድ እስረኛ ማሟላት የሚያስፈልገውን መስፈርቶች ይዘረዝራል፡፡ ይህም፡

– ‹ታራሚው በስራ ጠባዩ የተረጋገጠ መሻሻል አሳይቶ እንደሆነ…›

– ‹ካሳ የመክፈል ግዴታ ተጥሎበት ከነበረና ካሳውን መክፈሉ የተረጋገጠ እንደሆነ…›

– ‹አመሉና ጠባዩ መልካም አኗኗር ለመኖር የሚያስችለውና በአመክሮ መፈታቱ መልካም ውጤት ሊያስገኝ ይችላል ተብሎ የታመነ እንደሆነ..›

ነው ብሎ ይደነግጋል፡፡

ማረሚያ ቤት ወይስ ፍርድ ቤት?

ታራሚን በአመክሮ የመልቀቅ የመጨረሻው ስልጣን የፍርድ ቤት፡፡ ነገር ግን ጉዳዩን ማረሚያ ቤቱ በራሱ ተነሳሽነት ወይም በታራሚው አሳሳቢነት ለፍርድ ቤት ሲያቀርብ ነው ፍርድ ቤቱ ውሳኔ የሚሰጠው፡፡ እዚህ ላይ ማረሚያ ቤቱ ትልቁን ስልጣን ይዞ እናገኛለን፡፡ ማረሚያ ቤቱ ለፍርድ ቤት ማቅረብ ካልፈለገ ሊተወው የሚችልበት አግባብ አለ ማለት ነው፡፡ ነገር ግን ማረሚያ ቤቱ በሕግ ስር ያለ አካል እንደመሆኑ መጠን በወንጀል ሕጉ አንቀፅ 202 ላይ የተቀመጡ መስፈርቶችን ላሟላ ታራሚ አመክሮ ሊከለክል አይችልም – የታራሚው መብት ነውና!

በቀለ ገርባስ?

አቶ በቀለ ገርባ ከተፈረደባቸው የአምስት ዓመት እስር ውስጥ 2/3ኛውን ወይም 3 ዓመት የሚሆነውን ጨርሰው የአመክሮ ጥያቄያቸው በማረሚያ ቤቱ በኩል ለፍርድ ቤት እንዲቀርብላቸው ቢጠይቁም ማረሚያ ቤቱ  ‹አመክሮ መስጠትም አለመስጠትም መብታችን ነው› የሚል መልስ እንደሰጣቸው ተሰምቷል፡፡
1ኛ. አመክሮ መስጠት የማረሚያ ቤት መብት ሳይሆን ግዴታም ጭምር ነው፡፡ መስፈርቱን ያሟላ ታራሚ አመክሮ የማግኝት መብት ያለው መሆኑ በሌላ በኩል አመክሮ ሰጭውን አካል ላይ ግዴታ ይጥላልና፡፡
2ኛ ሌላው አቶ በቀለ ገርባ መስፈርቱን አሟልተዋል ወይስ አላሟሉም የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ 2/3ኛውን የእስር ጊዜ መጨረስ የሚለውን Objective መስፈርት እንዳሟሉ ግልፅ ሲሆን፡፡ ችግሩ የተፈጠረው Subjective መስፈርቱ ጋር በተያያዘ ነው፡፡ ይህም ማለት በእስር ወቅት መልካም ፀባይ አሳይተዋል ወይስ አላሳዩም የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ አንድ ታራሚ በእስር ወቅት ለመልካም ፀባይ ተቃራኒ የሆኑ ነገሮችን ካሳየ የቅጣት ማስጠንቀቂያ ከመፃፍ እስከ ብቻውን ማሰር (Solitary Confinement) ድረስ ያሉ እርምጃዎች በማረሚያ ቤቱ ሊወሰዱበት ይችላሉ፡፡

አቶ በቀለ ገርባ ከፀባያቸው ጋር በተያያዘ ምንም አይነት ቅጣት ያልተወሰደባቸው ከመሆኑም ሌላ መልካም ፀባይ እንዳሳዩ ከማረሚያ ቤቱ እንደተነገራቸው ራሳቸው ገልፀዋል፡፡ በቀለ ገርባ ምም መስፈር አሟልተዋል ማለት ነው፡፡ ታዲያ ምን ይሆን አቶ በቀለን በአመክሮ ከመፈታት ያገዳቸው?

አንዳንድ ነገሮች

ባለው አካሄድ አብዛኛው ታራሚዎች በአመክሮ ይፈታል፡፡ ከሌባ እስከ ሙሰኛ፡፡ High Profile በሆኑ ክሶች የተከሰሱ ሰዎች ሳይቀሩ በአመክሮ ሲፈቱ እንደነበር እናስታውሳለን ለምሳሌ ቴዲ አፍሮ 24 ወራት ተፈርዶበት 16 ወራትን ጨርሶ በአመክሮ ተፈቷል፡፡ አቶ አሰፋ አብርሃ 9 ዓመት ተፈርዶባቸው ሰባት ዓመታት ታስረው ከብዙ ውዝግብ በኋላ በአመክሮ ተፈተዋል፡፡ በሌላ በኩል በቅንጅት ክስ ስር ተከሰው የነበሩት አቶ ዳንኤል በቀለና አቶ ነፃነት ደምሴ 30 ወራት የተፈረደባቸው ሲሆን 20 ወራትን በእስር አሳልፈው አመክሮ ቢጠይቁም ማረሚያ ቤቱ ‹ፍርዳችሁን ጨርሳችሁ ውጡ› በሚል ምክንያት አመክሮ ከልክሏቸው ነበር፡፡

እንግዲህ አቶ በቀለ ገርባ በሕጉ የተቀመጠውን መስፈርት አሟልተው እያለ በአመክሮ የመፈታት መብታቸው አልተከበረም ወይም ማረሚያ ቤቱ ግዴታውን ሊወጣ አልፈለገም!

ምክንያት: በጉልበተኞች የምትተዳደር ሀገር ዜጋ ስለሆኑ!

ልዩ ማስታወሻ፡-ይህ ባለፈው ጥር  16 ቀን 2006 ዓ.ም. የዞን 9 ብሎገርና የአምቦ ዩኒቨርስቲ የህግ መምህር ዘለዓለም ክብረት ከመታሰሩ በፊት የፃፈው ቢሆንም፤በአሁን ሰዓት እሱ ራሱ በግፍ እስር አቃቂ ቂሊንጦ ወህኒ ቤት ይገኛል፡፡

#‎FreeBekeleGerba

የአዲስ ጉዳይ መፅሔት ጋዜጠኞች ተሰደዱ

በመንግስት በደረሰባቸው ጫና እና ክስ ምክንያት የ”አዲስ ጉዳይ” መፅሔት ማኔጂንግ ዳይሬክተር እንዳልካቸው ተስፋዬ፣ ምክትል ዋና አዘጋጅ ኢብራሂም ሻፊ፣ ከፍተኛ አዘጋጅ እንዳለ ተሺ እና አዘጋጅ እና የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች መድረክ (ኢጋመ) ገንዘብ ያዥ ሀብታሙ ስዩም ሀገር ጥለው ተሰደዱ፡፡ ጋዜጠኞቹ የተሰደዱት፤ የፍትህ  ሚኒስቴር አቃቤ ህግ በኢቴቪ አዲስ ጉዳይ መፅሔትን ጨምሮ 5 መፅሔቶች እና አንድ ጋዜጣ ላይ ክስ መመስረቱ ይፋ መደረጉን ተከትሎ ቢሆንም፤ ቀደም ሲል በመንግስት ደህንነትና ፀጥታ ኃይሎች ተደጋጋሚ ጫና ይደርስባቸው እንደነበርም ተጠቁሟል፡፡

addከአዲስ ጉዳይ መፅሔት ከፍተኛ አዘጋጅ አስማማው ኃይለጊዮርጊስ እና የፎቶ ጋዜጠኛ አዚዛ መሐመድ በቅርቡ መታሰራቸውና ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ እንደሚገኝ  ይታወቃል፡፡ የተሰደዱ ጋዜጠኞች ቁጥርም እየጨመረ ሲሆን፤ በቅርቡ የኢትዮጵ ጋዜጠኞች መድረክ ፕሬዘዳነት ጋዜጠኛ በትረ ያዕቆብ እና የህዝብ ግንኙነቱ ዘሪሁን ሙሉጌታን ጨምሮ እስካሁን የተሰደዱ ጋዜጠኞች ቁጥር ከ15 በላይ መሆኑን መረጃዎች አመልክተዋል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ሌሎችም ጋዜጠኞች ከፍተኛ ጫና ላይ መሆናቸው ታውቋል፡፡

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል ላይ ጉል ሚና ይጫወታል የተባለለት “ሰላማዊ ትግል 101” መፅሐፍ በገበያ ላይ ዋለ

በኢትዮጵያ በተለይም ከ1960ዎቹ ጀምሮ በርካታ የሰላማዊ ትግል ሙከራ ቢደረግም እስካሁን ለውጤት የበቃበት ጊዜ የለም፡፡ በአሁን ወቅት በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቢኖሩም ከጊዜውና ከሀገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማዛመድና ዓለም አቀፍ ተሞክሮን ከኢትዮጵያ ጋር በማያያዝ እንዴት ለውጤት መብቃት ይቻላል በሚል ሰፊ ጥናቶችን ያካተተ “ሰላማዊ ትግል 101” መፅሐፍ ለመጀመሪያ ጊዜ በግርማ ሞገስ ተፅፎ በገበያ ላይ ውሏል፡፡ መፅሐፉ በኢትዮጵያ ውስጥ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ስልትን ተጠቅመው ህዝቡን የስልጣን ባለቤት ለማድረግ እና ወደፊት የተሻለ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ለመፍጠር የሚያስችል ስልቶችንም አካትቶ መያዙ ተጠቁሟል፡፡

picbደራሲው ነዋሪነታቸው በሰሜን አሜሪካ ሲሆን፤ መፅሐፉን ከማዘጋጀታቸው በፊት የኢትዮጵያን ቀደምት፣ መካከለኛ እና ዘመናዊ ታሪክ፣ በዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያላቸውና ለውጤት የበቁ የተለያዩ የሰላማዊ ፖለቲካ ትግል ስልት ተሞክሮዎችን፣ ወቅታዊ የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ እና የገዥው ኢህአዴግን ባህሪ በማጥናት ዓመታትን የፈጀ መፅሐፍ መዘጋጀቱን ከደራሲው መረዳት ተችሏል፡፡ በተለይ በሀገሪቱ የተሻለ የመንግስት ስርዓት እንዲፈጠር የሚሹ እና ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር እንዲመጣ የሚንቀሳቀሱ ፖለቲከኞችን ጨምሮ ማንኛውም ዜጋ ቢጠቀምባቸው ውጤታማ መሆን እንደሚቻልም ታምኖበታል፡፡ “ሰላማዊ ትግል 101“ መፅሐፍ ለአንባቢያን በ50 ብር የቀረበ ሲሆን፤ በመፅሐፍት መሸጫ መደብሮች እንደሚገኝምምንጮች ጠቁመዋል፡፡

 

በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው የጋዜጠኞች ማኀበር ዛሬ በይፋ ተመሰረተ

በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው አዲሱ “የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች መድረክ” የተሰኘው የሙያ ማኀበር ዛሬ ጥር 22 ቀን 2006 ዓ.ም. በይፋ ተመሰረተ፡፡ ማኀበሩ አስታራ ሆቴል ባደረገው ጠቅላላ ጉባዔ የበጎ አድራጎትና ማኀበራት ኤጀንሲ፣ በኢትዮጵያ የአሜሪካ እና የእንግሊዝ ኤምባሲን ጨምሮ የተለያዩ ተወካዮች በታዛቢነት በተገኙበ መተዳደሪያ ደንብ በማፅደቅ አመራሮችንም መምረጡ ታውቋል፡፡ የማኀበሩ መመስረት ዋነኛ ዓላማም የጋዜጠኞችን መብትና ጥቅም ማስጠበቅ፣ የጋዜጠኞችን አቅም ማጎልበት፣ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ የህክምና እና የህግ አገልግሎት ድጋፍ መስጠት፣በጋዜጠኞች መካከል ጠንካራ ግንኙነት መፍጠር የሚሉት ይገኙበታል፡፡

ማኀበሩን በተመለከተ ከጠቅላላ ጉባዔ አባላት የተለያዩ ጥያቄዎች የተንሸራሸሩ ሲሆን፤ ከዚህ ቀደም እንደነበሩት ማኀበራት ሳይሆን የተሻለ በመስራት ለጋዜጠኞች መብትና ጥቅም መስራት እንዳለበትም ተጠቁሟል፡፡ ስለሆነም የማኀበሩን ዓላማ የመተዳደሪያ ደንቡ በሚያዘው መሰረት ለማስፈፀም ለጠቅላላ ጉባዔ ጋዜጠኛ አያሌው አስረስ ሰብሳቢ፣ጋዜጠኛ ጌታቸው ወርቁ ምክትል ሰብሳቢ እና ጋዜጠኛ ብሩክ ከበደ ፀሐፊ በመሆን ተመርጠዋል፡፡ በስራ አስፈፃሚነት ደግሞ ጋዜጠኛ በትረ ያዕቆብ ፕሬዘዳንት፣ ስለሺ ሀጎስ ምክትል ፕሬዘዳንት፣ ዘሪሁን ሙሉጌታ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ፣ነብዩ ኃይሉ ፀሐፊ፣ ሀብታሙ ስዩም (የገጣሚ በዕውቀቱ ስዩም ታናሽ ወንድም) ገንዘብ ያዥ፣ ብስራት ወ/ሚካኤል የትምህርት እና ስልጠና ኃላፊ እንዲሁም ኤልያስ ገብሩ ሒሳብ ሹም በመሆን መመረጣቸውን የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡

ማኀበሩ ከላይ ከተጠቀሱት አመራሮች በተጨማሪ ጋዜጠኛ ብዙዓየሁ ወንድሙን የማኀበሩ ኦዲተር አድርጎ መምረጡም ታውቋል፡፡ ማኀበሩ የአባላት መደበኛ ወርሃዊ መዋጮን ጨምሮ የተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ከመከረ ማኀበሩ በይፋ መመስረቱን ይፋ ማድረጉ ታውቋል፡፡ በአሁን ወቅት ለጋዜጠኞች መብት እና ጥቅም አልሰሩም ተብለው የሚወቀሱና በፌደራሉ የበጎ አድራጎትና ማኀበራት ኤጀንሲ ተመዝግበው የምስክር ወረቀት እንዳላቸው የሚነገርላቸው 5 ማኀበራት ቢኖሩም፤ እስካሁን በተግባር ለሙያውም ሆነ ለባለሙያው ያከናወኑት ተግባር የለም በሚል ከፍተኛ ወቀሳ እንደሚቀርብባቸው ይታወቃል፡፡ በዚህም ምክንያት አዲሱ የጋዜጠኞች ማኀበር ከሌሎች በተለይ በተግባር በርካታ ስራዎች ይሰራል ተብሎ በባለሙያዎቹ ብዙ ተስፋ ተጥሎበታል፡፡